>
5:21 pm - Thursday July 21, 6185

ችግራችን መዋቅራዊ ነው ስንል በምክንያት ነው...!!! (ጎዳና ያእቆብ)

ችግራችን መዋቅራዊ ነው ስንል በምክንያት ነው…!!!

ጎዳና ያእቆብ

*…. ባለቤትና መጤ/ሰፋሪ የሚል ስርአት ውስጥ እኩልነት የማይታሰብ ነው:: አድሎአዊነት የግድ ያሚል ነው የጎሳ ፓለቲካ:: ፍትህ እና ርትህ ደግሞ በእኩልነት መሰረት ላይ የሚቆሙ ናቸው:: ችግራችን መዋቅራዊ ነው ስንል በምክንያት ነው:: በነዚህ መዋቅራዊ ነገሮች ላይ ቢረፍድም ዛሬ መስራት ካልጀመርን እጣ ፋንታችን ግልፅ ነው:: መፍረስ ነው:: 
ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያዊያንን በትላንት ታሪክዊ ኩራትና በነገ መሰረት አልባ ተስፋ ላይ ተንጠለጠለን እንድንኖር አስበውና አቅደው እያደረግው ነውና አላማውም ዛሬ እየሆነ ያሉትን አስከፊ ነገሮች እንዳናይ አይምሮአችንን ቢዚ ለማድረግ ነው።
ከፊት ለፊታችን ያለችው ኢትዮጵያ የምታጓጓ ናት ይሉናል ዛሬ ያልተዘራ ነገ ይበቅል ይመስል።
ጄኖሳይድ፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ በማፈናቀል እና በጭፍጨፌ የዘር ማግስት ወንጀል እየፈፀሙ አለም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል በመሆን (ለመሆን) የገብቻቸውን ቃል ኪዳን ታግብር ሲባል የ3000 አመት ታሪክ ያላት ሀገር ተደፈረች ልዓሏዊነቷ ተነካ ከማለት አልፈው እኛ ሦስት ሺ አመታችን ስለሆነ እኛን ስሙን ብለው እንድ ሰማንታ ፓወርን ሊያስተምሩ ሲነሰ ስታይ ለውጥን መቀበል ምን ያህል እንደከበደንና አለም ላለፉት  70 አመታት የተመራችበት ስርአት ለመረዳት ፍቃደኝነትም ይሁን አቅም እንደ ጠፋ ያሳያል።
ልዓላዊ ነኝና ሕዝቤን እንደፈለግኩ ልጨፍጭፍ፣ ላስጨፍጭፍ፣ ላስርብ፣ ላፈናቅል፣ያሻኝን ልሰር፣ ያሻኝን ደግሞ ልፍታ የሚል ኃላ ቅርብ ዘመኑን የማይዋጅ አስተሳሰብ ሰለባ የሆነ አገዛዝ እጅ እንደወደቅን መረዳት አቅቶን ግል ስልጣኔ አደጋ ውስጥ ግብቷልና ተዋጉልኝ። ግደሉልልኝ። ሙቱልኝም። ማለት ስላልቻሉ የሀገር ህልውና አደጋ ውስጥ ግቡቷልና ዝመቱልኝ  ሲሉን ሆ! ብለን የምን ወጣ አሳዛኝ ፍጥረቶች መሆናችንን ሳይና የሀገር ፍቅራችችን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅመው ለነሱ ስልጣን ማስቀጠያ በልቶ ያልጠገበውን ወጣት ሲያስጨርሱ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ሆኖብኛል።
እንዘምታለ ካሉትና የወታደር ልብስ ለብሰው ትእይንት ህዝብ ከሚያሳዩት የአገዛዙ ባበሟሎችን ተጠቃሚዎች ላለፋት 11 ወራት በተደረገው ጦርነት ስንቶቹ ሞቱ? ስንቶቹስ ልጆቻቸውን አዘመቱ? ስንቶቹስ ልጆቻቸውን ቀበሩ?
 መሳሪያ ይዘው ፎቶ ከመነሳትን በማህበራዊ ሚዲያ ከመለጠፍ ያለፈ ስንቶቹ ጠላት ካሉት አካል ጋር ተታኮሰበት? እነሱ እየሰቡ የደሀው ልጅ ግን በጦርነት በረሀብ በበሽታ እያለቀ ይገኝል።
ከመፈክር ያለፈ ለኢትዮጵያ ህልውና እንዘምታለን የሚሉት ሁሉ ዛሬም በስልጣን፣ በህይወትና በምሽት አሉ። እኛ እስከፈቀድንላቸው ድረስ ወደፊትም ይኖራሉ። ከዚህ ሁሉ እልቂት ብኋላ አንድ ቀን ሀገራችን ፈርሳ በፍርስራሿ ላይ ሀገር ወዳዱና መሄጃ የሌለው ቆሞ ሀገራችን እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰች? ብለን በመደነቅ ስንጠይቅ እነእሱ ወይ እንደ ኤርትራ የራሳቸውን ስንል ሪፐብሊክ መስርተው ይስቁብናል ወይም ደግሞ ለህዝብ ሀብት ዘርፈው እነሱን ልጆቻቸው በምቾት በሌላ ሀገር ይኖራሉ።
አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪ ቅር አለሁ ብሎ ቃል የገባልን መንግስቱ ኃ/ማሪያም ያደረገው ያንን ነው። እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለን አብይ አህመድም የሚያደርገው ያንኑ ነው። ለኢትዮጵያ ሲሉ ስልጣን መልቀቅም ይሁን መከፋፈል ያልቻሉ ግለሰቦችም ይሁኑ ድርጅቶች ዉድ ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ ይሰጣሉ ማለት ዘበት ነው።
ቅጥ ካጣ ጥላቻ እና ከአጉል ፍቅር ወጥተን ስለ ሀገር እና ስለ ሀገር ብቻ ማሰብ ብንችል አሁን እየተጓዝን ባለንበት መንገድ ሀገር ትፈርሳለች እንጂ አትገነባም።
ጦርነት ድህነትን እንጂ ብልፅግናን አያመጣልንም።
ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም የሚል የተለመደ አባባል አለ። እኔ ደግሞ እላለሁ ሮም በአንድ ቀንም አልፈረሰችም።
እኛም የመፍረስ አደጋ ላይ ነን ያለነው። የበሽታው ምልክቶች ሁሉ አሉብን። በስክነት በሽታችንን ካላከምነው መፍረሳችን አይቀሬ ነው።
ቤት በጥበብ ይገነባል። በማስተዋልም ይፀና የሚለው ቅዱሱ መፅሀፍ ማስተዋል የማይችል ትውልድ ይገለበጣም ይላልና እናስተውል።
ኢትዮጵያ አምላክ አላት። ቃል ኪዳን አላትና አትፈርስም ለሚሉን ከእስራኤል በላይ ቆራሽ ማእድ አበላሽ ነው እላለሁ። እግዚአብሔር እንደ ንስር በክንፉ ጥላ ጠብቆ ቀን በዳመና አምድ፣ ለሊት በእሳት አምድ መርቶ ያወረሳቸው ምድር ለ1900 ፈርሳለች። ሕዝቧም  በመላው አለም ተቅበዝባዥ ሆኖ ኖሯል።
እግዚአብሔር በመካከላችሁ አድር ዘንድ ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ብሎ ለክብሩ ማደሪያ ጠቢቡ ሰለሞን የሰራለት መቅደስ ፈርሷል። ዳግም እስከዛሬ አልተገነባም።
ዛሬ ያለችው ጠንካራ እስራኤል <<እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኝም። አያንቀላፋም።>> የሚለውን ቃል ለስለላና ደህንነት ድርጅታቸው ለሞሳድ፤ በቀል የኔ ነው የሚለውን ቃል ደግሞ ለእስራኤል መከላከያ ሀይል በመስጠት እንጂ በፀሎት ብዛትና በትንቢት ጋጋታ አይደለም።
ከተለያየ አለም ተሰብስቦ የመጣው ሁሉ አንድ አላም እንግቦና እንድ ህዝብ ሆኖ በመቆም ነው የሀገር ባለቤት የሆነው። እኛ ግን እርስ በርሳችን ተከፋፍለን እና ተከፋፍተን በውስጣችን የሌለውን አንድነት በሀገርችን እናመጣለን ማለት እራስን ማሟኘት ነው።
በጥላቻ ሰክረን በግፍ በለው ደምስሰው ገርስሰው ላይ የተመሰረተ አንድነት ዘላቂነት የሌለውን የጠሉትን አስወግደው ሲጨርሱ (መጨረስ ከተቻለ ማለት ነው) እፍ ሙዙን ወደሌላው ማዞራቸው የማይቀር ነው።
በግልፅ ቋንቋ ከህዋሃት ጋር ሱጨርሱ አገዛዙ ወደ አማራ፣ አማራውም ወደ አገዛዙ ማዞሩና በማያባራ ጦርነት ውስጥ መኖራችን አይቀሬ ነው። ችግራችን አለም በአፈሙዝ መነጋገሩት ትቶ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን መፍታ ከጀመሩ ሰንበትበት ቢሉም እኛ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረጉ ችግርን ዛሬ የምንነጋገረው በጠብ-መንጃ ነው።
ህዋሃትም አሸንፌ ተራራውን ያቀጠቀጠ ትውልድ የሚል ሦስተኛውን ክፍል እፅፋለሁ ብሎ በ2014 የ1983 አስተሳሰብ እና ህልም ይዞ ዘምቷል።
ማእከላዊ መንግስቱም እንደ ደርግ ዘመነ መንግስት በባለ ዜማዎቹ <<አሳደህ በለው ይህንን አመፀኛ ተገንጣይ ወንበዴ። መድረሻ አሳጣው አስኪደው በዳዴ>> ሲያዘፍን ሳይ ለሰላሳ አመታት በኮማ ውስጥ ያለች ሀገርን ህዝብ ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
ወደ 2014 አስተሳሰብ እንደምንም ከመጣን ግን በዚህ ጦርነት የሚያተርፍ የሚከብር እናም የሚረጋገጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የለም:: በዚህ ጦርነት የሚረጋገጥ ነገር ካለ የኢትዮጵያ መፍረስ እንጂ አንድነት አይደለም:: እንወዳታለን  የምንላትን ሀገር በተባበረ ሀይል እያፈረስን ነውና ፈጣሪ ማስተዋልጅን ይስጠን:: ያስክነን::
በጦርነት ውድመት እንጂ ብልፅግና አይመጣም::
ሰላም ከአድሎ በፀዳ ፍትህ እንጂ በፀሎት አይመጣም::
ከአድሎ የፀዳ መንግስት ደግሞ እኛና እነሱ ብሎ ጎራ ለይቶና መዋቅራዊ በሆነ የጎሳ ፓለቲካ እንኳን የሚቻል የሚታሰብም አይደለም::
ባለቤትና መጤ/ሰፋሪ የሚል ስርአት ውስጥ እኩልነት የማይታሰብ ነው:: አድሎአዊነት የግድ ያሚል ነው የጎሳ ፓለቲካ:: ፍትህ እና ርትህ ደግሞ በእኩልነት መሰረት ላይ የሚቆሙ ናቸው:: ችግራችን መዋቅራዊ ነው ስንል በምክንያት ነው:: በነዚህ መዋቅራዊ ነገሮች ላይ ቢረፍድም ዛሬ መስራት ካልጀመርን እጣ ፋንታችን ግልፅ ነው:: መፍረስ ነው::
ስለዚህ በትላንትና በነገ መካከል መናጣችንን ትተን ዛሬአችንን በጥሞናና በስክነት እንስራ:: ያን ብናደርግ ለራሳችንም ለሀገራችንም ውለታ እንሰራለን:: ለልጆቻችን የምናወርሰው ሀገር ይኖረናል:: ከበረታንም የተሻለ ነገን ልናወርሳቸው እንችላለን:: አሁን በምንጓዝበት መንገድ በጥላቻና ቂም በቀል ሰክረው ባወረስናቸው ፍርስራሽ ላይ ቆመው ደም ከመፋሰስ ውጪ ተስፋ አይኖራቸውም::
ጦርነት ይቁም ስንል ሁለትኛ ተፈጥሮአች ሆኖ በቀላሉ ከምከውነው በጠብ-መንጃ የመነጋገ ልምዳችን ወጥተን ሞክረነው የማናውቀውንና ሀሳቡ እንኳን እጅግ ከሚያስፈራን አዲስ ልምምድ ጋር ምንም ያህል ለውጥ ቢያስፈራንም እንለማመድ:: ለሰላም እድል እንስጥ ማለታችን ነው::
ብዙዎች ሰላም ሰላም አትበሉ የሚሉን እንዳረጀ ውሻ አዲስ የአደን ስልትን መማር ስለማይችሉ ነው:: ሰላም ከባድ ስለሆነ ነው:: ድርድር አዲስ ልምምድ ስለሆነ ነው:: ጀግንነትን የሚያውቁት በአፈሙዝ ብቻ ስለሆነ ነው::  ለውጥን ስለሚፈሩ ነው:: ከዘመኑ ጋር መለወጥ ስላዳገታቸው ነው:: ከትላንት ወዲያ ላይ ተቸንክረው ስለቀሩ ነው:: ለውጥ ለፈሪ አይመችምና ነው!!!
መልካም የመስቀል በአል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እመኛለሁ!
Filed in: Amharic