>

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልታሳልፈው የነበረውን ውሳኔ አዘገየች... !!! (ኢ.ፕ.ድ)

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ልታሳልፈው የነበረውን ውሳኔ አዘገየች… !!!

(ኢ.ፕ.ድ) – መሐመድ ሁሴን

*… የኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የተቀናጀ ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው…!!!
 
የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕልማሲ ኣባለት እና የተለያዩ ትውለደ ኢትዮጵያዊያን (ዳያስፖራዎች) ባደረጉት የተቀናጀ ንቁ ተሳትፎና ዘመቻ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ተመስርታ በምክር ቤቷ በማቅረብ ልታስወስነው የነበረውን የ”ኤችአር445” ረቂቅ ማዘግየቷ ታውቋል።
የኢትዮጵያዊያን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት በተቀናጀ መልኩ ከአሜሪካ የኮንግረስ አባልዋ ካረን ባስ ጋር ባደረጉት ውይይት እውነታውን ማስረዳት ችለዋል። በዚህም የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች ኢትዮጵያን በውሸት በማጠልሸት ተጨማሪ ጫና ለማሳደር የሄዱበትን እኩይ ተግባር አክሽፈዋል።
የአሸባሪው ድርጅት አባላት የሕወሓት ታጣቂዎችና ካድሬዎች በዜጎች ላይ እየፈጸሟቸው ያሉ አስነዋሪ ድርጊቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የኢትጵያ መንግስት እንደፈጸማቸው በማስመሰል ለአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ በዚህም ምክንያት ለአሜሪካ ኮንግረንስ ሊቀርብ የነበረውና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው ኤችአር 445 (HR 445) የተሰኘው ሰነድ ከመጽደቁ በፊት እውነታውን ኢትዮጵያ ተገኝተው ለማጣራት የኮንግረስ አባልዋ ካረን ባስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
በአሸባሪው ሕወሓት እና  በርዝራዦቹ እየተፈጸሙ የሚገኙ ወንጀሎችን በተለይም  ሕጻናትን ለውትድርና እየተጠቀሙ መሆናቸውን፣ ግድያና ዝርፊያዎችን በስፋት እየፈጸሙ ስለመሆናቸውና  መጠነ ሰፊ ግፍ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የአሜሪካ መንግስት ይህን ድርጊት ማውገዝ ቀርቶ አንዲት ነገር ማንሳት አለመቻሉ ለምንድን ነው ሲሉም የኮንግረንስ አባሏን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጠይቀዋል።
የአሸባሪው ቡድን አባላት በንጹሀን የአማራ ተወላጆች ላይ በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በየአካባቢው የተፈጸሙ ግልጽ የሆኑ የንጹሀን ግድያዎች እና ተያያዥ ችግሮችን አሜሪካ ለምን አላወገዘችም? ሲሉም ጠይቀዋቸዋል።
 ከዚህ አልፎ አሸባሪው ቡድን በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ተግባር ለምን በቸልተኝነት ይታያል?፤ መንግስት ሕግ ለማስከበር የወሰዳቸው ተገቢ የሆኑ ርምጃዎች ስለምን እውቅና ተነፈጋቸው? የፈዴራል መንግስት ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፎችን ለማድረስ ያደረጋቸው ከፍተኛ ጥረቶች አሜሪካ ለምን በአዎንታዊ መመልከት ተሳናት ? የሚሉ ጉዳዮችንም የፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት ለካረን ባስ አንስተው ጠይቀዋቸዋል።
ካረን ባስም ይህንን ግልጽ የሆነ ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት እውነታውን ለመረዳት የፊታችን መስከረም ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ እስከዚያው ድረስም የተባለውን የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ እንደማያቀርቡት መግለጻቸውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት አስታውቀዋል።
Filed in: Amharic