>
5:30 pm - Tuesday November 1, 9098

ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ጥሪ...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ጥሪ…!!!

አሰፋ ሀይሉ

የትግራይ ህዝብ ጀግና ህዝብ ነው፡፡ ምናልባትም በአሁኑ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያውያን መሐል እውነተኛ የኢትዮጵያዊ አይበገሬነትና ጀግንነትን ተላብሶ የቆመ ሕዝብ ቢኖር የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ በጉልበት ሰባብሬ እገዛሃለሁ ብሎ የዘመተበትን ሀይል አፈር-ድሜ ግጦም ቢሆን፣ በጀግንነት ተፋልሞ፣ በጀግንነት ድል ነስቶ፣ አሳፍሮ የመለሰ ጀግና ህዝብ ነው፡፡ የኦሮሙማውን እብሪት አስተንፍሰው በመለሱት በትግራይ ጀግኖች እኮራለሁ!
የትኛውም ህዝብ በጉልበት ሊጨፈልቀው የመጣን ማኛቸውንም እብሪተኛ ሀይል መመለስ ያለበት በዚሁ መልኩ ነው፡፡ ነገ ኦሮሙማው በአማራው ህዝብ ላይ ጦሩን ሲያዘምት፣ የአማራው ህዝብ ልክ እንደ ትግሬው ወንድሙ ለህልውናውና ለክብሩ በጀግንነት ቆሞ እብሪተኛን አሳፍሮ ልኩን ማስገባት አለበት፡፡
እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይህ ነው፡፡ በቁም ከመገዛት፣ ከባርነት፣ ሞትን የሚመርጥ፣ ጀግና የጀግና ዘር ማለት ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡ ኢትዮጵያን የፈጠረው የትግራይ ሕዝብ፣ ዛሬም ከነጀግንነቱ እንዳለ በተግባር አስመስክሯል፡፡ ሊደነቅ፣ ሊከበር፣ ሊደገፍ፣ እና ለደረሰበት ሰቆቃ ሁሉ ሊካስና ቁስሉ ሊታበስለት ይገባል፡፡
ስለ ትግራይ ህዝብ ይህን ካልኩ፣ ስለ ወያኔ ሽማግሌዎች ደግሞ ጥቂት ልበል፡፡ የወያኔ ሽማግሌዎችን በማደንቅበት ነገር እጀምራለሁ፡፡ ከሆዳቸው ይልቅ ለህዝባቸው መሰዋትን በመምረጣቸው ትልቅ ክብር እንዳሳድርባቸው አድርገውኛል፡፡
ይህን ጀግንነት ተላብሰው ይገኛሉ የሚል ግምት አልነበረኝምና ከመጠን በላይ አስገርመውኛል፡፡ በዚህ ከሆድ ይልቅ ለመብታቸው ቆመው መሰዋትን ለመረጡበት ታላቅ አቋማቸው እንደ ሰው ልጅ ሳይሆን፣ በግፍ እንደ ውሻ እየታደኑ ለተገደሉት፣ እና በህዝባቸው መካከል ለሞቱት የወያኔ ሽማግሌዎች ሁሉ የተሰማኝን ሀዘን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ትልቁን የወያኔ ሽማግሌዎች ህጸጽ ደግሞ ልናገረው፡፡ የወያኔ ሽማግሌዎች አውቀውም ይሁን ተሳስተው ከመነሻቸው ያነገቡት የዘረኝነትና የጥላቻ መፈክር፣ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት የውድቀት ምዕራፍም፣ አሁን በትግራይ ህዝብ ላይ ለወረደበት መቅሰፍትም ዋነኛው መንሥዔ ነው፡፡
የወያኔ ሽማግሌዎች በአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል ፍቅርንና መቀራረብን፣ ዝምድናንና አንድነትን መስበክና ማለም ሲገባቸው፣ ዕድሜ ልካቸውን የዘር ልዩነትን፣ ከዚያም አልፈው የዘር የበላይነትንና የበታችነትን፣ ገዢነትንና ተገዢነትን፣ ቂምንና ጥላቻን ሲሰብኩ መኖራቸው ለብዙ የአሁን ውድቀቶቻችንና መተላለቆቻችን ምንጭ ሆኗል፡፡
በተለይም ደግሞ የወያኔ ሽማግሌዎች ወንድማቸውና ጎረቤታቸው፣ የታሪክም፣ የባህልም፣ የቋንቋም፣ የስነልቦናም፣ የእምነትም፣ የዘርም፣ የብዙ ሁለንተናዊ ማንነት መንታቸውና ቤተሰባቸው በሆነው በአማራ ህዝብ ላይ ያሳደሩት ተስተካካይ የሌለው ጥላቻ፣ ምናልባትም በዓለም ታሪክ የጀርመን ናዚዎች በአይሁድ ዘሮች ላይ ካሳደሩት ጥላቻ የማይተናነስ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
የወያኔ ሽማግሌዎች በአማራው ህዝብ በአጠቃላይ ያሳደሩት መሰረተ-ቢስ ጥላቻ፣ ስሁት የጥላቻ ትርክት፣ እና የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በአማራው ላይ በጠላትነት ለማስነሳት የሄዱበት የተንኮልና የክፋት ርቀት – በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ይቅር የማይባል ጥልቅ የጥላቻ አዘቅት ውስጥ ገብተው እንዲቀሩአድርጓቸዋል፡፡
ከስህተታቸውም እንዳይማሩ፣ ቢያንስ በእኛ ይቅር ብለው በአሁኑ ትውልድ ስህተታቸውን ሳያርሙ በጥላቻና ፍራቻ ትርክታቸው የሙጥኝ ብለው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም አሁን ለሚታየው የጠላትነት ስሜት፣ የህዝቦች መቃቃር፣ ቁርሾና በቀል ዋናውን የአንበሣ ድርሻ የሚወስድ መነሻ ምክንያት ሆኖ አገልግሏል፡፡
ሳጠቃልል – የአሁኑ የትግራይ ትውልድ የወያኔ ሽማግሌዎቹ ለከፈሉለት መስዋዕትነት ታላቅ ክብርና ጥልቅ ፍቅር መስጠት የሚጠበቅበትን ያህል፣ ሰከን ብሎ ማስተዋል ደግሞ ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ከወያኔ ሽማግሌዎቹ ጀግንነታቸውንና አይበገሬነታቸውን እንጂ ጥላቻቸውን መውረስ የለበትም፡፡ ከወያኔ ሽማግሌዎች ላመኑበት ዓላማ እስከመጨረሻው ፀንቶ የመቆምን ኢትዮጵያዊ የጀግንነት ባህልን እንጂ፣ የዘር ክፍፍልንና ዘረኝነትን መውረስ አይኖርበትም፡፡
የወያኔ ሽማግሌዎች በኢትዮጵያችን ላይ የጠነሰሱት የዘር ሽንሸና ለትግራይ ህዝብ ያተረፈለት ነገር ቢኖር፣ ከታሪክና ከክብር ማማው ላይ ተፈጥፍጦ፣ የትግራይ ነገሥታትና ህዝብ ለኢትዮጵያችን በየዘመኑ የከፈለው ወደር የሌለው መስዋዕትነትና የታሪክ ገድል ተረስቶ፣ የሚሊየኖች የትግራይ ተወላጆች ታላቅ ሀገራዊ ሚናና የብቃት ደረጃ አፈር ግጦ፣ አንደ አንድ ተራ ኢምንት ጎሳ በ6% የፖለቲካ ድምጽ ብቻ ተወስኖ የቀረ እዚህ ግባ የማይባል አናሳ ጎሳ ሆኖ መቅረትን ብቻ ነው፡፡
የወያኔ ሽማግሌዎች የዘሩት የዘረኝነትና ሀገርን በጎሳ የመሸንሸን አባዜ፣ ከዘሩት ጥላቻና አለመተማመን ጋር ተዳምሮ – ለትግራይ ህዝብ ያተረፈለት ነገር ቢኖር – በምንም ከማይለውጠውና ካልለወጠው የኢትዮጵያዊነት ክብሩ ዝቅ ብሎ፣ ብቻውን በሚቆምበት ጠባብ የጎሳ ቅርቃር ውስጥ ተነጥሎ ገብቶ መቅረትን ብቻ ነው!
የወያኔ ሽማግሌዎች ትግሬ፣ አማራ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ… እያሉ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች ሁሉ በመናድ፣ የአንድ ሀገር ወገንተኝነትንና ወንድማማችነትን ለማጥፋት 40 ዓመት ሙሉ ተግተው ባይሠሩ ኖሮ፣ ይሄን ጊዜ ምን ሊሆን ይችል ነበር?
ኤርትራም ሆነች ማንም ሀይል – የትግራይን ጫፍ ንክች ቢያደርግ – መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በቁጣ ተነስቶ የሚሰዋበት ታሪክ በተፈጠረ ነበር፡፡ ይህን ሲያውቁ፣ ማናቸውም የኢትዮጵያ ጠላትም ሆነ ወዳጅ፣ የትግራይንም ሆነ ማናቸውንም የኢትዮጵያ ጫፍ ደፍሮ ንክች የሚያደርግበት አሳፋሪ የውርደት ታሪክ ባልተፈጠረም ነበር፡፡
ሌላው የወያኔ ሽማግሌዎች ትልቅ ስህተት – ውሸትን እንደ እውነት አድርገው መቁጠራቸውና፣ ራሳቸውንም ህዝባቸውንም ለቂምና ለበቀል መዳረጋቸውና ወደጥፋት መምራታቸው ነው፡፡ ውሸት የቱንም ያህል ቢቀባባ፣ የቱንም ያህል የገዘፈ ተክለቁመና ቢሰጠው እውነት ሊሆን አይችልም፡፡
ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ፀለምት፣ ፀገዴ፣ ራያ – በትግራይ ክፍለሀገር ተዳድሮ የማያውቅ፣ ነገር ግን ብዙ የትግሬ ተወላጆች ሲኖሩበት የነበሩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ናቸው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ በየዘመኑ ሁሉ የትግራይ ተወላጅ በእነዚህ አካባቢዎች ሠርቶ፣ ሀብት አፍርቶ፣ ባህሉን ጠብቆ፣ ወልዶ ተዋልዶ እንዳይኖር የከለከለው አንዳችም መንግሥትም ሆነ አስተዳደር ኖሮ አያውቅም፡፡
ነገር ግን የወያኔ ሽማግሌዎች በብዙዎች የሀገር ሽማግሌዎችና አርቆ አሳቢዎች ቢመከሩም ቢዘከሩም እምቢ ብለው፣ እነዚህን አካባቢዎች ከአማራው ላይ (ከጎንደርና ከወሎ ክፍለሀገሮች ላይ) በጉልበት ቀምተው – በአካባቢው ላይ የነበሩ የአማራና ሌሎች ተወላጆችን በከፍተኛ ሸፍጥና ግፍ አሳድደውና አራቁተው፣ በአካባቢዎቹ ላይ የትግራይ ተወላጆችን ከተለያዩ አካባቢዎች እያሰፈሩ፣ ታሪክ የሚያውቀውን እውነት፣ ታሪክን በሚሸፍን ሸፍጥና ውሸት ሊሸፍኑና – ውሸትን እውነት ሊያስመስሉ ብዙ ርቀት ሄዱ፡፡
ይህ ጉዳይ ወደፊት በሁለቱ ህዝቦች (በአማራውና በትግሬው ሕዝብ) መካከል ከፍተኛ የደም መፋሰስና የመጠላላት የመቦጫጨቅ ምንጭ እንደሚሆንና በአግባቡ፣ በሥፍራዎቹ ላይ የሚኖሩ የትግሬ ተወላጆች የመኖር ዋስትና ተረጋግጦ፣ በሠላም አስተዳደሮቹን ከትግራይ አስተዳደር ወደ አማራው አስተዳደር የመመለስ በሀቅ ላይ የተመሰረተ ተግባር እንዲያከናውኑ ቢለመኑም፣ ቢዘከሩም፣ ሰሚ ጆሮ አልነበራቸውም፡፡
እንደ አሁኖቹ የኦሮሙማ እብሪተኞች ሁሉ፣ የወያኔም ሽማግሌዎች እውነትንና ሀቅን ወደጎን ብለው በእብሪትና በውሸት ህዝቡን ወደ ጥፋት ሊማግዱት ዓይናቸውን ሳያሹ ድርቅ ብለው ቀሩ፡፡
ይህን የውሸትና የሸፍጥ መንገድ ባይከተሉ ኖሮ፣ እና የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ የሚያለያየውንና የሚያከራክረውን እነዚህን የኢትዮጵያ ግዛቶች በተመለከተ ተቀራርቦ እውነትንና እውነትን ብቻ መሠረት ባደረገ ውይይት መፍታት ቢችሉ ኖሮ – ቀሪው ገለባ በሆነላቸው ነበር፡፡
የወያኔ ሽማግሌዎች በኢትዮጵያዊ ጀግንነታቸው መደነቅና መከበር፣ መስዋዕትነታቸውም ተገቢውን ክብር ማግኘት የሚገባውን ያህል፣ ነገር ግን ውሸትንና ዘረፋን የሙጥኝ ብለው ከአማራው ህዝብ ላይ በጉልበት ነጥቀው የወሰዱትን የወልቃይት ራያ አስተዳደሮች ለአማራው አልመልስም ብለው ድርቅ ማለታቸው – የትግራይን ህዝብም ሆነ የአማራን ህዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
ኢትዮጵያን ያልተረጋጋች ሀገር ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ፣ የወያኔ ሽማግሌዎች ከአማራው ላይ ነጥቀው የወሰዱት ይህ ግዛትና፣ ነገ አማራው ጉልበት አውጥቶ እንዳይወስድብን በማለት በስጋት፣ በፍራቻና በጥላቻ ላይ የተመሰረተው ተከታዩ ታሪክ ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ከዚህ በኋላም በአዲሱ የትግራይ ትውልድ፣ እና በአማራው ልጆች የጋራ ምክክርና ንግግር፣ እውነቱ ጠርቶ ወጥቶ፣ በሠላምና በሽምግልና በፍቅር ካልተፈታ፣ በተለይ በተለይ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚወድቅበት መጪ መከራ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡
ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይበልጣል እንደሚባለው – እነዚህ ሁለቱ ህዝቦች – እውነትን አስቀድመው – ይቅርታንና የወደፊቱን መጪ መንገድ አሰላስለው – በእርቅና በሠላም ጉዳያቸውን ፈትተው- ህዝቦቹ ወደቀደመው ሠላማቸው፣ አጋርነታቸው፣ ህብረታቸውና ዝምድናቸው መመለስ ካልቻሉ – በኢትዮጵያችን ህልውና ላይ ከባድ አደጋ እንደሚደቀን አውቀን መባነን ያለብን እጅግ ወሳኝ ሰዓት ላይ ነን፡፡
በተለይ የትግራይና የአማራ ወጣቶችና ልሂቃን ይህን መልዕክቴን ደግማችሁ ደጋግማችሁ አንብቡት፡፡ የወደፊቱ መንገድ በዚህ ዓይነት ከተሄደበት ለሁለቱ ህዝቦች ብሎም ለኢትዮጵያችን እጅግ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው፡፡
በቀደመው የውሸትና የድርቅና፣ የጥላቻና የእብሪት መንገድ ከተገባበት ደግሞ፣ በአሁኑ ትውልዶቻችን ብቻ ሊቆም የማይችል ረዥም የጥላቻና የመተላለቅ ታሪካችንን እናስቀጥላለን፡፡ በዚህም ድርጊታችን ኢትዮጵያችንንና አኩሪ ታሪኳን፣ እና ኢትዮጵያችንን በደምና በአጥንት የገነቧትን እነዚህን ሁለት ታላቅ ህዝቦች የሚጠሉትን የቅርብና የሩቅ ጠላቶች በማስደሰት ብቻ የተጠመድን የዓለም ጅል ህዝቦች እንሆናለን፡፡
ስለዚህ ዛሬ ላይ ያለን የትግራይና የአማራ ትውልዶች ቆም ብለን እናስብ፡፡ የደረሰብንን እንደራስ አድርገን ቆጥረን ሀዘናችንን እንዘን፡፡ እርስ በእርሳችን እንጽናና፡፡ ይቅር እንባባል፡፡ እንተሳሰብ፡፡ ቁስላችንን እንሸፋፈን፡፡ እንወያይ፡፡ እንስማማ፡፡ እና አብረን በፍቅር፣ በስክነት፣ እንደ አንድ ወገን፣ እንደ አንድ ሕዝብ ለልጆቻችን ብሩህ ተስፋ ሰንቀን እጅ ለእጅ ተያይዘን እናዝግም፡፡ እና ጠላትን እርር እናድርገው፡፡
ጥፋቱ በእኛ ይብቃና ቀሪው ጊዜያችን በፍቅር የተሞላ ይሁን፡፡ አበቦች በደጃችን ይፍኩ፡፡ ልጆቻችንን በሠላም ይቦርቁ፡፡ ላመነበት የሞተ ሁሉ በክብር ተዘክሮ፣ የሞተ ተቀብሮ፣ የቆሰለ አካል በፍቅር ታብሶ፣ የፈሰሰ ደም በፍቅር ታስቦ፣ ይቅር ለእግዜር ተባብለን – ኢትዮጵያችንን አብረን እንገንባ፡፡ የወደመብንን አብረን እናንጽ፡፡
እናቶቻችንን ከጭንቀት አውጥተን፣ ቤተመቅደስን በሠላም ይሳለሙ፡፡ ሠማያችን በባሩድ ጭስ አይጥቆር፡፡ አንዳችን ለሌላኛችን ልባችንን ከከፈትን ታላቅነታችንን የሚገድብ ምድራዊ ሀይል አይኖርም፡፡
ይህን ልብ ብለን እናስበው፡፡ በጥፋት ላይ ጥፋት አንደርብ፡፡ ልጆቻችንን ደግመን ደጋግመን እናስብ፡፡ ሞትንና ጥላቻን ለትውልድ አናውርስ፡፡ ፈጣሪ ይህን ለማሰብ፣ ለማድረግም ብርታቱን ይስጠን፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን፡፡ የታላላቅ አባቶቻችን አምላክ ይርዳን፡፡
ኢትዮጵያ በፍቅር ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic