>

ይልቁንስ፣ ከሿሿው በኋላ ስለሚሆነው ልንገርህ! (አምባቸው ዓለሙ - ከወልዲያ)

ይልቁንስ፣ ከሿሿው በኋላ ስለሚሆነው ልንገርህ! 

አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)


የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ ነው፡፡ ከእባብ ዕንቁላል እባብ እንጂ ዕርግብ ወይም ሌላ ፍጡር አይፈለፈልም፡፡ ሣይንስንና ሃይማኖትን እንዲሁም ባህልን መናቅ ውጤቱ የዜሮ ድምር ነው – ባዶ፡፡ ሣይንስ በዲኤንኤ የዘረመል ውርርስ ያምናል፤ ስለሆነም የዝንጀሮ ልጅ ዝንጀሮ መሆኑን አይክድም፡፡ ሃይማኖትም ብዔል ዘቡልን ብዔል ዘቡል እንደማያወጣው በግልጽ ይናገራል – የሰይጣን ልጅ የሰይጣንን ልጅ ሊቃረነው አይችልምና፡፡ ከሰይጣን የሚገኘው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ ባህላችንም “እባብ የወጣበትን ጉድጓድ አይረሳም” ሲል የእፉኝት ልጅ እፉኝት እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳል፡፡ ምን አዲስ ነገር አለ? ከሕወሓት/ኢሕአዲግ ማሕጸን ደህና ሰው ይወለዳል ብለሽ የተሞኘሽ ጅላጅል ሁላ ሒሣብሽን አገኘሽ፡፡ አቢይ አህመድ እማማ ፊሽካ ቀርቶ አባባ እግዚአብሔርን ሄዶ ቢያጫውት ተፈጥሮውን አይረሳም፡፡ ማታለልና ማስመሰል የርሱ quality ነው – በእንግሊዝኛ ልንገርህ፡፡ ማጭበርበር ከልጅነቱ ጀምሮ የሰየጠነበትና የሰለጠነበት ልዩ ተሰጥዖው ነው፡፡ ገድሎ ማልቀስ፣ ራሱ አስርቦ ያዘነ መምሰል የባሕርይ ስጦታው ነው፡፡ ጃዝ ብሎ በላከው ኦነግ-ሸኔ አንድ ከተማ ሲጠፋ ርህራሄ የሌለው ዐረመኔ የሀገር ቀርቶ የቀበሌ መሪ ሊሆን እንደማይችል የማይረዳ ሰው፣ ሰው አይደለም፡፡ እናም ሰው ባልሆኑ ፍጡራን የተከበበ ዐውሬ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ለነገሩ ከመለስና ከስብሃት ነጋ ሥር ሉጥ ሉጥ ሲል አድጎ ጥሩ ሰው ቢሆን ነበር የሚገርመው፡፡ የመለስን ስህተቶች ልቅም አድርጎ በመረዳትና በማጥናት እርሱ አሻሽሎ ነው ኢትዮጵያን መቀመቅ እየከተተ የሚገኘው፡፡ ልዩ ሰው ነው፡፡ አሁን አሁን የሚያሳዝኑኝ ያዞረባቸውን ያላወቁ እነዳንኤልን የመሰሉ ዞምቤዎች ናቸው፡፡ ዞምቤ (zombie) ማለት በአፈ ታሪኩ እንደሚነገረው ቡዳዎች በልተዋቸው ከገደሏቸውና ከተቀበሩ በኋላ ከመቃብር ወስደው እቤታቸው በመደበቅ ከእንደገና የሚስለመለም ነፍስ ዘርተውባቸው በሕይወትና በሞት መካከል በመሆን ሥራ የሚያሠሯቸው ናቸው – የማይሰሙ የማይለሙ ድንዙዛን ናቸው፡፡ ዋና ተግባራቸው መታዘዝ ብቻ ነው፡፡ 

አቢይ ምርጫውን ሿሿ ሠርቶናል – እኔን አይጨምርም በርግጥ፤ ምክንያቱም በፊቱንም እውነተኛ ምርጫ እንደማይኖር በግሌ ለፍልፌያለሁ፤ ከጮሌ ሰው አንደበት ማር ጠብ ሊል ይችላል እንጂ ተግባሩ ዲያብሎሳዊ ነው፡፡ ብዙ ሰው ግን የዚህን አጭቤ ሰውዬ የማስመሰል ድርጊቶች በማመን ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንደሚሆን ጠብቆ ነበር፡፡ ሰውዬው በመቶ ሽዎች የሚገመቱ አጋንንት ከርሱ ጋር ስለተሰለፉ ብዙ ሰው ቢወናበድ በበኩሌ አልፈርድም፡፡ ግን ማየቱ ጥሩ ነውና እንኳንስ ሰው ሂደቱን እያዬ እየተረዳ መጣ፡፡ ሰሞኑን ስታዘብ ብዙ ሰው በምርጫው ውጤት ግራ ተጋብቷል፡፡

የአቢይን ብልግና ፓርቲ ለመምረጥ መቼም ቀን ከሌት የሚሰለፍ ጅላንፎ የለም፡፡ ጥቂት ሆዳሞችና የዘረኝነት ልክፍት የተጠናወታቸው ሆዳሞች ብልግናን እንደሚመርጡ ቢጠበቅም ይህ ሁሉ ሕዝብ ያን ሁሉ እንግልት ችሎ በብርድና በዝናብ እየተሰቃዬ ገዳዩንና አስገዳዩን የብልግና ፓርቲ ለመምረጥ እንደዚያ አይቸገርም፡፡ ኑሮውን በየደቂቃው ሽቅብ ለሚያጉን ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት ያን ያህል ውጣ ውረድ ውስጥ መግባት የሚፈልግ ዜጋ አይኖርም፡፡ ጩልሌው አቢይ ግን ከወያኔ ጅልነትና ግትርነት ተማረና በልዩ ሥልት ምርጫዋን ገቢ አደረጋት፡፡ ይሁን፡፡ የሚጠበቅ ስለነበር ብዙ አይደንቅም፡፡

ቀጣዩ ትዕይንት ይህን ይመስላል፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፤ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ደግሞም አይጠራጠር፡፡

ብዙ ዜጎች ተደምመዋል፡፡ ድምፃቸው መሰረቁን አምነዋል፡፡ ብዙዎች መታለላቸውን ተገንዝበዋል፡፡ ግን እንደ97ቱ ወደ ዐመፅ አልገቡም፤አይገቡምም፡፡ አቢይ ከመለስ ተምሮ ብዙ የማስመሰልና የማጭበርበር ሥልቶችን ተግባራዊ እንዳደረገ ሁሉ ሕዝቡም ከዚያው የ97 የከሸፈ ምርጫ ተምሮ ይህንንም ምርጫ መሸወዱን በማመን ከሌላ አቅጣጫ ልዩ የትግል ሥልት እንደሚቀየስ ይገምታል – ያንን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሰብኣዊና መለኮታዊ የመጨረሻ አማራጭ በጉጉት ይጠብቃል፡፡ ያም ትግል በቅርብ ይጀመራል፡፡ ብዙ ጊዜም አይወስደም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለድል ይበቃል፡፡ አቢይን ያለ ሁሉ፣ በዚህ አጭበርባሪ የተወሰደ ደንቆሮና አጋሰስ ሁሉ ጥግ ጥጉን የሚይዝበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ያኔ ጨለማው ይነጋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ሂደቱን በመገምገም ነገሮች እንደተጠበቀው አለመሄዳቸውን ታምንና አንድም ሀገር ጥላ ትኮበልላለች፤ ወደቀደመ ኑሮዋም ትመለሳለች፤ አንድም እውነትን በመካድ የታሪክ ተወቃሽ በመሆን ከአቢይ ጎን ትሰለፍና የሚደርስባትን ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ ትሆናለች፤ አንድም ከዚህ አሳረኛ የሥራ ኃላፊነት በገዛ ፈቃዷ ለቅቃ ወደሚሆናት ሌላ ቦታ ትዛወራለች – እንጂ የወንጀል ተባባሪ አትሆንም፡፡ ጎላ ያለው ግምት ግን እውነትን ተከትላ በያበጠው ይፈንዳ ራሷን ነፃ ልታወጣ እንደምትችልና እንደሚገባትም ነው፡፡ ይህች በወያኔዎች ብዙ መከራና ፍዳ የደረሰባት እንስት ከኅሊናዋ ጋር እንደማትጣላ ትልቅ ግምት አለኝ፡፡ ምርጫው ግን የራሷ ነው – ከእውነት ጋር መጋፈጥና የሕዝብን ፍቅር ማስጠበቅ  ወይም ከሃሳዊ መሲሑ ጋር ሁለት ሞት መሞት፡፡ ይህን ማስታወሻ እንዲደርሳት ብታደርጉልኝ ባለውለታየ ናችሁ፡፡

አቢይና ወዳጅ ዘመዶቹ ታሪክ የሚወረውርላቸውን መቁነን ተካፍለው ይቃመሳሉ፡፡ ለብልግና ፓርቲ እንደእህት ኩባንያ በሚቆጠረው የብርሃኑ ነጋ ኢዜማም ሆነ በብልግና ፓርቲ በራሱ ውስጥ የሚገኙ መልካም ሰዎች ከመራራው ጽዋ ሳይጎነጩ ለዘር ይተርፋሉ፤ መዳን በሥራ እንጂ በድርጅት አባልነት ብቻ እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው – በሃይማኖቱም ጭምር፡፡ ኦርቶዶክስ ስለሆንሽ ብቻ አትድኝም – ሙስሊም ወይንም ሰባተኛ ቀን ስለሆንሽም አትጠፊም – ከፈለግህ አገለባብጠው፡፡ በመቶዎች የተቧደኑት ፓርቲዎችም እንደየድርሻቸው ለዚህች ሀገር ውድመት ያበረከቱትን ድርሻ በሚመጥን መልኩ ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ከነሚስቱና ልጆቹ ፓርቲ መሥርቶ የሀገርን ሀብት አላግባብ በፓርቲ ስም የተቋደሰና ያባከነ ሁሉ የቀባጭ ምሱን አያጣም፡፡ ለዚህች ድሃ ሀገር ቢያንስ ሁለት ቢበዛ ሦስት ፓርቲ አነሳትና “የአባትህ አገር ሲወረር አብረህ ውረር” በሚለው የቆዬ ፈሊጥ ተመርተው በሀገር ላይ የቀለዱ ሁሉ ዋጋቸው እንደሥራቸው ይከፈላቸዋል፡፡ ዛሬ አእምሮ ጠፍቶ ሀገር እንዲህ ብትማስን ነገ ሰዎች ይፈጠራሉ፤ ያኔ እንካሣለን፤ ሰውም እንሆናለን፡፡

ኢትዮጵያን ከዚህ ሁሉ ትርምስና የዘረኝነት ቱማታ ነፃ ለማውጣት አድፍጦ የሚጠብቅ ኃይል አለ፡፡ ይህ ኃይል ማንም የሚበግረው ኃይል አይሆንም – በቅዱስ መንፈስ የሚመራና በሀገር ፍቅር የተቃጠለ ነው፡፡ የሚጠብቀው አበቅቴውን ብቻ ነው – የፈጣሪን ፊሽካ፡፡ ከዚያ በኋላ አፈ ቅቤ ልበ ጩቤውን ጨምሮ ሁሉም የሀገራችን ጠላት የማሽላ እንጀራ ይሆናል፡፡ ከውጭም ከውስጥም ሆነው ሕዝቡን የሚያባሉት መዥገሮችና አልቅቶች ሁሉ እንደጉም ይበናሉ፤ እንደጤዛም ይረግፋሉ፡፡ አሁን ግን ጊዜያቸው ስለሆነ በጊዜያቸው እንዳሻቸው ይፈነጫሉ፡፡ ብዙ የተጠመዱ ፈንጂዎችና የተቀበሩ ቦምቦች ግን አሉ፡፡ እነዚያን በማክሸፍ ረገድ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሥራ አለ፡፡ በዚያም ሳቢያ ግፋፎ ግፋፎው እስኪራገፍ ወንዞችና ሐይቆች መልካቸው ይቀላል፡፡ ነፃነት የምርቃት ድግስ ወይም የሽኝት ፓርቲ አይደለምና ብዙ የንብረት ውድመትና የሕይወት ኅልፈት መከሰቱ አይቀርም፡፡ ወያኔና ኦነግ/ኦህዲድ የደገሱት የመከራ ድግስ ለእስፖንሰሯ ግብጽም ይተርፋል፡፡ ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ስትጎበኝ ሊያጠፏት ያሰፈሰፉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጠላቶች ሁሉ አፍረው ይደበቃሉ፡፡ በቃኝ …  

Filed in: Amharic