>

''ኣሰባሳቢ ማንነት፣ ባንድ ሃገር ልጅነት'' መጽሃፍ በኦስሎ ተመረቀ

Book signing Oslo
Ato Yussuf Yassin book signings 1በቀድሞው የጦቢያው መጽሔት ጸሃፊ ሃሰን ዑመር ኣብደላ – ኣቶ የሱፍ ያሲን የተጻፈው  ”ኣሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት፣
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ” በሚል ርዕስ ለንብብ ያቀረቡት መጽሓፍ የኦስሎ ነዋሪዎችና ከኣካባቢው ኣውሮፓ  ሃገሮች የመጡ እንግዶች በተገኙበት በደማቅ ዝግጅት ተመርቆኣል።
በኖርዌይ ኦስሎ ”ፔ” ሆቴል በተያዘው ኣዳራሽ የተዘጋጀው የመጽሃፍ ፣ምረቃ ስነ ስርዓት  የተጀመረው በቅርቡ  ከ 40 ዓመታት በላይ በስደት ኖረው በሞት ለተለዩት ደራሲና ባለቅኔ ሃይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው) በመዘከርና የህሊና ጸሎት በማድረግ ነበር።
 በ 16 ሰዓት የተጀመረው የመጽሃፍ ምረቃና ስነ ስርዓት በበዓሉ ኣዘጋጅና ኣስተባባሪ በኣቶ ዳዊት መኮንን ኣቅራቢነት በተዘጋጅለት መርሃ ግብር መሰረት የተጀመረ ሲሆን፣ በዚሁም መሰረት ኣዘጋጅ ኮሚቴው ቀደም ሲል መጽሃፉን ጊዜ ወስደው ኣንብበው ሙያዊ ክሆሎትን ያካተተ ግምጋሜያቸውን ለታዳሚው ያደርሳሉ ያላቸውን ሶስት ኣባላቶች  ማለትም  ኣቶ እንግዳሸት ታደሰ፣  ዶክተር ተክሉ ኣባተና ፓስተር ዮሃንስ ተፈራ  በመጋበዝ መጽሃፉን ኣንብበው የደረሱበት ውጤትና ”የኣሰባሳቢ ማንነት መጽሃፍ” ን የተመለከቱበትን ምልክታና ዕይታ ለደራሲውም ሆነ ለተደራሲው  ኣቅርበዋል።
ኣቶ የሱፍ ያሲንም በገምጋሚዎቹ በኩል የቀረቡትን ዕይታዎች የተቀበሉትና የተስማሙበት ሲሆን፣ ማብራሪያ ለሚፈልጉ ጥያቄዎችም ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ሶስቱ ገምጋሚዎች ከመጽሃፉ ሽፋን ጀምሮ ቴክኒኩን፣ የመጽሃፉን ምልከታ፣ ኣወቃቀሩን በኣጠቃላይ የመጽሃፉን ይዘት በጥልቅና በስፋት የገመገሙ ሲሆን፣ በኣቶ የሱፍ ያሲን የተጻፈውን ”ኣሰባሳቢ ማንነት፣ በኣንድ ሃገር ልጅነት የተሰኘው” መጽሃፍ  ኣከራካሪና ጊዜያዊ ውይይትን የሚፈጥር ሆኖ ነገር ግን ማሰሪያውና መደምደሚያው የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታን የሚነግር መሆኑን በገምጋሚዎቹ ለታዳሚዎች ተገልጾኣል።
ደራሲውም  በቀረቡት ሃሳቦች ላይ የራሳቸውን ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም መጽሃፉ ስሜታዊ ማነሳሳትንና የሃሳብ  ልዩነቶችን ከነመፍቻ መንገዳቸው የሚገልጽ ሆኖ፤ ነገር ግን በመጽሃፉ ጀርባ ላይ በዶክተር ደረጀ እንደተሰጠው ኣስተያየት ”የልቡን የሚናገር” በሚለው ተናግሬ ያወጣሁትን መጽሃፍ እናንተም ኣንብባችሁ የውስጣች ሁን ታካፍሉ ዘንድ  በማለት መጽሃፉን  ለኣንባቢ ማድረሳቸውን ኣሳስበዋል።
በኣጠቃላይ የኖርዌይ ማህበረሰብ የተገኘበት ይሄው የመጽሃፍ ምረቃ ስነ ስርዓት  በዝግጅት ይሁን  በይዘቱ የተዋጣለት እንደነበር ለመረዳት የቻልን ሲሆን፣ በመጨረሻም” ኣሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሃገር ልጅነት መጽሃፍ” በታዳሚ ኣስተያየት ተሰጥቶበት የዝግጅቱ ስነ ስርዓት ተጠናቆኣል።
Filed in: Amharic