መስፍን አረጋ
‹‹ያማራ ብሔርተኝነት ለኢትዮጵያ ስጋት ነው‹‹ (ዐብይ አህመድ፣ በድብቅ ከተቀረጸ ቪዲዮ)
”Faild coup in #Ethiopia’s Amhara state was an attempt by ethnic nationalists to restore Amhara hegemony over all of Ethiopia that existed for several centuries prior to 1991. That dream is now permanently dead.” (ባማራ ክልል ውስጥ የተካሄደው ያልተሳካው የመንግሥት ግልበጣ (ወያኔ ጦቢያን እስከተቆጣጠረበት) እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለምዕተ ዓመታት ሰፍኖ የነበረውን ያማራ የበላይነት ለማስመለስ ያማራ ብሔርተኞች ያደረጉት ሙከራ ነበር፡፡ ይህ ህልማቸው ለዘለዓለም አሸለበ፡፡) ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen) በትዊተር (twitter)
The numerous tribes who inhabit the Ethiopian state are being forcibly kept from European colonialism by Abyssinian rulers whose aim is to act as champions of all black people so as to attack and destroy Western culture. (የጦቢያን አያሌ ብሔረሰቦች የነጭ ባርያ የመሆን ምርጫቸውን የነፈጓቸው፣ ዓላማቸው በነጭ የባህል (እና የሐይማኖት) መቃብር ላይ የጥቁርን ልዕልና መገንባት የሆነው የሐበሻ መሪወች ናቸው፡፡) Roman Prochaska (Abyssinia: The Powder Barrel, Vienna, 1935)
ዐብይ አህመድ ባማራ ልዩ ኃይል ላይ በዚያውም ደግሞ በጠቅላላው ባማራ ሕዝብ ላይ የማያቋርጥ የማጠልሸት (vilification) ዘመቻ የከፈተው የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ባማራ ፖለቲከኞች ወሳኝ ድጋፍ በጁ ካስገባበት ዕለት ጀምሮ ነው፡፡ ባንድ ራስ ሁለት ምላስ የሆነው ዐብይ አህመድ፣ ባንድ ምላሱ የአማራን ልዩ ኃይልና አማራን ስም የሚያጠለሸው፣ በሌላኛ ምላሱ ያማራ ሕዝብ በፀራማራው የወያኔ መንግሥት የደረሰበትን ከፍተኛ በደልና የዘር ማጥፋት ወንጅል በጽኑ የሚያወግዝና መቸም እንዳይደገም በትጋት የሚሠራ መሆኑን አዘውትሮ እየደሰኮረ ነው፡፡
በመጀመርያ ያማራ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያ ስጋት ነው ሲል በድብቅ በተቀረጸ ቪዲዮ ተደመጠ፡፡ ይህ የአማራ ብሔርተኝነት ግን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በዙርያው በማሰባሰብ የአውሮጳ ቅኝ ገዥወችን አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያረጋገጠ፣ በዚያውም ደግሞ ቅኝ ገዥወችን ካፍሪቃ አህጉር ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ለማስወጣት በር የከፈተ ከመሆኑም በላይ፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች የማንነት ኩራት (black pride) እና የጥቁር ብሔርተኝነት (black nationalism) መሠረት የሆነ አፍሪቃዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ያማራ ክልል መሠረተ ልማት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እጅግ በከፋ ሁኔታ ቆርቋዛ የሆነው፣ የወያኔ መንግሥት ሥራየ ብሎ ይከተለው በነበረው ፀራማራ ፖሊሲ ሳቢያ ሳይሆን፣ ክልሉ ያለችውን ሐብት በልዩ ኃይሉ ላይ ስለሚያጠፋ ነው የሚል አስገራሚ ንግግር ተናገረ፡፡ ይህን አስደማሚ ንግግር የተናገረው ደግሞ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል (ባንድ ዙር ብቻ የሰለጠኑ) ጥቂት ሺ ወታደሮችን ብቻ ያቀፈ አነስተኛ ኃይል መሆኑ ሳይጠፋውና፣ የሱ የራሱ የሆነው የኦሮምያ ክልል ግን ከሠላሳ በሚበልጡ ዙሮች በማሰልጠንና በማስታጠቅ ያማራ ክልልን ልዩ ኃይል ካስር እጥፍ በላይ የሚበልጥ ልዩ ኃይል ለማደራጀት በመቶ ሚሊዮኖች (ምናልባትም በቢሊዮኖች) የሚቆጠር ያሜሪቃ ዶላር ማፍሰሱን እያወቀ ነው፡፡ ይህን አስደማሚ ንግግር ተናግሮ አንድ ሳምንት ሳይሞላው ደግሞ፣ እራሱ ዐብይ አህመድ ዋናውና ቀንደኛው ተጠርጣሪ በሆነበት እጀግ አጠራጣሪና ከንካኝ ክስተት፣ ያማራ ክልል ዋና ዋና ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች፣ ሥራየ ብሎ የተፈጠረ በሚመስል ከጥቂት ሰዓታት ባልዘለገ ቀውስ (controlled chaos) ውስጥ ተረሽነው አለቁ፡፡ ያማራ ክልል ዋና ዋና አመራሮች መሞታቸውን እንዳረጋገጠ ደግሞ፣ ባሜሪቃ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያፍሪካ ወንበር ኃላፊ የነበረው፣ የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochaska) ፀራማራ አጀንዳ አራማጅ መሆኑ የሚጠረጠረው፣ በወያኔ አፍቃሪነቱ የሚታወቀው ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen) ያማራ የበላይነት ሙቶ ተቀበረ (Amhara hegemony … is now permanetly dead) በማለት በትዊተር (twitter) ገጹ ላይ ተሸቀዳድሞ አወጀ፡፡
በመጨረሻም በራሱ ባብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ፣ ያማራ ልዩ ኃይል በራሱ ባማራ ክልል ውስጥ ዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) ፈጽሟል የሚል ውንጀላ መጋቢት 6(2013) ላይ በመግለጫ መልክ በማውጣት ባማራ ልዩ ኃይልና ባማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተውን የማጠልሸት ዘመቻ ከፍተኛው ደረጃ ላይ አደረሰው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ይሄው የኦነጋውያን የውንጀላ መግለጫ ባብይ አህመድ የይስሙላ ፓርላማ ውስጥ ቃል በቃል እንዲነበብና ለመላው የኦትዮጵያ ሕዘብ በቀጥታ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡
ያማራ ሕዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር የተጋባ፣ የተዋለደና የተዛመደ፣ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን በላይ አቃፊና ደጋፊ የሆነ፣ ሁሉን በልኩ የሚይዝ ሆደ ሰፊ ሕዝብ ነው፡፡ ያማራ ልዩ ኃይል ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ ሊሳተፍበት የሚችልበት፣ በራሷ በኢትዮጵያ አምሳል የተዋቀረ ሕብረ ብሔራዊ ኃይል ነው፡፡ ሕብረ ብሔራዊነቱ ደግሞ ጠቅላይ አዛዡ ራሱ አብይ አህመድ፣ ኢታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ፣ አየር ኃይል አዛዡ ይልማ መርዳሳ የሆኑበት፣ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በኦሮሞወች ብቻ የሚመራው፣ በስሙ የኦትዮጵያ በግብሩ ግን የኦሮሙማ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት ካለው ሕብረ ብሔራዊነት እጅጉን የላቀ ነው፡፡ በዘረኝነት ለመወቀስና ለመከሰስ ከሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች የመጨረሻው ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ነው፡፡
ጎሰኝነት ላማራ ሕዝብ ባዕድ ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ ያማራን ሕዝብ የጎሰኞች ሰለባ የዳረገው ትልቁ ድክመቱ ቀድሞ በወያኔ አሁን ደግሞ በኦነግ የሚመሩ ጎሰኞች እንደ አሸን በፈሉባት ጦቢያ ውስጥ በበቂ ደረጃ ጎሰኛ አለመሆኑና በብሔሩ አለመደራጀቱ ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን የተደራጀን አማራ ማንም ሊያጠቃው እንደማይችል ምስክሩ በሮኬት፣ በታንክና ባዳፍኔ ይታገዝ የነበረው የወያኔ ጦር፣ ነፍስ ወከፍ ነፍጥ ባነፈጡ ነፍጠኞች ድባቅ መመታቱ ነው፡፡ አብይ አህመድ በተለይ፣ ኦሮሙማውያን ደግሞ ባጠቃላይ አጥብቀው የሚፈሩት ደግሞ ይህን የአማራን እምቅ ነፍጠኝነት ነው፡፡ ያማራን ልዩ ኃይልና ያማራን ሕዝብ በዘር ማጽደት ወንጀል አስከስሰው በምዕራባውያን ቦምቦች ሊያስቀጠቅጡት የተነሳሱበትም ምክኒያት ይሄውና ይሄው ነው፡፡
ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት፣ ያማራ ሕዝብ አስገድዶ መድፈርንና መሀን ማድረግን (raping and forced sterlization) የሚጨምር፣ በደንብ የተቀናበረና እጀግ አስከፈ የሆነ፣ ባያሌ መረጃወች የተደገፈና ለሰላሳ ዓመታት የዘለቀ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡ ይህን ወንጀል የፈጸመበት ደግሞ ዋናውና መሠረታዊ ጠላቱ ያማራ ሕዝብ ብቻና ብቻ መሆኑን በመሥራች ማንፌስቶው ላይ በይፋ በገለጸው በጎሰኛው የወያኔ መንግሥት ነበር፡፡ ባማራ ሕዝብ ላይ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጅል ዋናወቹ ምስክሮች ደግሞ የወያኔ ተዋጊወችን ለማስፈር ሲባል በመቶ ሺወች የሚቆጠሩ አማሮች የተጨፈጨፉባቸው፣ የጠፉባቸውና የተፈናቀሉባቸው ወልቃይትና ራያ ናቸው፡፡ በነዚህ ቦታወች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሕዝቡን አሰፋፈር (demographis) በከፍተኛ ደረጃ ስለቀየረው፣ እነዚህን የአማራ ቦታወች በግድ ወደ ትግራይ የቀላቀለው ወያኔ ከተወገደ በኃላ እንኳን፣ የትግራይ ብሔርተኞች የሕዝብ ብዝሃነትን እየጣቀሱ እነዚህን ቦታወች የምዕራብና የደቡብ ትግራይ ክፍሎች ናቸው ማለታቸውን ቀጥለውበታል፡፡
የዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ደግሞ ያማራን ሰቆቃ መስቀጠል ብቻ ሳይሆን እጅግ የከፋ አደረገው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ፣ የራሱ ያብይ አህመድ ክልል በሆነው በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በሺወች (ምናልባትም ባስር ሺወች) የሚቆጠሩ አማሮች በሚዘገንን ሁኔታ እንደ ከብት ታርደዋል፣ በመቶሺወች (ምናልባትም በሚሊዮኖች) የሚቆጠሩ አማሮች ደግሞ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ፣ ያፈሩትን ሐብትና ንብረት ባለበት ጥለው እየተባረሩ ከክልሉ ሸሽተው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ይህን ሁሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመው ደግሞ ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር እየተመጋገበ ተቀናጅቶ የሚንቀሳቀሰው፣ ኤርትራ በነበረ ጊዜ አብይ አህመድ መረጃ ያቀብለው የነበረው፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ደግሞ ከነ ሙሉ ትጥቁ እንዲገባ የተደረገው፣ የኦሮሙማ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው፣ በዳቦ ስሙ ኦነግ ሸኔ የሚባለው ኦነግ ነው፡፡
ስለዚህም ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት፣ የመላው ጦቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ ምክኒያት፣ በሱ ያገዛዝ ዘመን በኦሮምያ፣ በተመከልና በሲዳማ ክልሎች ባማራ ሕዝብ ላይ ለተፈጸሙት፣ እየተፈጸሙ ላሉትና ወደፊትም ሊፈጸሙ ለታሰቡት መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በቀጥታና በተዛዋሪ ተጠያቂ የሆነው ዐብይ አህመድ፣ ያማራን ጩኸት ቀምቶ እራሱ ገርፎ ራሱ እየጮኸ ያማራ ልዩ ኃይል ባማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ኦሮሞወች ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽሟል ተብሎ እንዲወነጀል የፈለገበት ምክኒያት ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ የኦነጋዊ ዘር አጥፊወች ሰለባ የሆነው ያማራ ሕዝብ፣ የኦሮሞን ዘር በማጥፋት እንዲከሰስ የተፈለገበት ምክኒያት ምንድን ነው? ባንድ በኩል ያማራ ልዩ ኃይል አብናቶቹ በደም ባጥንታቸው አስከብረው ባቆዩለት አገሩ ላይ ደንቡን ጠብቆ የትም ለመሰማራት ስላለው መብት እየደሰኮረ፣ በሌላ በኩል ግን እሱ ራሱ በሚመራው በኦሮሞ ብልጽግና እና በአጣየ ዙርያ ባስቀመጣቸው ኦነጋዊ እንደራሴወቹ አማካኝነት ያማራን ልዩ ኃይል በዘር ማጥፋት ለማስከሰስ ምን አነሳሳው?
ዐብይ አህመድ የወያኔን ጡት እየጠባ ባማራ ጥላቻ ተመርዞና ተሰቅዞ ያደገ፣ አማራዊ ናት የሚላትን ጦቢያን አፈራርሶ በሷ መቃብር ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳ አክራሪ ኦነጋዊ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ዐብይ አህመድ ማለት፣ በቀንደኛው ኦነጋዊ በለማ መገርሳ አማካኝነት ኦነጋውያን ቆጥረው ያስረከቡትን ጥያቄወች በመመለስ የኦሮሙማን አጀንዳ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚያስፈጽም የዘመናችን ሉባ ነው፡፡ እሱ ራሱ በግልጽ እንደሚናገረው ደግሞ ራሱን የሚመለከተው እንደ ሉባ (ንጉሥ) ነው፡፡ የለየለት ፀራማራና ፀረጦቢያ ለመሆኑ ደግሞ ከንግግሮቹ ጋር ፍጹም ተቃራኒ የሆኑት የእስካሁን ድርጊቶቹ ሊስተባበሉ የማይችሉ ማረጋገጫወች ናቸው፡፡
ዐብይ አህመድ ጦቢያን አፈራርሶ የኦሮሞ አጼጌ በመመሥረት የኦሮሙማ ሕልሙን ማሳካት የሚችለው ግን ባንድ በኩል ወያኔን በሌላ በኩል ደግሞ ያማራን ልዩ ኃይል አሸንፎ ካፈራረሳቸው ብቻና ብቻ ነው፡፡ ወያኔና ኦነግ ጦቢያን ለማፈራረስ እጅና ጓንት ቢሆኑም፣ የፈራረሰችውን ጦቢያን ሲከፋፈሉ ግን ዓይንና ናጫ እንደሚሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው:: በመሆናቸውም (ባብይ አህመድ እቅድ መሠረት) ጦቢያ ከመፈራረስ አፋፍ ላይ እስከምትደረስ ድረስ ከወያኔ ጋር መመሳጠሩንና መተባበሩን ይቀጥልበትና፣ ጦቢያ ልክ ልትንኮታኮት ስትል ግን በእንኩትኳቹ ክፍፍል ላይ ጦርነት እንዳያነሳ ራሱን ወያኔን ባፋጥኝ ያንኮታኩተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ላማራ ሕዝብ የተሰዋውን ጀነራል አሳምነው ጽጌን በመሰለ በሚታፈርና በሚከበር ጠንካራ መሪ እስከተመራ ድረስ (የኦሮምያ ልዩ ኃይልን፣ የኦነግ ኃይልንና በስሙ የጦቢያ የሚባለውን አብዛኛውን የመከላከያ ኃይልን የሚያጠቃልለው) ያብይ አህመድ የኦሮሙማ ኃይል ያማራን ልዩ ኃይል ሊያሸንፍ ቀርቶ በቅጡ ሊገዳደር እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡፡ ይህን ሐቅ ይበልጥ የሚያጠናክረው ደግሞ ወልቃይትና ራያ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ወደ አማራ ክልል ተመልሰው ተቀላቅለው፣ ክልሉን በሕዝብ ብዛትንና በተፈጥሮ ሐብትን ጨምሮ በሁሉም ረገዶች የሁሉም ክልሎቸ የበላይ ማድረጋቸው ነው፡፡ ስለዚህም (የአብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልም ይሳካ ዘንድ) ወልቃይትና ራያ በምንም ዓይነት ያማራን ክልል መቀላቀል የለባቸውም፣ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ደግሞ ባመችው ጊዜና ቦታ፣ ባመችው ዘዴ ድባቅ መመታት አለበት፡፡
ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ድባቅ መመታት ያለበት ግን ወያኔን ድባቅ እንዲመታ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ የኦነግ ሠራዊት ብዛቱ እንደጤፍ፣ መሣርያው በገፍ ቢሆንም፣ የወያኔን ጦር ማጥፋት ቀርቶ መግፋት ስለማይችል ነው፡፡ የኦነግን ውስጠ ሚስጥር አብጠርጥሮ የሚያውቀው የወያኔው ሰየ አብርሃ፣ ኦነግን ካምስት ሳንቲም አንቆጥረውም ያለው፣ ለማዋረድ ሲል ሳይሆን፣ ባለመታጠቃቸው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰላማዊ ሰወችን ጨለማን ተገን አድርጎ ከማረድና ከማወራረድ የዘለለ ሊጠቀስ የሚችል የውጊያ ችሎታም ሆነ ጀግንነት የሌለው፣ በባሩድ ጭስ በርግጎ በገደል የሚንኮታኮት አንኩቶ ሠራዊት መሆኑን ስለሚያውቅ ነበር፡፡
የኦነግ ሠራዊት ዕድሜው ከግማሽ ምዕተ ዓመት ያለፈ አዛውንት ሠራዊት ቢሆንም፣ በዚህ ረዥም እድሜው ግን፣ ፖሊስ ወይም ቀበሌ ጠባቂ የሌለባቸውን የገጠር ቀበሌወችና አናሳ ከተሞች በድንገት አጥቅቶ፣ የደም ጥማቱን ለማርካት የሚያርደውን አርዶ ባፋጣኝ ከመሸሽ ባሻገር፣ ጓንዴ ከታጠቀ ባላጋራ ጋር እንኳን ፊት ለፊት ገጥሞም ሆነ አሸንፎ አያውቅም፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ዐብይ አህመድ ይህን ቱሪናፋ የኦሮሙማ ጦር በቀጥታና በተዛዋሪ ያለ የሌለ መሣርያ ቢያስታጥቀውም፣ የወያኔን ኃይል ወይም ያማራን ልዩ ኃይል ፊት ለፊት ልግጠም ካለ ግን ትርፉ መሣርያውን ማስረከብ ብቻ እንደሚሆን ራሱ አብይ አህመድ ያውቃል፡፡
በማታለል ጥበብ እጅጉን የተካነው ሸፍጠኛው ዐብይ አህመድ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ እያንዳንዱንና ሁሉን የጦበያ ነገር በኬኛ ፖለቲካ አማካኝነት የኦሮሞ፣ በኦሮሞ፣ ለኦሮሞ በማድረግ ጦቢያን ከመፈራረስ አፋፍ አድርሷታል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ጦቢያን ለማፈራረስ እስካሁን ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ ዐብይ አህመድን በከፍተኛ ደረጃ ያግዝ የነበረው ወያኔ፣ በፍርስራሹ ክፍፍል ላይ ጦርነት እንዳያነሳ ባፋጣኝ የመወገጃው ጊዜ አሁን ነው ማለት ነው፡፡
ወያኔ ደግሞ (ምናልባትም ራሱ ዐብይ አህመድ በተዛዋሪ መንገድ ገፋፍቶትና አደፋፍሮት ሳይሆን አይቀርም) ባማራ ክልል ላይ ተረማምዶ ድፍን ጦቢያን የመቆጣጠር እቅድ ካወጣ በኋላ፣ ጥቅምት 2(2013) ላይ ማዕከላዊ እዝን በድንገት በማጥቃትና አማራ መኮንኖችን እየመረጠ በማረድ፣ ባማራ ሕዘብ ዘንድ የባሰ ቁጭት አሳድሮ፣ ዐብይ አህመድ ካጠመደለት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፡፡ ዐብይ አህመድ እንደገመተው ደግሞ የአማራ ልዩ ኃይል ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ወያኔን ብትንትኑን በማውጣት ያማራን ሕዝብ መታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ያብይ አህመድንም መንግሥት ከመገልበጥ አዳነው፡፡ ዐብይ አህመድ ግን ድለኛውን (victorious) ያማራ ልዩ ኃይል የተመለከተው ወሮታውን ሊከፍለው እንደሚገባው ኃይል ሳይሆን፣ ከወያኔ የሚቀጥለው ሁለተኛውና የመጨረሻው አደገኛ ኃይል አድርጎ ነው፡፡ ባብይ አህመድ እቅድ መሠረት ያማራ ልዩ ኃይል ወያኔን ድባቅ እንደመታ ተልእኮውን ስለጨረሰ (mission acomplished)፣ ወደ ኦሮሞ አጼጌ የሚያመራውን መንገድ ክፍትና ግልጽ ለማድረግ ባፋጣኝ ድባቅ መመታት አለበት፡፡
የዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ኃይል ግን የአማራን ልዩ ኃይል ፊት ለፊት ገጥሞ ድባቅ መምታት ቀርቶ ዝንቡን እሽ ሊለው አይችልም፡፡ ያማራ ልዩ ኃይል – መሣርያው ነፍስ ወከፍ ብቻ ቢሆንም – ዐብይ አህመድ ሊያሰማራው የሚችለውን አስካፍንጫው የታጠቀን ማናቸውንም የኦሮሙማ ኃይል በቀላሉ መመከት እንደሚችል ራሱ ዐብይ አህመድ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልሙን እንዳያውን (realize) የሚያደርገውን ይህን ያማራ ልዩ ኃይል ማስወገድ የሚችለው፣ በዘር ማጥፋት ወንጅል አስከስሶ ምዕራባውያን ባለ በሌለ መሣርያቸው እንዲረባረቡት ካደረገ ብቻና ብቻ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ደግሞ ዐብይ አህመድ ችግር አይኖርበትም፡፡ ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochaska) በትክክል እንዳስቀመጠው አማራወች ኩሩ ጥቁሮች (“champions of all black people”) በመሆናቸው፣ ያማራ ብሔርተኝነት ያውሮጳ ቅኝ ገዥነትን አድዋ ላይ ስለገታው (“forcibly kept European colonialism”)፣ በተጨማሪ ደግሞ አማራወች ማናቸውንም ነጭ የሚመለከቱት በሰውነቱ ብቻ እንጅ አንረውም አኮስሰውም ባለመሆኑ ሳቢያ፣ አማራወችን አምርረው የሚጠሉ ኸርማን ኮኸንን (Herman Cohen) የመሳሰሉ ፀራማራ ከፍተኛ የመንግስት ሹሞች በምዕራባውያን መንግስታት ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፀራማራ ሹሞች ደግሞ በስማበለው (hearsay) ብቻ ተመርኩዘው፣ ያማራን ልዩ ኃይል በዘር ማጥፋት ሰበብ የዘመናዊ መሣርያወቻቸው መፈተሻ አድርገው፣ ድምጥማጡን ለማጥፋት ከደስተኛ በላይ ናቸው፡፡
ዐብይ አህመድ ባማራ ክልል ላይ ያሰማራቸውን ኦነጋዊ እንደራሴወቹን በመጠቀም ያማራ ልዩ ኃይልን ሊከሰስበት በማይችልበት በዘር ማጥፋት ወንጀል በሐሰት ያስከሰሰበትም ዋና ምክኒያት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ ክሱን ለማቅረብ የይስሙላ ፓርላማውን የመረጠበት ምክኒያት ደግሞ፣ ለውንጀላው ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት፣ ይልቁንም ደግሞ ራሳቸውን ምዕራባዊ ያልሆኑ የጦር ወንጀለኞን አዳኝ አድርገው የሾሙት ምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ አሜሪቃኖች፣ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች) በግልጽና በደንብ እንዲሰሙት በማሰብ ነው፡፡
በመጨረሻም ለብአዴኖች ምክር ቢጤ፡፡
ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አገኘኹ ተሻገር … ላማራ ሕዝብ ብላችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ ብላችሁ አጭበርባሪው አብይ አህመድ እናንተን እንደሚያጭበረብረው ሊያጭበረብራቸው ለማይችል ዓይነ-ንሥር ልበ-ነብር ወጣት አመራሮች ስልጣናችሁን ባስቸኳይ አስረክቡ፡፡ አለበለዚያ የፊጥኝ ታስራችሁ፣ ወደ ሄግ (Hague) ተግዛችሁ፣ የምዕራባውያንን ጥቅም ለማስከበር በተቋቋመው ፍርድቤት (International Criminal Court) ገብታችሁ፣ ባማራነታችሁ ብቻ በሚጠሏችሁ ነጭ ዳኞች ፊት ቀርባችሁ፣ ያለጥፋታችሁ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተወንጅላችሁ፣ ዘብጥያ የምትወርዱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ በተለይም ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቅፈህ የሰቀልከው ዐብይ አህመድ ዘሎ ሳይከመርብህ በፊት ገሸሽ ብለህ እንዲፈጠፈጥ ብታደርገው፣ ራስህንና አማራን ብቻ ሳይሆን ድፍን ጦቢያን በልቶ ከማይጠረቃው ከስግብግቡ የኦሮሙማ ጅብ ታድናለህ፡፡
መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com