>

የፎረሙ የመጨረሻ መሳይ ሙከራና የሀገር ውስጥ ቀውሱ የሴራ ክሮች ወዴት ወዴት...?  (ሙሉአለም ገ/መድህን)

የፎረሙ የመጨረሻ መሳይ ሙከራና የሀገር ውስጥ ቀውሱ የሴራ ክሮች ወዴት ወዴት…? 

 

ሙሉአለም ገ/መድህን

ትላንት ቀትር ላይ የG7 ሀገራት (አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ካናዳ) በውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸው በኩል  “ተደራደሩ” የሚል መግለጫ ማውጣታቸውን ተመለከትኩ።
“ተደራደሩ” የሚሉት የሀገረ-መንግሥቱን ዘብ ከጀርባ በመውጋት ታሪክ ይቅር የማይለውን ክህደት ከፈጸመው ትህነግ ጋር ነው። ያውም አቅሙ ተዳክሞ የተከዜ ሸለቆ ሽፍታ ከሆነ ኃይል ጋር ነው “ተደራደሩ” የሚሉት።
ከልምድ ካየነው የG7 ፎረም አባል ሀገራት ያነሱት ሃሳብ በቀላል አይታይም:: ይህ ፎረም ብዙ ጊዜ እንዲህ ዐይነት ውሳኔም ሆነ ሃሳብ ሲያቀርብ አልተለመደም:: ፎረሙ ከ1970ዎቹ መግቢያ ጀምሮ በይበልጥ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በሞኒተሪንግ ዘርፍና በነዳጅ ጉዳዮች የሚመክርና የፋይናንስ ቀውሶችን በፎረሙ ተጽዕኖ ስር ባሉ ተቋማት ቁጥጥር መግራት/መንዳት የሚፈልግ ስብስብ ነው። ፎረሙ በፖለቲካዊ ያውም  ከባድ የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸመን ኃይል ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር ቀርቦ ይደራደር ሲል በፎረሙ ታሪክ ብዙም ያልተለመደ እንግዳ አካሄድ ነው። ይሄ መንገድ ለፎረሙ የመጨረሻ አማራጭ ይመስላል::
ይህም ሲባል በክስተት ደረጃ ከሚገለጸው የፎረሙ አባል ሀገራት በሚዘውሯቸው ቡድኖች ውስጥ ‘ልዩ ልምዶች’ በመነሳት ነው። አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣… በተናጠልም ይሁን በጋራ በጸጥታው ምክር ቤት ማስፈጸም ያልቻሉትን ጉዳይ (G 8 ጨምሮ) ወደዚህ መሰል ፎረም አምጥተው ከመከሩበትና ሊያጠቁት የፈለጉትን አካል የሚያሳጣ ሃሳብ/Statements ካወጡበት በኋላ መልሰው የተገብሩበት አጋጣሚዎች አሉ።
ማሳያ:- ሰርቢያና ሊቢያ ተጠቃሽ ናቸው። በዩጎዝላቪያ መፈራረስ ሂደት ውስጥ (በጦርነቱ ፍጻሜ አካባቢ) ሰርቢያ በኮሶቮ የነባራትን የተሻጋሪ ግዛት ትስስር ለማጠናከርና በኮሶቮ የሚኖሩ ሰርቦችን ህልውና ለመታደግ ጦሯን በዚያው አስፍራ የነበረ ቢሆንም (1999) በ G 8 አባል ሀገራት (በዋናነት አሜሪካና ብሪታኒያ) ጫና ነበር ከኮሶቮ ለመውጣት የተገደደችው፡፡ በኔቶ መሪነት ለሰባ ሁለት ቀናት (NATO air Campaign) የተፈጸመው የአየር ድብደባው በሰርቢያ ጦር ላይ ያደረሰው ጉዳት ብዙ የተጻበት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ስሙ ጎልቶ ከሚነሱ የፎረሙ አባል ሀገራት ቀዳሚው ነው፡፡ ኮሶቮ ውስጥ ከኔቶ ጦር በተጨማሪ በመጨረሻው ሰዓት የሩሲያ ጦር የገባ ቢሆንም የሰርቦችን ጉዳት ለመታደግ ረፍዶበት ነበር፡፡
በዚያ ውሳኔ ሰርቦች ጦራቸውን እስኪያስወጡ በሚል በአውሮፕላን ሁለት ወር ተኩል ያል ሲደበደቡ በአንጻሩ 800,000 የአልባኒያ ስደተኞች ኮሶቮ ላይ እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡  በተመድ የተሾመ አስተዳደር የኮሶቮን መንግሥት ሲረከብ አልባኒያዎችን በሚጠቅም መልኩ ነበር እንዲዋቀር የተደረገው፡፡  በሚሎሶቪች ይመራ የነበረው የቤልግሬድ መንግሥት  ከአውሮፕላን ድብደባው ለመሸሽ ከመሞከር ውጭ አቤት ቢል ሰሚ አልነበረውም፡፡ ከነዚህ ክፉዎች እጅ ቀን አይጣልህ አባቴ!
