>
5:13 pm - Monday April 18, 9385

የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን -ኢሠመጉ አስታወቀ...!!! (D W)

የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን -ኢሠመጉ አስታወቀ…!!!

D W

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ከተሞች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በምህጻሩ ኢሰመጉ አስታወቀ።የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ትናንት ባወጣው አስቸኳይ ዘገባና ለዶቼቬለ በሰጠዉ መግለጫ እንዳለዉ ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸዉና የንግድ ተቋሞቻቸዉ መዘጋታቸዉን የሚጠቁሙ መረጃዎች ደርሰዉታል።የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን መብት ለማስከበር አስፈላጊዉን ጥረት እንዲያደርግም ኢሰመጉ ጠይቋል።እዚያዉ ትግራይ ዉስጥ ያለዉን የሰብአዊ መብት ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቅቆ ከወጣ ወዲሕ የስልክና የኢንተርኔት መስመሮች በመዘጋታቸዉ ሁኔታዉን ለመከታተል መቸገሩን ድርጅቱ ገልጧል።ትግራይ ዉስጥ የሚሰሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆችና በየዩኒቨርስቲዉ የሚማሩ ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ ለማወቅ መቸገራቸዉን ወላጆችና የቤተሰብ አባላት ለዶቸ ቬለ በተደጋጋሚ እያስታወቁ፣ ድጋፍም እየጠየቁ ነዉ።የኢሠመጉ ዋና ኃላፊ አቶ ዳን ይርጋ እንዳሉት ድርጅታቸዉ  ከትግራይ ዉጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ይታሠራሉ፣ ይንገላታሉ የንግድ ተቋማቸዉ ይዘጋል የሚለዉን ጥቆማ እያጣራ ነዉ።ማጣራቱ እስኪደረግ ድረስ ግን መንግሥት ፈጣን ርምጃ እንዲወስድ ኃላፊዉ ጠይቀዋል።
Filed in: Amharic