>

"አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ"!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

“አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ”!!

የትናንቱ ሌባ፣ ሙሰኛ፣ እስረኛ… የዛሬው የሽግግር መንግስት አዋላጅ…ታምራት…?!!!? 
ዳንኤል ገዛህኝ

ታምራት ላይኔ ከሰሞኑ በአሽከርነት የሚተውኑበት የወያኔው ሌላ ስርአት በአሜሪካ ፋይናንስ እውን ለማድረግ ከወዲሁ ከሌላው የሙስና አባት ከስዬ አብርሃ ጋር እንዲሁም እድሜ ዘመኑን ስለ ጓደኝነት ፍቅር እያለ በረከት ስምኦንን ሲያወድስ ከኖረው ያሬድ ጥበቡ ጋር ጓዳ ጓዳ ማለት ጀምሯል
የእነዚህ የከሸፉ ፓለቲከኞች ሴራ እና የአሜርካዎች የገንዘብ ድጋፍ ቅጥቅጥ መንግስት በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የማለም እንቅስቃሴ ከህልም የሚያልፍ እንደማይሆን እሙን ነው። የሆነው ሆኖ እነዚህ ፓለቲከኞች በንጹሀን ዜጎች እልቂት እጃቸው በደም የጨቀዩ መሆናቸውን ተገፊው ህዝብ አሳምሮ ያውቃል። ስዬ አብርሀ በበደኖ እና ወተር፣ አርሲ አርባ ጉጉ እልቂት ዋና ተዋናይ ናቸው። ታምራት ላይኔም ቢሆኑ የህንጻ ኮንስትራክሽን  ድርጅቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ አፍርሰው መላውን ሰራተኛ እና ቤተሰብ ለጎዳና የዳረጉ ፣ በሌላ በኩል የአፋር እና የሶማሌ ብሄረሰቦችን በሰፊው የአማራ ህዝብ ላይ ለጥቃት እንዲነሳሳ በሚያደርጉ ቅስቀሳቸው፣ የህዝብ ሀብት በመመዝበር ተለይተው የሚታወቁ ርካሽ ፓለቲከኛ ናቸው።
ታምርራት ላይኔ ከእስር ከወጡ በሁዋላ ያጎደሉበትን ህዝብ በአግባቡ ይቅርታ ይጠይቃሉ ብለን ስንጠብቅ ጭራሽ እርሳቸው በባርነት የሚያገለግሉበት ሌላ የወንበዴ ስርአት በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን የእንቅስቃሴው ፊት አውራሪ ሆነው ብቅ ማለታቸውን ብሰማ በነጻው ፕሬስ ውስጥ በነበሩኝ የአመታቶች ቆይታዬ ያለ ጥፋታችን ከጣቢያ ወደ ፍርድ ቤት፣ ከፍርድ ቤት ወደ ወህኒ የተጋዝንበትን የዚሁ ፓለቲከኛ የቡና ስርቆት ታሪክ ትውስ አለኝ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ቤተክርስቲያን ስማቸውን ለጊዜው በማልጠቅሳቸው ጳጳስ ይተዳደር በነበረበት በታምራት ላይኔ የስልጣን ዘመን ፣ በተጠቀሰችው ሀገረ ስብከት ለደረሱ የአብያተ ክርስቲያናት ውድመት እና የቃጠሎ አደጋ ለልማት ይውል ዘንድ ከፍተኛ የቡና ሽያጭ ይፈቀዳል። የቡናው ሽያጭ በጣም ከፍተኛ ብዙ ሚልዮናት ለሀገረ-ስብከቷ የሚያስገኝ እና በገቢውም የወደሙ አብያተ-ክርስቲያናት የልማት ስራ እንዲውል የተወሰነበት ነበር። ይሁን እና የቡናውን ከፍተኛ የሽያጭ ድርሻ ታምራት ላይኔ የመዘበሩ ሲሆን በተዋረድ ሰማቸውን የማልጠቅሳቸው ጳጳስ እንዲሁም ሁለት አሁንም ስማቸውን የማልጠቅሳቸው ረዳቶቻቸው የሆኑ በ1990ዎቹ ዘመናዊ ሀች ፓክ ቶዮታዎች የተንበሸበሹ የስራ ደረጃቸው ዲያቆኖች ለአብያተ-ክርስትያኖቹ ምንም አይነት ገንዘብ ለልማቱ ሳያውሉ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመውታል። በግርድፉ ከላይ የጠቀስኩትን የደቡብ ጎንደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሀገረ- ስብከት የቡና ምዝበራ ዘገባ በገመና ጋዜጣ ለንባብ ካበቃን በሁዋላ የጋዜጣዋ አሳታሚ እና ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ሀይማኖት ቀደም ብሎ ለጥቆ እኔ በወረዳ 14 ፓሊስ ቁጥጥር ስር ዋልን።
ልብ በሉ! ይህ ሲሆን ታምራት ላይኔ በምዝበራ ሌብነት እና ሙስና ተመክሬ ተመክሬ ከድርጊቴ ልታቀብ ባለመቻሌ …ገለመሌ ብለው ስልጣናቸውን ተገፈው ለእስር በተዳረጉበት ወቅት ነው። በጊዜው በ48 ሰአት ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታችን ተገፎ ለ15 ቀናት ፍርድ ቤት ሳንቀርብ ወረዳ 14 ግቢ ውስጥ ተበላሽተው በቆሙ፣ በበሰበሱ ፣ እጅግ በጣም በዛጉ፣ በውስጣቸው አረም በሞላባቸው አይጥ በሚርመሰመስባቸው  ሁለት ቮልስ ዋገን መኪናዎች ውስጥ ታስረን ቆየን።  በሁዋላም ከጣብያው እስረኞች ጋር እንድንቀላቀል ስንደረግ በአጋጣሚ ከህግ አግባብ ውጭ የታሰሩ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ስራተኛዎችን ብሶት የሙስና ታሪክ አግኝተን ከእስር ለተረፉት ባልደረቦቼች መረጃውን ከእስር ቤት አጠናቅረን በመላክ ገመና ጋዜጣ ላይ ለንባብ እንዲበቃ ስናደርግ ፓሊስ ጣብያው ታመሰ። ከጉዳዩ ሌላ የሙስና መረብ በመዘርጋት ላይ የነበረውን የሌባ ቡድን ራቁቱን አስቀረነው። በዚህ መሀል
ክሱ የሚመለከተው ዋና አዘጋጁን ነው በሚለው የዘመኑ የፕሬስ ህግ/አዋጅ/ መሰረት እኔ በእስር እንድቆይ ተደረግኩ ። በእስር ቆይታችን ሁለታችንም ሆን ተብሎ በውሻ እንድንነከስ ተደርገናል ።
ከሀያ ቀናት በላይ በእስር ቆይቼ ፍርድ ቤት እንድንቀርብ ሲታወቅ ጳጳሱ እና ሁለቱ የታምራት ላይኔ የቡና ዘረፋ ኔትወርክ ባለሟሎች በመርማሪ ወታደር ውብእሸት አማካኝነት እስር ቤት ድረስ በመምጣት ተደጋጋሚ ማስፈራራት አድርገውብኛል።  በሁዋላም ጊዮርጊስ አራዳ ምድብ ችሎት ከሀያ ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት ልቀርብ ስል ግቢው ውስጥ ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ።
መዝገብ አቅራቢው ስሜን ጠራ ከተቀመጥኩበት ድንጋይ ተነሳሁ መርማሪዬ እና መሳርያ የታጠቀው ወታደር ተነጋገሩ። ግራ ሲጋቡ አየሁዋቸው ። መዝገብ አቅራቢው ደግሞ ደጋግሞ ስሜን ጠራ። ነገር ግን መርማሪዬ እና ታጣቂው አጃቢዬ የእጅ መታሰርያ ካቴናዬን ቁልፍ መክፈቻ ባለመያዛቸው ሌሎች እስረኞች ይዘው የመጡ መርማሪዎች የያዙዋቸው እስረኞች የታሰሩባቸው ካቴናዎች መክፈቻ ቁልፍ የእኔን ይክፍት እንደሆነ ትብብር ጠየቁ። ነገር ግን ከዘጠኝ በላይ የካቴና ቁልፎች እኔ የታሰርኩበትን ካቴና አልከፍት አለ። መዝገብ አቅራቢው ለሶስተኛ ጊዜ በቁጣ ተጣራ እናም መርማሪዬ እየተርበተበተ የካቴናው ቁልፍ መጥፋቱን ነገረው። ምርጫ ባለማግኘታቸው እጆቼ ወደፊት… ስሬቱ ጀርመን በሆነው ካቴና እንደታሰርኩ ዳኛ ፊት ቀረብኩ። ዳኛው መዝገቡን ቀደም ብሎ ስላየው ወጣት ዳኛ ነው ፣ በካቴና በመቅረቤ ይብሱኑ እየተበሳጨ በዚህ መልኩ ልታቀርቡት አይገባም ሲል ለመርማሪው ሲነግረው እኔም በበኩሌ አቤቱታ አለኝ በማለት የደረሰብኝን ዘረዘርኩ። ዳኛው በበቂ ዋስ እንድለቀቅ ወሰነልኝ።
ይሁን እና ወደፓሊስ ጣቢያ ተመልሼ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጸመብኝ። ይደረግብኝ የነበረውን ሁኔታ ፓሊስ ጣቢያው ውስጥ ይከታተሉ የነበሩ ሰብአዊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች ለአዲስ አበባው አለም አቀፍ የቀይመስቀል ኮሚቴ አሳወቁ። ቢሮው ሊጎበኘኝ ቢመጣም ፍቃድ ሳያገኝ ቀረ እና በውጭ ተመለሰ። ይህ ሁሉ የሚፈጸመው ታምራት ላይኔ ቡና መስረቁን አምኖ በሙስና ወህኒ በወረደበት ወቅት ነው። ታምራት ላይኔ እኔ እና መሰል ዜጎች በእርሳቸው የሌብነት ተግባር የተነሳ የደረሰብን ቁስል ሳይጠግ ዳግም የኢትዮጵያን ህዝብ ሞግዚት ሊሆኑት ተነሱ።
ይቀጥላል…
Filed in: Amharic