>
12:41 pm - Tuesday June 6, 2023

ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የጻፈችው ደብዳቤ (አሳዬ ደርቤ)

ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የጻፈችው ደብዳቤ 

አሳዬ ደርቤ

ከእግዜሩና ከጠፈሩ በታች ያለውን ይሄን ምድር የምትዘውሪው፣ ሰላሙንም ሆነ ጦርነቱን የምታከፋፍይው አንቺ መሆንሽን ስለማውቅ ስለ ሰላምሽና ጤንነትሽ አልጠይቅሽም። ይልቅስ እኔ ስላለሁበት ሁኔታ ከእኔ ከታማሚዋ በላይ  አንቺ ሐኪሜና ሕመሜ ብዙ ስለምታውቂ  ‹‹ሰላም ነኝ ወይ? አንድነቴ እና ጤንነቴስ እንዴት ነው?›› እልሻለሁ።
ውድ አሜሪካ፡- የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያለኝ እናት አገር መሆኔ ቀርቶ ያንቺ የኮረዳዋ 51ኛ ስቴት ሆኜ መመዝገቤን ሰማሁ፡፡ ወሬው እውነት ከሆነ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽዕ እደዊሀ ሀበ እግዚአብሔር›› ማለቴን ትቼ ‹‹ጋድ ብለስ አሜሪካ›› እል ዘንዳ ግልጹን ብትነግሪኝ ጥሩ ነው፡፡ የምገበያይበትን ብርም ወደ ዶላር ብትቀይሪው ሼጋ ነው፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ባንድ ቋንቋ እናወራ ዘንዳ እንደ ‹‹ፋክ ዩ›› እና ‹‹ቡልሽት›› ያሉ የእንግሊዘኛ ስድቦችን የያዘ መዝገበ ቃላት ትልኪልኝ ዘንድ አደራ እላለሁ፡፡
ቀልዱን ትቼ ወደ ቁምነገሩ ስሸጋገር ባልተማረ ኋላ ቀር ጭንቅላቴ የሰሞኑን ሁኔታሽን ሳስበው ‹‹ሥልጣኔ ደንቆሮ ያደርጋል እንዴ?›› ማለት ጀምሬያለሁ፡፡
የምሬን እኮ ነው…
ቆይ እኔ እምለው… መምረጥ ያለብኝን መሪ እና መከተል ያለብኝን ሥርዓት የምትወስኚልኝ አንቺ ከሆንሽ ምርጫውና ዲሞክራሲው ምን ያደርጋል? የሕዝቤን ማንነትና የክልሎቼን መሬት የምትወስኚው አንቺ ከሆንሽ ሃይማኖቴን’ስ ለምን አትመርጪልኝም? ጠይም ሚኒስትር ጋር ከምትዳረቂ’ስ ነጭ ሴናተር ለምን አትልኪም?
ሲቀጥል ደግሞ… በርሐብ ወቅት የምትልኪውን የእርዳታ ስንዴ እኔ ለበላሁት አንቺን በጥጋብ መንፋት የቻለው እንዴት ነው? በብድርና በእርዳታ የምትሰጪኝን ብርም በሙሥና የሚበሉት የኔ ባለሥልጣኖች ሆነው ሳለ የሞራል ዝቅጠቱ ያንቺ መሪዎች ላይ የተከሰተው በምን ምክንያት ነው?
ውድ አሜሪካ፡- ድህነት እንደሚያስንቅ አውቃለሁ፡፡ አንቺ ግን እድገቴንም የማትፈልጊ ነሽና ይሄን ያህል ልትንቂኝ አይገባም፡፡ የእርዳታ ስንዴ የሚሰጥ እጂሽም ከዳቦውና ከንፍሮው አልፎ ሉአላዊነቴን በጣሰ መልኩ በሁሉም ነገሮች ላይ መፈትፈት አይችልም፡፡
ሌላው ደግሞ የፑቲን አምላክ ፍርስርስ ያድርግሽና ‹‹ኢትዮጵያ ልትፈርስ ትችላለች የሚል ስጋት አለኝ›› ማለትሽን ስሰማ ‹‹አፈርሳታለሁ›› የሚለው ግብረሃይል- ትፈርሳለች በሚል ስጋት የሚሰቃይ መሆኑ እንዳሳቀኝ ልደብቅሽ አልሻም፡፡አይ አሜሪካ!
ለዚያ እኮ ነው ድህነቴን እና መሪዎቼን እንጂ ሕዝቤን እና ማንነቴን ስለማታዉቂ ሤራሽን ጋብ አድርገሽ ታሪኬን አንብቢ የምልሽ፡፡ ለዚያ እኮ ነው የኔ አማልክት እንደ አንቺ ሃብት እና መና የሚያፈስሱ ሳይሆኑ ሃይልና ሕግ የሚለግሱ ናቸው ማለቴ..
ምንም እንኳን ሲርበኝ መና በማውረድ ፈንታ ሰማዩን ደመና አልባ ቢያደርጉትም፣ በዘመናዊ ጦር መሣሪያው የሚኩራራ እንዳንቺ አይነት ሃያል አገር ሲነሳብኝ  ‹‹ከእኛ ውጭ አንቺን ማጥፋት የሚችል የለም›› ከሚል ሕግ ጋር የማይታይ ሃይል አስጨብጠው ዘመናዊ ጦር የታጠቀን ወራሪ በጎራዴና በጦር እንዳሸንፍ ያደርጉኛል፡፡ እንደ ቬትናም ያበረቱኛል፡፡
ብሊንከን እና ደብረ ጽዮን ሲመካከሩብኝ አላህና እግዜሩ ክንዳቸውን ያስጨብጡኛል፡፡ ግብጽና ሱዳን ሲተባበሩብኝ አማራን እና ኦሮሞን፣ አፋርና ደቡብን… አበርትተው ያስከብሩኛል።
‹‹ትግራይን እገነጥላለሁ›› የሚል ባንዳ ሠራዊቴን ሲጨፈጭፈው ‹‹ተገነጠለ›› የተባለውን ወደ ቦታው መልሰው ኢሳያስን ይልኩልኛል፡፡ ‹‹የውሃ ችግር ያጋጥመኛል›› በሚል ሰበብ አፈር ግጬ በላቤና በደሜ የገነባሁትን ግድብ በቦንብ ማፍረስ የሚመኝ ጎረቤት ሲነሳብኝ ከቦንብ የሚከብድ በረዶና ዝናብ ጥለው በጎርፍ ይጠርጉልኛል፡፡
በተረፈ ዶላር የሌለው ድሃ አገር ሁሉ ክብር የሌለው አይምሰልሽ፡፡ የቪዛ እገዳ ጥሎ መንግሥትን እንዳትመጣ በማለትና በእራሳቸው ምድር ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ‹‹አንተ ግባ፣ አንተ ውጣ›› በማለት መሃከልም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ስለሆነም በግድቤና በሕዝቤ ላይ ልወስን ማለትሽን ታቆሚ ዘንድ ስጠይቅሽ… ከነቀዝ ጋር እየተካፈልኩ ስበላው ለኖርኩት ስንዴሽ ያለኝን ምሥጋና እየገለጽኩ ነው፡፡
ያንቺው ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic