>

ብአዴን እስካለ ድረስ ሲዋረድ የሚኖረው አማራ ዛሬም በኦሮሞ ልዩ ኃይልንና በኦነግ ጦር በምስራቅ ወለጋ እየተጨፈጨፈ ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ብአዴን እስካለ ድረስ ሲዋረድ የሚኖረው አማራ ዛሬም በኦሮሞ ልዩ ኃይልንና በኦነግ ጦር በምስራቅ ወለጋ እየተጨፈጨፈ ነው! 
አቻምየለህ ታምሩ
 
ብአዴን የሚባለውን የሕወሓት ፍጥረት በዐቢይ አሕመድ የሚመራው ኦሕዴድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ያዋረደውንና ያራከሰውን ያህል የፈጠረው ሕወሓት እንኳን በሀያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያን ያህል ያዋረደውና ያራከሰው አይመስለኝም። ባለፈው ሳምንት ባለፈው ዓመት የተፈጠረው የሲዳማ ብል[ጽ]ግና ፓርቲ የኦሮሞ ብልጽግና በክልሉ ያካሄደበትን ወረራ ድባቅ መትቶ መቀልበሱን ነግሮናል። ሽንፈት የተከናነበው የኦሮሞ ብልጽግናም ልዩ ኃይሉ  ድጋሚ የሲዳማን ክልል እንደማይወር ለሲዳማ ብልጽግና ዋስትና በመስጠት ባካባቢው ያሰፈረውን ልዩ ኃይል ወደ ሌላ ቦታ አዛውሮታል።  
 
አርባ አመቱን ያከበረው ብአዴን በኦሕዴድ ፊት ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን የሲዳማ ብልጽግና አንድ መቶኛ ያህል ሞገስ የለውም። ከኦሕዴድ ጋር ተዋህጄ ብል[ጽ]ግናን ፈጥሬያለው የሚለው ብአዴን የኦሮሞ ልዩ ኃይል አማራንና አማርኛን ከኦሮምያቸው ለማጥፋት በየቀኑ ወለጋ ውስጥ በአማራ ሕጻናትና ሴቶች ላይ ፍጅት ባካሄደ ቁጥር ሽመልስ አብዲሳ ቢሮ እየተጠራ “አብረን ለመስራት ተስማምተናል” የሚል መግለጫ አብሮ እንዲያወጣ ይደረግና መግለጫው በዜና ተነቦ ሳያልቅና እግሩ ከሽመልስ አብዲሳ ቢሮ ሳይነቅል የኦሮሞ ልዩ ኃይል የአማራ ተወላጆችን ከቦ እንደ ደገዛ እየጨፈጨፈ መሆኑን ግፉዓን ከወለጋ በሚያሰሙት የሲቃ ድምጽ መሰማት ይጀመራል። 
 
ባለፈው ሳምንትም እንዲሁ ውርደት የማይሰለቸው ብአዴን ሺመልስ አብዲሳ ቢሮ እንደመጣ ተደርጎ በዝግ ትዕዛዝ ሲቀበል ሰንብቶ “የአማሮችን ግድያ ለማስቆም ከኦሕዴድ ጋር ተስማምቻለሁ” የሚል መገለጫ ከኦሕዴድ ጋር እንዲያወጣ ከተደረገ በኋላ የወጣው መግለጫ በዜና ተበስሮ ሳያልቅ እነሆ ዛሬም በኦሮሞ ልዩ ኃይል ሌላ ዙር የአማራ ፍጅትና ጭፍጨፋ በወለጋ እየተካሄደ እንደሆነ ከእልቂቱ በተዓመር ሕይወታቸውን ያተረፉ ግፉዓን ሸሽተው ከሚገኙበት ጫካ ከሚያስሙት የድረሱንል ጥሪ ለማወቅ ችለናል። 
 
በዛሬው እለት ብቻ በምስራቅ ወለጋ ውስጥ በተለምዶ መንደር 10 በሚባለው አካባቢ የኦሮሞ ልዩ ኃይልና የኦነግ ጦር በጋራ በከፈቱት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ  የአማራ ተወላጆች ተፈጅተዋል።   
 
ከአርባ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአማራ ሕዝብ  ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን የሲዳማ ብልጽግናን አንድ መቶኛ ያህል እንኳን ክብር ያጣው እወክለዋለሁ የሚለው ብአዴን በኦሮሞ ብል[ጽ]ግና ዘንድ እጅግ የተናቀና የተዋረደ ሎሌ በመሆኑ ነው። በኦሮሞ ብል[ጽ]ግና እጅጉን የተዋረደውና የተናቀው ብአዴን በአማራ ሕዝብ ላይ ተጭኖ እስከቀጠለ ድረስ ጠላቶች የአማራ  ጭፈጨፋ፣ ሞትና ውርደት ገና ይቀጥላል። ብአዴንም እንደልማዱ ከኦሕዴድ ጋር መግለጫ እንዲሰጥ ወደ ሺመልስ አብዲሳ ቢሮ መጠራቱ፤ ካድሬዎቹም ከኦሕዴድ ካድሬዎች ጋር በዝግ መከሩ ተብሎ ትዕዛዝ ለመቀበል ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ መመላለሳቸው ይቀጥላል. . 
Filed in: Amharic