>
5:31 pm - Friday November 12, 1480

አዲስአበቤ-Watch Out 2 - ኤርሚያስ ለገሰ

አዲስአበቤ-Watch Out 2

ኤርሚያስ ለገሰ

ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የአዲስ አበባን ክልል ምክርቤት ምርጫ ለአንድ ሳምንት ወደ ኃላ በመጐተቷና የአዲስአበቤን ቅስም ለመስበር መሞከሯ ታሪክ የማይረሳው ጥቁር አሻራ ነው። ለዘላለምም ተመዝግቦ ይኖራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ለእህታችን ብርቱካንም ቢሆን የእድሜ ልክ ፀፀት መሆኑ አይቀርም። በተለይም በፓለቲካው አካሄድ ጨዋ ከመሆን የግንዛቤ እጥረት የመጣ ከሆነ። 
በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሰውን “በዐብያዊ ኦሮሙማ” የተጠነሰሰውን ሸፍጥ ለመሻገር አዳዲስ ከሁኔታዎች ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ስትራቴጂ እና ታክቲክ መንደፍ ያስፈልጋል።
በዚህም መሠረት አዲስአበቤ እንደ ሰጐኗ አይኑን መትከል ያለበት በመጀመሪያው ዙር በግንቦት መጨረሻ ለሚካሄደው የፓርላማው 23 መቀመጫ ላይ መሆን ይኖርበታል። በ23ቱ ወንበር ብልፅግና በመቶ ፐርሰንት በዝረራ መሸነፍ አለበት። የግድ ነው። በምንም ተአምር ለድርድር የሚያቀርብ አይደለም።
አዲስአበቤ ለህልውናው የሚያስብ ከሆነ የግንቦቱ የፓርላማ ውጤት ሙሉ ለሙሉ ብልጽግናን ማባረር በሰኔ ወር ለአዲስ አበባ ክልል ምክርቤት የሚካሄደውን ምርጫ አልጋ በአልጋ ያደርገዋል። ስለዚህ የብልፅግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረታችሁ የፓርላማው 23 ወንበር ላይ ይሁን።
 
     ” የባቱስታን ሕግ በኢትዮጵያ!”
የዛሬ 26 አመት የአፓርታይድ ወለድ ሕገ-መንግስት ሲፀድቅ አዲስአበቤዎች (አዲስአበቤዎች ብቻ!) አንገት ለአንገት ተናንቀው ነበር። ለምሳሌ “የክልሎች አወቃቀር” በሚለው ርዕስ ላይ ውይይት ሲካሄድ አንድ የአዲስአበቤ ወጣት እንዲህ በማለት ከአባይ ፀሀዬ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አባተ ኪሾ፣ ሐሰን ዓሊ ጋር በሃሳብ ተሞሻልቋል።
እንዲህ ነበር ያለው፣
” ዴሞክራሲያዊ መንግስት አወቃቀሩ አሃዳዊ ወይም ፌዴራላዊ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር የነበረውን ጭቆና የሚያስቀረው ቋንቋ ተኮር ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር አልቀበለውም። ቀደም ሲል የነበረውን አከላለል በመሻር በቋንቋና በጎሳ ላይ የተመሰረተው የክልሎች አወቃቀር በእኩልነት እና በፍቅር ለመኖር አያግዝም። ሌላው ቀርቶ ተቻችሎ መኖርን እንኳ እንዳላስቻለ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱትን ግጭቶች በምሳሌነት እጠቅሳለው። አዲሱ በቋንቋ ላይ የተመሰረተው አከላለል ከእንዲህ ዓይነቱ የተወዛገቡ ሁኔታዎች የማያወጣ ከመሆኑም በላይ የክልሎች ድንበር በግልጽ ባለመቀመጡ ችግሩ ቀጣይነት ይኖረዋል። ችግሮቹ እየተባባሱ ሄደው የእርስ በርስ ግጭት እየተበራከተ ሄዶ ሀገሪቷን ሊበትናት ይችላል። ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጥርቅም አድርጎ አድርግ ማየት ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ዘርና ቋንቋ ያለው ቢሆንም ፤ አኩሪ ታሪክ ያላት አገር ባለቤት የሆነ አንድ ሕዝብ ነው።”
ስማ አዲስአበቤ! ይሄን ከ26 አመት በፊት የተናገረው ልጅህ ነው። በትንቅንቅ መርጠህ አንተን ወክሎ እንዲናገር የላከው ወጣት! ዘለሌ ፀጋስላሴ ይባላል።
ዘለሌ ዛሬም አዲስ አበባ የህልውና አደጋዋን ለመታደግ ከአውሮፓ ሲውዲን ኑሮውን ትቶ አዲስ አበባ ገብቷል። በቀጣዩም ምርጫ ወረዳ 7 ላይ በድጋሚ ድምፅ ሊሆንህ ባልደራስን ወክሎ መጥቶልሃል። ምርጫው የአንተ ነው!
(ምስጋና ፡ የሕገ-መንግሥቱ ፈረሰኞች፡ አስራት አብርሃም)
ይድረስ በወረዳ 7 ለምትኖሩ አዲስአበቤዎች፣
ከዛሬ 26 አመት በፊት የኢትዮጵያዊነት እና አዲስ አበባ ፀር የሆነው ሕገ-መንግስት ሲዘጋጅ ህይወታቸውን ሰጥተው በተቃራኒ የቆሙት እና ሻለቃ አድማሴ፣ ዳንኤል በላይነህ፣ ዘለሌ ፀጋስላሴ፣ መኩርያ ታፈሰ፣ አዳሙ ደገፉ እና ዮሐንስ አሰፋ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የአዲስአበቤ የምንግዜም ባለውለታዎቻችን ናቸው። ጊዜው ሲደርስ በይፋ እናመሰግናቸዋለን።
ዛሬ ደግሞ ሌላ የብስራት ዜና አለን። የአዲስ አበባ ክልልነት ጥያቄ ሳይመለስ እረፍት አላገኝም ያለው ዘለሌ ፀጋስላሴ በአውሮፓ/ሲውዲን የነበረ ህይወቱን ትቶ አዲስ አበባ ከትሟል። በዚህም ሳይወሰን ባልደራስን በመወከል በወረዳ 7 ይወዳደራል። ይህን ያወቀው ብልፅግና ስለ አዲስ አበባ የትግል እንቅስቃሴ ምንም እውቀት የሌለውን ወይንም በተቃራኒ ሊሰለፍ የሚችል ታዋቂ ግለሰብ ተቀናቃኝ አድርጎ አምጥቷል። የነፃነት ትግሉንም ለማዳፈን በኃይማኖት መከፋፈሉን ከወዲሁ ጀምረዋል።
እናም የወረዳ 17 አዲስአበቤዎች እንደ ሰጐኗ አይናችሁን ቁልፍ ጉዳያችሁ ላይ አተኩሩ። እንደ ዝንጀሮዋም “ቅድሚያ መቀመጫዬን” በሉ።
አዲስአበቤነት-ይለመልማል!
•አዲስአበባ- በትግላችን-ክልል-ትሆናለች!
Filed in: Amharic