>

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ! (ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ)

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!

ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ

የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል የምናከብረው በተስፋና በተጋድሎ መካከል ውስጥ ሆነን ነው። በአንድ በኩል የሀገራችንን ትንሣኤ አሻግረን እያየን በተስፋ፣ በሌላ በኩል ከፊታችን የተደረደሩ ፈተናዎች ከትንሣኤው እንዳያስቀሩን ከባድ ትግል እያደረግን ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጌታችን ስለ ሕመማቱ፣ ስለ ስቅለቱና ስለ ትንሣኤው ቀድሞ የነገራቸውን እውን ሆኖ እስኪያዩት ድረስ በታላቅ ተስፋና በከባድ ተጋድሎ ውስጥ ማለፋቸውን እናውቃለን። በተሰቀለ በሦስተኛው ቀን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱና ለተከታዮቹ የተገለጠው በአንድ ጊዜ አይደለም። ምክንያቱም በትንሣኤው ሰዓት አንዳንዶች አንቀላፍተው ነበር፤ አንዳንዶች ስለመነሳቱ እርግጠኞች ስላልነበሩ ወደ ተቀበረበት ሥፍራ አልሄዱም። እንቅልፍና ጥርጣሬው በጊዜ ሂደት ሲሸነፍ ግን ሁሉም የክርስቶስን ትንሣኤ ማየትና መስማት ችለዋል።
የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዛሬ ለብዙዎች ጭለማ መስሎ የሚታይ፣ ቢነገር የማይሰማ፣ ቢዳሰስ የማይጨበጥ መስሎ ሊቆጠር ይችላል። ዳሩ ግን ይሄ የሀገራችንን ትንሣኤ እውን ከመሆን የሚቀር አይደለም። ሁላችንም ይሄን እውነት አይተንና በእጃችን ዳብሰን እስክናረጋግጥ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ያ ጊዜ መምጣቱና እውን መሆኑ ግን አይቀርም። እስከዚያው፣ ለጥቂቶች የታየው ቀስ በቀስ ለብዙዎች እየታየ፣ በምዕራፉ ሀገራዊ ትንሣኤአችን እየተበሰረ ይቀጥላል።
ከፊታችን ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ከሚበሰርባቸው ምዕራፎች አንዱ ነው። ለዘመናት ዴሞክራሲን ስንናፍቅ ኖረንአል። መንገዳችን በጭለማና በሁከት፣ በእሾህና በአሜኬላ፣ በስቃይና በሞት የተሞላ ነበር። ነገር ግን ከሞት በኋላ ትንሣኤ እንደሚመጣ፣ ከስቃይ በኋላ ደስታ እንደሚከተል፣ ከጨለማ ወዲያ ብርሃን እንደሚመፈነጥቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ተምረን ለሀገራችን ዴሞክራሲ መሳካት ተስፋ እንደሰነቀን የብርሃን ውጋጋኑ የሚታይበት የተራራው አናት ላይ ደርሰናል።
በተመሳሳይ ለዓመታት በስስት ስንጠብቀው የነበረው፣ በላብና በወዛችን የገነባነው የሕዳሴ ግድባችን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በመጪው ሐምሌ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ለማድረግ ተዘጋጅተን በጉጉት እየጠበቅን ነው። ይበልጥ ወደ ተስፋችን በቀረብን ቁጥር ፈተናውም በርትቶብን ቆይቷል። እኛ በዚህ በኩል ምርጫ ለማድረግ እና ግድባችንን በስኬት ሞልተን ለማጠናቀቅ ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር ትግል ስናደርግ፣ ፈታኞቻችንም በሌላ አቅጣጫ እኛን የሚያሰናክሉበትን የመጨረሻ ድንጋይ ከመወርወር እንደማይቆጠቡ መዘንጋት አይገባም።
ዛሬም ሽፍቶች በመንገዳችን ላይ አደጋ እየጣሉ ትንሣኤአችንን እንዳናይ የቻሉትን ያደርጋሉ፤ እያደረጉ ነው። ወገኖቻችንን እየገደሉ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው እያፈናቀሉ፣ ሰይጣናዊ ተልእኳቸውን ገፍተውበታል። ወገባችን ዝሎ ከትንሣኤ ጉዟችን እንድንሰናከል ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን ምንም ያህል የሞት በትራቸውን ቢሰነዝሩብንም ድርጊታቸው የክፋታቸውን ጥግ ከመግለጥ ውጭ በዚያ መንገድ የሚያሳኩት አንድም ዓላማ የለም። የጀመርነው ትግል እስከ ቀራኒዮ እንደሚጓዝ በቅርቡ ይገባቸዋል። ለጊዜው የፈተኑን ቢመስሉም በመጨረሻ ኢትዮጵያዊነት አሸንፎ የሀገራችን ትንሣኤ ይበሠራል። ያኔ እነሱ ከትንሣኤው ብርሃን ፊት የመቆም አቅም እንዳይኖራቸው ሆነው ይወድቃሉ።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
አሁን የቆምንበት ጊዜ የትንሣኤ ብስራቱ ከመበሰሩ በፊት ባሉት የመጨረሻዎቹ አስጨናቂ ቀናት መካከል ነው። በእነዚህ ቀናት ብዙ ነገሮች ይለዋወጣሉ፤ ከማንጠብቃቸው አቅጣጫዎች ጭምር ፈተናዎች ይመጣሉ። በክርስቶስ ዙሪያ ካሉት አንዳንዶች ውልደቱና እድገቱን፣ ትምህርትና ተዓምራቱን፣ ግርፋትና ስቅለቱን እያዩ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት በጽናት ቆይተዋል፤ ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች ደግሞ ሄደው ሄደው ከትንሣኤው በፊት ባለው አንድ ሳምንት ውስጥ ከማመን ወደ አለማመን፣ ከመከተል ወደ መሸሽ፣ አንድ ገበታ ከመቁረስ አሳልፎ እስከመስጠት በደረሱ የስሜትና የድርጊት ለውጦች ውስጥ አልፈዋል።
ከትንሣኤው ዕለት በፊት ያለችውን ልዩ ቀን ኢትዮጵያውያን ‹ቅዳም ስዑር – የተሻረች ቅዳሜ› ይሏታል። ይህቺ ዕለት አወዛጋቢ ዕለት ናት። አወዛጋቢ ያደረጋት ብዙ ነገሮች ግልጽ ያልሆኑባት ቀን በመሆኗ ነው። ድል ያደረገው ማነው? አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነውን? ለሥልጣናቸው ሲሉ ፈርደው ለሮማውያን የሰጡት ሊቀ ካህናት ቀያፋና ሐና ናቸውን? ወይስ በእሥራኤል ላይ ያላቸው ጥቅም እንዳይነካ ሲሉ የሞት ፍርድ የፈረዱበት ሮማውያን ናቸው? ወይስ ሁሉም ተባብረው ለሞት ያበቁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ያሸነፈው?
አማኞችም ሆኑ በሩቅ ትምህርቱን ሰምተው ተአምራቱን አይተው ያደነቁ ሁሉ አንድ ተስፋ ነበራቸው። የመበለቷን ልጅ፣ የኢያኢሮስን ልጅ እና አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣ አይተዋል። ስለዚህ ክርስቶስ ወዲያውኑ ከሞት ይነሣል ብለው ጠብቀው ነበር። ዓርብ አልፎ ቅዳሜ ሲተካ ግን ብዙዎች ተስፋ ቆረጡ። ‹ክርስቶስ ከሞት ይነሣል› የሚለው ነገር ውሸት መሰላቸው። ይበልጥ ተስፋቸው እንዲመናመን ያደረጉ ሁለት ተጨማሪ ምክንያቶችም ነበሩ።
ጌታን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ በነገሩ ተፀፅቶ ብሩን ወርውሮ ቢጥልም ያመጣው ለውጥ ግን አልነበረም። እስከ ዓርብ ዕለት ድረስ ‹በርታ በርታ፣ አፍርስ አፍርስ› ሲሉት የነበሩት ሁሉ ከቁም ነገር አልቆጠሩትም። ከውስጥ ሆኖ ለጠላቱ የሚሠራ ሰው ክብሩና ጥቅሙ ለአጭር ጊዜ መሆኑን አሳይቷል። በይሁዳ ድርጊት ቀያፋና ሐና ስቀዋል፤ ሮማውያን ቀልደዋል። ይሁዳ የሠራው ነገር ስሕተት መሆኑን ዘግይቶ ቢናገርም በእነ ቀያፋና በሮማውያን ዘንድ ለውጥ አላመጣም። አልተፀፀቱም፤ አልተገረሙም። ይህ አማኞችን ግራ ያጋባ አንዱ ምክንያት ነበር። ምን ቢተማመኑ ነው የይሁዳን ፀፀት ከቁብ ያልቆጠሩት? በቃ ነገሩ አልቋል ማለት ነው? ብለው እንዲያስቡ አጋጣሚው ምክንያት ሆኗል።
እንዲሁም አይሁድና ሮማውያን በየራሳቸው በክርስቶስ መቃብር ላይ ማኅተም አሳርፈው ነበር። ማኅተም የአንድን ነገር መጠናቀቅ፣ ፈጽሞ መዘጋት ያሳያል። ከተማዪቱ በዚህ ወሬ ተናውጣ ነበር። እውነቱን የያዙ ሰዎች ጥቂት ሆኑ። ጥቂት ብቻ ሳይሆን በሐሰተኞችና በሽብር ዜና ነዥዎች ድምጽ ተዋጡ። እውነት መንምና የምትበጠስ መሰለች። አንዳንዶችም ለሦስት ዓመታት ከክርስቶስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ካዱት። ተታልለን ነበር ብለው አመኑ። ብዙዎች የሐሰት ምስክሮች ሆነው መጡ። በደስታ የሰከሩበትንና በነጻነት እልል ያሉበትን ወቅት ዘነጉት። በዕለተ ዓርብ አይሁድና ሮማውያን ያሳዩት ጭካኔ የብዙዎችን ልብ ሰለበው። ‹ከክርስቶስ ጋር ሲተባበር የተገኘ ቤቱ ይበረበራል፤ ሀብቱ ይመዘበራል፤ አንገቱ ይቆረጣል› ተብሎ የታወጀው ዐዋጅ የብዙዎችን ሐሞት አፈሰሰው። ብዙዎች መካዳቸው ብቻ ሳይሆን፤ እውነቱን የተቀበሉት ጥቂቶች እንኳን በአደባባይ ለመመስከር ፈሩ። ቅዝምዝሙንና ክፉውን ቀን ከመጋፈጥ ይልቅ ጎንበስ ብለው ማሳለፍን መረጡ። ጎርፉ እስኪያልፍ እንደ ወንዝ ዳር ቄጤማ ድምጽ አጥፍተው መነጠፍን ወደዱ።
ቅዳሜ እንዲህ ያለችው ቀን ነበረች። አወዛጋቢ ቀን። ደግሞም እጅግ ረዥም ጊዜ ነበረች። የመከራ ቀን ረዥም ነው እንደሚባለው። ከዓርብ 9 ሰዓት እስከ እሑድ እኩለ ሌሊት፣ ወደ 33 ሰዓት ትሆናለች። ሮማውያን የእሥራኤል ነገር አለቀ ብለው ደመደሙ። አይሁድ የወንጌል ነገር አበቃላት ብለው ፈጸሙ። አማኞች ግን በሁለት ሐሳብ ተወጥረው ቀሩ። በአንድ በኩል በውዥንብር፣ በሌላ በኩል በተስፋ። እምነታቸው ወደ ተስፋ እንዳይወስዳቸው ውዥንብሩ ይጠልፋቸዋል። ውዥንብሩ ጠልፎ እንዳያስቀራቸው እምነታቸው ተስፋ ይጭርባቸዋል።
ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ከስቅለት በኋላ እና ከትንሣኤ በፊት ያለችውን ቅዳሜ ትመስላለች። በውዥንብርና በተስፋ መካከል የምትዋዥቀውን ቅዳሜ። በአንድ በኩል በዓርብ ዕለቱ ጭካኔ የምትሳቀቅ፤ በሌላ በኩል የእሑዱ ትንሣኤ ይመጣ ይሆን? ብላ የምትጠይቅ። በአንድ በኩል ሀገር ማጥፋት የሚፈልጉት ሮማውያን፣ የገዛ ሀገራቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም ብለው ከሚያፈርሱት የአይሁድ ማኅበር ጋር ሆነው የፈጠሩት ግንባር አሸንፎ ይሆን? ብላ የምትጠራጠር፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጧ ባለው እምነቷ ለመጽናት የምትጥር።
ቅዳሜ ከጠዋት ወደ ተሲዓት፣ ከተሲዓት ወደ ምሽት እየተራዘመ ሲሄድ እሑድ እስከመጨረሻው የቀረች መስላ ነበር። የሞት ቀን ሲረዝም የትንሣኤ ሌሊት መቼም የማይደርስ መስሎ ነበር። ግን እንደዚያ አልሆነም። ምን ቢረዝም ቅዳሜ ያልቃል፤ የሐሰት ጉም ምንም ያህል አየሩን ቢሞላው፣ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ይተንናል።
ኢትዮጵያ አሁን ከከበቧት መከራዎች፣ ግድያዎች፣ ውዥንብሮችና ጩኸቶች በላይ ናት። በርግጥ እንደ ቅዳም ስዑር የውዥንብሩ ጊዜ የረዘመ መስሎ ይሰማል። ምን ቢረዝም ግን መጨረሻ አለው። ሳይጨርስ ይጨረሳል። የይሁዳ የውስጥ ተንኮል፣ የነ ሊቀ ካህናት ቀያፋ የቡድን ሥራ፣ የሮማውያንም ሀገር የማፍረስ ዓላማ እሑድ እኩለ ሌሊት ብትንትኑ ወጣ። ክርስቶስ ሞትና መቃብርን ድል አድርጎ ሲነሣ፣ ታሪኩ ሁሉ ተቀየረ። ያለቀ የመሰለው ነገር ሁሉ እንደገና ተጀመረ። የተዘጋው መቃብር ተከፈተ፤ የተቆረጠው ተስፋ ተቀጠለ። አሸናፊዎቹ ተሸናፊ ሆኑ። የተዘጋው መቃብር፣ የታተመውም ማኅተም ከንቱ ሆኖ ቀረ።
ቅዳሜ ተሻረች። ስሟም ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተባለ። የትንሣኤዋ እሑድ ግን ተሾመች። ቅዳሜ አበቃች። እሑድ ግን ይሄው እስከ ዛሬ እንደቀጠለች ናት። በየዓመቱም በድምቀትና በእልልታ እናከብራታለን። የኢትዮጵያ ትንሣኤም እንደዚሁ ነው። ከውዥንብሯ ቀን በኋላ ይመጣል። አሸነፍናት ያሏትን ሁሉ ድል አድርጋ፤ የተዘጋባትን ሁሉ ከፋፍታ፣ የተገነዘችበትን አውልቃ ጥላ፣ ባዶ መቃብር ትታ፣ ተነሥታ እናያታለን።
የተወሩት የሐሰት ወሬዎች ሁሉ እውነት ይመስላሉ። ያለነው ቅዳሜ ውስጥ ስለሆነ። ነገ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ሲሆን ግን እነዚህ አየሩን የሞሉት ወሬዎች ሁሉ ሐሰት መሆናቸውን ዓለም ሁሉ ያያል። የተፈጸሙብን ግፎችና፣ የተደረጉብን ስቅላቶች ሁሉ ኢትዮጵያን ለማቆም ያሰቡ መሆናቸውን ትውልድ ሁሉ በግልጥ ይረዳል። ኢትዮጵያ ሁሉን አሸንፋ ትነሣና ጠላቶቿን ሁሉ ታሳፍራለች። አይቀርም – ይህ የኢትዮጵያ እውነት ነው።
በድጋሜ መልካም የትንሣኤ በዓል!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዚያ 23፣ 2013 ዓ.ም.
Filed in: Amharic