>

“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ” (ሕወሓት) እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ አስተላለፈ  (ኢ ፕ ድ) 

“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ” (ሕወሓት) እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ አስተላለፈ 
(ኢ ፕ ድ) 

“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ” (ሕወሓት) እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ አስተላልፏል፡፡
“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ” (ሕወሓት) እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የስራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩ በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባው ወስኗል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የበርካታ ዜጎች  ሕይወት ጠፍቷል፤ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ንብረታቸውም ወድሟል፡፡
እነዚህ ድርጅቶች ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የነበረው የጥፋት ተግባር የሽብር ወንጀል ተግባራት በመሆናቸው ድርጅቶቹ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የደረሰን መግለጫ  እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መሰየም
ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ እና የመብት መከበር ጥያቄዎች እና ትግል አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ መሆኑ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ እንዲሁም ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል።
እነኚህ ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል። እነዚህ ሁሉ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
እነኚህ ጥቃቶች ከጀርባቸው የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ ዓላማን ወይም ግብን ለማሳካት በማሰብ በንጹሐን ዜጎች እና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት እነኚህ ጥቃቶች የተለያዩ ፈጻሚ አካላት ነበሯቸው። ከጥቃቶቹ ጀርባ ግን በዕቅድ፤ በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሰው ኃይል ሥልጠና በመደገፍ፤ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ። ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፤ የማዳከም እና የማፍረስ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች በቅጥረኝነት እየተጠቀሙባቸው እንድሆነም ግልጽ ነው።
እነኚህ ድርጅቶች ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አወጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። እነዚህን የሽብር ተግባራት የፈጽሙ ድርጅቶች አባላትና እና ደጋፊዎቻቸውን እንደግለሰብ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን የሽብርተኛ ድርጅት አድርጎ በመሰየም በሕጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል።
ስለዚህ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ወሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል።
እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 23 መሠረት በተመሳሳይ ተግባር በተሰማሩ እና በዚህ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት ከተሰየሙት የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ትብብር፤ ትሥሥር ወይም የሐሳብ እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ይህ ውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚ ይሆናል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት
ሚያዚያ 23/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic