አሳዬ ደርቤ
የምንወዳት አገር መሪ እንደመሆንዎ መጠን ጠላታችንን ድባቅ መትተን ድል ልናስጨብጥዎ ብዙ ጊዜ ሞከርን፡፡ ፓርቲዎና እርስዎ ግን በዜጎች መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ወደ ትግል እየቀየራችሁ አስቸገራችሁን።
እያንዳንዱን ውጤት ወደ ስኬት በመቀየር ፈንታ የትግሉ እኩሌታ ላይ ‹‹የአገራችን ቀንደኛ ጠላት የተበተነ ዱቄት ሆኗል›› የሚል ድል እያበሰሩ የሚያዘናጉ ሆኑብን፡፡ ጂራቱን እና ወገቡን የተመታውን እባብ ጭንቅላቱን ፈጥፍጦ ዳግም እንዳይነሳ ማድረግ ሲቻል ‹‹ጂራቱን ከተመታ መሞቱ አይቀርም›› ብለው ወደኋላ እየተመለሱ በጠበጡን፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
በጦር ሜዳ ላይ ይቅርና በሩጫው ሜዳም ላይ አትሌቶች ወደ ፊት እየገሰገሱና ወደኋላ እየተመለሱ ተጋጣሚያቸውን ያዳክማሉ፡፡ የተሻለ ጉልበትና ፍጥነት ያላቸውም በውድድሩ ፍጻሜ ላይ ድል ያደርጋሉ፡፡
እርስዎ ግን አትሌቶቹ ውድድሩን እስኪጨርሱ በመጠበቅ ፈንታ በሩጫው መሃከል ላይ ‹‹ይሄን ያህል ከፊት ከፊት በመገስገስ አቅማችሁን ካሳያችሁ በቂ ስለሆነ ወደኋላ ተመለሱ›› ወይም ‹‹አቋርጧችሁ ውጡ›› የሚሉ አሰልጣኝ ሆኑብን፡፡ በሆነ ስቴዲየም ላይ ጎል አግብቶ መምራት የቻለ ቡድኑን ‹‹ቀሪውን አርባ አምሥት ደቂቃ ደግሞ የምንጫወተው በሌላ ስቴዲየም ነው›› ብሎ በእረፍት ሰዓት ከእነ ቡድኑ የሚጠፋ አሰልጣኝ ሆነው አስቸገሩን፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ መቆየት የቻለችው የእርስዎ ፓርቲ ሕዝብና አገርን ማስተዳደር ስለቻለ ሳይሆን መንግሥቱን እና አገሩን የሚያስተዳድር ሕዝብ በመፈጠሩ ነው፡፡ መንግሥት ሲቸገር የእለት ጉርሱን ሰጥቶ ጦሙን የሚያድር፣ አገር ስትደፈር ሕይወቱን የሚገብር፣
ሊያፈርሱት ሲሞክሩ እንቢኝ ብሎ የሚጣመር፣ መንግሥት የተወሰደበትን የዲፕሎማሲ ብልጫ ለማስመለስ ትዊተር ላይ ሲዘምት የሚያድር፣
የኢትዮጵያ ጠላቶችን የሚያጓጓ ምርጫ ሲዘጋጅ በሚፈልገው ፈንታ የማይፈልጉትን መርጦ እቅዳቸውን የሚያጨናግፍ፣
ምዕራባውያን በደካማ መንግሥቱ ላይ ሲያሴሩበት ማንም ሳይጠራው ‹‹እጃችሁን አንሱ›› ብሎ በአደባባይ የሚሰለፍ፣ አሸባሪ ሲነሳ ስንቅና ትጥቁን ችሎ እንደ ወታደር የሚሰለፍ “መንግሥታዊ ሕዝብ” በመፈጠሩ ነው፡፡
በበቂ ምክንያት ከትግራይ ወታደርዎን ባወጡ ማግሥት ያላንዳች ምክንያት ከኮረምና ከአላማጥም ሲደግሙት ‹‹ለምን?›› በማለት ፈንታ ‹‹ከባድ አደጋ አጋጥሞት ይሆናል›› በሚል ምክንያት ግራካሶ ላይ ዳግም ለመሰዋት ተሰልፎ የሚወጣ ሕዝብ በየስፍራው በመፈጠሩ ነው፡፡
የእርስዎ መንግሥት ግን…
ዛሬ ከሕዝቡ፣ ነገ ከምዕራቡ ጋር እየተሰለፈ የሚወዛገብ፣ ከድክመቱ ተምሮ ጠንካራ በመሆን ፈንታ በቁማርና በሤራ ጨዋታ የሚተበተብ፣ በማፈግፈግ ሰበብ ወታደሩን እየሳበ ሕዝቡንና አገሩን ለአሸባሪ የሚያስረክብ፣ በደገፉት ቁጥር እራሱን አንቅፎ እየጣለ መሬት ለመሬት የሚሳብ፣
ጦር ሜዳ ላይ ክላሹን ጥሎ ችግኝ መትከል የሚያስብ፣ በእራሱ አመራር እንዝላልነት መሳሪያውን እና ጦሩን ለጠላት የሚያስረክብ፣ በአሉላ ሥም የተሰየመ የክህደት ዘመቻ ሲሰነዳ የችግን ተከላ ዘመቻ አውጆ የሚያነጅብ… ሆኖ አሸናፊውን ሕዝብ ተሸናፊ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ጠላታችን ጠላትዎ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ትግላችን ግን ትግልዎ ነው ወይ? ድላችንስ ድልዎ አይደለም ወይ?
➜ለምን ይሆን በስንት ትግል የተገኘውን ድል ወደ ሌላ ትግል የሚቀይሩብን?
➜ለምን ይሆን አገሩን እና ሕዝቡን በመጠበቅ ፈንታ ‹‹ትተኸን አትሄድም›› እየተባለ በሕዝብ የሚጠበቅ ወታደር የፈጠሩብን?
➜አሸባሪው ክላሽ አስይዞ ያዘመታቸውን ሕጻናት ላለመጉዳት ቤታቸው ውስጥ ጡጦ ይዘው የተቀመጡት ለጥቃትና ለስዴት የሚዳረጉት እስከ መቼ ድረስ ነው?
➜የተናጠል ተኩስ አቁሙን ሰርዘው በሙሉ አቅምዎ የምድርና የአየር ጦርዎን በማንቀሳቀስ ለአሸባሪው የሚመጥን መልስ የሚሠጡት ጦርነቱ የትኛው ከተማ ላይ ሲደርስ ነው?
➜አላማጣና ቆቦ ሆኖ ወልድያን ለማውደም የሚመኘውን ርሃብተኛ መንጋ ወደ ጉሬው መመለስ ያልተቻለው ከአሸባሪው ያነሰ ሕዝብ ወይስ ገንዘብ፣ ወታደር ወይስ አመራር፣ ትጥቅ ወይስ ስንቅ? ስላለዎት ነው?
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- የምር ግን እርስዎም ሆነ ፓርቲዎ ይሄን ጦርነት በድል አጠናቅቆ የአገርን ቀጣይነት የማስቀጠል ፍላጎት አለው ወይ? እኔ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፡-
አገር መምራት የሚፈልግ መንግሥት እርሻውን አስትቶ ለውጊያ የጠራውን ገበሬ ጦር ሜዳ መሃከል በትኖ አይጠፋም፡፡ ጦር መሣሪያ አስይዞ ያስገባውን ወታደር በቅጽበታዊ ውሳኔ ባዶ እጁን እያስወጣ ጠላቱን አያስታጥቅም፡፡ ሕዝቡን እና ከተማውን ለተራበ ጅብ አያስረክብም፡፡ በአሸባሪ የተሞላውን ቀጠና ማጽዳት ሲገባው የጨዋታውን ሜዳ ቀይሮ ደጀኑን አያስወጋም፡፡ በጦርነት መሃከል ሠራዊት ምልመላ ውስጥ አይገባም፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ከአሸባሪ ጋር የሚደረገው ውጊያ መንግሥታዊና አገራዊ ነው በማለት እስካሁን ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ግን ይብላኝ ለአገራችን እንጂ በእኛ ላይ የመጣውን ጥቃት ስደተኛ በመሆን ፈንታ አርበኛ ሆነን እንመክተዋለን፡፡
በተመረጠው ደካማ መንግሥት ፈንታ የጎበዝ አለቆቻችንን መርጠን ለእራሳችን ጥያቄ የእራሳችንን መልስ እንሰጣለን፡፡ በእኛ ሕይወት የሁሉንም አሸናፊነት ማረጋገጡ ቢቀርም በእራሳችን ትግል የእራሳችንን ድል እንደምንጎናጸፍ አንጠራጠርም፡፡ ያንንም ማድረግ ጀምረናል፡፡
አበቃሁ፡፡