>
5:21 pm - Saturday July 21, 5381

በምስራቅ ወለጋ እየተባባሰ የመጣው ግድያ እና መፈናቀል  አሳስቦናል....!!! (ኢሰመኮ) 

በምስራቅ ወለጋ እየተባባሰ የመጣው ግድያ እና መፈናቀል  አሳስቦናል….!!!

ኢሰመኮ 


የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ያሳስባል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪራሙ ወረዳ የሚገኙ  ሲቪል ሰዎች ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው የሚያሳስብ መሆኑን ገለጸ። በዚሁ ወረዳ፣ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18  ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፤ እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን  ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

በኪራሙ ወረዳ ባለው አሳሳቢ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው በኖሌ ቀበሌ፣በሀሮ  እና ኪራሙ ከተሞች  ተጠልለው የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለወራት አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታና ሌሎች ድጋፎችን ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎች አክለው ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ኪራሙ ወረዳን ከቡሬና ነቀምቴ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ለተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተዘግተው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል።

ኢሰመኮ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና  በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎችን  እንዲወስዱ  ያሳስባል። በተጨማሪም በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው መመለሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተፈናቃዮቹ ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ከመጋለጣቸው በፊት በአፋጣኝ ወረዳውን ከሌሎች አከባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች እንዲከፈቱና  አስፈላጊው ሰብአዊ እርዳታ መድረሱን እንዲያረጋግጡ ኢሰመኮ በጥብቅ ያሳስባል።

Filed in: Amharic