>

አቶ ብሊንከን ጦቢያን ማዋረዱን የቀጠለበት ለምን ይሆን? (መስፍን አረጋ)

አቶ ብሊንከን ጦቢያን ማዋረዱን የቀጠለበት ለምን ይሆን?

 

መስፍን አረጋ


አቶ ብሊንከን በማናቸውም ቀን ከዐብይ አህመድ ጋር ምክክር (consultation) ካደረገ፣ ከዐብይ አሕመድ ጋር ፍሬያማ ምክክር ማድረጉን በመጥቀስ በዚያኑ ቀን ወይም በነገታው የጦቢያን ሉዓላዊነት የሚያዋርድ መግለጫ (press statement) (በተለይም ደግሞ ያማራ ልዩ ኃይል “ከትግራይ” ባስቸኳይ ለቆ ይውጣ የሚል ቀጭን ትዛዝ) እንደሚያወጣ ሳይታለም የተፈታ ሁኗል፡፡  በተለይም ደግሞ አቶ ብሊንከን ከዐብይ አሕመድ ጋር ፍሬያማ ምክክር ለማድረግ የሚሽቀዳመው የአማራ ክልል አስተዳዳሪወች የክልላቸውን ሕዝብ መብትና ደሕንነት ለማስከበር የመነሳሳት ጭላንጭል ሲያሳዩ ሥራየ ብሎ እየጠበቀ ነው፡፡  የሚገርመው ደግሞ አቶ ብሊንከን አማራን ከሚወክለው ከኢትዮጵያዊ አቻው ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተመካከርኩ ቀርቶ ተነጋገርኩ ሲል ተሰምቶ የማያውቅ መሆኑ ነው፡፡  ያሜሪቃው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከጦቢያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር ለሰዓታት ከተመካከረ በኋላ የሚያወጣው መግለጫ፣ ለጦቢያው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሰበር ዜና ነው፡፡  ይህ ደግሞ አንድምታው ከዲፕሎማሲያዊ ደንብ ጥሰት እጅግ የከፋ ነው፡፡ 

እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የሚያመሩት ወደ አንድና አንድ ሕቅ ነው፡፡  አቶ ብሊንከን ሉዓላዊነቷን በመድፈር ጦቢያን ክፉኛ ማዋረዱን የቀጠለው፣ ዋና ሥራው የጦቢያን ሉዓላዊነት ማስከበር የሆነው ዐብይ አሕመድ አይዞህ ስለሚለው ብቻና ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም ቁልፉ ጥያቄ የሚከተለው ነው፡፡  አቶ ብሊንክን ጦቢያን ክፉኛ እንዲያዋርድለት ዐብይ አሕመድ በጥብቅ የሚፈልግበት ምክኒያት ምንድን ነው?  ጦቢያን ማዋረዱን ከቀጠለው ከአቶ ብሊንከን ጋር ዐብይ አሕመድ ፍሬያማ ምክክር ማድረጉን የሚቀጥለው ለምንድን ነው?  ምክኒያቱን ለማወቅ የአቶ ብሊንከንን መግለጫወች ይዘቶች እናጢን፡፡   

  • ትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ ተብለው የሚዘገቡት አሰቃቂ ወንጀሎች አሜሪቃን እጅጉን ያሳስባትል  (@SecBlinken, Feb 27, 2021)
  • የታጠቁ ኃይሎች በትግራይ ቤታደሮች (civilians) ላይ ከፍተኛ ወንጀሎችን እየፈጸሙ መሆናቸውን የሚያወሱ አያሌ ተዓማኒ ዘገባወች ተዘግበዋል፡፡  በተለይም ደግሞ የኤርትራና የአማራ ኃይሎች አድራጎት አሰቃቂ ነው … የኢትዮጵያ መንግስት ያማራ ክልል ኃይሎችን ከትግራይ አስወጥቶ ምዕራብ ትግራይን ለትግራይ ክልል መንግስት እንዲያስረክብ እናሳስባለን (Press Statement, Anthony J. Blinken, May 15, 2021)
  • የኤርትራና ያማራ ክልል ኃይሎችን ጨምሮ ለትግራይን ቀውስ ተጠያቂ በሆኑ ኃይሎች ላይ የቪዛ ማዕቀብ ተጥሏል  (Press Statement, Anthony J. Blinken,  May 23, 2021)   
  • ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ የኤርትራና ያማራ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ለማስወጣት ቃል እንዲገባ እናሳስባለን፡፡  የጦቢያ ውስጣዊ ድንበሮች ሕገመንግስቱን በመጣስ መለወጥ የለባቸውም (Secretary Blinken’s call with Ethiopian Prime Minister Abiy, Office of the Spokesperson, July 6, 2021)

 

በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰወች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ወንጀል አቶ ብሊንከንን ክፉኛ የሚያሳስበው፣ በትግሬወች ላይ ሲፈጸም ወይም ደግሞ ተፈጸመ ተብሎ ሲዘገብ ብቻ ይመስላል፡፡  እርግጥ ነው፣ በትግራይ ቤታደሮች (civilians) ላይ ሰቅጣጭ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያወሱ አያሌ ዘገባወች ተዘግበዋል፡፡  እነዚህ ዘገባወች ግን አቶ ብሊንከን እንደሚላቸው ተዓማኒ ዘገባወች (credible reports) ሳይሆኑ በገለልተኛ አጣሪ ያልተረጋገጡ፣ በይስሙላ ላይ የተመሠረቱ፣ ቦስተን የሚኖሩ ተዋኞችን (actors) ጨምሮ የተለያዩ አጠራጣሪ ዓይን እማኞችን ያጣቀሱ ኢተዓማኒ ዘገባወች ናቸው፡፡  ዘጋቢወቹ ደግሞ (በተለይም ደግሞ የ CNN, BBC እና AP ዘጋቢወች) ባፍቃሪ ወያኔነታቸው የሚታወቁ፣ አድልኦኛ (biased) ዘጋቢወች ናቸው፡፡  ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግራይ ቤታደሮች ለሰቆቃ የተዳረጉት ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡  ጦርነት ሲባል ጦሰኛ መሆኑን ደግሞ ላሜሪቃ መንገር ቀባሪውን ማርዳት ይሆናል::  ተጓዳኝ ጉዳት (collateral damage) የሚለውን ሐረግ ለመላው ዓለም ያስተዋወቀው ማን ሆነና?  ራሷ አሜሪቃ አይደለችም እንዴ?  

በሌላ በኩል ግን ዐብይ አሕመድ መንበረ ስልጣን ላይ ከተቀመጠ በኋላ የአማራ ሕዝብ እንደ ትግሬ ሕዘብ በዘገባ ብቻ ሳይሆን በቋሚና በተንቀሳቃሽ ምስሎች የተደገፈ፣ አሌ ሊባል የማይችል እጅግ አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ ዕለት በዕለት በሚባል ደረጃ በተደጋጋሚ ተፈጽሞበታል፡፡  ጭፍጨፋወቹ የተፈጸሙትና እየተፈጸሙ ያሉት ደግሞ የዐብይ አህመድ ክልል በሆነው በኦሮምያ ክልልና፣ ኦነጋውያን በበላይነት በሚቆጣጠሩት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡  አቶ ብሊንክን ግን ስለ አማራ ሕዝብ መጨፍጨፍ አንድም ቃል ሳይተነፍስ የቪዛ ማዕቀቡን የጣለው ለትግራይ ክልል ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ባላቸው ኃይሎች ላይ ብቻ ነው፡፡  

በትግራይ ቤታደሮች ላይ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚሉት ዘገባወች አቶ ብሊንከንን እጅጉን ቢያሳስቡትም፣ ባማራ ቤታደሮች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በገሃድ የሚመሰክሩት ፎቶወችና ቪዲዮወች ግን ዴንታ አይሰጡትም፡፡  ጆሮወቹን ለትግራይ ሴቶች መደፈር ቢከፍትም፣ ዓይኖቹን ግን ላማራ ሴቶች ማሕፀን መዘርከት ጨፍኗቸዋል፡፡  ተዓማኒነታቸው አጠራጣሪ በሆኑ ዘገባወች ላይ ብቻ ተመርኩዞ የኤርትራና ያማራ ኃይሎችን ነክሶ ቢይዝም፣ ሁለት ከተሞችን (አጣየንና ሸዋ ሮቢትን) ደምጥማጣቸውን አጥፍቶ፣ አስር ሺወችን ጨፍጭፎ፣ መቶ ሺወችን ያፈናቀለውን ኦነግ ሼኔን ግን ስሙን አንስቶት አያውቅም፡፡  ምክኒያቱን በትክክል ሳይናገር የአማራን ፋኖ በቪዛ ክልከላው ውስጠ ቢያካትትም፣ በማይካድራው ጭፍጨፋ የተከሰሰውን የትግሬውን ሳምሪን ግን በሱዳን በኩል እርዳታ ያደርግለታል፡፡    

የትግሬ ጎሰኞች (tribalists)  “ምዕራብ ትግራይ” የሚሉት መሬት፣ ወያኔው መለስ ዜናዊ ከጎንደር ክፍለ ሀገር ነጥቆ ወደ ትግራይ ያካተተውን ሰፌና ለም የአማራ መሬት እንደሆነ አቶ ብሊንከን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡  በዚህ የአማራ መሬት ላይ ደግሞ ወያኔ አማራወችን እያፈናቀለ ታጋዳላዮቹን በመትከል ከፍተኛ የሕዝብ አሰፋፈር ለውጥ (demographic change) ማድረጉን አቶ ብሊንከን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡  የማያውቅ ከሆነ ደግሞ ወያኔ በገፍ ያፈናቀላቸው አያሌ ወልቃይቴወች ወደሚኖሩበት ኦሃዮ (ኮሎምበስ) የራሱን ዘጋቢ ቢልክ እስኪያንቀው እየተነገረ፣ እስኪበቃው ያውቃል፡፡  አቶ ብሊንከን ግን አውቆ ስለተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም፡፡  

  • የአማራ ክልል ኃይል ከ”ምዕራብ ትግራይ” ብቻ ባስቸኳይ ወጥቶ ቦታውን የትግራይ አስተዳደር ባስቸኳይ እንዲረከበው አቶ ብሊንከን አጥብቆ የፈለገበት ሚስጥር ምንድን ነው?  “ደቡብ ትግራይ”ን ለማን አስቦት ነው?   
  • ኦነጋውያን ራሳቸውን የፈጠሩትን ቀውስ ሰበብ አድርገው “ደቡብ ትግራይን”  በኮማንድ ፖሰት ከተቆጣጠሩ በኋላ ኦሮምያን ከትግራይ ጋር ድንበርተኛ ለማድረግ የሚሯሯጡት ለምንድን ነው?   
  • በጦቢያ ለተከሰተው የዘረኝነት ቀውስ ብቸኛወቹ ተጠያቂወች ሕብረ ብሔራዊ የሆኑት አማሮች ሳይሆኑ አማራ የሚባል ብሔር የለም የሚሉት ወያኔወችና ኦነጋውያን መሆናቸውን አቶ ብሊንከን አውቆ እንዳላወቀ የሚሆነው ለምንድን ነው?  አማራ የሚባል ብሔር የለም ማለት አማራ ነኝ የሚል ሁሉ ይጥፋ ማለት አይደለም ወይ?  ወያኔወችና ኦነጋውያን ይሄን ማለታቸው ብቻ ወንጀለኞች አያደርጋቸውም ወይ?  
  • ሕዳጣኑ ወያኔ በሰፊው የኣማራ ሕዝብ ላይ ለሃያ ሰባት ዓመታት የዘር ጭፍጨፋ ዶፍ ሊያወርድ የቻለው፣ ምዕራባውያን በእርዳታና በበጀት ድጎማ ሰበብ ቢሊዮኖችን እያዘነቡለት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ስለደገፉት ብቻና ብቻ እንደነበር፣ የአፍቃሪ ወያኔዋ የሱዛን ራይስ ምክትል የነበረው አቶ ብሊንከን እንዴት ይረሳዋል?
  • በ 2007 ዓ.ም ባደረኩት የሕዝብ ቆጠራ 2.5 ሚሊዮን አማሮች ድራሻቸው ጠፍቶብኛል በማለት ወያኔ ያወጣውን ይፋ መግለጫ፣ በዘመኑ የጦቢያን ጉዳይ ባንክሮ ይከታተል የነበረው አቶ ብሊንከን እንዴት ላይሰማ ይችላል?
  • አቶ ብሊንከን ለትግራይ ቀውስ ተጠያቂ ያደረጋቸው የኤርትራና የአማራ ኃይሎችን ብቻ እስከሆነ ድረስ፣ የወያኔ አባሎችን ቪዛ የከለከለበት ትክክለኛ ምክኒያት ምንድን ነው?  ምክኒያቱን ለመናገር ያልፈለገውስ ለምንድን ነው?  ወያኔን በቪዛ ክልከላው ውስጥ ያካተተው ፍትሐዊና ሚዛናዊ ለመባል ብቻ ከሆነስ?  ለነገሩማ አብዛኞቹ የወያኔ ከፍተኛ አመራሮች ወይም ስለሞቱ፣ ወይም ስለጃጁ፣ ወይም ደግሞ እዚያው አሜሪቃ ስለሚኖሩ የቪዛ ክልከላው አይነካቸውም፡፡  
  • የቪዛ ክልከለው በክልከላነቱ ትርጉምቢስ ቢሆንም አንድምታው ግን ትርጉምበሽ ነው፡፡  ዋናው ትርጉሙ ደግሞ በዘር ጭፍጨፋ ለመክሰስ መንደርደርያ መሆኑ ነው፡፡  አቶ ብሊንከን በዘር ጭፍጨፋ ከስሶና አስከስሶ በሄግ ፍርድ ቤት ሊገትር ያሰበው እነማንን ነው? 
  • ወደ ትክክለኛው የትግራይ ክልል ዝር ብሎ የማያውቀው ያማራ ክልል ኃይል፣ ትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ ተብለው ለተዘገቡት ወንጀሎች ተጠያቂ የሚሆንበት ምክኒያት ምንድን ነው?  
  • በትግራይ ሰላማውያን ላይ ተፈጸሙ ተብለው የተዘገቡት ወንጀሎች በርግጠኝነት ከተፈጸሙ፣ ዋናው ተጠያቂ መሆን ያለበት ራሱ ወያኔ አይደለም ወይ?  ወያኔ ለፖለቲካዊ ጠቀሜታ ሲል ብቻ ሰላማዊ ትግሬወችን እንደሚጨፈጭፍና እንደሚስጨፈጭፍ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ አይደለም ወይ?  ወያኔ ትግሬንም ቢሆን ጭዳ ከማድረግ እንደማያቅማማ ሐውዜን ላይ በግልጽ አስመስክሮ የለም ወይ? 
  • በኮሮና ዘመን የዓለም ጤና ድርጅት መሪ በመሆኑ በዓለም ላይ ከፍተኛ ታዋቂነት ያለውን የዲባቶ (ዶክተር) ቴድሮስ አድሃኖምን ቤተሰቦች ገድሎ ወይም አስገድሎ ዲባቶውን ባደባባይ ማስለቀስ፣ ለወያኔ ዓለም አቀፍ አዘኔታና ከፍተኛ ድጋፍ አያስገኝለትም ወይ?  የወያኔነት አንዱና ዋናው መለያ ዓይን ዓውጣ ቀጣፊነት ስለሆነ፣ የወያኔ ከፍተኛ አባል የሆነው ቴድሮስ አድሃኖም ለወያኔ ድጋፍ ለማስገኘት ሲል ብቻ ዘመዶቸ ተገደሉብኝ ብሎ በውሸት አልቅሶ ከሆነስ?  የትኛው የአማራ ልዩ ኃይል ዐባል ነው የቴድሮስ አድሃኖም ቤተሰቦችን ለይቶ የሚያውቀው?
  • ወያኔን ከተፋለሙት ሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎች ውስጥ፣ የአማራ ክልል ኃይል ብቻውን ተነጥሎ የሚወቀስና የሚከሰስበት ምክኒያት ምንድን ነው?
  • የትግራይን ዘመቻ የሚመራው፣ ጠቅላይ አዛዡ ኦሮሞ፣ ኢታማዦር ሹሙ ኦሮሞ፣ መከላካያ ሚኒስትሩ ኦሮሞ፣ አየር ኃይል አዛዡ ኦሮሞ የሆነበት የፌደራል መከላከያ ኃይል ሆኖ ሳለ፣ አቶ ብሊንከን ሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በዘመቻው ውስጥ ንዑስ ተሳታፊ በሆነው ባማራ ክልል ኃይል ላይ ብቻና ብቻ የሆነበት ምክኒያት ምንድን ነው?  የክልል ኃይል በመሆኑ ከሆነ፣ የአፋርና የሱማሌ ክልል ኃይሎችስ በዘመቻው ተሳትፈው የለም ወይ?
  • ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ አሮሞወች የተቆጣጠሩትን የፌደራል መከላከያ ኃይልን ስም ላለማጥፋት አቶ ብሊንከንና ወያኔወች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?  ትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል ተብለው ከተዘገቡት አያሌ ወንጀሎች ውስጥ ባንዱም እንኳን የፌደራል መከላከያ ኃይልን ያልከሰሱበት ምክኒያት ምንድን ነው?  የኦሮሞ ወታደሮች ትግሬ አፍቃሪወች፣ የአማራና የኤርትራ ወታደሮች ደግሞ ትግሬ ጠሎች ናቸው ለማስባል ይሆን?  የትግሬና ያማራን ፀብ ዘላለማዊ ለማድረግ ታቅዶ ከሆነስ?
  • ከሁሉም የኢትዮጵያ የክልል ኃይሎች እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነው የኦሮምያ ክልል ኃይል የትግራይን ቀውስ በተመለከተ ስሙ ተነስቶ የማያውቀው ለምንድን ነው?  በትግራዩ ቀውስ ውስጥ ኦሮሞ እጁ ንጹሕ ነው እንዲባል ይሆን?
  • ሱዳን የአማራን ግዛት በይፋ መውረሯን አቶ ብሊንከንና ዐብይ አህመድ ማውገዝ ቀርቶ በይፋ የማይናገሩት ለምንድን ነው?  ወረራውን ስለሚስማሙበት ወይም ስለሚደግፉት ወይም ስላመቻቹት ይሆን?
  • ወያኔ ያማራን መሬት የነጠቀው ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቁ በፊት መሆኑን እያወቀ፣ አቶ ብሊንከን ኢትዮጵያ ውስጣዊ ድንበሮች ሕገመንግስቱን በመጣስ መለወጥ የለባቸውም ያለበት ምክኒያት ምንድን ነው?  አማራን በጨቋኝነት የሚፈርጅ፣ አማራን ያላሳተፈ፣ በአማራ ጥላቻ ጥርሳቸውን በነቀሉ ጽንፈኛ ወያኔወችና ኦነጋውያን የተረቀቀ ፀራማራ ሕገመንግሥት አማራን በተመለከተ ፍትሓዊ ሊሆን እንዴት ይችላል?
  • ያቶ ብሊንከን የዘወትር ፀራማራ መግለጫወች ዋና ዓላማቸው የአማራ ክልል መሪወችን በዘር ጭፍጨፋ ወንጀል በማስፈራራት ለአብይ አሕመድ ዐሜን ብለው እንዲገዙ ለማድረግ ቢሆንስ?

 

ጥያቄወቹ ማለቂያ ባይኖራቸውም መልሶቻቸው ግን የሚያመሩት ወደ አንድና አንድ ድምደማ ብቻ ነው፡፡  ወያኔ፣ ዐብይ አሕመድና አቶ ብሊንከን በመመሳጠር፣ በመተባበርና በመቀናበር የኢትዮጵያ ምሰሶ የሆነውን አማራን በታትነው ጦቢያን ለማፈራረስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡  የመጨረሻ ግባቸው ደግሞ “ምዕራብ ትግራይን” በቅርቡ ለምትፈጠረው የትግራይ ሪፓበሊክ፣ “ደቡብ ትግራይን”  አብይ አህመድ ሰባተኛ ንጉስ ሊሆንበት ላቀደው ለኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) በመስጠት፣ እነዚህ ሁለት አገሮችና ሱዳን ክፉኛ የተዳከመውን የአማራን ክልል ሙሉ በሙሉ በመክበብ የምሥራቅ አፍሪቃ አርመኒያ (Armenia of East Africa) ማድረግ ነው፡፡ 

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic