>

እውን ኢትዮጵያ ወደፊት እየሄደች ነውን ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

እውን ኢትዮጵያ ወደፊት እየሄደች ነውን ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


‹‹ አምሃራ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው፡፡ አምሃራ አንድ ጠላት ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ጠላት ነው፡፡ ስለሆነም አምሃራን ማጥፋት አለብን፡፡ እርምጃ ካልወሰድን ትግራይ በነጻነት መኖር አትችልም፡፡ለመመስረት አሁን  የምንፈልገውን መንግስት እንዳንመሰረት ዋነኛው እንቅፋታችን አምሃራ ነው፡፡ ›› ( የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ማኒፌስቶ)

Amhara is the enemy of the Tigray people. Amhara isn’t only one enemy, but it is a double enemy. Therefore, we must destroy Amhara. Tigray can’t live freely unless action is taken. Amhara is a major obstacle to the government we want to create now. (Tplf Manifesto).

ይህ ከላይ ያሰፈርኩት መራር እውነት ተጽፎ የሚገኘው በትግራይ ደደቢት በርሃ ተጸንሶ በተወለደው በወያኔ (ተሃህት) መስራቾች ሰነድ ወይም ባዘጋጁት የድርጅታቸው ማኒፌስቶ ውስጥ  ነበር፡፡ ይህ የፖለቲካ  መርዝ  ከተጻፈ ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን እየተጠጋው ነው፡፡ ይህ በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መስራቾችና መሪዎች የተቀመመው መርዝ ዛሬ ኢትዮጵያን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያን ቋንቋና ጎሳ ላይ ባደረጉ ክልሎች በመከፋፈል  አንድነቷን  በማዳከም፣ታሪኳን በመከለስና በማጥፋት፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ወደ እድገት ጎዳና እንዳትራመድ ያደረገ ታላቅ ሴራ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና አንድነቷን ለማላላት በመጀመሪያ አማራ የጠባለውን ብሔር ማዳከም፣እንዲሁም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቀኖናን መበረዝ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጦር ማፈራረስና በምትኩ በራሳቸው አምሳል የሀገር መከላከያ ሰራዊት መመስረት የወያኔ ድብቁ አጀንዳ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ በ1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያን የጦር ሃይል የደርግ ሰራዊት በሚል መበተኑ በሀዘን የሚታወስ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶችን ለሁለት ከመከፋፈል አኳያ( የውጭ ሀገርና ሀገር ቤት ሲኖዶስ በሚል ማለቴ ነው፡፡) የወያኔ እጅ ረዥም ነበር፡፡ በቤተክርስቲያኗ ሳይቀር የዘረኝነት መርዙን ረጭቶም ነበር፡፡

መግቢያ

ኢትዮጵያ የሚወርድባትን መአት ዝም ብላ ከተቀበለች ወይም በጀርባዋ መሸከሙን ከቀጠለች፣ከተደቀነባት ብሔራዊ አደጋ ለመውጣት ወይም ለመዳን የሚረዱ የአዋቂዎችን  ምክረሃሳብ (ማስጠንቀቂያ) ጆሮ ዳብ ልበስ ካለች፣የሀገሪቱ ብሔራዊ ሉአላዊነት ( አንደነቷ) አደጋ ላይ ሊወድቅ ይቻለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጎሳ ማንነት ብቻ የተከበረባት ሀገር ከመሆን ባሻግር ኢትዮጵያውያን ዜጎቿ ሁሉ በግዛቷ ውስጥ እኩል መብትና ፍትህ ማግኘት የማይችሉባት ሀገር ከሆነች የጎሳ አስተሳሰብ የበላይነት የሆነባት ሀገር መሆን እድሏ የሰፋ ነው፡፡ ይህም ማለት ቀሪው አለም በሰውነት ደረጃ ላይ ሲቆም እኛ እንደ ጥንቱ እንደ ጠዋቱ ከጎሳ አስተሳሰብ መውጣት ሳንችል እዛው እየዳከርን አለም በስልጣኔ ገስግሶ ቀድሞን ይሄዳል ይነጉዳል፡፡ ይራመዳል፡፡ ለመለያየት ያዘነበሉ የጎሳ ክልሎች ሊፈጠሩ ይቻላቸዋል፡፡ በአጭሩ አክራሪ ጎሰኝነት አስተሳሰብ ስር ይሰዳል፡፡ በውጤቱም ኢትዮጵያ እንኳን ወደፊት ለመራመድ ቀርቶ ባለችበት፣ በነበረችበት ቁመና ለመገኘት ያስቸግራታል፡፡

 

If Ethiopia fails to heed the warnings, and delays imbuing citizens with a strong sense of a common or shared national identity/destiny, then archaic identities will inevitably become dominant. Centrifugal forces will prevail

የአንድ ሀገር ህዝብ ስለ ዜግነት መብት፣ባህል፣ሙዚቃ፣ ቋንቋ ( ለአብነት ያህል አንዳንድ በሀገራችን የሚነገሩ ዋና ዋና ቋንቋዎች የግእዙን ፊደል መጠቀም ሲገባቸው የውጭ ሀገር ላቲን ቋንቋ ፊደል መጠቀማቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡) ወዘተ በተመለከተ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ካልቻሉ ወንደማማችነት ማስፈን አይችሉም፡፡ ትብብር ይጎድላቸዋል፡፡ የውጭ ወራሪን እንኳን ለመከላከል በአንድነት ለመሰለፍ ይቸግራቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ባለው ሁኔታ ሀገሪቱ ወደፊት ለመራመድ ያዳግታታል፡፡ ኢትዮጵያ ምድር ላይ የተሞከረው የጎሳ ፖለቲካ እንደማያዋጣ ባለፉት ሰላሳ አመታት በገቢርም በነቢብም የታየ ይመስለኛል፡፡  ስለሆነም በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በፖለቲካ አዋቂዎች መዘጋጀት አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህም የጎሳ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን የሚያስታርቅ ወደ መሃል መንገድ የሚወስድ የፖለቲካ ፈውስ ለማግኘት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኤሊቶች ( የጎሳ ፖለቲካ ያዋጣንል የሚሉና ሌሎች ከጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለብን የሚሉ ምሁራን አንድ ላይ ቁጭ ብለው ወደመሃል መንገድ የሚወስዳቸውን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲፈልጉ ኢትዮጵያ አበክራ ትማጸናለች፡፡ አሊያ ግን በነበረው መቀጠል እጅጉን አዳጋች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም ፡፡ ታላቁ የጋናው ምሁር አቼቤ እንዳለው ማእከሉ ከወደቀ ( ከተናጋ)  ሁላችንንም የሚይዘን ነገር የለም፡፡ ‹‹ ነገሮች ሁሉ ይወድቃሉ፡፡››

. As Achebe wrote: when the center collapses, or, no longer holds, “things fall apart…”

ችግሩ

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ምክንያት ውስጣዊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡( የታሪካዊ ጠላቶቻችን እና የምእራባውያን ስውር ሴራን ሳንዘነጋ ማለቴ ነው) የችግሩ ስረ መሰረት ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ በተቋም ደረጃ ወይም ከመንግስት አኳያ ( በተለይም ከ2010 ዓ.ም. በፊት ኢትዮጵያን የገዘቱ የወያኔ-ኢህአዲግ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች)  የኢትዮጵያን የረዥም ዘመን ታሪክ በአደባባይ የካዱ ነበሩ፡፡ ከዚህ ባሻግርየኢትዮጵያን ታሪክ እያዛቡ ለሚጽፉ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያንን ለማፋጀት የውሸት ትርክት በውብ ቃላት በማሰናዳት ይጽፉ ለነበሩ እንደነ ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብርአብ ( ግብረእባብ) ለመሰሉ እኩይ ሰዎች  የሚሰጡት ምላሽ አለንበረም፡፡ ራሳቸውም በተለይም የወያኔ ኢህአዲጊ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ አመት ታሪክ ብቻ ነው በማለት በአደባባይ ተናግረውም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳላ በአንዳንድ ክልሎች የሚቀርባቸውን የግእዝ ፊደል ከመጠቀም ይልቅ ለቋንቋቸው የመረጡት የላቲን ፊደልን ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደው ዝም ብሎ የተሰራ አልነበረም፡፡ ለዘመናት ሚሽነሪዎች በረጩት መርዝና የወያኔ ኢህአዲግ በአማራው ብሔር ለዘመናት ባካሄደው የጥላቻ ዘመቻ ሌሎች የጎሳ ፖለቲከኞች እና የጎሳ ፖለቲካ ተከታዮቻቸው በአማርኛ ቋንቋ ላይ ሚዛኑን የሳተ ጥላቻ በማሳደራቸው ነበር፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ወያኔ እና የትግል አጋሮቹ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫኑት ህገመንግስት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በህገመንግስቱ መሰረት በአንድ የጎሳ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት፣ የመንግስት ባለስልጣን ለመሆን፣የመንግስት ስራ ለማግኘት ወዘተ ቅድሚያ የሚሰጠው ለጎሳው ተወላጆች ነው፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ ደግሞ የሀገሩ ባለቤቶች እኛ ብቻ ነን የሚሉ አክራሪ የጎሳ ብሔረተኞች ኢትዮጵዊ ዜጎችን ለዘመናት ከኖሩበት የእርሻ መንደር ያፈናቅላሉ፣ የሰው ህይወትም ይቀጥፋሉ፡፡ ይሄን ሁሉ ችግር የቀፈቀፈብን ህገመንግስቱ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ተጋሩ እና ኦሮሙማ የሚባሉት ጽሰ ሃሳቦች እንደው ድንገት ዝም ብለው የመጡ አይደሉም፡፡ እነኚህ ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ መሬት ውስጥ ቀብሯቸው የሄደው የግዜ ቦምብ ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ስለመሻሻሉ በተመለከተ ከብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አኳያ ምንም አይነት ፍንጭ ባለመታየቱ ኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ህሊናን የሚረብሸው ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ከሰማኒያ በላይ ጎሳ( ብሔረሰብ) በሚኖርባት ኢትዮጵያ ሁሉም ጎሳዎች ( ብሔሮች) የራሳቸውን መስተዳድር መጠየቅ የመቻላቸው ሀቲት ነው፡፡ እስከአሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ አስር ጎሳ ክልሎች እንዳሉ ልብ ይሏል፡፡ ብዙዎቹ የራሳቸውን የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ባህል ሉአላዊነት እንደሚፈልጉ ማስተዋል ለሚችል ሰው ለመገንዘብ አይከብደውም፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ክልሎች ራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ መብት የሚሰጠው አደገኛ አንቀጽ በዚች ምድር ላይ በሚገኙ ሀገራት አይገኝም በኢትዮጵያ ግን ይገኛል፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ 

አሁን ያለው እና መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅማት ባለፉት ሰላሳ አመታት ውስጥ በገቢርም፣በነቢብም የታየ መራር እውነት ይመስለኛል፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ህዝብን ከፋፍሎ ለመግዛት አመቺ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻግር የእኛን መዳከም እና አንድነታችን መላላቱን አድፍጠው ለሚጠብቁት የጂኦፖለቲካ እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ቢሆን እኛን ለማጥቃት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ካመቻቸውም የጥቃት ሰበዝ ይምዙብናል፡፡ በእጅጉ ያጠቁናል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵውያን ሁሉ በመተባበር ኢትዮጵዊ ፍልስፍና በፖለቲካው ስርአት ውስጥ ለማስፈን  በሰላማዊ መንገድ፣ በሰለጠነ መንገድ መታገል ይኖርብናል፡፡ ሌሎች የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም ሀገራት ይህን እንዲያደርጉ መጠበቅ አስቂኝ ይሆናል፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጩሀት፣ ምሁራን የምርምር ስራ ኢትዮጵያን አያድናትም፡፡ በጎሳ ፖለቲካ አኳያ የተሰለፉ ወይም በጎሳ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርአት ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰራሄ መፍትሔ ያመጣል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች በኢትዮጵያ ምድር ላይ ስር ሰደዋል፡፡ ስለሆነም በሁለቱም የፖለቲካ ጎራ የተሰለፉት ኢትዮጵያውያን ( በጎሳ ፖለቲካ ስርአትና ኢትዮጵዊ የፖለቲካ ስርአት አኳያ የተሰለፉትን ማለቴ ነው) ግዜ ወስደው በሰከነ መንፈስ ወደ መሃል የሚያደርሳቸውን የፖለቲካ መንገድ ማበጀት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ነገ በጣም ሩቅ ነው፡፡ አደጋው ከፊታችን ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ በተለይም የክልል ጥያቄን ማለቴ ነው፡፡ዛሬ ሲዳማ አዲስ ክልል እንደሆነው ሁሉ( ሁላችንም ሲዳማ አዲስ ክልል ለመሆን እንደበቃ የአይን ምስክሮች ነን)  ነገ ተነገወዲያ ኢሮብ ወዘተ የክልል ይገባኛል  ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም የዚቺን ታሪካዊት ሀገር አንድነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵዊ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰቡ መሪዎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኢትዮጵያ መንግስትና የተፎካካሪ የፖለቲካ መሪዎች በሰከነ መንፈስ ፣ በቅን ልቦና እንዲነጋገሩ እንማጸናለን፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የተመሰረተችው በሴሜቲክና ኩሽቲክ የስልጣኔ ሃሳብ እንደሆነ በብዙ የታሪክ አዋቂዎች እውቅና ቢቸረውም፣ ይህ የሴሜቲክና ኩሽቲክ የስልጣኔ ውጤት የግለሰብ መብትን ያከብር እንደነበር ከታክ እንማራለን፡፡ ዛሬ ይህን የታሪክ እውነት የማየቅበሉ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ አንዳንዶቹ ባለማወቅ፣ ብዙዎች ደግሞ የታሪክ እውነታውን መቀበል አይፈልጉም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ አጼ ዘራ ያቆብ ከአውሮፓውያን ፈላስፎች  (European Enlightenment thinkers. ) በፊት ቀድሞ ስለ የግል መብት መጠበቅ አስፈላጊነት ይናገር ወይም ጽፎ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ አንድነት የሚቆረቆሩትን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ በደምሳሳው አሃዳዊ ወይም ጀብደኛ ብሎ መሰየም ከባድ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሀም ብቻ አይደለም የታሪክም ስህተት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ አንደነት አቀንቃኞች አውፓውያን ቅኝ ገዥዎችን ያሸነፉ፣ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ባርነት ስር እንዳንወደቅ ያደረጉ መሆናቸውን የአሁኑ ትውልድ በጥልቀት መረዳት አለበት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያዊነት አንድነት መንፈስ አፍሪካና ቀሪው የጥቁር አለም ቅኝ ገዢዎቸን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየ ምልክት ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተጨቆኑ አለም ህዝቦች እንደ ምልክት ወይም ማንነት ተጠቅመውበት ከባርነት ያወጣቸው መሳሪያ ነበር፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት የተጨቆነው አለም ነዋሪዎች በራሳቸው ፈቃድ፣ ማንም ሳያስገድዳቸው የተቀበሉት ማንነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ዙሪያ ብርቱ ጥላቻ ያደረባቸው ቅኝ ገዢ የነበሩና የእነርሱ አሻንጉሊት ገዢዎች ብቻ ነበሩ፡፡

በነገራችን ላይ አሁን ባለንበት የፖለቲካ አስተሳሰብ የምንቀጥል ከሆነ የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና እየቀዘቀዘ፣ የጎሳ ፖለቲካ ይበልጥ ስር እየሰደደ መሄዱ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ከዚህ ባሻግር ምንም እንኳን የገዢው ቡድን ስም ተቀይሮ ‹‹ ብልጽግና ›› የሚል ስያሜ ቢሰጠውም  ብዙዎች በጎሳ ፖለቲካ መስመር መንጎድን መርጠዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ብሔራዊ ፍላጎትና የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለማየት ተስፋ ያደረባቸውን ኢትዮጵያውያን ለአንደነቷ መከበር የሚያደርጉትን ጥረትና ፍላጎት ሊያሰናክለው ይቻለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዝሃነታችን በትክክል ገቢራዊ እንዲሆን የምንፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ሰብዓዊነት እና ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ልዩነትን ብቻ በማጉላት የጎሳ ፖለቲካ ተከታይ መሆኑ የትም አያደርሰንም፡፡ የምንፈልገውን ምኞትም አያሟላልንም፡፡

በአጭሩ በጎሳም ሆነ በፖለቲካ ልዩነት ጎራ ለይተን መጋጨቱ፣በጎሳ ከረጢት ውስጥ መደበቁ፣ እኛ እና እነርሱ መባባሉ፣ አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ለመባባል መንፈሳዊ ወኔ ከከዳን ፣ የሰብዓዊ ስሜት በውስጣችን ከሌለ፣ ወዘተ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት ላሰፈሰፉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራችን ተበርግዶ እንዲከፈት ያደርጋ፡፡ እዚህ ላይ በፊት በር ቀርቶ በኋላ በር ወደ ሀገራችን ድንበር መግባት ልቻለቸው ሱዳን በማንአህሎተኝነት ተነሳስታ የኢትዮጵያን ለም መሬት መያዟ፣ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምታካሂደው የዲፕሎማቲክ እና የትምክህት  ዘመቻ እንደው ዝም ብሎ የተከፈተብን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮቿ ተቀስፋ ተይዛለች፣ ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማዳከም አመቺው ግዜ ፖለቲካዊ ስሌት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበረችው አሜሪካና ሌሎች የምእራብ ሀገራትም ቢሆኑ እኛ የውስጥ አንድነታችንን ማስከበር ቢቻለን፣ በውስጥ ሀገር ቤት ያሉትን ፖቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር ለመፍታት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ብንችል ኖሮ እንዲህ በአደባባይ አይዘባበቱብንም ነበር፡፡ ደርሰው የህልውናችን ወሳኝ እስኪመስሉ ድረስ እንዲህ አድርጉ፣ይህን ካላደረጋችሁ የምንሰጠውን ወረት እናቆማለን ወዘተ ወዘተ በማለት እያስፈራሩን በሚገኙበት አሳዛኝ ግዜ እንገኛለን፡፡ ይህች ታሪካዊት ሀገር ልክ እንደ ጋለሞታ ቤት ነገ ልትፈርስ ትችላላች እየተባለ በክንቱ ከንቱዎች እና በታሪካዊ ጠላቶቻችን አንደበት ሲነገር መስማቱ በእውነቱ ልብን ያደማል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እኛ የውስጥ አንድነታችንን ማስከበር ባለመቻላችን የተነሳ መዘባበቻ እየሆን ስለመሆኑ የአሁኑ ትውልድ በአንክሮ ልብ ሊለው ይገባል፡፡

እንደ መደምደሚያ

በእኔ በኩል ከገባንበት የፖለቲካ ማጥ ለመውጣት ከተፈለገ በዋነኝነትና የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ወደ ብሔራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚወስደንን መንገድ ቁጭ ብለን፣በሰከነ መንፈስ በመነጋገር፣በመደማመጥ ሰራሄ መፍትሔ መፈለግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንክሮ መገንዘብ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር የፖለቲካ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረታዊ ችግሮቻችን የመፍቻ ሁነኛ ቁልፍ የሆነው ትምህርት ልዩ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው ይህም ማለት  የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ እንደገና የሚከለስበት ሁኔታ በተለይም ትውልዱን ወደ ብሔራዊ እና አለም አቀፋዊአስተሳሰብ የሚወስድ እንዲሆን፣ ትውልዱን ችግር ፈቺ ሊያደርግ የሚያስችል፣የአካዳሚክ ነጻነትን የሚፈቅድ የትምህርት ፖሊሲ ለመንደፍ እና እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን የትምህርት ባለሙያዎች ሁሉ በነጻነት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው፣ የአይምሮ ሃይላቸውን በመጠቀም መምከር አለባቸው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ይህ ደግሞ የታሪክ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡

በሌላ በኩል ዘመናዊው የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ታሪክን ስንቃኝ ፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ፖሊሲ ስረ መሰረት ከቅኝ ገዢዎች የተቀዳ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በቅኝ ገዢዎች ርእዮት አለም በመጠለፋችን ነበር፡፡ አውሮፓውያንን መምሰል፣ የእነርሱን ባህል፤ታሪክ ወዘተ ከራሳችን ባህልና ታሪክ ሳናስታርቅ ሁሉንም አግበስብሰን በመቀበላችን፣ ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ነጭ አምላኪዎች ለመሆን የበቃነው በአብዛኛው ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ፖሊሲያችን ውድቀት  ውጤት ነው፡፡ ስለሆነም የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያዊ የአርበኝነት ስሜት እንዲያድረበት ለማድረግ ፣ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ ያካተተ፣የኢትዮጵያን ባህልና ሃይማኖት የማይጻረር የትምህርት ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህ ባሻግር አንዱን ጨቋኝ፣ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ የሚስል የታሪክ ትምህርት ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት አይደለም፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ሰብዓዊነትን የሚያስቀድም የትምህርት ስርአት በሚያስችል መልኩ መቀረጽ አለበት የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአውሮፓውያንን ጠቃሚ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት መገብየቱ ምንም ክፋት አልነበረውም፡፡ እኛ ግን ክፉ ክፉውን የማይጠቅመውን ስላገበሰበስን ነው ጉድ ሆነን የቀረነው፡፡ ጋሼ ከነደ ሚካኤል ‹‹ ጃፓን እንደምን ሰለጠነች›› እና ‹ስልጣኔ ምንድን ነው››  ገብረህይወት ባይከዳኝ ‹‹ መንግስትና ህብረተሰብ ›› በሚባሉት መጽሀፍቶቻቸው ገና ድሮ ነግረውን አስተምረውን ነበር፡፡ ሰሚ አድማጭ አገዛዞችን ያገኙ ግን አለመሰለኝም፡፡ እንደ እኔ ያለውም አብዝሃው ተራ ዜጋም የገባው አልመሰለኝም፡፡ ለማናቸውም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት ሁሉም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን የፖለቲካ አስተሳሰብ በነጻ መድረክ አቅርበው ለህዝብ የህሊና ፍርድ እንዲገዙ እማጸናለሁ፡፤

   በመጨረሻም ኢትዮጵያ አንድነቷ ከተጠበቀ ጠንካራ እና በኢኮኖሚ የበለጸገች ሀገር እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  እንደ ቀደሙት ሶስት አስርተ አመታት ሁሉ ጎሰኝነትን በማስቀደም የውስጥ አንድነታችንን ማስጠበቅ ካልቻልን ዘላለም የውጭ ጥገኛ ሆነን እንቀራለን፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ህልውናችን ሳይቀር አደጋ ላይ ስላለመውደቁ ምንም ዋስትና የለንም፡፡ በአጠቃላይ በብዝሃነታችን ውስጥ ለታሪካችንና ብሔራዊ አንድነታችን ዋጋ ለመስጠት መንፈሳዊ ወኔ ከከዳን ሰላምንና ብልጽግናን እንመኛታለን እንጂ ልናገኛት አይቻለንም፡፡ . In sum, there can be no peace or prosperity without first valuing our history and its national unity in diversity!

አረ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ግን ወዴት እየሄደች ነው ለማናቸውም የኢትዮጵያን ክፉዋን አታሳየን እያልኩ ልሰናበት፡፡ ሰላም፡፡

Filed in: Amharic