>

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ ...!!! (D W)

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ …!!!
D W

ጥቃቱ የተፈጸመው ልዩ ወረዳውን ከኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን ሶሮ ባርጉዳ ወረዳ ጋር በሚዋስነውና ዳኖ በተባለ ቀበሌ ውስጥ የእርቅ ስረዓት እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ነው ተብሏል::
በስፍራው ነነበሩ የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ (DW) እንዳሉት ታጣቂዎቹ በሰዎቹ ላይ ግድያውን የፈጸሙት የአማሮ ልዩ ወረዳ እና በኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሐይማኖት አባቶች በእርቅ ጉዳይ ላይ ለመምከር በተሰባሰቡበት ወቅት ነው።
ከዕርቅ ስረዓቱ ታዳሚዎች አንዱ ነበርኩ የሚሉት አቶ ተክሌ ገነነ የተባሉት የቀበሌው ነዋሪ << ዳኖ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ከሰዓት በኋላ የተሰባሰብነው በአማሮ የኮሬ እና በጉጂ የአሮሞ ማህበረሰብ መካከል ቀደም ሲል የነበረውን ግጭት በእርቅ ለመፍታት ነበር ። የእርቅ ውይይቱን ለመጀመር ፀሎት ተካሂዶ አንዳበቃ ከየአቅጣጫው የተኩስ ድምፅ ተሰማ። ይሄኔ ተሳታፊው በሙሉ መሸሽ ጀመር ። በመሸሽ ላይ ከነበሩት ሰዎች መካከል በጥይት ተመተው ሲወድቁ አይቻለሁ ። ነገር ግን እኔም በድንጋጤና በሽሽት ላይ ስለነበርኩ በትክክል የሞቱና የቆሰሉ ሰዎችን አልቆጠርኩም >> ብለዋል ።
ዶቼ ቬለ (DW) በስልክ ያነጋገራቸው የአማሮ ልዩ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ይልማ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱት በልዩ ወረዳው ዳኖ ቀበሌ ውስጥ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሐይማኖት አባቶች በተሰበሰቡበት ነው።
በሰዓቱ ስብሰባው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ አመራሮቹን ወደ መድረክ ጋበዝኩ የሚሉት አቶ ኤሊያስ ታጣቂዎቹ ድንገት ዙሪያውን በመክበብ በከፈቱት የተኩስ እሩምታ የልዩ ወረዳው የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዳናቸው አቼላና አንድ የፖሊስ ባልደረባን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ወዲያው መሞታቸውን ተናግረዋል::
በተጨማሪም የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪና ሌሎች ስድስት ሰዎች በጥይት ተመተው መቁሰላቸውንም አቶ ኤሊያስ አስረድተዋል ።
ዶቼ ቬለ (DW) የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎችና በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን አመራሮችን ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካለት አልቻለም።
ያም ሆኖ የደቡብ ክልል መንግስት በተጠቀሰው ስፍራ ጥቃት ደርሶ የሰው ህይወት ማለፉን አረጋግጧል።  ጉዳት ለደረሰባቸው የሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድህረ ገጹ ገልዷል ።
በቀጣይም ክልሉ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመሆን በዜጎች ላይ ግድያ የፈፀሙ ሀይሎችን በመከታተል በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡
በደቡብ ክልል የአማሮ ልዩ ወረዳ እና በኦሮሚያ የጉጂ ዞን አዋሳኝ ቀበሌያት የታጠቁ ቡድኖች በመንግስት  የፀጥታ አባላትና በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጥቃቶችን ሲያደርሱ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ታጣቂዎቹ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በእነዚሁ አካባቢዎች ባደረሷቸው ጥቃቶች ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ከቀዬአቸው ተፈናቀለው ኑሯቸውን በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ አድርገዋል።
Filed in: Amharic