ኢትዮጵያውያን በራሳቸው መተማመን ያዋጣቸው ይሆን?
ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
‹‹ የሰላም አስከባሪዎች የሞራል እና የህሊና የበላይነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ››
በርካታ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኞች እና ጋዜጠኞች እንደሄሱት ከሆነ የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ጆይ ባይደን የኢትዮጵያን ፌዴራል መንግስት፣የኤርትራን መንግስት፣የአማራ ክልል መስተዳድርን በተናጥል ለመቅጣት እንደወሰኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አቢይ ነጥብ ቢኖር የተባበረችው አሜሪካ ሰልፍ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ በተቃራኒው ሰልፍ ላይ እንደምትገኝ ነው፡፡
በእኔ በኩል በሞራል እና ስነምግባር መልካም አቋማቸው በብዙ የአለም ምሁራን የተመሰከረላቸው ጆይ ባይደን በመሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ እርሳቸው አጠቃላይ እውነታውን የሚረዱ ከሆነ ወይም የሚያውቁ ከሆነ ሰላም ለማስከበር ሲባል የሞራል ኮምፓስ አቅጣጫቸውን የሚያስተካክሉ ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አሸባሪ ድርጅትን በመርዳት የአካባቢውን አጠቃላይ ሰላም አዘቅት ውስጥ ከመዶል ይልቅ ኢትዮጵያን ለመርዳት መንፈሳዊ ወኔ ይታጠቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አስተያየት ነው፡፡ የአንዲት ሉአላዊት ሃያል ሀገር መሪ አስተያየቱን አግኝተው ያነቡታል የምል ተላላ ሰውም አይደለሁም፡፡ የወያኔ አሸባሪ እና ለከት በሌለው ዝርፊያው ኢትዮጵያን ስላደሀየው ወያኔ በተመለከተ እውነተኛ መረጃ እንደ ፕሬዜዴንት ባይደን ለመሰሉት ታላላቅ ሰዎች ለማድረስ መንገዱ ረዥም ነው፡፡ ወያኔ ለኢትዮጵያም ሆነ ለተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ለምን እንደማይበጅ ለማስረዳትም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አተኩረው በአማርኛ የሚጻፉ አስተያየቶችን ተመልክቶ የሚተረጉም የአሜሪካ የፕሬስ አታሼ መልእክቴ ጠቃሚ ነው ብሎ ካሰበ ኢትዮጵያን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ያቀብላል ብዬ አስባለሁ፡፡
በዚሁ መንፈስ መሰረት የተባበረችው አሜሪካ ህዝብም ሆነ ፕሬዜዴንት ጆይ ባይደን በኢትዮጵያ እና በተባበረችው አሜሪካ መሃከል ያለውን ወይም የነበረውን የረጅም ዘመን ግንኙነት በተመለከተ ችላ እንዳይሉ እማጸናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለተባበረችው አሜሪካም ሆነ ለመላው አፍሪካ ያላት ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ሰፊና ወደ ኋላ የማይባል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ናት የምትባለው በሚከተሉት ምክንያት ነው፡፡
- አንዱና ዋነኛው ምክንያት የኢትዮጵያ የጂኦግራፊ አቀማመጥ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ የጂኦግራፊ አቀማመጥ በቀይ ባህር ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችል ነው፡፡ ( በነገራችን ላይ በቀይ ባህር ላይ የአሜሪካን የሚሊተሪ አታሺዎች ‹‹ The Interstate-95 of the Planet ›› እና ‹‹the Bab al-Mandab በማለት የሚጠሩት ኮሪደር በአለም ላይ የሚገኙ ሃያል ሀገራት የባህር ሀይሎች በከፍተኛ ደረጃ የሚፎካከሩበት የውሃ አካል እንደሆነ ማስታወሱ አይከፋም፡፡) ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽና ሱዳን የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር የሚጎነጉኑት የእጅ አዙር ጦርነትም ቢሆን ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ የአባይ ምንጭ ባለቤት ሀገር በመሆኗ ያላት ስትራቴጂክ ጠቀሜታ መተኪያ የለውም፡፡
በአጭሩ በትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ጸብጫሪነት የተጀመረውና ከፍተኛ የህይወት ዋጋ የጠየቀው የርስበርስ ጦርነት ኢትዮጵያን በአዲሱ የቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ሁነኛ ተዋናይ እንድትሆን እያስገደዳት ይገኛል፡፡ ይህም መዘዙ የከፈና የተራዘመ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በእኔ የግል አስተያየት መሰረት የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሸባሪውን ወያኔ አላማ በደገፈ መልኩ መሆን የለበትም ባይ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ የወያኔ ዘራፊና ነውረኛ ቡድን፣ ከአሁን በኋላ በምንም አይነት መልኩ፣ሰማይ ዝቅ፣ መሬት ከፍ ብትል ኢትዮጵያን ለመምራት የሞራልም ሆነ የህና ብቃት የለውም፡፡ የወያኔ ቡድን የጦር ወንጀል የፈጸመም ቡድን ነው፡፡ The TPLF is done. It can never ever rule Ethiopia. It committed treason after all.
የተባበረችው አሜሪካ የጦር ሀይል ከ20 አመታት የአፍጋኒስታን ቆይታ በኋላ ለቆ እንደወጣ በአለም ላይ ዝነኛ በሆነው የታይምስ መጽሔት ላይ የናቶ ጦር ቃልኪዳን የጦር መሪ የሆኑት ጄኔራል ስታርቪዲስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት ከሆነ ‹‹ በአፍጋኒስታን ቆይታ ታላቅ ትምህርት ተገኝቷል›› የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም የአንድን ሀገር ታሪክ፣ባህል እና ቋንቋ በቅጡ መረዳት አስፈላጊና ተገቢም ነው፡፡ በአንድ ሀገር ላይ ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ከመግባት በፊት የዛችን ሀገር ታሪክ፣ባህልና ቋንቋን ማወቁ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ጄኔራሉ አክለው ሲገልጹ በአፍጋኒስታን ይህን እውነት ገቢራዊ ከማድረግ አኳያ ክሽፈት አጋጥሞናል፡፡በአፍጋኒስታን ምድር እንደ ወረርሽኝ የተዛመተውን የሙስና ቅሌት መረዳት ባለመቻላችን ወይም አውቀን ዝምታ በመምረጣችን የአፍጋኒስታን ተልእኳችን አልተሳካም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ቡድን በሰላማዊ መንገድ ከስልጣኑ አሽቀንጥሮ የጣለው ወያኔ በትግራይ ምድር ስለበቀለ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ወያኔ የጦር ወንጀለኛ እና ዘራፊ፣ጨካኝ፣በንግግር የማያምን፣ዲሞክራት ያልሆነ ወዘተ ወዘተ ቡድን ስለሆነ ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንጡራ ሀብት ያራቆተ ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባህር በር ያሳጣን እኩይ ቡድንም ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ህዝብንም ይሁንታ ያጣ የወሮበሎች ስብስብም ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያን ያዋረደ፣ስሟን መጠየፈ መለያ ባህሪው ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ለግብጽና ሱዳን የእጅ አዙር ጦርነትም አገልጋይ ነው፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ የረጅም ግዜ ስትራቴጂክ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከፈለገች ወያኔን መርዳት እንደሌለባት ማሳያ ነው፡፡
