>
12:35 pm - Friday March 24, 2023

የእዳጋ ሀሙሱ አዛውንት እንባ (ነጻነት ሸዋንግዛው)

የእዳጋ ሀሙሱ አዛውንት እንባ

ነጻነት ሸዋንግዛው

ታሪኩ ፤  በትግራይ ክልል እዳጋሀሙስና አካባቢው ላይ ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ በማቅረብ ተልዕኮ ወደተሰማራ አንድ የሰራዊቱ ክፍል  ለስራ ጉዳይ  ስልክ በደወልኩ ጊዜ የተነገረኝ ነው ።
 
የእዳጋ ሀሙሱ አዛውንትና ታሪኩን ያካፈለኝ የሰራዊቱ አመራር ጊዜ ወስደው የሆድ የሆዳቸውን ብዙ የተጨዋወቱ ቢሆንም ፤ እኔ ግን እንዳንሰለች አንዷን ነጥብ ብቻ መርጫለሁ ፤ ጁንታውን በተመለከተ አዛውንቱ በምሬት የተናገሩትን ። 
 
የእዳጋ ሀሙሱ አዛውንት እንባ ብየዋለሁ መልካም ንባብ:-
ሲመቻቸው መሀል አዲስ አበባ ገብተው ከሚረሱን ፤ የግል ጥቅማቸው ሲነካ ደግሞ በየዋሻው ተወሽቀው ለጦርነት ከሚያጩን አዋራጆች ይልቅ ፤ በክፉውም በበጎውም ጊዜ እኛን መስሎ የኖረው ሠራዊት ነው – የእኛ።
“የራሷን ግልገል  የበላች ድመት ለዶሮ ጫጩት ምን ግድ አላት” እንዲሉም ፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሻለ ሀሳብ ባላቸው ታጋይ ልጆቻችን ደም እየታጠበ እዚህ የደረሰው ሰውበላ ቡድን ፤  መብራት አጥፍቶ በጥቁር ምሽት የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያን በደልና ግፍ ሲፈፅም ፤ የመሸው የእኛ ልብና ህሊና ውስጥም  ነበር።
አክሱም ፅዮን አስቀድሰን ፤ አልነጃሺ መሰጊድ ሶላት ሰግደን ፤ ስጋ ወደሙን ተቀብለን ፤ እንደየ እምነታችን ለፈጣሪያችን ተገዝተን ለምንኖረው ለእኛ ፤ ክቡሩ የዕምነት ቤታችንን የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ያደረጉት እምነት የለሾች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር።
ለሩብ ክፍለ ዘመን በቀረበ ዕድሜ ከሰራዊቱ ጋር የገነባነውን  ወዳጅነት ፣ የመሰረትነውን ትዳር ፣ ያፈራነውን የጋራ ሀብትና የቀለስናትን የጋራ ጎጆ በአንዲት ምሽት  በእብሪት የናዱብን ከሀዲዎች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር።
ለጊዜው የምናፈርሰውን መሰረተ ልማት መልሰን በሶስት ወር ውስጥ እንገነባዋለን አትጨነቁ ብለው ፤ ለሶስት ወር ያህል ጭለማ ውስጥ ያቆዩን ፤ ያለ ምግብና ውሀ በቤት ውስጥ አሽገውን የራሳቸውን ህይወት ለማትረፍ በየጢሻው የተደበቁት ከሀዲዎች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር።
ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ሲባል የመከላከያ ሰራዊቱንና የኤርትራን  ሰራዊት ወታደራዊ አልባሳት አምርተው በወንጀለኞች ግፍ ያስፈፀሙብን ግፈኞች  ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።
በለኮሱት የጦርነት እሳት ማህበራዊ ቀውስ የፈጠሩብን ፤ ቀውሱን ፈጥረውብንም ሰብአዊ እርዳታው እንኳን እንዳይደርሰን እንቅፋት የሆኑን ጉዶች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር።
“ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” እንዲሉ ግን ፤ ዛሬም  እንዳለመታደል ሆኖ ፤ የዚሁ ህሊና ቢስ ቡድን የውስጥና የውጪ ርዝራዦች ፤ በፕሮፓጋንዳዎቻቸው  ለይቅርታ ሳይሆን ለተጨማሪ በደል ፤  ለፍቅር ሳይሆን ለተጨማሪ ጠብና ጥላቻ  እያፈላለጉን ስለመሆኑ ስሰማ ፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሰዋ ልጄን አስታውሼ አልቅሻለሁ።
የእኔ ልጅ ፤ ልጄ በረሀ ወጥቶ የነበረው  ለዕኩልነት መሆኑን ሳስብና ፤  ይህ ቡድን ደግሞ ዕኩልነትን እንደ ውርደት ቆጥሮ ” አለቅነት ወይም ሞት ! ” ብሎ በስተርጅናም ተራራ ለተራራ መንጠላጠልን ገንዘቡ አድርጎ ሳይ ፤ ልጄን ያጣሁት አሁን እንደሆነ ያህል ተሰማኝ። ለካስ የተሰለፈው በአላማ ከማይመስሉት ጋር ኖሯል አልኩ።
በእነዚህ ሰዎች ህሊና ውስጥ  እውነትም ፣ እምነትም ፣ ፍቅርም ፣ ሚዛናዊነትም ፣ ግብረ ገብነትም ፣ ጥበብም ፣ ማስተዋልም የለም።
በእነዚህ ሰዎች ህሊና ውስጥ ታጭቆ የሚገኝ ሁለት ነገር ብቻ ነው ፤ የበዛ ዘረኝነትና አለቃ ሆኖ የመኖር ፍላጎት።
እንደልብ ሰውነቴ የሚታዘዝ ቢሆን ፤ ልጄ ያኔ የወደቀለትን አላማ ፤  ዛሬ እኔ  ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ተሰልፌ ባሳካሁት ነበር።
ነገር ግን እንደምታየኝ አቅመ ደካማ ነኝ ፤  የማውቃቸውን ወንጀለኞች ለመጠቆምና መንገድ ለማመላከቱ ግን ዛሬም ቢሆን አልሰንፍም።
የፈረሰ ቤቴን ሲጠግን ፤ እንኳን ወዳጅ ጠላትም ቢሆን እተባበራለሁ እንጂ ፤ የሚያፈርሰው ነው የኔ ወገን ብዬ ጎጆዬን ከሚያፈርሰው ጋር ስለምን እተባበራለሁ።
እነኚህ ሰዎች ዛሬም አሳቻ ሰአት እየጠበቁና ቤት ለቤት እየዞሩ ፤ “ኑ ሀገር እናፍርስ” በሚል ወጣቱን በድብቅ ለዕልቂት ለመመልመል እየሞከሩ ነው ፤ ምንም እንኳን ሰሚ ጆሮ ባያገኙም።
እንዲያም ስል ግን ፤ አንድ ፣ አንድ አላዋቂን ወይም ደግሞ እንደነሱ በዘረኝነት የታወረና ለእኩልነት ሳይሆን ለበላይነት መታገል የሚሻ ይጠፋል ማለቴ አይደለም።
የሆነው ሆኖ ፤ እኛ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ነን ። የፈረሰውን እንጠግናለን እንጂ ፤ ዳግም ለማፍረስ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለተጠመደው አጥፊው ሀይል ጆሮ አንሰጥም።
መከላከያ ሰራዊት
Filed in: Amharic