ሊቢያ የሆነውም ተመሳሳይ ነው፡፡ የያኔው የፈረንሳዩ መሪ Nicolas Sarkozy እና Barack Obama  በጸጥታው ምክር ቤት ማስወሰን ያልቻሉትን የአየር ድብደባ በዚሁ ፎረም አጣድፈው ነበር አጀንዳ ያደረጉት፡፡ እንዴውም ፈረንሳይ ከጸጥታው ም/ቤት የአስቸኳይ ስብሰባ በፊት ነበር ድብደባውን የጀመረችው። ቀጥሎም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በኩል ‹Security Council authorizes ‘all necessary measures’ to protect civilians in Libya› የሚል የውሳኔ ሃሳብ (ለማሟያ) አሳለፉ፡፡ በኔቶ አባል ሀገርነት ስም ሊቢያን ወደአመድነት ለመቀየር አሜሪካና ፈረሳይ የጦር አውሮፕላኖችን በገፍ ሲያሰልፉ ጣሊያን የአየር ክልሏንና ለ Air Campaign መነሻ ቤዝ ሆናለች፡፡
25 February, 2011 ለጀመረው የሊቢያው አመጽ 17 March,2011 ነበር በፎረም የጨረሱትን ለይስሙላ (UNSC Resolution 1973) ውሳኔውን በጸጥታው ምክር ቤት ደረጃ ያስወሰኑት፡፡ ሲጠምዱህ እንዲህ ነው፡፡ ያላቸውን አደረጃጀት ከፎረም እስከ ካውንስል አሰልፈው ይዘምቱብሃል፡፡ እንደ ጋዳፊ ለኃያላኑ ተንበርካኪ መንግሥት ሳትሆን የውስጥ ቅራኔዎችህን በጥበብ ካለለፍክ ሀገርህ ከፍረስት አንተም ከትቦ ስር ተጎተህ ከመውጣት አትድንም፡፡ ቀሪው ነገር ታሪክ ነው! በፍርስራሽ ህንጻ ስር ድንኳን የጣሉ የሀገር ውስጥ ስደተኞች ያምናውን ቀን እየናፈቁ ዘንድሮን ሲራገሙ ታያቸዋለህ፡፡ ሲመጻደቁብህ አይጣል ነው፤ ሀገርህን  ካፈረሱ በኋላ ከሆነ የሕግ ትምህርት ቤታቸው ሆነው American Bombing of Libya: An International Legal Analysis በሚል በቁስልህ ላይ ጨው ይነሰንሳሉ፡፡
እናልህ የትላንቱን የ G7 ፎረም ‹ተደራደሩ› መግለጫ የመጨረሻው የፎረሙ መንገድ አካል ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥርጣሬ እያሰብክ፤ ግብጽን ያዘለችውን አሜሪካንና ትህነግን ለምስራቅ አፍሪቃ ግርድና ስትጠቀምበት የኖረችውን ብሪታንያንና በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላይ የነበራትን አደናቃፊነት እያሰላሰልክ፤ በጀግኖች አርበኞቻችን ተጋድሎ፣ ድል በመንሳት ጥቁር ሰው መሆኑን ያስመሰከርንባት ጣሊያን የዚህ ቡድን አባልነቷን ደምረህ ከዓለም አቀፉ ቁማር ጋር አውጠንጥነው፡፡
በአናቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ የሚያደርገው ጥረት (የዲፕሎማሲ ስብራቱን ሳንዘነጋ) እና የሀገር ውስጥ የዘር ጥቃቶችንና የአመጽ ኃይሎች መበራከት፤ እንዲሁም በገዥው ኃይል ውስጥ የተፈጠረው ቅራኔ ከሚገመተው በላይ ማጎንቆሉ ነገሮች መቆሚያ በሌለው መልኩ tensions escalate በማድረግ ላይ መሆናቸውን ታዝብና የወለጋውን ውጥርት መርምረው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በስምንት ግንባሮች ውጊያ ገጥሟል የሚለው የጠቅላዩ የዛሬ ንግግር ‹ቀደዳ ነው› ብሎ ማለፉ ከፖለቲካ  አዋቂ አይጠበቅም፡፡ ቢያንስ የጠቅላዩ ንግግር ለነዚህ የ G 7 ፎረም አባል ሀገራትና ከጀርባቸው ላዘሏቸው ግብጽን ለመሰሉ ጠላቶቻችን ጭምር መልስ መሆኑን አስታውሰህ ነገሮችን ማሰላሰሉ ይጠቅማል፡፡
ጠቅላዩ በውጭ ጠላት ፈጠራ ድጋፍ እየሸመቱ አልያም ሕዝቡን እያስቦኩት ነው የሚል ጥርጣሬ መያዝ ያንተ መብት ቢሆንም፤ የአባይ ፖለቲካንና የቀጣናውን ውስብስብነት ከዐብቹ የጎረምሳ ዲፕሎማሲ ጋር ማዛመድህን ግን አትርሳ!
እናማ የነዚህ ድምር ውጤት ምስጋና ለሩሲያ፣ ቻይናና ሕንድ እንጅ በ UNSC የታጣውን የውሳኔ ሃሳብ በፎረሙ በኩል ለማሳጣት (ለማብሰል ልትለው ትችላለህ) ‹‹ተደራደሩን›› እንደ መፍትኄ ሃሳብ ማቅረባቸውን ያዝልኝ! ከማን ጋር? ከትህነግ! ቀጥሎ ምን ሊሉ ነው ‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሠላም ወዳድ አይደለም› ከዛስ ጉዳዩን ወዳ ጸጥታው ምክር ቤት ይወስዱና ‹Security Council authorizes ‘all necessary measures’ to protect civilians in Ethiopia› የሚል ውሳኔ ሀገር ላይ ይወስኑብሃል!! ይሄን ነው ቁማር ማለትስ! አውቃለሁ የሆነ አክቲቪስት ትዝ ብሎሃል… ተከተለኝ ታገኘው የለ!?
አሁን ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው ክልል ውስጥ ያለውን ሀገራዊ ቀውስ ከተከዜ ሸለቆው ሽፍታ ህልውና ጋር ነጠብጣቦችን ለማገናኘት ሞክር…
እናልህ ሰሞነኛውን የወለጋውን ጭፍጨፋ ብዙሃኑ ከተረዳበት ትንተና ሰፋ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል:: ምንልባትም እነዚያ ሀገራት  የኢትዮጵያ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ላይ ያላቸውን ኔትዎርክ ተጠቅመው የፈፀሙት ይሆናል:: እዚያ ክልል አደገኛ ሥውር መንግሥት (Deep State) እንዳለ ደጋግመን ገልጸናል፡፡ የኃይል አሰላለፉም ለጉድ ነው፡፡ ትህነግ እንዲመለስ የሚፈልግ ቡድን አለ፡፡ ብልጽግና ውስጥ የአቻዎች አውራ ሆኖ ሄጂሞኒ ፈጥሮ መቀጠል የሚፈልግ አለ፤ የኩሽ መንግሥት የሚያልምም አይጠፋም፡፡ በርግጥ ቁጥሩን አላውቅም እንጅ እውነተኛ ወንድማማችነትን በመፍጠር ጠንካራ ኢትዮጵያ መገንባት የሚያልሙ የኦሮሞ ልጆች አይጠፉም፤ መዋቅራዊ አቅማቸውን ግን አትጠይቀኝ! ዜሮ ከፊቱ የሆነ ነገር ካልገባ ምን ዋጋ አለው? ፖለቲካ መነሻው ሃሳባዊነት ቢሆንም እንኳ ገቢራዊነት መመዘኛው ነው፡፡
እዛ ክልል ያለውን የኃይል መከፋፈል እያሰብክ ስውር መንግሥቱ ከምዕራባውያኑ ጋር (ሰሜን አፍሪካዊቷን ግብጽ በቅንፍ አስገባልኝ)  ሊኖረው ስለሚችለው ግንኙነት (ቢያንስ የፋይናንስ፣ የፖለቲካዊ ጫናና የፕሮፖጋንዳ) ጉዳይ ጠርጥር!
ወጉን ላስጠረው መሰል!
ከላይ ያነሳሁትን ሃሳብ ደግሜ የሴራ ክሮቹን ወደመስፋት ልዝለቅ፡- ሰሞነኛውን የወለጋውን ጭፍጨፋ ብዙሃኑ ከተረዳበት ትንተና ሰፋ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል:: እኒያ ሀገራት ውስጥ አንዳቸው ጭፍጨፋው እንዲፈጸም አድርገው ቢሆንስ? ለምን ዓላማ? ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው::
አንደኛ፡- አማራን እና ኦሮሞን ወደለየለት የእርስ በርስ ግጭት በማስገባት ብልፅግናን ማፈርስና ማዕከላዊ መንግሥቱን በጣም አዳክሞ ትህነግን ማዳን ይፈልጋሉ::
ሁለተኛ፡- “ከእኛ አፈንግጧል” ብለው የሚያስቡትን የኢትዮጵያ መንግሥት አዳከመው ወይም ነጣጥለው ወደ ራሳቸው ጎራ መመለስ የሚችል ኃይል ሥልጣን ላይ እንዲወጣ ይፈልጋሉ::
ሦስተኛ፡- ሁለተኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በታሰበለት የጊዜ ገደብ ይካሄዳል የሚለውን የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም እያሰብክ የአባይ ፖለቲካንና ከውስጣዊ የአንድነት እጦት ሊመነጭ የሚችለውን መዘዙን ልብ በልልኝ! በአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ ግብጽን ከጀርባዋ አዝላ አህጉሩን የምትዘውረው አሜሪካ በዚህ ወቅት ሚናዋ ምን ሊሆን እንደሚችል አትርሳ! የትኛው ባለቅኔ ነበር “የአባይ አሳ እሾህ ይበዛበታል” ሲል የተቀኘው? እንጃ ብቻ የአባይን አሳ ተስገብግበህ አትበላውም በጥንቃቄ ካልሆነ!!
ማስታወሻ:- ጃል መሮ “ጲላጦስ ነኝ” ብሎ በአደባባይ ለሚያቀርበው ክርክር ጨርሶ ጆሮ መንፈግ የፖለቲካ አዋቂ ባህሪ አይደለም:: መጠየቅ ባለባቸው ጉዳዩች ይጠየቃል፤ ግን ደግሞ ኦነግ ሸኔም በለው አባ ቶርቤ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኃይል ክፍፍል የወለዳቸው አናኪስቶች ናቸው፡፡ ‹ማን ‘ለማ’ን ቡድን አማራውን ሲጨፈጭፍ ኖረ?› የመንግሥት ኃይሎችና ተቋማት ላይ ስለምን ጥቃት ሲፈጽሙ ከረሙ ለሚለው ጥያቄ ገለልተኛ አካል ገብቶ ያጣራው ይሆናል መልሴ!
አማርኛ ቋንቋ ላይ ቀሽም ካልሆንክ በነጠላ ሥርዓተ ትምዕርተ ጥቅስ የሚቀመጡ ቃላትን መፍተል ተፈቅዶልሃል፡፡
መፍትኄ አለ? 
የሰሜኑን ዘመቻ ለፖለቲካ ዓላማ ከማጓተት ይልቅ ለሀገር ህልውና ሲባል በሙሉ ዘመቻ ተረፈ-ትህነግን ጨርሶ መደምሰስ፡፡ ለሕግ የሚቀርቡትን ለቃቅሞ ማቅረብ! መደበኛዋን ትግራይ እንዲመራ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜዊ አስተዳደር ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ ሽኩቻ ማያዳግም መፍትኄ መስጠት (የአድዋ ሥርወ-መንግሥት አይደለም ለትግራይ ለምስራቅ አፍሪቃም ጠንቅ ነው! የነጋ ልጅ የጀርባ መደብ ብቻ ሳይሆን አካሄድ አደገኛ ነውና ጊዜ ባይሰጠው) ሁሉም ነገር እንደሚጻፈው ቀላል ባይሆንም ሀገር ነችና ከዘመን ቡድተኝነት (Aka ተረኝነት) ነጻ ሆኖ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅምና የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን ያለበት መሆን አለበት!
ሌላው የምዕራብ ኢትዮጵያ (ወለጋና መተከል) ወታደራዊ ዘመቻዎች ሙሉ በሙሉ በፌደራል ደረጃ በሚመራና ከልዩ ዘመቻና ከሪፐብሊካን ጋርድ ኃይሎች በተውጣጣና በተቀናጀ የጸረ-ሽምቅ ግብረ ኃይል ለግዳጅ ማሰማራት፤ ይህ ግዳጅ ኢታማዡሩን ጨምሮ እነ ሌ/ጀኔራል አበባው ታደሰ አባል በሆኑበት በሚሊተሪ ካውንስሉ እንዲመራ ማድረግ ይገባል። የፌዴራሉ የፖለቲካ አመራር የአፈጻጸሙን ሪፖርት እየተከታተለ እንዲገመግም በማድረግ (ወታደራዊ ዕውቀት ባይኖራቸው አንኳ ሂደቱን በበላይነት ማወቅ ይኖርባቸዋል) ዘመቻው እንደተጠናቀቀ ቀጥሎ በወለጋና መተከል የተፈጸሙ የንጹሃንን ጭፍጨፋ በጊዜና በድርጊት አፈጻጸም አንድ በአንድ እየሰፈረ የሚያጣራ ገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲያካሂድ ማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር ላይ ተጠያቂነትን ለማንበር ዕድል ይሰጣል!! ምርጫውን ረስቸው አይደለም! ነገሩ ያለው ወዲህ ነው፥ የኢትዮጵያ ችግር በምርጫ የማይፈታ ከመሆኑ አኳያ ነው መፍትሄው መታየት ያለበት! (በደህንነት ስጋት ምርጫ ከማይካሄድባቸው የምርጫ ወረዳዎች የወለጋ ዞኖች ከፍ ያለ ቁጥር እንደሚኖራቸው እሙን ነው)
***
ማሳረጊያ!
ነገር ሲበዛ የተነሳንበትን ዋናውን ነጥብ እንዳንስት፥ የፎረሙን ወጥመድና በሌሎች ሀገራት የነበረውን አሉታዊ የታሪክ ማህደር እንዳትረሱት!  አለቃ Ze Addis ን ምንጭ ጠቅሼ ሌላም ነገር ላስታውሳችሁ፥ እንግሊዝ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል አትፈልግም። ቀድሞ የያዘችው የጸና አቋም አላት፤ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረችው ማርጋሬት ታቸር፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ አለብን ብላ በፓርላማ አስጸድቃ፣ የኢትዮጵያን መንግስት ለማፍረስ መንግስቷ የነደፈውን ዝርዝር እቅድ እዚህ ሊንክ ላይ አለ፤ ሊንኩን ዳብሰው ያንብቡት፡፡
የፎረሙን አባል ሀገራት ፈትሻቸው፥ ያው ጀርመን ጀርመን ነች! የዬኻን ክራፍን ተልዕኮ ሳንዘነጋ ከሃምሳ ዓመቱ ታሪክ ብናጣቅስ በመካነ እየሱስ በኩል ኦነግን የመደገፍ ታሪክ ያላት ስለመሆኗ እናውቃለን። ጣሊያንን ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጀምረን ለኢትዮጵያ ምን እንደምታስብ እናውቃታለን። አሜሪካ የአረብ አብዮትን ተከትሎ ሊቢያና መካከለኛው ምስራቅ ላይ የፈጸመችውን ስህተት እኛ ላይ አትደግመውም ማለት የሚቻል አይደለም!  ያኔም አስተዳደሩን ይዘውት የነበሩት ዲሞክራቶች ነበሩ፤ ዛሬም እነሱ ናቸው። እንደኢትዮጵያ የኛ የውስጥ ጥንካሬ የሚወስነው ቢሆንም የነገሮች አመጣጥ እጅግ አስፈሪ ነው። ለሁሉም  የአማራ ልሂቅ ከሰማይ በታች የትኞቹንም የፖለቲካ  አማራጮች ሊፈትሽ ይገባል። ሌሎች  ኢትዮጵያዊያንን የማስተባበር ኃላፊነት ወስዶ በጋራ መቆም ወይስ እንደሀገር ለመቆም የራስን ቤት ማጠናከር? …ወዘተ ስትራቴጅክ አማራጮች ከዛሬና ነገ ዕድልና ፈተናዎች አንጻር ሊተነተኑ ይገባል!!
Filed in: Amharic