ድንገት ለሚከሰቱ ችግሮች በቅድሚያ መረዳት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም
ያልታሰቡ ችግሮች ሊከሰቱ መቻላቸው አይቀሬ ሀቅ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በከፍተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት መሞከር ወይም ጣልቃ መግባት የሚያመላክተን ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ፣እንዲሁም የህዝቡን ስነ ልቦና በተመለከተ ያላቸው እውቀት አናሳ መሆኑን ነው፡፡ ወይም በተጠቀሱት አውዶች ላይ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ወይም ሆን ብለው ችላ ብለውታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አለም አቀፉን የብይነ መንግስታት ቻርተር የጣሰም ነው፡፡ ቸጋር እና በውጭ ሀይሎች ጥገኛ መሆን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሊያደበዝዘው አይገባም፡፡ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነተና ጫናም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን አያጠፋውም፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ሌላ ከባድ ስህተት ላለመፈጸም ስትል በእጅጉ መጠንቀቅ ይገባታል ባይ ነኝ፡፡ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መስከረም 17 ቀን 2021 የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ባይደን በኢትዮጵያ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ማእቀብ ሀገራቸው እንድትጥል መወሰናቸው ይታወሳል፡፡ ማእቀቡ በማን ነው ታርጌት የተደረገው ? የመልስ ምቱን አጥንተውት ይሆን ? በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ስለተከፈተው ጦርነት በተመለከተ የምእራባውያን የዜና አውታሮች ወገንተኝነት አባዜ ሲታሰብ ያሳምማል፡፡
ለተደጋጋሚ ግዜ በግሌ፣በሰከነ መንፈስ ለመከታተል እንደሞከርኩት ወይም እንደመረመርኩት ከሆነ የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደደር ቁልፍ ወዳጆች ወይም አባላት የሆኑት የአውሮፓ ህብረት፣ የብይነ መንግስታቱ ልዩ ወኪል የሆኑት ለአብነት ያህል ዩኒሴፍ፣ የሲቪልና ማህበራዊ መብቶችን ለማስከበር የተቋቋሙ አንዳንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች፣ አለም አቀፍ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ አንዳንድ የምእራቡ አለም ተጠባቢዎች ( አሰላሳዮች) (influential think-tanks ) ፣ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች፣ ( ለአብነት ያህል ቢቢሲ፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ሲኤን ኤን ወዘተ ወዘተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለበርካታ ጊዜያት በተጻራሪ ሁኔታ ሲቆሙ ተስተውሏል፡፡ ለምን መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼለሁ፡፡ በእኔ በኩል የምእራባውያን የዜና አውታሮች ሁሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያወጡት ዘገባ ከገለልተኝነት እሳቤ ያፈነገጠ ሚዛናዊ ያልሆነ ነው በሚል በደምሳሳው የምወቅስ ተላላ ሰው አይደለሁም፡፡ የምእራባውያን የዜና አውታሮች በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የነበሩ፣ አሁንም ያሉ አምባገነን አገዛዞቸን በማጋለጥ የሚታወቁ ስለመሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አገዛዞች የሚደብቁትን ድርቅና ጠኔ መቅሰፍትን ሳይደብቁ በማውጣትም የሚታወቁ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የ1966ቱን ድርቅና ችጋር ያስከተለውን የሰው እልቂት ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በመለጠቅ ያጋለጠው የቢቢሲ ዜና አውታር ጋዜጠኛው ጆናታን ዲምብልቢ ነበር፡፡ በ1977 ዓ.ም. ሆነ በወያኔ አገዛዝ ግዜ የተከሰቱትን ድርቅና ጠኔ ለአለም ያሳወቁት የምእራባውያን የዜና አውታሮች ስለመሆናቸው መዘንጋት የለብንም፡፡ የአለም ሀብታም ሀገራት ለተራበው ምግብ፣ብርድ ልብስና መድሃኒት ወዘተ የሚያቀርቡት መረጃ ሲኖራቸው ነው፡፡ የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች አማራጭ የዜና ምንጮችም ናቸው፡፡ አለምን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ የምእራቡን አለም ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ይረዱናል ለሚሏቸው መንግስታት ወይም አማጺ ቡድኖች በማዳላት የሚያቀርቡት ዘገባ ደግሞ አሳዛኙ ገጽታቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህል ለአሸባሪው የወያኔ ቡድን የሚያሳዩት ወገንተኝነት ከቆሙለት የጋዜጠኝነት ስነምግባር ያፈነገጠ ይመስለኛል፡፡ ወያኔ የፈጸመውን ግፍ ሙሉ በሙሉ ለማጋለጥ መንፈሳዊ ወኔ ከድቷቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1945 ላይ የአለሙ መንግስታት የመንግስታትን ባህሪና ድርጊት ለመቆጣጠር፣ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን፣ ሀገራት ያላቸውን ወታደራዊና የምጣኔ ሀብት ጥንካሬ ከግምት ሳይከት፣ ለሁሉም ሀገራት መልካም እድገት ሲባል ያጸደቁት ስምምነት የከሸፈ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል በኤሽያ አህጉር የምትገኘው አፍጋኒስታን ዋነኛ ምሳሌ ናት፡፡ እውን ለዚህ ለአፍጋኒስታን ምስቅልቅል፣ ለአፍጋኒስታን አሳዛኝ ውድቀት የተባበረችው አሜሪካ ተጠያቂ አይደለችምን?
ዛሬ በጥቁር አፍሪካዊቷ ምድር ኢትዮጵያ ስለሚፈጸሙ ግፎች፣የጦር ወንጀሎች፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች ዘገባ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አጥቂው፣ ግፍ የሚፈጽመው የወያኔ አሸባሪ ቡድን ከለላ እየተሰጠው ፣ተጠቂው ፣ግፍ የሚፈጸምበት የኢትዮጵያ ህዝብ ችላ ተብሏል፡፡ የጦር ወንጀለኛው የወያኔ ዘራፊ ቡድን የጦር ወንጀለኛ ተብሎ እንዲጠራ ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም ሰሜን ኢትዮጵያ ( የትግራይ ክልል እና ሰሜን ወሎ ማለቴ ነው) ድርቅና ረሃብ መከሰት ተጠያቂው ማን ነው ? እውን ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነውን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ በእኔ በኩል በዋነኝነት በተለይም ሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ዜጎች መፈናቀልና ለችጋር መጋለጥ ተጠያቂው የወያኔ አሸባሪና ወራሪ ቡድን ነው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሰሜን ትግራይ ድንበር ጠባቂ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት የጦር ወንጀል ፈጻሚውና የጦርነት ጀማሪው የወያኔ ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአንድ ወገን የተኩስ አቁም በማድረግ የትግራይ ምድርን የለቀቀው የማእከላዊ መንግስት መከላከያ ሰራዊት በፍጥነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች የሚወስዱ መንገዶችንና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎችን እንዲጠብቅ ትእዛዝ በፍጥነት ባለመሰጠቱ ሊሆን ይችላል ወይም ጸሃፊው በማያውቀው ሌላ ምክንያት የተነሳ የወያኔ ወራሪ ሰራዊት በአማራ ክልል በተለይም ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ጎንደር፣ ዘልቆ በመግባት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል፡፡ የሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስት የወያኔ ጦር በተለይም በሲቪል ዜጎች ላይ ሰቆቃና ግድያ ከመፈጸሙ በፊት መከላከል ባለመቻሉ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች ግን በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ለተከሰተው ድርቅና ችጋር፣ሰቆቃ፣ስቃይና መከራ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል፣የሲቪል ዜጎች ግድያ ወዘተ ወዘተ በዋነኝነት ተጠያቂ የሚያደርጉት የማእከላዊ መንግስቱን ነው፡፡ ይህ ፍጹም አድሏዊና ከጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የመንግስት ባክ ቤቶችን ጨምሮ ሁሉንም የመንግስት ተቋማት የዘረፈው፣ እንሰሳትን ሳይቀር የገደለው የወያኔ አሸባሪ ቡድንን ተጠያቂ ላለማድረግ የሚሄዱት እርቀት ሲታሰብ ግርምትን ያጭራል፡፡ይህም ብቻ አይደለም ህሊናን ያደማል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች በወያኔ ቡድን ጸብ ጫሪነት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 4 2020 ከተጀመረ በኋላ የጦርነቱ ዋነኛ ተዋናይ የወያኔ አሸባሪ ቡድንና ደጋፊዎቹን ጥቃት እንደደረሰባቸው መቁጠር፣ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ያሉትን የኢትዮጵያ መንግስትንና የኤርትራ መንግስትን፣ እንዲሁም የአማራ ሃይሎችን እንደ ጥቃት አድራሽ የመቁጠራቸው ዋነኛ ምክንያት የወያኔ ቡድን በአለም አቀፍ ህግ እንዳይከሰስ ከለላ ለመስጠት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሌላው አሳዛኝ ገጽታ ደግሞ በሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በተመለከተ የምእራቡ አለም ችላ ባይነት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በምእራብ ኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በወለጋና ቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ከእብድ ውሻ በከፉ አረመኔዎች አመሃኝነት በኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍና ግድያ በተመለከተ አንድም የምእራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ሲዘግበው አለመሰማቱ ወይም አለመታየቱ ሲታይ ያማል፡፡ በሰለጠነው አለም፣ መገናኛ ብዙሃን እንደ አሽን በፈሉበት ዘመን፣እጅግ የረቀቁ የዜና መሳሪያዎች በተፈበረኩበት በዚህ ዘመን ምድራዊ ሲኦል እየሆነ ባለው የወለጋ ክፍል የንጹሃን ዜጎች መከራና ስቃይ ለአለም መደበቁ ሲታይ በእውነቱ በአለም ላይ የሰውነት ደረጃ ዝቅ እያለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በሊቢያ ምድር በስደተኞች ላይ ስለሚደርሰው ግፍ፣ በአፍጋኒስታን አጥፍቶ ጠፊዎች የሚያፈሱትን የሰው ደም በተመለከተ በየደቂቃው የሚዘግቡልን የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች በወለጋ ጫካ የሚንቀሳቀሱ ብረት አንጋቾች ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚያወርዱትን የግፍ መዓት በተመለከተ ወሬውን ለአለም ለመናኘት አለመፈለጋቸው ሲታሰብ ያማል፡፡
አንባቢው ለራሱ አንድ ጥያቄ ሊያቀርብ ይቻለዋል፡፡ ይሄውም የሚከተለው ነው፡፡ ለምንድን ነው ምእራባውያን የዜና አውታሮች የወያኔ አሸባሪ ቡድን የፈጸማቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ለከት የሌለውን ዝርፊያውን፣የንጹሃን ሲቪሎችን ግድያ በተመለከተ የማያጋልጡት ለምንድን ነው ? በኢትዮጵያ ምእራባዊ ክፍል በተለይም በወለጋ ኦነግ ሸኔ በሚባል ቡድንና ቤንሻንጉል ክልል ደግሞ ብረት ያነገቱ ሀይሎች በሲቪል ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙትን ግድያ ለምን ለአለሙ ህብረተሰብ አያሳውቁም ? እስቲ ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡
በነገራችን ላይ በተባበረችው አሜሪካ ኑሮአቸውን ያደረጉት የኢትዮጵያና ኤርትራ ተወላጆች በነጩ ቤተመንግስት ፊትለፊት በአደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተባበረችው አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ወያኔ የሚፈጽመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ድምጻቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ሰጪዎች ጆሮአቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በሌላ በኩል በሌላ አጋጣሚ ግን የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሃላፊ የሆኑት ብሊንከን (State Department Chief Anthony Blinken )በቲውተር ገጻቸው አመሃኝነት ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ 7 የሚገመቱ እና ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር በቀጥታ የስራ ግንኙነት የነበራቸውን የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን በማባረሯ ምክንያት ክፉኛ ተችተው ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የተባበረችው አሜሪካ በበኩሏ ኢትዮጵያ ውሳኔዋን ደግማ ደጋግማ እንድታጤናው ከማሳሰቧ ባሻግር አጻፋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደማንታገራግር በገድምዳሜ አስጠንቅቃለች፡፡
እኔ አንደ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብሆንም፣ ድምጼ ባህር ሰንጥቆ፣ አድማስ አቋርጦ ላይሰማ ቢችልም ለብይነ መንግስታቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ እና ለተባበረችው አሜሪካ ስቴት ሃላፊ ሚስተር ብሊንከን የሚከተለውን ጥያቄ አቀርባለሁኝ፡፡ ይኀውም የሚከተለው ይሆናል፡፡ ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ በማይካድራ ከተማ ከተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በአፋር እና አማራ ክልሎች ውሰጥ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የሢቪል ዜጎችን ህይወት ሲያጠፋ ለምንድን ነው ዝምታን የመረጣችሁት ? ለምን የዚህን አረመኔዎች ድርጊት ለማውገዝ መንፈሳዊ ወኔ ከዳችሁ ?
ለምን ይሆን የወያኔ አሸባሪ ቡድንን ዝርፊያ ችላ የምትሉት ? ለምንድን ይህ አሸባሪ ቡድን ከ428 በላይ የእርዳታ እህል የሚያመላልሱ ከባድ ተሸከርካሪዎችን ሲወርስ ዝምታን የመረጣችሁት? ( አንዳንዶቹ ተሸርካሪዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንብረቶች እንደሆነ ይነገራል፡፡) ለምንድን ነው ወያኔ ዜጎችን በሰብዓዊ ጋሻነት ለመጠቀም ሲል ብቻ የእርዳታ ስርጭትን ሲያስተጓጉል የማይከሰሰው ? የእርዳታ እህል አመላላሽ ተሸከርካሪዎች ሲዘረፉ፣የእርዳታ እህል በፍጥነት እንዳይደርስ መሰናክል መፍጠር አናንተ የምትጨነቁለትን የችጋር መጠን አያስፋፋው ይሆን ? ለምንድን ነው የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር በየግዜው በአለሙ የጸጥታው ምክር ቤት ጠረቤዛ ላይ ለውይይት የምታቀርቡት? ይህ የአለሙን መንግስታት ድርጅት ቻርተር መጣስ ሊሆን አይቻለውምን?
የተባበሩት መንግስታት ቻርተር የሚለው ምን ይሆን ?
አንቀጽ 2 ( ከቁጥር 1-5) የሚገኘውን ቻርተር ኢትዮጵያ በጽኑ የምታከብረው ፣ሆኖም ግን ሃያላን እና ሀይለኛ ሀገራት ስልዚህ አንቀጽ ምንም መናገር አይፈልጉም፡፡
‹‹ የአለሙ መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት በአንቀጽ‹‹1›› ላይ የሰፈረውን አላማ ገቢራዊ ለማድረግ በሚከተለው መርህ መሰረት አክት (act) አለባቸው፡፡
Article 2(1 to 5) of the Charter to which Ethiopia adheres but powerful nations do not say this:
“The Organization and its Members, in pursuit of the Purposes stated in Article 1, shall act in accordance with the following Principles.
1.የተባበሩት መንግስታ ድርጅት መሰረቱ በአባል ሀገራቱ ሉአላዊነት እኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህም ማለት ሁሉም የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት ሉአላዊነት በእኩል ደረጃ የተጠበቀ ነው የሚል ይሆናል፡፡
- ሁሉም አባል ሀገራት በአባልነታቸው የሚያገኙት መብትና ጥቅም በቀና መንፈስ የሚተገበር ሲሆን፣ግዴታቸውም አሁን ባለው ቻርተር የሚፈጸም ይሆናል፡፡
- ሁሉም አባል ሀገራት የሚጋጥማቸውን አለም አቀፍ ግጭቶች መፍታት ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ ይሆናል፡፡ ሀገራት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱ ከሆነ ፍትህና ሰላም ፣ እንዲሁም የአለሙ ጸጥታ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይቻለውም፡፡
- ሁሉም አባል ሀገራት የሌላውን ሀገር ድንበርና ሉአላዊ ግዛት ከመድፈር መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ከተባበሩት መንግስታት መርህ ያፈነገጡ ማናቸውንም ድርጊቶች መፈጸም የለባቸውም፡፡
- አሁን ባለው የተባበሩት መንግስታት ቻርተር መሰረት ማናቸውም ሀገራት የተባበሩት መንግስታትን መርዳት ይገባቸዋል፡፡ ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር ውጭ አንደኛው ሀገር ወዳጅ ለሚለው ሀገር ድጋፍ በመስጠት በሌላኛው ሶስተኛ ሀገር ላይ ጉዳት ማድረስ አይፈቀድም፡፡
ከላይ ያሰፈርኳቸውን የተባበሩት መንግስታት አንቀጽ 1 (ከ1-5) በእንገሊዘኛ ቋንቋ የሰፈረውን የበለጠ ገላጭ ስለመሰለኝ እንደሚከለተው ጠቅሼዋለሁ፡፡
What does the Charter say?
Article 2(1 to 5) of the Charter to which Ethiopia adheres but powerful nations do not say this:
“The Organization and its Members, in pursuit of the Purposes stated in Article 1, shall act in accordance with the following Principles.
- The Organization is based on the principle of thesovereign equality of all its members.
- All Members, to ensure to all of them the rights and benefits resulting from membership, shallfulfil in good faith the obligationsassumed by them in accordance with the present Charter.
- All Members shall settle their international disputes by peaceful means in such a manner that international peace and security, and justice, are not endangered.
- All Members shall refrain in their international relations from the threat or use of force against theterritorial integrity or political independence of any state,or in any other manner inconsistent with the Purposes of the United Nations.
- All Members shall give the United Nations every assistance in any action it takes in accordance with the present Charter and shall refrain from giving assistance to any state against which the United Nations is taking preventive or enforcement action.”
የግዜው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ስለወሰነባቸው 7 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወኪል ቢሮ ሃላፊዎችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደከተታቸው ለአለም መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል፡፡፣ የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ወኪል ድርጅቶች ተወካዮች እንዲባረሩ ያደረገበትን ተጨባጭ ምክንያት በማቅረብ እንዲያስረዳ መጠየቃቸውን፣ ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ህግን ማክበር ከተሳናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመለትን አለማ ለማከናወን ይገደዳል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል ሁላችንም እንደምናስታውሰው እነኚህ በኢትዮጵያ የአለሙ መንግስታት ድርጅት ወኪል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ወገንተኛ መሆን እንደሌለባቸው፣ የሀገሪቱን ህግና ደንብ አክብረው የዘውትር ተግባራቸውን እንዲከውኑ በየግዜው ከኢትዮጵያ መንግስት አኳያ እንደተነገራቸው ሆኖም ግን የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት የማይገባ ተግባር ሲፈጽሙ በመገኘታቸው ከሀገር እንዲወጡ መወሰኑን ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ እውን እነኚህ 7 ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወኪሎች የኢትዮጵያን ህግ አክብረው ሰርተው ነበርን ? እውን ቴክኒካል ሙያቸውን ብቻ ነበር ሲከውኑ የነበሩት ? ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡
በእኔ የግል አስተያየት መሰረት ንጹሃን ኢትዮጵያዊ ዜጎችን በጅምላ መጨረስ፣የወያኔ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ለመሸንሸን የሚያደርገው እኩይ ሴራ በተመለከተ የብይነ መንግስታቱን ዋና ጸሃፊ እጅጉን ያስደነገጠ አልመሰለኝም፡፡ እርሳቸውን ያስደነገጣቸው ወይም ያስቆጣቸው በሃላፊነት የሚመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወኪል ቢሮዎች የስራ ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ምድር መባረራቸው ነው፡፡ ባልካናይዝ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው የወያኔና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊን ልብ ሊያርድ አልተቻለውም፡፡ የርሳቸው ራስ ምታት እኔ የመደብኳቸው ሰራተኞች በኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ለምን ይባረራሉ የሚለው ነው፡፡
በእኔ የግል ግምገማ መሰረት አንቶኒዮ ጉቴሬስ ከሃላፊነታቸው ውጭ አለፈው የሄዱ መሰለኝ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አሸባሪውን የወያኔ ቡድን አቋም የደገፉ መሰለኝ፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ እኚህ በአለማችን አስቸጋሪ ስራ የሚያከናውነውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመሩት ታላቅ ሰው በዚሁ ከቀጠሉ የጥቁር አፍሪካውያንን አመኔታ ሊያጡ ይችላሉ ብዬ እሰጋለሁ፡፡ እርሳቸው በተባበረችው አሜሪካ ተጽእኖ ስር የወደቀውን የተባበሩት መንግስታት አላማ እና ተልእኮ ለማስከበር የታሪክ አደራ አለባቸው፡፡ በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ ስቴት ሴክሬቴሬ በግሉ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት 7ቱን ከፍተኛ የአለም አቀፍ ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎችን በማባረሩ ምክንያት ደስተኛ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ መንግስትም ላይ ጥርስ የነከሰ ይመስላል፡፡
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ጸጥታ፣ ክብር፣ እና ስብእናዋን ለማስጠበቅ የተወሰደው እርምጃ ለምን እንዳስደነገጣቸው ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ጣልቃ ገብነት ከአለሙ ማህበር ቻርተር ጋር የሚጣረስ ነው፡፡
አለም ሁለት የተለያዩ አለም አቀፍ ልማዶቸን ማዘጋጀት አትችልም፡- በአንድ በኩል ለሃያላኑ ሀገራት፣ በሌላ በኩል ለድሃና ደካማ ሀገራት በተለያየ መንገድ የሚዘጋጁ አለም አቀፍ ልማዶች ሊኖሩ አይቻላቸውም፡፡ ለአለም ሀገራት ሁሉ ሁለት አይነት አለም አቀፍ ልማዶች (international norms☺ የሉም፡፡ አለም አቀፍ ልማዶች ለሁሉም ሀገራት በእኩል ደረጃ መስራት ይገባቸዋል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት መንቃት አለባቸው፡፡ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች 30 ሀገራት የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር አለበት በማለት በመከራከራቸው ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡
የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር 118 አመታት የቆየውን የኢትዮጵያንና የተባበረችው አሜሪካን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተመለከተ ቸልታ ያሳየ ይመስላል
በተበዳይ ኢትዮጵያ ላይ፣ግፍ በተሰራባት ኢትዮጵያ ላይ ፣ ፍትህ በተነፈጋት ኢትዮጵያ ላይ፣ የተባበረችው አሜሪካ የገለልተኛ አቋም ለመወስድ ባለመቻሏ ምክንያት፣ወይም ከኢትዮጵያ ሉአላዊ ጥቅም በተጻራሪ አቋም ላይ በመገኘቷ በብቸኝነት ተቃውሟቸውን ያሰሙት የተባበረችው አሜሪካ ሪፐብሊካን ፓርቲ ወኪልና የኮንግሬስ አባል ክርሰቶፈር ስሚዝ ብቻ እንደነበሩ ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡( Congressman Christopher Smith ) የስሚዝ ጉብዝናን፣ለኢትዮጵያ ያላቸው ወዳጅነት፣ድፍረት በተመለከተ በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው፡፡ በእኔ በኩል ኢትዮጵየዊና ኤርትራዊ የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊና ኤርትራውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ አሜሪካውያን የክርስቶፎር ስሚዝን አቋም በፍጥነት ደግፈው እንዲወጡ እማጸናለሁ፡፡
የተባበረችው አሜሪካ መንግስት የአስመሳይነት ጨዋታ (US Government hypocrisy at play )
ይህ ከላይ የተጠቀሰው ርእስ የተባበረችው አሜሪካ በነቢብባ በገቢር የምታከናውነውን ተግባር ይወስደኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ቃልና ተግባር አልተገናኝቶም እንዲሉ አሜሪካ በቃል የምትናገረውና ገቢራዊ የምታደርጋቸው ድርጊቶች ለየቅል ናቸው፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 4 2009 ግብጽ መዲና ካይሮ በመገኘት የሚከተለውን ንግግር አድርገው እንደነበር የሚያሳይ መረጃ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በአንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ይመስላል፡፡
‹‹ ግነኙነታችን በልዩነታችን ላይ( ወይም ብሔራዊ ጥቅማችን ከተጠበቀ በሚል ምክንያት) የሚመሰረት ከሆነ ከሰላም ይልቅ ጥላቻ ለሚዘሩ፣ከትብብር ይልቅ ግጭቶችን የሚያራምዱ፣ ቡድኖች ሃይልና ጉልበት እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን፡፡ ›› የሚል ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ንግግር ማብቃት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የወያኔ ቡድን በተባበረችው አሜሪካ ጥቁር መዝገብ ውስጥ በአሸባሪነት ተመዝግቦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚስተር ጆባይደን የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ሆነው ከተመረጡ ወዲህ ይህ የለየለት አሸባሪ የጎሳ ቡድን የጦር ወንጀል ፈጽሟል፡፡ የንጹሃን ኢትዮጵያውያንን ደም አፍስሷል፡፡ ዛዲያ እንዲህ አይነት ነውረኛ ድርጅትን ደግፎ መቆም ከሰላም ይልቅ ግጭትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የሚነዛውን ቡድን ሃይል እንዲያገኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አይሆንምን ?
የተባበረችው አሜሪካ የቀድሞው ፕሬዜዴንት የነበሩት ሚስተር ባራክ ኦባማ አሰምተውት በነበረው ንግግራቸው ላይ አልሻባብ፣ወያኔ እና አጋሮቹን አሸባሪ ሲሉ መፈረጃቸው የሚታወስ ነው፡፡ እውን የወያኔ ቡድን አሸባሪ አይደለምን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ ፕሬዜዴንት ባራክ ኦባማ አሸባሪነትን እንዋጋለን ሲሉ ነበር አክለው የተናገሩት፡፡ በስመ የጎሳ ብሔርተኝነት ጭቆናና ማንነት፣( በዋነኝነት በወያኔ ይመራል)፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ የትግራይ የበላይነት መጠበቅ አለበት በሚል ሰንካላ ምክንያት ኢትዮጵያ የአሸባሪዎች ሰለባ ሆናለች፡፡ በአረቡ አለም አሸባሪነትን መዋጋት እንደ መልካም ነገር የሚቆጥሩት ምእራባውያንና የተባበረችው አሜሪካ ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ምድር ሽብርተኝነትን መዋጋት ከምእራባውያን አኳያ ለምን ተቀባይነት ሊያጣ ይቻለዋል ? የተባበረችው ከብሔራዊ ጥቅሟ በተጻራሪ የቆሙ ቡድኖችን አሸባሪ ብላ ስትሰይም ህጋዊ እውቅና ከተሰጣት፣ ለምን ይሆን በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ወይም ህጋ ውሳኔ፣ ህጋዊ ተቀባይነት ያጣው ?
የሀገሮችን ሉአላዊነት ማክበር
የቀድሞው ፕሬዜዴንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያቀረቡት መርህን የተከተለ ንግግር በባይደን አስተዳደር ችላ ተብሏል፡፡ የባራክ መርህን ያከበረ ንግግራቸው የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹ አሜሪካ ራሷን የምትከላከላው የሀገሮችን ሉአላዊነትና የህግ የበላይነትን በማክበር ነው››ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም የተከበሩ ፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር በቅጡ መረዳት ቁምነገር ቢኖር አሸባሪው የወያኔ ቡድን ጥንታዊቷን እና ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ አንድነት ለማፈራረስ ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ነው፡፡
The Biden Administration knows fully that the TPLF had declared its commitment to the “Balkanization of Ethiopia
ወያኔ ይህን እኩይና ያልተቀደሰ አላማውን እውን ለማድረግ ሲል ብቻ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አንድ ላይ መቆሙን ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እውን ኢትዮጵያን ከአለሙ ማህበር መነጠል፣ ባይተዋር ማድረግ፣ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማእቀብ መጣል፣ የአሸባሪዎች መፈንጫ እንድትሆን መመኘት ወይም መፈለግ የተባበረችው አሜሪካ መንፈስ ነውን ? በጭራሽ አይደለም፡፡ የተባበረችው አሜሪካ መንፈስ መሰረቱ የሰብዓዊ መብት ማክበር ላይ የቆመ ነው፡፡ እውን የተባበረችው አሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ማክበር ይገባዋልን ? ፕሬዜዴንት አባማ በካይሮ አድርገውት የነበረው ንግግር ምክንያታዊ ከሆነ መልሱ አዎንታዊ ይመስለኛል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ላይ የተፈረሙ አለም አቀፍ ህጎችን መቀበል፣እንደ አልሸባብ፣ወያኔና ኦነግ ሸኔ የተሰኙ ቡድኖችን አሸባሪ ቡድኖች በማለት መጥራት አሲድን እንደ መቅመስ የሚቆጠር አይመስለኝም፡፡ አሸባሪዎችን መዋጋት የአሜሪካ መርህ ከሆነ ለ፣ምን ይሆን የባይደን አስተዳደደር የወያኔ አሸባሪ ቡድንን በስሙ ለመጥራት ወደኋላ ያለው? እስቲ ሁላችሁም ጠይቁ፡፡
የተለየ አመለካከት ያስፈልጋል
ለደረሰኩበት ድምዳሜ ምክንያታዊነት ይረዳኝ ዘንድ የፓቫን ኩልካርኒስ አስተያየትን መርጫለሁ፡፡ ( Pavan Kulkarni’s opinion) ይህ አስተያየት ጊዜ የማይሽረው ሲሆን ለሚዛናዊ እና ፍትሃዊ ግምገማው ምንም የሚያገኘው ጥቅም አልነበረም፡፡ ሰውየው የጻፈው ለህዝብ ለማሰራጨት ነበር፡፡ ይህ በቅርቡ የተመሰረተ አማራጭ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲሆን በአለም ዙሪያ የሚገኙ ማህበራትን፣ድርጅቶችን፣ ንቅናቄዎችን ድምጽ ለማሰማት የተቋቋመ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት በአበዳሪ ሀገራት፣በጉልበተኞች ሀገራት ተጽእኖ ስር ለወደቁ ሀገራት እንዲህ አይነት ድምጽ በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል፡፡
አንባቢውን የቀድሞው ፕሬዜዴንት ጆን ባይደን ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩትን ቁም ነገር ወደ ኋላ በመሄድ እንዲመረምር አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ወይም እየተካሄደ የሚገኘው የርስበርስ ጦርነት እጅግ አሳዛኝ ከመሆኑ ባሻግር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን አንድነት በእጅጉ እየተፈታተነ የሚገኝ ነው፡፡ እንደነ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራን የመሰለ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ጠበብት በጥናታቸው እንደ ደረሱበት ከሆነ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በችጋር መሰል ህይወት ውስጥ እንዲዶሉ ያደረገ ነው በሰሜን ኢትዮጵያ የወያኔ ቡድን የከፈተው ጦርነት፡፡ ሌሎች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሠሜኑ ጦርነት ቀጥተኛ ጥቃት ምክንያት የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሸባሪው ወያኔ መሰሪ ተንኮል ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ሰራተኞች ስራቸው ተስተጓጉሏል፣ተሰቃይተዋል፣ የተገደሉም ነበሩ፡፡ የምእራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ምድር የጅምላ ግድያ ስለመፈጸሙ፣አስገድዶ መድፈር ወንጀል እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማው በየግዜው የዘገቡት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአብዛኛው የሚፈጸመው በወያኔ ቡድን መሆኑ እየታወቀ በዜና ዘገባቸው ላይ የወያኔን እኩይ ድርጊት ማንሳት አይፈልጉም፡፡ በሁሉም ቦታዎችና ሁል ግዜ ለተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂው የወያኔ ቡድን ብቻ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የአንበሳው ድርሻ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡
የወያኔ ቡድን ታርጌት ያደረገውን አንድ ብሔር ወይም ቡድን ወይም መንግስት የሚያጠቃው ያለምንም ይሉኝታ እና ጭካኔ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአማራ( ሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር) እና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት ወይም በአደረገው ወረራ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት አድርጓል፡፡ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ብር የሚገመት የሕዝብና የመንግስት ንብረት ዘርፏል፣ ይዞ መሄድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል፡፡ ወያኔ እንሰሳትን ሳይቀር የገደለ አረመኔ ድርጅትም ነው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት መሰረት የተባበረችው አሜሪካ ተረዘ ዜጎች የወያኔ ብረት አንጋቾች ላሞችን፣በሬዎችን፣ፈረሶችን፣ አህያና ዶሮዎችን መግደላቸውን የሚያሳዩ የዜና ዘገባዎችን ማዳመጥ ቢችሉ ኖሮ አመለካከታቸው የሚለወጥ ይመስለኛል፡፡ ይህም ማለት ወያኔ ስላደረሰው መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመት፣ ለተዋጊ ወታደሮቹ ከብቶች እያረደ ከመገበ በኋላ የተረፉትን እንሰሳት በመግደሉ ምክንያት፣ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ በመፈጸሙ ለአብነት ያህል ከ3000 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማትንና 1000 ግድም የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችን በመዝረፉ፣በማውደሙ፣ ጥንታዊ ቤተክርስቲያናትንና መስጊዶችን በማውደሙ፣ ዋጋ የማይተመንላቸውን ጥንታዊ ቅርሶችን በመዝረፉ ፣ህጻናት ወታደሮችን በሰብዓዊ ጋሻነት መጠቀሙ፣ ጭካኔ የተሞላበት አረመኔ ተግባራትን በመፈጸሙ ምክንያት የአሜሪካ ተራ ዜጎች የውግዘት ናዳ ሊያወርዱበት ይቸላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች እውነታውን በመደበቃቸው ዜናው ለተራው ህዝብ ሊደርስ አልተቻለውም፡፡ የምእራቡ አለም ፖለቲከኞችና መሪዎች፣ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊና የስራ ባልደረቦቻቸው አውነታውን ቢያውቁትም ዝምታን መምረጣቸው እሙን ነው፡፡
በአጭሩ ከአመታት በፊት በተባበረችው አሜሪካ፣ በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ፓርላማ ‹‹ አሸባሪ›› ተብሎ የተሰየመው የወያኔ ቡድን ከቀድሞ ግብሩ አልተመለሰም፡፡ ዛሬም ቢሆን በቀድሞው ባህሪው፣ስልቱ ቀጥሎበታል፡፡ ወያኔ ዜጎችን ይጨቁናል፣የጎሳ ማጽዳት እና ዘርማጥፋት ወንጀሎችን ፈጽሟል፣ወይም እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ካለፉት 27 አመታት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የንብረት ዝርፊያ እና ውድመት የየእለት ግብሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለ27 አመታት ያህል የወያኔ ዘረኛ ቡድን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንደ ብረት ቀጥቅጦ ፣ እንደ ሰም አቅልጦ በመግዛቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ጸጥታ ያስከበረ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ከባድ ስህተት ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን አንድነት ያላላ እና ሰላሟን የነፈገ እኩይ ቡድን ነበር፡፡ ወያኔ ከአፍጋኒስታን ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ለከት በሌለው ዝርፊያ ባዶዋን ያስቀረ፣ በጉቦ ከእግር እስከ ራሱ የተነከረ ቡድን ነው፡፡ ለዚህም ነው በህዝባ አመጽ ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑ ተሸቀንጥሮ የወደቀው፡፡
የምእራቡ አለም በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ወደ ፍትህ ፣የህግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር ሲመጡ ታሪክን እንዲያጠኑ ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ጥቁር አፍሪካውያንን ችላ ማለትና ወደ ጎን መተው የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አይነት ስርዓትን እንደ መደገፍ ይቆጠራል፡፡ ይህ ስህተት ይመስለኛል፡፡ የምእራባውያንን ወይም የተባበረችው አሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የትኛውን መደገፍ ይሻላል ? ከአመታት በፊት ልክ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ገቢራዊ እንዳደረገው የምእራቡ አለም የዘረኛውን የደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ አፓርታይድ ስርዓት ይደግፍ እንደነበር እሙን ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ፣ ወይም ቁራን ወይም የተባበሩት መንግስታትን ቻርትር መጥቀስ ጥችላላችሁ፡፡ በእኔ አስተያየት ችግር ፈጣሪዎች፣በሌላ ሰው ሀዘን የሚደሰቱ፣አረመኔዎች ወዘተ ወዘተ ሰላምን አያስገኙም፡፡ እንዲህ አይነት እኩይ ቡድኖች ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊያስጠብቁ ይቻላቸዋል ብለው ካሳቡ፣ የምእራቡ አለም ባጠቃላይ፣ በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ስንት አምባገነኖችን?፣ ስንት ቅኝ ገዢዎችን?፣ ስንት የመንግስት ሌቦችን?፣ ስንት ዘረኛ መንግስታትን ?ማበረታታት ወይም መርዳት አለባቸው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት በጣም ብዙ የሚለው መልስ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
የእኩልነት እጦት
ምንም እንኳን የተባበረችው አሜሪካ ግንዛቤ ቢኖራትም (ኢትዮጵያ ወስና የነበረውን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ማለቴ ነው፡፡ ) ትኩረት አልሰጠችውም ነበር፡፡ ወያኔ የተኩስ አቁም ውሳኔ ሳያደርግ በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ ሲፈጽም መልሳቸው ዝምታ ነበር፡፡ የብይነ መንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊም ሆኑ የተባበረችው አሜሪካ መንግሰት ጸሃፊ ለኢትዮጵያ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ተመሳሳይ ውሳኔ ከወያኔ ቡድን እንዲደረግ ማስገደድ ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ግን አላደረጉትም፡፡ ለምንድን ነበር የእኩልነት መንፈስ የራቃቸው ? አሁን ከመሸ በኋላ ነው ለወራሪው ወያኔ እና ለተበዳይ ኢትዮጵያ በአስተላለፉት ትእዛዝ ከጦርነት አዙሪት እንዲወጡ እየጠየቁ ያሉት፡፡ ጦርነት ክቡር የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ መቅሰፍት ሲሆን፣የሰው ልጅ ለፍቶ ደክሞ ለዘመናት ያጠራቀመውን ንብረቱን በጥቂት ግዜ ውስጥ ዶግአመድ የሚያደርግ ነው፡፡ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ሳይከሰት፣ንብረት ሳይወድም ጦርነቱን ማስቆም እየተቻለ ባለመደረጉ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ለማናቸውም የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ባስከበረ መልኩ ውይይትና ንግግር ቢደረግ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ጸሃፊው ያምናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብዓዊ እርዳታን እንደ መሳሪያ በማድረግ ማን የበለጠ እንደሚጠቀም በተገቢው ሁኔታ ሳይመረምሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የተባበረችው አሜሪካ የመንግስት ጸኃፊ ስለ ሰብዓዊ እርዳታ መስተጓጎል በየጊዜው በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ሲናገሩ ይሰማል፡፡
ፓቫን ኩልካርኒ (Pavan Kulkarni) የተባበረችው አሜሪካን አለም አቀፍ የእርዳታ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ሃላፊን ሲን ጆንስን ጠቅሶ እንደጻፈው (the head of USAID’s mission in Ethiopia, Sean Jones,) የወያኔ ቡድን በወረራ በያዛቸው ከተሞች መንደሮች ውስጥ መኖሪያ ቤቶችን ያወድማል፣በመጋዘን ውስጥ የተከማቹ አህልና መድሃቶችን ዘርፏል፡፡ በነገራችን ላይ ከተዘረፉ ንብረቶች መሃከል የተጠቀሰው ድርጅት እንደሚገኝበት ሲን ጆንሰን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ነሀሴ 25 2021 ከሰጡት መግለጫ ለማወቅ ይቻላል፡፡ ይህ በመሬት ላይ የሚታይ፣የሚዳሰስ፣የሚጨበጥ ማስረጃ በባይደን አስተዳደር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አስተዳደር የተጎዱ ሰዎች እርዳታ ማግኘት አለባቸው ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ የወያኔ ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ የተለያዩ ሸፍጦችን ገቢራዊ ሲያደርግ ያለምንም ማመንታት ማውገዝ ያበት ይመሰልኛል፡፡ እንዲህ አይነት ዒሰብዓዊ ድርጊቶችን ማውገዝ የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ አስተያየት አቅራቢዎች እነደሚናገሩት ከሆነ የተባበረችው አሜሪካ መንግስት መሬት ላይ ላሉት ባለስልጣናቱ ትክክለኛ መረጃ የማይሰጥ ከሆነ፣ የባይደን አስተዳደር ለኢትዮ አሜሪካውያንና ለኢትዮጵያ መንግስት ክብር እንደማይሰጥ ማሳያ ነው፡፡ እደግመዋለሁ ለምክንያት አይንን እንደመክደን፣ጆሮን እንደ መድፈን ይቆጠራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ሚዛኑን የሳተ አቋም ፣ የዲፕሎማቲክ ክሽፈት ይመስለኛል፡፡ የዚህም ውጤት አሳዛኝ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት መንገድ ከፍቶ ይገኛል፡፡
ፓቫን ኩልከሪን (Pavan Kulkarni) እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር መስከረም 2021 እንደጻፈው ከሆነ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ተሸንፎ እየሸሸ በሚሄድበት ግዜ ሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ጭና ተክለሃይማኖት በሚባል አካባቢ ከ100 በላይ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል፡፡ የአማራ ክልል የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት አቶ ግዛቸው ሙልነህ ለዜና አውታሮች ሰጥተውት በነበረው አስተያየት ‹‹ ወያኔ ከቤት ወደ ቤት(ከበር ወደ በር) በመዘዋወር ወጣቶች፣ሽማግሌዎችን፣ሴቶችን፣ህጻናትን፣ቄሶች ቤተክርስቲያን አስቀድሰው ሲመለሱ ገድለዋቸዋል፡፡
ለምን ይሆን ግፍ ፈጻሚውን ችላ የሚሉት ?
ሁላችንም በሀዘን እንደምናስታውሰው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2020 በማይካድራ ከተማ ይኖሩ የነበሩ 1500 የሚደርሱ ኢትዮጵያዊ የአማራ ተወላጆች በወያኔ ነብሰ ገዳዮች በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አውሮፓው ህብረትም ሆነ የተባበረችው አሜሪካ መንግስት ለ 11 ወራት ያህል ዝምታን ነበር የመረጡት፡፡ ይህን የሚያውቀው የወያኔ ቡድን ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ቀጥሎበታል፡፡ በአለም አቀፉ ህብረተሰብ እስይ አበጀህ የተባለው የወያኔ ቡድን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ጎንደርና አፋር ክልል ውስጥ ወረራ በመፈጸም ለግዜው በተቆጣጠራቸው አከባቢዎች የንጹሃንን ሲቪል ዜጎች ህይወት ቀጥፏል፡፡ ንብረት አውድሟል፡፡
እንደ ኩልካርኒ የመሰሉ የውጭ ሀገር ተወላጅ ጸሃፊዎች ሳይቀሩ በጭና የተፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ገና በትኩሱ ነበር ለአለም ያጋለጡት፡፡ እጅግ የማከብረው ኢትዮጵያዊው የመብት ተሟጋች ጋዜጠኛው ጌታቸው ሽፈራው በበኩሉ በቆቦ፣አላማጣ፣አበርገሌ፣ማይጠመሪ፣ጋይንት፣ ጋሽና እና መርሳ ከተሞች በሚኖሩ የወያኔ ቡድን አባላት የተፈጸሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ በማስረጃ አስደግፎ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ነገ ነጻ ፍርድ ቤት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች በፍትህ አደባባይ ሲቀርቡ የሰነድ ማስረጃ ሆነው እንደሚቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር የወያኔን ቡድን ማበረታቱን ማቆም ያለበት ይመስለኛል
የባይደን አስተዳደር ትእዛዝ ከሰጠ ከሁለት ቀናት በኋላ የወያኔ ቡድን በአዎንታዊ መልኩ እንደተቀበለ ከመነገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሰማቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2021 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ላይ በሰሜን ወሎ ቆቦ ከተማ እና ገጠር አካባቢዎች በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የተቀመጡ ሲቪል ነዋሪዎች ገድለዋል፡፡ ንብረት ዘርፈዋል፣አውድመዋል፡፡ ኩልካሪን( Kulkarni.) የተባለው የውጭ ሀጀገር ጸሃፊ ስለ ወያኔ ቡድን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ሲጽፍ ‹‹ ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር ወያኔ ለሚፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ›› በተመለከተ ምእራባውያን በተለይም አሜሪካ ግድ እንደሌላቸው ነው፡፡ ለምንድን ነው የወያኔ ቡድን አፈቀላጤ በግብጽ ቴሌቪዥን ቀርበው የባይደንን ትእዛዝ እቀበላለሁ ያሉት ?ለምንድን በግልጽ በአደባባይ በመውጣት የወያኔ አፈቀላጤ የሆኑት አቶ ጌታቸው እረዳ ኢትዮጵያን እንደ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እናፈርሳታለን በማለት የፎከሩት?
ለማጠቃለል ያህል ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ፓቫል ኩልካሪን የሰጠውን አስተያየት ጠቅሰው ያሰፈሩትን የሚከተለውን ሃሳብ አቀርባለሁ፡፡ ‹‹ የተባባረችው አሜሪካ ኢትዮጵያን እንደ ሰም አቅልጠው፣ እንደ ብረት ቀጥቅጠው ለ 27 አመታት የገዙት ወያኔዎች፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 6 ፐርሰንት ያህሉን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያህለውን የትግራይ ህዝብ ወኪል ነን የሚሉትን ወያኔዎች ከመደገፍ አኳያ የቆየ ታሪክ አላቸው፡፡ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን የፖለቲካ ነጻነት እንዳልነበረ የታወቀ ነው፡፡ የነጻው ፕሬስ በአንድ ወቅት የገሞራ የነበረ ቢሆንመ በኋላ ላይ ጠፍቶ ነበረ፡፡
ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ በክብርና ኩራት ተቀባይነት ማግኘት ይሻሉ፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ይሻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከታችኛው እስከ የላይኛው የመንግስት መዋቅር ውስጥ በዲሞክራቲክ መንገድ የተመረጡ ሰዎች እንዲመሩት ይሻል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ጉቦኝነት እንዲቀንስ ወይም እንዲጠፋ፣በስልጣን መባለግ፣ጎሰኝነት፣አሻጥረኛ ነጋዴዎች እንዲጠፉ፣ ወዘተ ወዘተ ለዘመናት ከህዝቡ የቀረቡ የዘመናት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለአንድ ዘመናዊና መልካም አስተዳደር ላለው መንግስት ጠቃሚ እርሾ ናቸው፡፡ ዘመናዊና መልካም አስተዳደር መገንባት ያሆነለት መንግስት ቀጣይነት ያለው እድገትና ልማት ማምጣት አይቻለውም፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች፣ ከበርካታ ግንባሮች የገጠማት ሀገር ናት፡፡ በእኔ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ከገጠማት መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመውጣት ያላት ዋነኛ አማራጭ የራሷን ብሔራዊ የሰው ሀብት፣እውቀቷን፣ባለሙያዎቿን፣የገንዘብ ሀብቷን እና ሌሎችን ሀብቷን በአንድነት አስተባብራ መነሳት አለባት ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከወዳጅ ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር መተባበሩ አማራጭ የለውም፡፡
በመጨረሻም የሚከተለውን መልእክቴን በማስተላለፍ የዛሬውን ጽሁፌን እቋጫለሁ፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ሊጠበቅ የሚቻለው ፡-
- አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ
- ሰላም በሰፈነባት ኢትዮጵያ
- በተረጋጋች ኢትዮጵያ
- ዲሞክራክና በአደገች ኢትዮጵያ መሆኑን ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡
በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ የተባበሩት አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም በሚከተሉት አውዶች እንደማይጠበቅ አስታውሳለሁ፡፡ የጦር ወንጀል እና ዝርፊያ የፈጸመውን ወያኔ፣ በሲቪል ዜጎች ላይ ግድያ የፈጸመውን ወያኔ አጋር በመሆን ከኢትዮጵያ የምትፈልገውን በምንም አይነት መልኩ የምታገኝ አይመስለኝም፡፡ የሚያዋጣው የተባበረችው አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት ባማከለ መልኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መልካም ግንኙነት ለመመስረት መሞከር ነው፡፡( በነገራችን ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ወይም አለመጠበቅ የጸሃፊው እራስ ምታት አለመሆኑን አንባቢውን ያስታውሳል፡፡ ይህች ሃያል ሀገር ብሔራዊ ጥቅሜን አስጠብቃለሁ በሚል ስሌት ብቻ የኢትዮጵያን አንድነት ለሚያናጉ ቡድኖች መርዳቱ አግባብ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው፡፡) በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የጦር ወንጀል የፈጸመውን ወያኔ፣ የኢትዮጵያን ብሔራ ሀብት የዘረፈውንና ኢትዮጵያን ማፍረስ አለብኝ በማለት በእብሪት ለተወጠረው ወያኔ ድጋፍ በመስጠት፣ ምርኩዝ በመሆን የሚፈልጉትን የሚገኙ አይመስለኝም፡፡
እንደ አንድ አለምን እንደሚወድ ሰው የታመመው የተባበረችው አሜሪካ እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት 117 ሚሊዮን ግድም የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት እንዳያናጋ ምኞቴም ጸሎቴም ነው፡፡ በመጨረሻም የተባበረችው አሜሪካም ሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ወደ ህሊናቸው በመመለሰ የኢትዮጵያ ህለውና ችግር ውስጥ እንዳይዶል በሰከነ መንፈስ፣ በመከባበር መልሰው ቁጭ ብለው እንዲነጋገገሩ በመማጸን እሰናበታለሁ፡፡
ማስታወሻ፡- የዛሬውን ጽሁፌን ለማዘጋጀት የፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራን ጥናታዊ ጽሁፍ ተጠቅሜአለሁ
‹‹ ኢትዮጵያ እደዊሃ ሀበ እግዛብሔር››
ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም.