>

ነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ሊላክ ነው...!!!  ዘጋቢ፡- (አዳሙ ሽባባው )

ነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ሊላክ ነው…!!! 

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ባሕር ዳር: መስከረም 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ)አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኀይል በአማራና በአፋር ክልል የፈጸመውን ግፍ የሚያሳይ መልዕክት ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የሚላክ መሆኑን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ 
የአሸባሪውን ሴራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለማሳወቅ የተዘጋጀው መልዕክት ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የሚላክ መሆኑን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም አለኽኝ አስታውቀዋል፡፡
አሸባሪውና ወራሪው ትህነግ የሀገርና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በመጣስ በገባበት ቦታ ሁሉ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ንጹሐን ዜጎች እየጨፈጨፈ ነው ብለዋል፡፡
ጭፍጨፋውን ለማሳወቅ ደግሞ እንደ ሀገር 5 ሚሊዮን እንደ ክልል ደግሞ 500 ሺህ ወጣቶች የሚፈርሙበት ደብዳቤ ዛሬ የመፈረም ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
እንደ ኀላፊው ገለጻ ❝በአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ❞ ብሎ አውጆ የተነሳው የሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ዘረፋ፣ ግድያ፣ ማፈናቀልምና አስገድዶ መድፈር ተግባራትን ፈጽሟል ፤  ዜጎች የሚገለገሉበትን የትምህርት፣ የጤና እና የሃይማኖት ተቋማትንም ዘርፏል፤ ከፍተኛ ውድመትም አድርሷል ብለዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ ግፍ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።
ወደ ነጩ ቤተመንግሥት የሚላከው ደብዳቤም የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን የሠራውን ግፍ ማስረጃ የያዘ መሆኑን አቶ አብርሃም አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ የሠራውን ግፍ እና ወንጀል የበለጸጉ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተሳሳተ መንገድ እየተረዱት ነው ብለዋል፡፡
ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሚላከው ደብዳቤ ዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከተጎጂዎች ጎን እንዲቆሙ ጥሪ የሚቀርብበት፣ ወራሪው የፈጸማቸው ግፎች የሚጋለጡበት እንደሆነ ነው አቶ አብርሃም የገለጹት፡፡ “ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገራት በሽብርተኛው ትህነግ መወረራችንን ሊያውቁ ይገባል” ያሉት አቶ አብርሃም አሸባሪው ትህነግ በወረራቸው የክልሉ አካባቢዎች ሁሉ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ጥሷል፤ የተሳሳተ መረጃ በመያዝ የጠላት የክህደት ፖለቲካ አራማጆች እየኾኑ ነው ብለዋል፡፡
የግፉዓንን መልዕክት በያዘው ደብዳቤ ላይ ምሁራን፣ ወጣቶችን እና ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በመፈረም ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት እንዲላክ መረባረብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አብርሃም እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ራሳችንን ለመከላከል የሚደረግ ነው፤ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል፤ እናሽነፋለንም ብለዋል፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ተቀባ እንዳስታወቀው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የሚላከው ደብዳቤ የፊርማ ሥነ ሥርዓት እስከ መስከረም 10 ይካሄዳል፡፡ መስከረም 15 ደግሞ ወደ አሜሪካ ይላካል ብሏል፡፡ በሂደቱም በወረዳ ደረጃ እስከ 1 ሺህ 500፣ በዞን ደረጃ እስከ 2 ሺህ፣ በትልልቅ ከተሞች ደግሞ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ነው ያለው፡፡  በዚህም ሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ቡድን የፈጸመውን ግፍ እና ወንጀል  ያልተረዳው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ የሚደረግበት ነው ብሏል፡፡ ይህም ዜጎች በትዊተር የሚያደርጉትን ዘመቻ የሚያጠናክር እንደሆነም ኀላፊው ገልጿል፡፡
Filed in: Amharic