>

ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ለማስወገድ ሕዝብና መንግሥት ተባብረው በመሥራት ላይ ነን...!!!የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ

ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ለማስወገድ ሕዝብና መንግሥት ተባብረው በመሥራት ላይ ነን…!!!የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አሸባሪው ሕወሓት እንደ ሸኔ ካሉት የሽብር ኃይሎች ጋር በመመሳጠር የብሔርና የኃይማኖት ግጭቶችን በመፍጠር የአያሌ ዜጎችን ሕይወት ለቀውስ ዳርጓል:: ብዙዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ-ልቦና እና የንብረት ጉዳት አጋልጧቸዋል:: የትህነግ ተላላኪ የሆነውን ሸኔ ከክልሉ ለማስወገድ ሕዝብና መንግሥት ተባብረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ ብሏል::

የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የትህነግ አሸባሪ ቡድንን ለመደምሰስ ሰሞኑን እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ እየሰጠ መሆኑን መግለጫው አመልክቶ፤ የትህነግ ተላላኪ የሆነውን ሸኔ ከክልሉ ለማስወገድ ሕዝብና መንግሥት ተባብረው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል::

የክልላችን ሕዝብ እንደ ትናንትናው አንድነታችሁን ጠብቃችሁ፣ በውጭና በውስጥ ኃይሎች ያስመዘገባችሁትን ድል ዛሬም በአንድነት የአገራችን ጸር የሆኑ ኃይሎችን በማስወገድ የአገራችንን ብልጽግና እንደምታሳኩ ጥርጥር የለውም ያለው መግለጫው፤ የኦሮሞ ሕዝብ በክልላችን ለብዙ ዘመናት በሰላም ከኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመተባበር በሕዝቦች መካከል ጥርጥር የሚረጩና ጥላቻን የሚያሰራጩ የጥፋት ኃይሎችን በመታገል፣ ለክልላችን ልማት በመደማመጥና በአብሮነት መሥራት ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን አስፈላጊ መሆኑን አብራርቷል::

በተለይም ከክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የአካባቢያችሁን ሰላምና መረጋጋት በንቃት እንድትጠብቁና ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን እያደረጋችሁ ያለውን እርዳታ እንድትቀጥሉበት በሚል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን አስታውቋል::

አሸባሪው የትህነግ ኃይል በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ አያሌ ዜጎች ላይ መከራና እንግልት በማድረስ የአገርን ሐብት ሲዘርፍና ሲያዘርፍ እንደነበር ይታወቃል::

ትህነግ በውስጥና በውጭ እንዲሁም በሐሳብ በመድረክ ላይ በተደረገው የተቀናጀ ትግል የአገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚመጥን ሐሣብ የማመንጨት አቅም መንምኖበት በ2010 ዓ.ም ከሥልጣን ተወገደ:: ይህ ትግል ያስገኘው ድል ለአገራችንና ሕዝባችን በተስፋ የተሞላ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ችሏል::

ይሁን እንጂ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በጠብመንጃ የራሱ አድርጎ ከነበረው የመንግሥት ሥልጣን በሕዝባዊ

ተቃውሞና በመድረክ ትግል ቢነጠቅም፣ በሥልጣን ዘመኑ የዘረፈውን ሐብት በመጠቀም ላለፉት አራት ዓመታት በአገራችን ረብሻ እና ግጭቶችን በመፍጠርና በማስፋፋት አገራችንን ለማፍረስ ያለውን ዓላማ ለማሳካት አቅሙን ሁሉ አሟጦ ሲሠራ ቆይቷል::

የትህነግ የሽብር ኃይል ግጭትና ሁከት በመፍጠር የዜጎችን ሕይወት ለመከራ ከማጋለጥ አልፎ፣ በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የሰሜን ዕዝ ላይ ባደረሰው የክህደት ጥቃት የአገራችንን ሉዓላዊነት፣ ሠላምና መረጋጋት ለአደጋ አጋልጦ ነበር::

ይህ የሽብር ቡድን በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ሕዝቦች ላይ ባደረሰው ወረራ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ከመኖሪያ ቀያቸውና ከሐብት ንብረታቸው በማፈናቀልና በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ዘግናኝ ግድያዎችን በመፈጸም ተወዳዳሪ የሌለው ጭካኔ አሳይቷል::

አሸባሪው የትህነግ ኃይል ከተላላኪዎች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመበተን የፎከረበትን ህልሙን ለማሳካት፣ ያለውን ኃይል ሁሉ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን ከአገራችን ጠላቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል:: በአገር ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር የማይደራደር የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይለያይ፣ የትህነግ የሽብር ቡድን የሰነዘረበትን እኩይ ጥቃት በአንድነት እየቀለበሱ እንደሚገኙም መግለጫው አብራርቷል::

ትህነግ ትናንት እንደለመደው የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በትናንሽ ልዩነቶች በመለያየት በመካከላቸው ጥርጣሬን ፈጥሮ እየገዛ ነበር:: ዛሬም አንድነታችንን ለማዳከም የውሸት ፕሮፖጋንዳ ማምረትና ማሰራጨት ቀጥሎበታል:: በተለይም በኦሮሞ ሕዝብና በአማራ ሕዝብ መካከል ያለውን ወንድማማችነት ለማዳከም ያልተበተበው ሴራ፣ ያልተሰራ ፕሮፖጋንዳ፣ ያላሰራጨው የጥላቻ መርዝ አልነበረም ሲል መግለጫው አስታውሷል::

Filed in: Amharic