>
5:13 pm - Saturday April 19, 5547

አበበ ገላው፤ ስለ ዜግነት ፖለቲካ ፍንጭ የሌለው የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ (መስፍን አረጋ)

አበበ ገላው፤ ስለ ዜግነት ፖለቲካ ፍንጭ የሌለው የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ

መስፍን አረጋ


አቶ አበበ ገላው፣ ከባልደረባህ ከደረጀ ሐብተወልድ ጋር ባደረከው ቃለ  ምልልስ ላይ ‹‹በአማራ ላይ የሚደርሰው ግፍ ከኤርምያስ በላይ እኔን ይመለከተኛል›› በማለት ስትናገር ተደምጠኻል፡፡ የኤርምያስ ለገሰን ሞራል ለመንካት በሚል እሳቤ  እንደ ዘበት ጣል ያደረካት ይህች አንድ ዐረፍተ ነገር፣ ያንተን ማንነት ቁልጭልጭ አድርጋ እርቃንህን አስቀርታኻለች፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይህች ንግግርህ ምን ያህል የመሠሪነት ጥግ እንደሆንክና ፣ ለዐብይ አሕመድ ካደርክ ወዲህ ምን ያህል እንደዘቀጥክ ፍንትው አድርጋ አሳይታለች፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ ብትልም፣ ስለዜግነት ፖለቲካ ፍንጭ የሌለህ ግልብ እንደሆንክ ይህችው ንግግርህ ቁልጭ አድርጋ መስክራብኻለች፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ማለት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱና በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ መመልከት ማለት ነው፡፡  ስለዚህም የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ የሚል ግለሰብ እኔ አማራ ስለሆንኩ የአማራ ጉዳይ አማራ ካልሆነ ሰው በላይ እኔን ይመለከተኛል አይልም፣ ሊልም አይችልም፡፡

የአማራ ጉዳይ ከኤርምያስ በላይ እኔን ይመለከተኛል ያልከው፣ የኤርምያስ አያት በኦሮምኛ ስለተሰየሙ ብቻ ኦሮሞ ናቸው ብለህ በመደምደም ከሆነ ደግሞ፣ የኦሮሙማን እንቶ ፈንቶ ሳታላምጥ ውጠህና ሰልቅጠህ ካስተሳሰብህ ጋር አዋህደኸዋል ማለት ነው፡፡    የኦሮሞ ስም ስለተለጠፈበት ብቻ ኦሮሞ ነው ከሚባለው ሕዝብ ውስጥ ከዘጠና በመቶ በላይ ኦሮሞ ያልሆነ፣ ከዘር ጭፍጨፋ መልስ ጉዲፈቻ ወይም ሞጋሳ የተደረገ መሆኑን አታውቅም፣ ይልቁንም ደግሞ እንዳታውቅ ተደርገሃል ማለት ነው፡፡    

ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያወርደውን የመከራ ዶፍ፣ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል ቀን በቀን የሚያጋልጠው ኤርምያስ ለገሰ ነው፡፡  አንተ አበበ ገላው ግን የአማራ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የዐብይ አሕመድ ቀንደኛ ደጋፊ ብቻ ሳትሆን በቀንደኛ ደጋፊነትህ የምትኮራ ግለሰብ ነህ፡፡  ስለዚህም የአማራ ጉዳይ ከኤርምያስ በላይ እኔን ይመለከተኛል ያልከው ስምህ አበበ ገላው ስለሆነ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡  ይህ ማለት ደግሞ ከወያኔወችና ከኦነጋውያን በላይ አማራን ፍዳውን ያሳዩት የአማራ ስም የወጣላቸው ወይም የተለጠፈባቸው አማራ መሳዮች መሆናቸውን የረሳን ይመስልሃል ማለት ነው፡፡  

አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋና ከበደ ጫኔ ስሞቻቸው ቆንጆ ያማራ ስሞች ቢሆኑም፣ እነሱ ግን ከወያኔ በላይ አማራን የሚጠሉ፣ የወያኔን ፀራማራ ፖሊስ ወያኔ ከሚጠብቅባቸው በላይ የተገበሩና ያስተገበሩ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸሟቸውና ላስፈጸሟቸው ዘር ማጥፋትን የሚጨምሩ ከባባድ ወንጀሎች ገና ያልተጠየቁ የቁጩ አማሮች ናቸው፡፡  ያንተ ጓደኞች ፋሲል የኔዓለምና መሳይ መኮንን ደግሞ ስማቸው አማራዊ ቢሆንም፣ የጭቃ ጅራፋቸውን ለማንሳት የሚሽቀዳደሙት ግን በወያኔወች ወይም በኦነጋውያን ላይ ሳይሆን፣ የአማራ ፖለቲካ ያራምዳሉ በሚሏቸው ልደቱ አያሌውንና እስክንድር ነጋን በመሳሰሉት ላይ ነው፡፡  

አንተ አበበ ገላው ደግሞ አማራ ሆንክም አልሆንክም፣ ከዐብይ አሕመድ ውጭ አማራጭ የለም የምትል፣ ዐብይ አሕመድን እንደ መሲህ የምታይ የዐብይ አሕመድ አምላኪ ነህ፡፡  ከዐብይ አሕመድ ውጭ አማራጭ የለም የምትለው ደግሞ ዐብይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሆነ ድረስ በሱ ጠቅላይነት ዘመን ባማራ ሕዝብ ላይ ለተፈጸሙት ሁሉም ወንጀሎች በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ዋናው ተጠያቂ እሱና እሱ ብቻ መሆኑን እያወክ ነው፡፡  ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ በወያኔ መረጃ ድርጅት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረውን፣ ወያኔ እስከወደቀ ድረስ የወያኔ ታማኝ አገልጋይ የነበረውን፣ አሁንም ድረስ ከወያኔ ጋር ውስጥ ለውስጥ እየተገናኘ ባማራ ሕዝብ ላይ ደባ የሚፈጽመውን፣ ዐብይ አሕመድ የሚባለውን የወያኔ ቅጥቅጥ ብቸኛ አማራጫችን እያልክ፣ ወያኔን አንቅሮ ተፍቶ ወያኔን ለመጣል ቁልፍ ሚና የተጫወተውን ኤርምያስ ለገሰን ግን ከበረከት ስምዖን ጋር በማጎዳኘት ጥላሸት ለመቀባት የምታደርገው አጉል መውተርተር ነው፡፡    

አበበ ገላው የምባል አማራ ነኝ እስካልክ ድረስ አማራነትህን መቀበል የግድ ነው፡፡  አማራ ነህ ማለት ግን የአማራ ጉዳይ ያሳስብሃል ማለት አይደለም፡፡  አማራ ሁኖ የፀራማሮች ሎሌ የሆነ ሆዳም አማራ አለ፡፡ አማራን መስሎ አማራን ለመጉዳት ሲል ብቻ፣ አማራ ሳይሆን አማራ ነኝ የሚል የቁጩ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ያማራ ጉዳይ ግድ የማይሰጠው ባይተዋር አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ አማራነቱን እንዲጠላ የተደረገ በሽተኛ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ የፀራማሮችን የጭቃ ጅራፍ ስለሚፈራ ብቻ አማራነቱን የሚያድበሰብስ ቱርቂ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ከአማራነት በላይ ነኝ በሚል ውሃ በማይቋጥር ምክኒያት የአማራን ሰቆቃ ዓይቶ እንዳላየ የሚያልፍ ተመጻዳቂ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ጎጠኞች እንዳይቀየሙና ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ አማራ ሲሞት አማራ ሞተ አትበሉ የሚል፣ የኢትዮጵያ ምሰሶ ተነቅሎ ኢትዮጵያ ትገነባለች ብሎ የሚያስብ ነፈዝ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ….    

ኤርምያስ ለገሰ ስሜን አጠፋው ስትል፣ በብዙወቻችን ዘንድ ስምህ ከጠፋ መቆየቱን አታውቅም ማለት ነው፡፡  አንተ የዘቀጥከው፣ ዐብይ አሕመድ ኢንሳ ውስጥ ሁኖ የሠራቸው ወንጀሎች ዓመታትን ስላስቆጠሩ ሊቆጠሩበት አይችሉም ብለህ ከኤርምያስና ከሐብታሙ ጋር ለመከራከር የሞከርክ ጊዜ ነው፡፡  አንተ የዘቀጥከው፣ የዐብይ አሕመድን ዶክተርነት ለማረጋገጥ፣ ለራስህ ዶክተርነት ሊያሰጥህ የሚችል ሐተታ ለማተት የተነሳህ ጊዜ ነው፡፡  አንተ የዘቀጥከው 120 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት አገር ላይ አንድን ዋልጌ ግለሰብ ብቸኛ አማራጭ ነው ለማለት የደፈርክ ጊዜ ነው፡፡  አንተ የዘቀጥከው …..  

ጉዱ ተዘርዝሮ መቸ ይዘለቃል

እንደው በደፈናው ባጭሩ በጥቅል

ጭምልቅልቅ ብሏል ማለቱ ይበቃል፡፡ 

ባንድ ወቅት አንተን አበበ ገላውን ከፕሮፌሰር አሥራት ሞት ጋር ሲያጎዳኙህ ሰምቸ፣ አንገቴ ይቆረጥ ብየ ሽንጤን ገትሬ ተከራክሬልህ ነበር፡፡  አሁን ግን አንገቴ ይቆረጥ የምትለው ቃል አትወጣኝም፣ ምን በወጣኝና፡፡

የኤርምያስን ደጋፊወች መንጋወች ብለህ ለመሳደብ ሞክረኻል፡፡  ይቺ ስድብ ደግሞ ካለቃህ ከአንዳርጋቸው ጽጌ የተማርካት ሳትሆን አትቀርም፡፡  እንዳርጋቸውና መሰሎቹ በጥያቄ ወይም በመረጃ ሲፋጠጡና ማጣፊያው ሲያጥራቸው ማምለጫቸው መንጋ የምትለው ቃል ናት፡፡  አንተስ የኤርምያስን ደጋፊወች ኤርምያስን ስለደገፉ ብቻ መንጋ ያልከው ማጣፊያው ስላጠረህ ይሆን?  አንተ የኤርምያስን ደጋፊወች መንጋ ካልክ፣ ባጸፋው ደግሞ አንተ የዐብይ አሕመድ መንጋ መባልህ አግባብ አይመስልህም?  አንድ ሰው የኤርምያስ መንጋ የሚሆነው ኤርምያስን በሐገር ጉዳይ ለማገዝ እንጅ፣ ከኤርምያስ የግል ጥቅም ለማግኘት አይደለም፣ ከኤርምያስ የሚገኝ የግል ጥቅም የለምና፡፡  አንድ ሰው የዐብይ አሕመድ መንጋ የሚሆነው ግን ….

ነገረ ሥራህ ሁሉ መለስን አንገት ያስደፋሁ ጀግና ነኝ በሚል እሳቤ በእብሪት የተወጣጠርክ ያስመስልብሃል፡፡  ይህ እብሪትህ የመነጨው ግን ፈረንጆቹ እንደሚሉት ትንሹን ጎራ ተልቅ ተራራ በማስመሰል ነው፡፡  አንተ በመለስ ዜናዊ ላይ ያደረከው፣ እነ ስብሐት ነጋ ወደ አሜሪቃ ብቅ ባሉ ቁጥር አያሌ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በየ ኤርፓርቱና በየ ሻሂ ቤቱ እግር በእግር እየተከታተሉ፣ በስልካቸው እየቀዱ ልክ ልካቸውን ከነገሯቸው ቢያንስ እንጅ አይበልጥም፡፡ ልዩነቱ አንተ ተግባሩን የፈጸምከው፣ ሙያህ የፈጠረለህን ዕድል በመጠቀም መለስ ዜናዊን ብታጋልጥ ምንም ችግር በማይፈጥርብህና በሰፊው እንዲታወቅልህ በሚያደርግህ ቦታ ላይ መሆኑ ብቻ ነው፡፡  

መለስ ዜናዊን አንገቱን ያስደፋው ደግሞ እኩይ ሥራው እንጅ ያንተ ጩኸት አልነበረም፡፡  የዐብይ አሕመድ እኩይ ሥራ ደግሞ ከመለስ ዜናዊ እኩይ ሥራ እጅጉን የከፋ ነው፡፡  ስለዚህም ብቸኛው አማራጫችን ያልከው ያንተ ጀግና ዐብይ አሕመድ የመለስ ዜናዊ ዕጣ ቢገጥመው፣ እንደ መለስ ዜናዊ አንገቱን ከመድፋት አልፎ ሱሪው ላይ እንደሚለቀው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡  

ዐብይ አሕመድ ማለት በአማራ ሕዝብ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እስኪፈጸም ድረስ ሥራየ ብሎ እየጠበቀ፣ በነገታው አዳባባይ ወጥቶ አበባ በመትከል፣ ወይም ደግሞ በፌስቡክና በትዊተር ስለ አበባ ውበት በመደስኮር የአማራን ሞት ከዝንብ ሞት እንደማይቆጥረው በግልጽ ያሳየ የኦነግ አውሬ ነው፡፡  እንደሱ ዓይነት ጨካኝ ሰው ደግሞ የጭካኔውን ያህል ፈሪ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ላንተና ለመሰሎችህ አቻ የሌለው መሪ ቢሆንም፣ ለዐማራ ሕዝብ ግን ወደር የሌለው መሠሪ ነው፡፡ 

ያንተን ዓይነት ሙያ የመረጠ ሰው ሁልጊዜም የሚመዘነው በአሁናዊ ሥራው ነው (you are as good as your last report)፡፡  አንተ ግን ትንሿን ጎራ ትልቅ ተራራ አስመስለህ በመኮፈስ፣ የመለስ ዜናዊን አንገት ያስደፋሁ ጀግና ነኝ በሚል ስሜት እየታበይክ እዚያችው ቅጽበት ላይ ቆመህ የቀረህ ትመስላለህ፡፡  አለበለዚያማ ባሁኑ ጊዜ ትልቅ ሥራ እየሠራ ያለውን ኤርምያስ ለገሰን ቢጤህን ፈልግ ለማለት አትደፍርም ነበር፣ ቢጤህን ፈልግ ለማለት የሚያስችልህ ምንም ምክኒያት የለህምና፡፡  በነገራችን ላይ ቢጤህን ፈልግም አቶ አንዳርጋቸው በሐሳብ የሚበልጡትን ሰወች አፍ ለማስዘጋት የሚጠቀምባት ፈሊጥ ናት፡፡  አንተ አበበ ገላው ደግሞ ያለቆችህን ዘይቤ ልቅም አድርገህ የምትይዝ ጎበዝ ተማሪ ነህ፡፡  ስለምታመልካቸው ይሆን?  

በመጨረሻም ምክር ቢጤ ለውድ ለወንድሜ ለኤርምያስ ለገሰ፡፡  በመጀመርያ ደረጃ አበበ ገላው አንተን እየዘለፈ ሐብታሙን ለማሞገስ የሚሞክረው፣ ሐብታሙን ወዶት ሳይሆን አንተንና ሐብታሙን በማቃቃር ኢትዮ360ን ለማፍረስ እንደሆነ አውቀህ፣ በዚህ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ፡፡  ዐብይ አሕመድ ባማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውንና የሚያስፈጽመውን ወንጀል ሳታሰልስ የምታጋልጠው ኢትዮ360 ናት፡፡  አማራ የለም የሚለው አቶ አንዳርጋቸውና መሰሎቹ ቆርጠው የተነሱት ደግሞ ይህችን ድምጽ ለማጥፋት ነው፡፡  ስለዚህም አንዳርጋቸውና መሰሎቹ ኢትዮ360ን ለማፍረስ በማናቸውም በር እንዳይገቡ ሁሉንም በሮች ጥርቅም አድርጋችሁ ዝጉባቸው፡፡  በዚህ ረገድ ደግሞ እነ ታማኝ በየንን ወደ ኢትዮ360 በመጋበዝ ባለፈው የሰራችሁትን ስሐትት አትድገሙ፣ ዐብይ አሕመድ የለከፈው ሰው አይታመንምና፡፡  ወይም ደግሞ አንተው ራስህ እንደምትለው ዐብይ አሕመድ የነካው ሁሉ የሞተ ነውና፡፡  ይዘዋችሁ እንዳይሞቱ፣ የዐብይ አሕመድን ሙትቻወች ወደ ኢትዮ360 አታስቀርቡ፡፡       

አብናቶቻችን (ማለትም አባቶቻችንና እናቶቻችን) እንደሚሉት ሲደርስ ያዳርሳል፣ ወይም ደግሞ ሊነጋ ሲል ይደቀድቃል (the darkest hour is just before dawn).  ስለዚህም ወንድም ኤርምያስ፣ በኢሳት፣ በዜና ቲዩብ፣ በዘሐበሻ … በያቅጣጫው ወጥረው የያዙህ፣ ከዐብይ አሕመድ ጋር መውደቂያቸው ስለደረሰ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፡፡  ታላቁ ማሕተማ ጋንዲ እንዳለው “በመጀመርያ ይንቁሃል፣ ቀጥለው ይሳለቁብሃል፣ ከዚያም ጦር ይሰብቁብሃል፣ በመጨረሻም ይወድቁልሃል” (First they ignore you, then they ridicule you, then they fight you, then you win )::  ስለዚህም ያሁኖቹ ጦር ሰባቂወች የነገወቹ ወዳቂወች መሆናቸውን አውቀህ በያዘከው መንገድ በቁርጠኝነት ቀጥል፡፡  ፈጣሪ ብርታቱን ይስጥህ፡፡   

ያማራ ሰቆቃ በጅቦች እንዳይታፈን የምትፈልጉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን (በተለይም አማሮች) ደግሞ፣ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዳይሆንባችሁ፣ ከነ ኤርምያስ ጋር ቁማችሁ፣ ባላችሁ አቅም ሁሉ እነ ኤርምያስን የምታግዙበት የቁርጥ ቀን አሁን መሆኑን እወቁ፡፡     

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic