ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ!
በሃገር መከላከያ ሰራዊት እየተመራ ወራሪውን የሽብር ቡድንና ያሰለፈውን መንጋ እየመከተ የሚገኘው መላው የፀጥታ ሃይላችን በፀረ ማጥቃት እርምጃው ቀጥሏል።
በተለይ ደሴን ለመያዝ አሰፍስፎ የመጣውን ወራሪ ሃይል በመመከት አኩሪ ገድልን እየፈፀመ ይገኛል።
ሌሊቱን ሙሉ ከተለያዩ ግንባሮች ጠጋግኖ በማሰባሰብ ደሴን ለመያዝ በኩታበር; ቦሩ ስላሴና በሃይቅ መስመር የመጣውን ወራሪ መንጋ የፀጥታ ሃይላችን በታላቅ ጀብዱ መክቶታል። አሁንም ደሴና አካባቢዋ በፀጥታ ሃይላችን ስር ነው።
ቀደም ብለውም ስደተኛ በመምሰልና የመከላከያ ሃይላችንን ወታደራዊ አልባሳት ለብሰው ሊዘርፉ የሞከሩና ቡድኖችና በከተማዋ የሚኖሩ ለጥፋት ሃይሉ የሚሰሩ ባንዳዎች ከትናንት ጀምሮ የጁንታውን አላማ ለማስፈፀም ከግንባር ውጊያው ባልተናነሰ ሲሰሩ ውለዋል።
የደሴ ወጣቶችና መላው የፀጥታ ሃላችንም ይህንን ሃይል በተደራጀ መንገድ እየመከቱት ይገኛሉ። የከተማዋ ወጣቶችም በጀመሩት መንገድ ከተማቸውን ከባንዳ የመጠበቅ ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ያለውን ሃይል ሁሉ አሰባስቦ በዚሁ ግንባር ያመጣው የሽብር ቡድኑ በጦር ግንባር ያቃተውን በወሬ ለማግኘት አሁንም መፍጨርጨሩን ቀጥሏል።
አንዳንድ የውጪ መገናኛ ብዙሃንም የሽብር ቡድኑን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እያስተጋቡ ይገኛሉ።
በወሬ የሚያዝ ከተማ የለም ሊኖርም አይችልም ብሎ መላው ህዝብ በደሴ ከተማ ዙሪያ ለሚነሳው አሉባልታ ጆሮ ሳይሰጥ አሁንም የሃገሩን ህልውና ለማስከበር የሚያደርገውን ተጋድሎ ቀጥሏል።
በዚሁ አጋጣሚ በተለይ ያልተጣራ መረጃን በመያዝ ህዝብን ለማሸበር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙና የሽብር ቡድኑ መጠቀሚያ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት ያሳስባል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት