>
5:18 pm - Friday June 14, 2819

ጊዜው አሁን ነው...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ጊዜው አሁን ነው…!!!

አሰፋ ሀይሉ

አንድ ሕዝብ ወይም አንድ ሀይል ባለድል የሚሆነው፣ በትክክለኛው ጊዜ መገኘት ከቻለ ብቻ ነው! ጊዜ ለሁሉም ድል እጅግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል! የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲከኞች የመንግሥትን ሥልጣን በብቸኝነት የጨመደደው አምባገነን በተለያየ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ በሚገባበትና የሥልጣን ሥጋቶች በተደቀኑበት ሰዓት ነው ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ አፋፍመው ማቅረብ፣ እና ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ ግልብጥ አድርገው አውጥተው ለሞት ሽረት ትግል መነሳት ያለባቸው!
ይህን ጉዳይ ምናልባት አሁን ለአስረኛ ጊዜ ይሆናል ደግሜ የምናገረው፡፡ አሁን የምናገረው ትክከለኛ ወቅቱ ስለሆነ ነው! ትክክለኛውን ዕድል ደግመን ደጋግመን ማባከናችን ሳያንስ አሁንም እንዳናባክነው ነው የምጮኸው፡፡
በአምባገነኑና ውሸታሙ አብይ አህመድ ከወያኔ ሽማግሌዎች እኩል እስርቤት የተወረወረውን – ዕድሜ ልኩን ከወያኔ ጋር ሲተናነቅና በወያኔ ሲማቅቅ የነበረውን የነጻነት ታጋይ – እስክንድር ነጋንና የነጻነት ታጋይ ጓዶቹን ከእስር ለማስፈታት – ባልደራስም ሆነ ሌሎች ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በማናቸውም ምድራዊ መንገድ ሁሉ ቆርጠን መነሳትና መታገል ያለብን ጊዜው አሁንና አሁን ነው!
እስክንድር ነጋ እስርቤት ውስጥ ልጁን እስኪወልድ ድረስ ከነባለቤቱ ከወያኔዎች ጋር አንገት ላንገት ተናንቆ ስለነጻነት ትልቅ የስቃይ ዋጋን ሲከፍል፣ አብይ አህመድ ከወያኔዎች ጋር የሚኒስትርነት ካባ ተደርቦለት በጥቅምና በምቾት ጎዳና እየተንጎማለለ፣ ባለቤቱንና ልጆቹን አሜሪካ ልኮ ያኖር ነበር! አሁን ለውጥ መጣ ተብሎ – አብይ አህመድ ቅዱስ አምላክ፣ እስክንድር ነጋ ደግሞ ከወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች ጋር በቂሊንጦ የሚማቅቅ ወንጀለኛ ሆኖ ተገኘ?!
እስክንድር ነጋ ቅስሙ ሳይሰበር፣ በሕዝቡና በተበላው የፖለቲካ ጨዋታ ተስፋ ሳይቆርጥ ደግሞ ምርጫ ተወዳደረ፣ ታጨ፣ አሸነፈ፡፡ አሁንም አብይ አህመድ ከወያኔ-ዘመን የከረሙ ጀሌዎቹ ጋር ቢሊዮኖች ብሮችን እንዳሻው እየመነዘረ በሚንፈላሰስባት በአዲስ አበባ ከተማ – እስክንድር ነጋና ንጹሃን ጓዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ያለአስታዋሽ በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ!
ይህንን ዓይን ያወጣ ሰብዓዊ መብት ረገጣና ግፍ የዓለማቀፍ ተቋማትና ሀያላን ሀገራት በእኩል ድምጽ አውግዘዋል፡፡ በቅርቡ አሜሪካና ሸሪኮቿም የአብይ አህመድ መንግሥት የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ያለቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈታና ሁሉን-አቀፍ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር የማያወላውል ጥሪያቸውን አቅርበዋል! ራሳችንን ነጻ ካላወጣን፣ ማንም ነጻ አያወጣንም፡፡ አንድ እውቅ ፀሐፊ እንዳለው ‹‹ሌላው ነጻ እንዲያወጣው የሚጠብቅ ባርያ ብቻ ነው››፡፡ ባሮች ካልሆንን ሌሎች ስለ እኛ ቢጮሁም፣ ቢያግዙንም፣ ዋነኛውን ራሳችንን ነጻ የማውጣትና ከፈጣሪ የተሰጠንን ነጻነት የማስከበር ሃላፊነታችንን ራሳችን መወጣት ይኖርብናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ ዘረኛ ሥርዓት የመጨረሻው አስጠባቂ ሆኖ የተጠላውን ሥርዓት ሊያስቀጥል እየተሟሟተ የሚገኘው ውሸታሙና አምባገነኑ አብይ አህመድ – ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም ህዝብ አይኑን በጨው አጥቦ የዋሻቸው ውሸቶቹና ግፎቹ እየተጋለጡበት ያለበት የአጣብቂኝ ወቅታቸው ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የዋሸውና በሺህዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ያጋለጠው የኢትዮጵያ ህዝብ በቁርጠኝነት ሆ ብሎ ተነስቶ ሊፋረደው ጥቂት ነገሮችን ቆም ብሎ ማጤን ብቻ የቀረው ህዝባዊ የጽሞናና የውሳኔ ወቅት ላይ ነን፡፡
ጦሩም ያለምንም ውጤትና በውሸት ደሙን አፍስሶ በተጨፈጨፈበት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘመቻ በህይወትና በሞት ውስጥ እንዲያልፍ ከተደረገ በኋላ፣ ያለምንም ምክንያት በከንቱ ልጆቹን አስበልቶ፣ በኢትዮጵያውያን ደም ቀልዶ ከተቆጣጠረው ክልል ለቆ እንዲወጣ በመደረጉ ከፍተኛ ቅሬታና ጉርምርምታ ላይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም!
ለዚህ ሁሉ አሰቃቂ ድርጊትና ያልተቋረጠ የውሸት ፋብሪካ ሃላፊነቱን የሚወስድና ተጠያቂ የሚደረግ የጦር መሪም ሆነ የፖለቲካ መሪ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ህዝብ በአስቸኳይ የሚፈለጉበት ወቅትም ላይ ነን! በቀጣፊው አብይ አህመድ የሚመራው ተረኛው መንግሥት የሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት፣ ብሎም የአጠቃላይ ኢትዮጵያውያንን ደህንነትና ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተበት አሳሳቢ ሰዓትም ነው፡፡
በአብይ አህመድ ግልጽ ሸፍጥና በሚመራው መንግሥትና በሚታዘዙት ክልሎች ከፍ ያለ ንዝህላልነት የተነሳ በአሁን ወቅት በብዙ የሀገራችን ክፍሎች መንግሥት የማይቆጣጠራቸውና ሀላፊነት በማይወስዱ ታጣቂ ጎሰኞች ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የአደባባይ እውነት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ መንግሥት የዜጎች ጠባቂና ወንጀለኞችን ለህግ አቅራቢ፣ ወንጀልን ተከላካይ መሆኑ ቀርቶ፣ እንደ ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ከዳር ተቀምጦ ይህን ያህል ሰው ሞተ፣ ይህን ያህል ንብረት ወደመ፣ ይህን ያህል ጉዳት ደረሰ እያለ አሃዞችን የሚዘግብ አካል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
በዚህ አብይ አህመድ ሸፍጦቹና ውሸቶቹ ሁሉ በተጋለጡበትና በውሸት ባማለለው ሕዝብ ፊት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት፣ የዓለማቀፍ ጫና በበረታበት፣ እና የበሰበሰው ሥርዓት ከያቅጣጫው የቀጣይነት አደጋ በተጋረጠበት በዚህ ወቅት ላይ – ነጻነት ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ – እና በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብ – ለእኛ ኢትዮጵያውያን ነጻነት ሲሉ ያለምንም ሃጢያት በተረኛው ገዢ አብይ አህመድ እስርቤት ተወርውረው እየተሰቃዩ ላሉት ለእነ እስክንድር ነጋ በቁርጠኝነት አደባባይ መቆምና መጮህ ያለበት – ትክክለኛው ውጤት የሚመዘገብበት እጅግ ወሳኝ የትግል ሰዓት ነው ያለንበት ወቅት!
ስለሆነም በማናቸውም መንገድ ጀግናው የነጻነት ታጋይ እስክንድር ነጋና አብረውት በእስር እየማቀቁ የሚገኙት የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ ዛሬ ነገ ሳይባል ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ ያስፈልጋል!
በአሁኑ ወቅት የባልደራስ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ 500 ሆነው ተሰብስበው አደባባይ ወጥተው እስክንድርና ጓዶቹ በግፍ ከታጎሩበት እስርቤት እንዲፈቱ ቢጮሁ – በዚህ በዓለም ፊት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ሰዓት – አብይ አህመድና አፋኝ ግብረአበሮቹ ሊወስዱ የሚችሉት የከፋ እርምጃ ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይህን ካደረጉ በዚያው ደቂቃ ተቀርጾ ለዓለም እንደሚጋለጥና የአውሬውን ተክለሰብዕና ለመላው ዓለምና ለመላው ኢትዮጵያውያን እንደሚያስጣጣው ግልጽ ነው! ካደረገውም ለማይቀረው ታላቅ ሀገራዊ ነጻነት ሁሉንም በቆራጥነት የሚያነሳሳና ለክቡሩ ነጻነት የተከፈለ ታላቅ ዋጋ ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል!
በመንግሥታዊ የውሸትና የማምታታት ፋብሪካ በቋሚነት ውሸትን ለህዝብ እየፈበረከና፣ በመሐል መዲናችን ሰላማዊ ሰልፈኞችን እየረሸነና እየደበደበ አራት ኪሎ ላይ ለሁልጊዜ በሥልጣን ተንጎማሎ መቀመጥ የሚችል ግለሰብም ሆነ ቡድን ሊኖር የማይችልበትን ዘመን መፍጠር – በእኛ በአሁኑ ትውልዶች ላይ የተጣለ፣ አሁን ዛሬ ነገ ሳንል ልናደርገውና ልንሰለፍለት የሚገባ ሀገርንና ትውልድን አኩሪ ተግባር ነው!
ትግል በትክክለኛዋ ድል በሚቆጠርባት ቅጽበት፣ በትክክለኛዋ ጊዜ ካልተደገፈ ዋጋ የለውም! ይህን ታሪክና ጊዜ የጣለብንን ታላቅ የትውልድ አደራ አንግበን፣ አሁኑኑ ለመብታችን እንነሳና ለእኛ ሲሉ በግፍ የታሰሩት እስክንድር ነጋና የትግል ጓዶቹ እንዲፈቱ የሚጠይቅ – ምድር-አንቀጥቅጥ ሠላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ከተማ እናካሂድ!
በአጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ማማጥ የአምባገነኖች ሥራ ነው፡፡ ለእነሱ እንተውላቸው፡፡ የእኛ የዜጎች ሥራ መብታችንን በትክክለኛዋ አቅማችን ከፍ ባለባትና ልንቀዳጃት በምንችላት ሰዓት ላይ በጋራ ተነስተን በሠላማዊ መንገድ መጠየቅ ብቻ ነው!
እደግመዋለሁ፡፡ ሥልጣናቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ቀጣፊ አምባገነኖች ስለራሳቸው ይጨነቁ፣ ይጠበቡ! የእኛ የዜጎች ሥራ መብታችንን በትክክለኛዋ ጊዜ አሁኑኑ መጠየቅና ማስከበር ነው! ሕዝብ ሁልጊዜም ያሸንፋል! ሕዝብን ያፈኑ ሁሉ በመጨረሻ በሕዝብ ሀይል ይወድቃሉ! የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም!
ኃይል የእግዚአብሔር ነው! 
ጊዜው አሁን ነው! 
ነፃነት! ነፃነት! ነፃነተ! 
የነፃነት ደሴት ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር!   
Filed in: Amharic