>

ስለ ኢምፔርያሊዝም፥ አልልም ዝም...!!! (በእውቀቱ ስዩም ፤ የውስጥ አርበኛ) 

ስለ ኢምፔርያሊዝም፥ አልልም ዝም…!!!

(በእውቀቱ ስዩም ፤ የውስጥ አርበኛ) 

 ያንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ  የሆነ Bully   የሚያደርገኝ ልጅ ነበር ፤ ስሙ ራሱ ሙሉጌታ ቡሊ  መሰለኝ ካልተሳሳትኩ  ፤ እና አንድ ቀን ሄጄ ኮሌታውን ጨምድጄ ያዝኩት፤ እሱም እጁን ወደ አንገቴ በመስደድ አጻፋውን ለመመለስ ኮሌታየን ይፈልግ ጀመር ፤ በጊዜው ኮሌታ ስላልነበረኝ የቡዳ መዳኒቴን ጨምድዶ  ለመያዝ ተገደደ ፤ በዚህ አጋጣሚ፥  እኛ ሰፈር የነበረው ቡዳ ፥  መልክ ሳይሆን   ጸባይ ያለውን  እየመረጠ  እሚበላ እንደነበር ላስታውስ እፈልጋለሁ ::
ተያያዘን፤ ተንሽ ተንገዳገድን ፤ ተንሸ ተቦጫጨርን፤  በቴስታ ልመታው ስሞክር ራሱ በጣም ራቀብኝ፤ ብቻ በድብድብና በዳንስ መካከል ያለ እንቅስቃሴ ስናካሄድ አንድ ሃያ ደቂቃ ሞላ፤ ደሞ ባጋጣሚ ሞላ የተባለ ቦርድ የወጣ  አየር ወለድ በጋሪ ወደ አብማ ማርያም አቅጣጫ ሲሄድ ያየናል፤ ከጋሪው አክሮባት ሰርቶ  ወረደና  ‘ ሰላም ፍጠሩ ብያለሁ   “ ብሎ ወደኛ ሲንደርደር ትዝ ይለኛል፤  ቀጣዩን አልተከታተልኩትም፤  ለመንግስት ተመላሽ ባላደረገው ከስክስ  ጫማው  ሲያፍሰኝ በካህሊል  ጅብራን ስእል ላይ እንዳሉ ሰዎች ደመና ላይ ተገለባብጨ ዘነብሁ፤ ብቻ ከነበርኩበት አጭር ኮማ ነቅቼ አካባቢየን ሳማትር ሙሉጌታ የተጋጋጠ ቁርጭምጭሚቱን እያሸ እንዲህ ሲል ሰማሁት፥
“  አየ !  ጋሽ ሞላ!  ቀኑን ሙሉ ብንደባደብ ብንውል  ራሱ አንተ የጎዳኸንን ያህል አንጎዳም ነበር ”
የአሜሪካ በሰው አገር ገብታ የምታደርገውን ጣልቃገብነት ባሰብኩ ቁጥር ትዝ የሚለኝ ይህ ነው ፤   አንድ ህዝብ የሆነ ሰበብ ፈጥሮ ሲፋለም ፤ በገላይነት ይገቡና በሰፈር ጠብ ደረጃ የሚተመነውን ግጭት አባብሰው ለአቅመ አርማጊዶ ያበቁታል ::
 እኛ በግጭትና በቅራኔ ከሌሎች አገሮች የተለየን አይደለንም፤ ከሌሎች አገሮች የሚለየን ለአገር በቀሉ ችግር አገር በቀል መፍትሄ አለመፈለጋችን ነው፤ በዚህ ምክንያት የኢምፔሪያሊስቶች ሰለባ እንሆናለን  ::
 የተወሳሰበ ፖለቲካ ለማይመቻችሁ ኢምፔርያሊዝም በየፈርጁ እንዴት እንደሚሰራ በምሳሌ ላሳያችሁ፤  ለምሳሌ  ሱዳኖች መአት  ነዳጅ ዘይት  አላቸው፤ ግን ማውጣት የተሳናቸው ናቸው ፤ ቻይና  ይህንን ጉደለት በማጤን መቆፈርያ መሰርሰርያና ማጥለያ ይዛ ብቅ ትላለች፤ ከዚያ እንደ በርሚል ከአንድ ባልዲ ነዳጅ ታወጣለች ፤  በርሚሉን ለራሷ ታስቀርና ወደ ሱዳን ጎንበስ  ብላ “ ባልዲው ውስጥ ያለውን ደግሞ  ከደቤ ጋራ ተካፈሉ  “ ትላታለች ፤ በነገራችን ላይ ደቤ የደቡብ ሱዳን ማቆላመጫ ነው፤  ከዚያ  ጠይሟ ሱዳን  ባልዲውን ከእግሮቿ ስር አድርጋ ወደ  ደቤ  ቁልቁል እያየች “  አንድ ጣሳ ብተውልሽ ይደብርሻል ? “ ብላ ነገር ትፈልጋለች ፤  ብጥብጥ ይነሳል፤ ብዙም ሳይቆይ  የተባበሩት መንግስታት   እንደ ሞላ ያለ የእብድ ገላጋይ አስመርቆ ይልካል ፡:
 ካፍጋኒስታን ትራጀዲ እንማር ፤ ባለፈው የኖህ መርከብን በሚመስለው  የአሜሪካ አውሮፕላን ክንፍ ላይ ተንጠላጥለው ሊበሩ ሲሞክሩ  እንደ ሾላ የረገፉ ሰዎችን ማየት ቅስም ይሰበራል ፤
 በነገራችን ላይ ከክንፉ ከወደቁት መካከል አንዱ የአፍጋን  የብሄራዊ  ቡድኑ ኩዋስ ተጫዋች ነበር ፤ ይሄንን ለጉዋደኛየ  ለበየነ ስነግረው፥
“  እኔም  በክንፍ በኩል ሲሸማ ጠርጥሬ ነበር “    ስላለኝ ተጣልተናል፤
 ድሃ በድሃ ሲጨክን  ይደብራል  : :
Filed in: Amharic