>

ችግር የለም! — ችግር ነው ጌትነት! ( በፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፤ 2010 ዓ.ም.)

ችግር የለም! — ችግር ነው ጌትነት!

በፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፤ 2010 ዓ.ም.
    “ሆድ ሲያውቅ ዶሮማታ መሆኑን አውቃለሁ፤
         አልቀበር እንጂ እኔኮ ሞቻለሁ፤”
                     (— መ.ወ.ማ.፣ እንጉርጉሮ)
አሳፍ ሀይሉ

«ኪዩባውያን አንድ መጥፎ ነገር አስተምረውን ሄደዋል፤ “ችግር የለም” የሚባል ነገር! በችግር ውስጥ እየዋኘን ችግር የለም ማለት እንወዳለን፤ ሥራ አጥቶ በየመንገዱ የሚንከራተተው ችግር የለም! ይላል፤
«ቤቱ በመደርመሻ መኪና ውልቅልቁ ወጥቶበት ባቡር መንገድ ላይ የተኛው ችግር የለም! ይላል፤ የሚታከምበት አጥቶ የሚያጣጥረው ችግር የለም! ይላል፤ ወይ የተማሪ ቤት ዩኒፎርም መግዛት አቅቶት፣ ወይ እርሳስና ደብተር መግዛት አቅቶት ትምህርቱን ያቋረጠ ተማሪ ችግር የለም! ይላል፤
«ጥፋቱን ሳያውቅ ፍርድ ቤት ተከራክሮ ማስረጃ ቀርቦበት ሳይረታ በማእከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በዝዋይና በሌሎችም እስር ቤቶች እነሱና ቤተሰቦቻቸው የታሰሩ ሰዎች ችግር የለም! ይላሉ፤ በእስር ቤቶች እየታመሙ ህክምና ባለማግኘት ሰብአዊነት በጎደለው ስቃይ የሚጮሁ እስረኞችና ቤተሰቦቻቸው ችግር የለም! ይላሉ፡፡
«ረሀብ ችግር ካልሆነ፣ ውሀ ጥም ችግር ካልሆነ፣ መጠለያ ቢጤ ማጣት ችግር ካልሆነ፣ መታረዝ ችግር ካልሆነ፣ ፍትህ አለማግኘት ችግር ካልሆነ፣ ሥራ ማጣት ችግር ካልሆነ፣ ትምህርት ማጣት፣ ህክምና ማጣት፣ መብራት ማጣት፣ ….. ማጣት፣ ስልክ ማጣት፣ ኢንተርኔት ማጣት፣ ….. ማጣት … ማጣት … ማጣት … ማጣት ችግር ካልሆነ፣ ችግር ምንድን ነው?
«እንግዲህ በኢትዮጵያውያን ግንዛቤ ‘ችግር’ ማለት ማጣት ሳይሆን ‘ማግኘት’ ነው፤ ረሀብን ማግኘት፣ ጥምን ማግኘት፣ እርዛትን ማግኘት፣ ሜዳ ወይም ባቡር መንገድ ላይ መተኛትን ማግኘት፣ በደልን ማግኘት፣ ፍዳን ማግኘት፣ ጭቆናን ማግኘት፣ መናጢ ደሀነትን ማግኘት፣
«እንግዲህ ችግር ማለት ሁሉም ነው፤ ማጣትም፣ ማግኘትም፣ አግኝቶ ማጣትም፣ አጥቶ ማግኘትም ያው ችግር ነው! ችግር ነው ጌትነት! የሚባለው ለዚህ ነው፤ ኢትዮጵያዊ ከችግር የሚወጣበትን መንገድ ገና አላበጀም፤ እንዘጭ!-እምቦጭ!
«…’ችግር ነው ጌትነት’ ባንድ በኩል፣ ‘ችግር የለም’ በሌላ በኩል፣ በሚሉ የአነጋገር ፈሊጦች የሚጠቀም ሕዝብ ስለአገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ፍልስፍና ወይም እምነት መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፤
«ምናልባት ለአንዳንድ ሰዎች ችግር ውስጥ እየዋኙና በችጋር እየተጠበሱ የሚኖሩ ሰዎች ‘ችግር የለም’ ማለት፣ ወይም ጌትነትን እንደችግር ማየት ግራ ይሆንባቸው ይሆናል፤ አልተሳሳቱም፤ ነገሩም ግራ ነው፤ ደሀነትና ሀብታምነትን አጥፍቶ ሰዎችን ሁሉ እኩል የሚያደርግ የግራ ፖሊቲካ ነው፡፡
«’እግዚአብሔር ላይክስ አይበድልም’ ይባላል፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮችን ዓይነት በዓይነት አስታቀፈና መደኃኒቱንም አብሮ ሰጠው፤ በችግርና በችጋር ለተተበተበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባህላዊ መፍትሔ አድርጎ የቸረው የተከበረ ልመናን ነው፤ ልመናን ዋና ሥራ አድርጎ ሰጠው፤ የተከበረ ሥራ አድርጎ ተቀበለው፤
«በልመና ሥራ ለመሰማራት ጾታ፣ ዕድሜ፣ ትውልድ አያግደውም፤ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ለማግኘት የሚጠቀምበት ዘዴ ልመና ነው፤ ሴት ለአዳር መጋበዝ የሚቻለው በልመና ነው፤
«ሚስትም ደግሞ ማግባት የሚቻለው በልመና ነው፤ መሬት ማግኘት የሚቻለው በልመና ነው፤ ሥራ የሚገኘው በልመና (ደጅ-ጥናትም ይባላል) ነው፤ ሹመት የሚገኘው በልመና ነው፤ እንግዲህ ከኑሮ ውስጥ ዋና የሚባልና በልመና የማይገኝ ምን ቀረ?
«ዘመናዊ ሥልጣኔ የሚባል ነገር መጣና አባቶቻችንና እናቶቻችን በልመና ሲያገኙ የነበሩትን ሁሉ በገንዘብ መግዛትን ፈሊጥ አደረገው፤ ዱሮ በልመና የሚገኘው ሁሉ ዛሬ በሺያጭ ብቻ ሆነ፤ ልመና ግን በገበያ ላለመበለጥ እየተውተረተረ ነው፤ ዛሬም ቢሆን ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ መቅደስ ልመና መቆሚያው መሠረት ያልሆነ ሰውም ሆነ ድርጅት የለም፤
«’ልመና’ የሚለው ስያሜ ትንሽ ስለሚያሳፍራቸው የክርስትና ስም አውጥተውለት “እርዳታ” ይሉታል፤ በእኛ በተቀባዮቹ በኩል ልመና የሚለው ስያሜ አዲስ ስም ወጥቶለት ‘እርዳታ’ እንደተባለው ሁሉ በምዕራባውያን በኩልም ዓለምን የሚቆጣጠሩበት ዘዴ ”ስለላ” ነበር፤ እነሱም ያንን ስያሜ ለውጠው “ዓለም-አቀፍ እርዳታ” ብለውታል፡፡
«ድንቅ ነው፤ ልመናና ስለላ በዓለም-አቀፍ መድረክ ላይ ሲገናኙ “እርዳታ” የጋራ ስም ሆነላቸው፤ ስለዚህም ልመና ስለላ፣ ስለላ ደግሞ ልመና ሆነ!
«ጠጋ ብሎ ለተመለከታቸው በመሠረቱ የልመና መነሻው ማጣት ነው፤ የስለላም መነሻው ማጣት ነው፤ ነገር ግን የልመና ማጣት ከስለላ ማጣት የተለየ ነው፤ ስለዚህ ማጣትና ማጣት የሚፈልጉትን ለማግኘት ቢረዳዱ አያስደንቅም!
«ልመና የሚያጣውን ከስለላ ያገኛል፤ ስለላ የሚያጣውን ከልመና ያገኛል፤ የልመና ማጣትም ሆነ የስለላ ማጣት እየታደሱ የሚቀጥሉ እንጂ በተወሰነ ጊዜ የሚያበቁና የሚቆሙ አይደሉም፡፡
«የሀብታሞች ማጣትም በየጊዜው የሚታደስ፣ እየተራባም የሚቀጥል ነው፤ ምኞት ማጣትን ይወልዳል፤ ማጣት በበኩሉ ለማግኘት ይጥራል፤ በተለይ ለሀብታም ልመናን ሳይለቅ የማግኘት መንገዱ ብዙ ነው፤
«ረሀብ የሚያሰቃየው ችግሩ አንድ እንጀራ ከአንድ ጭልፋ ወጥ ጋር ማጣት ነው፤ የሚፈልገውን ሁሉ አግኝቶ፣ አንድ አውቶሞቢልም ጭምር ያለው ሰው ችግሩ አንድ አውቶሞቢል ለሚስቱ ማጣቱ ነው፤ የአንድ እንጀራ ከአንድ ጭልፋ ወጥ ጋር ችግርና የአንድ አውቶሞቢል ችግር — ሁለቱም እኩል እንደ ችግር ይቆጠራሉ ወይ? መልሱን ከባለቤቱ ሌላ የሚያውቀው አለ?
«… ችግሮቹ የተለያዩ ናቸውና ጌታ መሆን እንደሚቸግር ደሀ አያውቅም፤ ደሀ መሆን እንደሚቸግር ጌታ አያውቅም፤ ችግር ማጣት ብቻ ይመስለናል፤ በእጃችን ባለው ነገር አለመጠቀሙም ችግርን እንደሚፈጥርብን ብዙ ጊዜ አንገነዘብም፡፡ ችግር ነው ጌትነት! …እንዘጭ!-እምቦጭ፡፡»
[ጽሑፉ የተወሰደው (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
— ከመስፍን ወልደ ማርያም (ፕ/ር )፤ «እንዘጭ!- እንቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ»፣ ገጽ 181-185፣ አዲስ አበባ፣ 2010 ዓ.ም.፡፡
አምላክ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡… ችግር ብልሃትን ትወልዳለችና… ትውልዳችን የመፍትሄ-መካን እንዳይሆን በበረከቱ ይጎብኝልን፡፡ ነፍስ ይማር ለፕ/ር መስፍንም።
የብዙሀን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር ትኑር! 
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic