ጀግና ማለት ለእኔ….?!?
አሳፍ ሀይሉ
*…. ሰው ነኝ፣ መናገር በተፈጥሮ በፈጣሪ የተቸረኝ ስጦታ ነው፣ ማሰብ ከፈጣሪ ሰው ተደርጌ ስፈጠር የተቀበልኩት የተፈጥሮ ፀጋዬ ነው፣ ብዕርና ቃላት ብቻ ናቸው የእኔ ጉልበት፣ ብለው፣ አፋቸውን መቆለፍ፣ ጭራቸውን መቁላት፣ ለባለጊዜ ማሽቃበጥና፣ ብልጠትን ከላያቸው ላይ አራግፈው፣ ሰው መሆንን የመረጡ፣ እግዜር ሰፍሮ ከሰጣቸው ሰውነት ላለማነስ የመረጡ፣ ጀግና የሃሳብ ተፋላሚ ስለሆኑ – ትልቅ ክብር አለኝ፡፡
ጀግናዬ የሆኑት የሚናገሩትን ሁሉ ስለማምንበት አይደለም፡፡ እንዲያውም ብዙ ቅር የሚሉኝና ብዙ የማልስማማባቸውን አቋሞች አይቼባቸዋለሁ፡፡ በእኔ እይታ የእሳቸው ታላቅነት ለህሊናቸው መታመናቸው ነው፡፡ ለራሳቸው ህሊና ያላቸው ታዛዥነት ነው፡፡
ልክ ከፊቷ የቆሙትን ደጋፊዎቿና ባላጋራዎቿ አይታ ከህሊናዋ ላለማፈግፈግ ዓይኖቿን በጨርቅ ግጥም አድርጋ እንዳሰረችው፣ እና ህሊናዋ የነገራትን ብቻ እንደምትፈርደው የፍትህ ሀውልት ሁሉ፣ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱም ከፊታቸው ለቆሙት ባለጠብመንጃዎችና አሸብሻቢዎች ብለው ከህሊናቸው ማማ ሳይወርዱ፣ ያመኑበትን፣ ሳይሸራርፉና ሳይቀባቡ፣ ፊት ለፊት ይናገራሉ፡፡
ሰው ነኝ፣ መናገር በተፈጥሮ በፈጣሪ የተቸረኝ ስጦታ ነው፣ ማሰብ ከፈጣሪ ሰው ተደርጌ ስፈጠር የተቀበልኩት የተፈጥሮ ፀጋዬ ነው፣ ብዕርና ቃላት ብቻ ናቸው የእኔ ጉልበት፣ ብለው፣ አፋቸውን መቆለፍ፣ ጭራቸውን መቁላት፣ ለባለጊዜ ማሽቃበጥና፣ ብልጠትን ከላያቸው ላይ አራግፈው፣ ሰው መሆንን የመረጡ፣ እግዜር ሰፍሮ ከሰጣቸው ሰውነት ላለማነስ የመረጡ፣ ጀግና የሃሳብ ተፋላሚ ስለሆኑ – ትልቅ ክብር አለኝ፡፡
አብዛኞቻችን ከሰውነት በታች የወረድን አሳሞች ሆነናል፡፡ አውቀን የኑሮና የህይወት ብልሃት አድርገነው፣ አሊያም ሳናውቅ ህሊናችንን ሳንጠይቅ በተቀደደልን ቦይ ሁሉ እንደ ውሃ እየፈሰስን፣ ፊታችን ዓይኑን አፍጥጦ ጠብመንጃ ደቅኖ ለቆመ ባለጊዜ ተንበርክከናል፡፡ እጅ ሰጥተናል፡፡ ተማርከናል፡፡ ሰብዓዊ ማመዛዘኛችንን አስረክበናል፡፡ አብዛኞቻችን ህሊናችንን ጨጓራችን ውስጥ ቅርቅር አድርገን አይናችንን አፍጠን ህሊና ያላቸውን የምንወርፍ ነን፡፡ ይህን ስናደርግም ምንም የማይሰማን በሰው አምሳል የተፈጠርን ጉዶች፡፡
እንደ ጋሼ ታዲዮስ ዓይነት ሰዎች – ሰው ሆነው ተፈጥረው፣ ሰው ሆነው ኖረው፣ ሰው ሆነው ይሞታሉ፡፡ ሲኖሩም፣ ሲሞቱም ሰው እንደሆኑ፡፡ ይህን ከሰውነት ደረጃ በታች ራሱን ዝቅ ለማድረግ የማይፈቅደውን ሰብዕናቸውን ነው እጅግ የማደንቀው፡፡ ለዚህ ነው እጅግ የማከብራቸው፡፡ ለዚህ ነው በሺህ ጠብመንጃዎች ፊት የማይልመጠመጠውን ግዙፍ ህሊናቸውን በክብር የማስበው፡፡
እንጂ የሚሉትን ሁሉ ስለምስማማበት አይደለም፡፡ በጭራሽ የሚያስደነግጡኝ ሀሳቦች ሁሉ አላቸው፡፡ ግን ለአንድም ቀን በክፉ አስቤያቸው አላውቅም፡፡ ክፉ ሰውን የሚገድል ነው፡፡ ባለጌ የሰውን ልጅ ክቡር ነፍስ የሚያጠፋ ነው፡፡ ወራዳ የተከበረውን የሰውን ልጅ በእስር የሚያንገላታ ነው፡፡ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ፣ ያመኑበትን እውነትና የማይደራደሩበትን ህሊና ይዘው፣ ሰው መሆንን መርጠው፣ ሰው ሆኖ የመገኘትን ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉትን ዕዳ እያወራረዱ ያሉ – የዘመናችን አብሪ ኮከብ ናቸው፡፡
የዘመኑ የሰብዕና ተምሳሌት ናቸው፡፡ ዛሬ ‹‹እኖር›› ብሎ አንገቱን በጉልበቶቹ መሐል ቀብሮ እንዳላየ እንዳልሰማ የሚያልፈው ኑሮውን-ኗሪ ጮሌ ትውልድ – ነገ እኚህን ዓይነት ልበሙሉ ጀግና ሽማግሌዎችን ማጣቱ በመጪው የልጆቹ መጪ ዓለም ላይ በሚያየውና በሚያጭደው ‹‹ህሊና ቢስነት›› ያወራርደዋል፡፡
እንደማንኛውም የህይወት ትግል በመጨረሻ ሰው ማሸነፉ አይቀርም፡፡ አሳሞች ሁሉ ደግሞ ወደ ግርግማቸው መጣላቸው አይቀርም፡፡ እኚህን የሰማንያ ዓመት ምሁርና፣ ጀግና ባለህሊና ብዕረኛ በግፍ እያሰቃዩ ያሉ ሰብዓዊ አሳሞች ሁሉ – ነገና ከነገ ወዲያ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አሳማ ተጥለው፣ የአጋሰስነት ሥራቸውን ሁሉ ዋጋ ሲቀበሉ የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡
ሰው መሆንን መርጠው መከራን እየተቀበሉ ላሉት፣ የዘመኔ ጀግና፣ የዘመናችን ባለህሊና፣ ለጋሼ ታዲዮስ ታንቱ፣ ባሉበት መልካም አዲስ ዓመት፣ መልካም በዓልን እመኝላቸዋለሁ፡፡
ለእውነት የቆመ የቤተሰብ አባል በማፍራታቸው፣ ለህሊናው የታመነ አባት በመያዛቸው፣ ለመከራና ለመሳቀቅ ለተዳረጉት ምስኪን ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡ አይዟችሁ፡፡ ፍርድ ተዛብቶ አይቀርም፡፡ ሰይፍ ያነሱ በሰይፍ፣ በሰው ላይ የከፉም፣ በክፉ ሰዎች ይጠፋሉ፡፡ አንድ ቀን ግፈኞች ሁሉ በግፈኞች እጅ የሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፡፡ ይኸው ነው፡፡
ረዥም ዕድሜ ለኢትዮጵያዊው የህሊና ምልክት ለጋሼ ታዲዮስ ታንቱ ይሁን!
የፍትህን ቀን ለማየት ያብቃቸው!