>

ዳውድ ኢብሳን በጨረፍታ...!!! (ጸሐፊ: ተስፋዬ ገብረአብ)

ዳውድ ኢብሳን በጨረፍታ…!!!

—-
ጸሐፊ: ተስፋዬ ገብረአብ

ዳውድ ኢብሳ ትውልዱ ሆሮ ጉዱሩ ነው። እንደ መለስ ዜናዊ የዊንጌት ተማሪ ነበር፡፡መለስን በሁለት አመት ይቀድመዋል፡፡ አራት ኪሎ ዩንቨርስቲ ገብቶ ስታትስቲክስ አጥንቷል፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ፍሬው ይባል እንደ ነበረ በወለጋ አሰተዳዳሪ በንጉሴ ፋንታ ስር የነበረው የደህንነቱ ቅርንጫፍ ለተሰፋዪ ወ/ስላሴ የጻፈው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ደርግ ዳውድን ለሁለት አመታት አሰሮ ፈቶታል፡፡ከእስር ሲለቀቅ ወደ ኦነግ የትጥቅ ትግል ገባ። ኦነግ በ1968 ሃያ ስምንት ማእከላዊ ኮሚቴ ስመረጥ ዳውድ አንዱ ሆነ ተመረጠ፡፡
በ1971 ኦነግ ትግሉን በምእራብ ኢትዮጵያ ለማሰፋፋት ይወሰናል። ዳውድ እና የኦቦ ሌንጮ ለታ ወንድም አባ ጫላ ለታ ዋናና ምክትል ሆነው የምእራቡን ትግል እንዲመሩ ይመደቡና በጥቅሉ 17 ሆነው በሱዳን በኩል አቋረጠው ወለጋ ቤጊና ጊዳሚ አካባቢ እንቅሰቃሴ ይጀምራሉ፡፡
ደርግ ይህን የኦነግ የምእራብ እንቅስቃሴ ለማፈን ትኩረት ሰጥቶ ማጥናት ይጀምራል፡፡ የጊዳሚ ወረዳ አሰተዳዳሪ ሂካ መሳዲ እና የወለጋ ክ/ሀገር አስተዳዳሪ ንጉሴ ፋንታ የትግሉን ጅማሮ ለማጨናገፍ አንድ መላ ይዘይዳሉ፡፡
በዳውድ ኢብሳ ይመሩ ከነበሩት 17 ታጋዮች የአንዱ ወንድም ዘካሪያስ ሾሮ ይባላል፡፡ ሂካ መሳዲ ዘካርያስን ጠርቶ ግዳጅ ይሰጠዋል።
“ወንድምህንና ጓደኞቹን ቤትህ ራት ጋብዛቸው፡፡ የምንሰጥህን መርዝ ምግቡ ውስጥ ትጨምርና ታበላቸዋለህ፡፡ ይህን የማትፈጽም ከሆነ ከእነ ቤተሰብህ ትገደላለህ! ከብትህ ይዘረፋል! መሬትህን ታጣለህ! ዘርህ ከምድረ ገጽ ይጠፋል”። ዘካሪያስ ግዴታ ሆኖበት እንደ ተስማማ የደህንነቱ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል፡፡
ዘካሪያስ ወንድሜን “እንዴት እገላለው” ብሎ አቅማምቶም ነበር፡፡
“ከቻልክ ወንድምህን ለይተህ እንዳይበላ አድርገው፡፡ ካልተቻለ ግን “አብሮ ይሙት! ወንድምህ አገር ሊያጠፋ የተቀጠረ ከሃዲ ነው” ፊት ለፊት ይነግሩታል፡፡
የገበሬ ልብስ የለበሱ ወታደሮች በአከባቢው አድፈጠው ዘካርያስ ሾሮ እንዳያመልጥ ይጠብቁት ነበር፡፡ ምግብ ውስጥ የሚጨመር መርዝ ከአዲሰ አበባ ተልኮ በንጉሴ ፋንታ በኩል ለሂካ መሳዲ ተሰጠ፡፡ ሂካ መሳዲ ለዘካርያስ አሰረከበው፡፡
ዘካርያስ ለወንድሙና ለጓደኞቹ የራት ግብዣ ጥሪ ከላከባቸው በሃላ በግ አርዶ ጥሩ ምግብ አዘጋጀ፡፡ በዚያን ሰሞን 17፥የኦነግ ታጋዮች ለሁለት ተከፍለው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አባ ጫላ ዘጠኝ ራሱን ሆኖ በሌላ አቅጣጫ ይንቀሳቀሰ ነበር፡፡ ዳውድ እና ቀሪዎቹ ታጋዮች የዘካርያስን የራት ግብዣ ተቀብለው ማምሻው ላይ በገበታው ዙሪያ ተገኙ፡፡
ዘካርያስ ወንድሙን ለይቶ ለማስቀረት ሳይቻለው ቀረ፡፡ “አንተ ቆይ በሃላ ትበላለህ” ቢለው ወንድሙ አሻፈረኝ ብሎ ለገበታው ቀረበ፡፡ ወንድሙና ጓደኞቹ በመርዝ የተለወሰውን ምግብ ስበሉ ዘካርያስ የጎጆውን ምሰሶ ተደግፎ በትካዜ ይመለከታቸው ነበር፡፡
ዳውድ ከምግቡ ትንሽ ቀማምሶ ሲያበቃ ደጅ ጥበቃ ላይ የነበረውን ጓደኛቸውን ለመተካት ገበታውን ትቶ ወደ ደጅ ወጣ፡፡ ሌሎቹ መርዙን መብላቱን ቀጠሉ። ብዙም አልቆዩ።  ታጋዮቹ ሰውነታቸው እንደ እሳት እያቃጠለ እየጮኽ ይወድቁ ጀመረ፡፡ ዘካርያስ የወንድሙን ሬሳ እጁ ላይ ታቀፈ፡፡ ዳውድ ብዙም የተመገበ ባይሆንም ከመመረዝ አላመለጠም፡፡
በጥበቃው ላይ እያለ ሰውነቱ ሲቃጠልበት ቅጠላ ቅጠልና አፈር እየቃመ ውሃ በብዛት ጠጣበት፡፡ ደግሞ ደጋግሞ አሰታወከ፡፡ ሆኖም ከመውደቅ አልዳነም፡፡ራሱን ስቶ እንደ ጓደኞቹ ከዘካርያስ ጓሮ ወደቀ፡፡
የገበሬ ልብስ ለብሰው በአከባቢው አድፍጠው ውጤቱን ይጠብቁ የነበሩት ወታደሮች በተያዘላቸው ቀጠሮ ዘካርያስ ቤት ሲደርሱ ሰባቱ ታጋዮች ሞተው ዳውድ ግን ነፍሱን እንደሳተ አገኙት፡፡ ዳውድን ይዘው ወደ ደምቢዶሎ ከነፉ፡፡ የኦነግን ሚስጢር ከእሱ ለማገኘት ፍላጎት ሰለ ነበራቸው ፈጣን ህክምና ሰጥተው ህይወቱን አተረፉት፡፡ ከደምቢ ዶሎ ወደ ነቀምት አዛዋውረውም ተጨማሪ ህክምና ሰጡት፡፡
ነቀምት ላይ እንዳገገመ ወደ እስር ቤት ወስደው ገልብጠው ይገርፉት ጀመር፡፡
የወለጋው የደህንነት ሪፖርት እንደሚገልጸው ከፍሬው አንደበት አንዳችም ሚሰጢር ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ሲያቅታቸው ወደ አዲሰ አበባ ወደ ማእከላዊ ላኩት፡፡ በቤንዚንና በቆሻሻ ውሃ የተሞላ በርሜል ውሰጥ እየደፈቁ መረመሩት፡፡ ዳውድ ለመሞት ዝግጁ ሰለ ነበር አንዳችም የተነፈሰው ነገር የለም፡፡ ደግመው ደጋግመው ማእከላዊና አለም በቃኝ እያመላለሱ በተለያዪ ማሰቃያ ሰልቶች እንደ መረመሩት የደህንነቱ መ/ቤት ሰነድ በዝርዝር ያብራራል፡፡
ዳውድ በአለም በቃኝ አምስት አመታት ታሰረ፡፡ ከመላመድ ብዛት ጠባቂ የነበረውን ፖሊስ ማግባባት ቻለ። ለህክምና ሲወጡም ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር ከሆስፒታል አምልጦ ወለጋ ገባ፡፡ የቤንሻጉል ጫካዎች አቋረጠው ኦነግ ከአለበት ቦታ ለመድረስ የሁለት ሳምንት የሌሊት ጉዞ አድርገዋል፡፡ እሱ መርዝ በልቶ ሲማረክ ምእራብ ወለጋ ጫካ ውሰጥ የቀሩት አባጫላ ለታ እና ዘጠኝ ጓደኞቹ ከአንድ ብርጌድ በላይ ሰራዊት ሆነው ጠበቁት፡፡ የመሪያቸውን በህይወት መመለስ ማመን ያልቻሉት ታጋዮች በታላቅ ደሰታ ተቀበሉት!!
—–
ተስፋዬ ገብረአብ
የጋዜጠኛው ማስታወሻ
ገጽ 330-332
Filed in: Amharic