(ስትራቴጂክ ጠቀሜታ የላትም!)
አሳፍ ሀይሉ
አዲሳባ ግን ለስም (እና ምናልባት አሁን ለፈረደበት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዋ) ካልሆነ በስተቀር፣ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያላት መሬት አትመስለኝም። ያንንም ያልኩት በታሪክ ላይ ተመሥርቼ ነው።
ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ያስገበሩት ከሰሜን ጎንደር ሆነው ነው። ሸዋ አንኮበር የመጡት አንዴ፣ እሱም ለመቀጣጫ ዓላማ ነበር።
አፄ ዮሐንስ ከመቀሌ ቤተመንግሥታቸው ሆነው ኢትዮጵያን የገዙት አንድም ቀን አዲሳባን ሳይረግጡ ነው።
እምዬ ምኒልክ አብዛኛውን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት ከአንኮበር ሆነው ነው። አዲሳባ የገቡት ሥልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ የንጉሥ መናገሻ ከተማ ለማነፅ ነው።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ አዲሳባ ላይ ተቀምጠው ነው ከቤተመንግሥት ወደ ኦንጦጦ ማርያማቸው የተሸኙት።
የሙሶሎኒዋ ፋሺስት ኢጣልያ አዲሳባ በሙሉ ቁጥጥሯ ሥር እያለ ነው መሣሪያዋን አውርዳ እንግሊዞችንና የኛን አርበኞች እያጨበጨበች በሠላም አስወጡኝ እንጂ እንኩ አዲሳባችሁን ያለችው።
ቀኃሥ በበኩላቸው አዲሳባን የአፍሪካ፣ የዓለም፣ የኢትዮጵያ የደምሥር ከደርጋለሁ ሲሉ ነው ከአዲሳባ ቤተመንግሥት በቮልስ ወደ እስራትና ሞት የተሸኙት።
ጄነራል ተፈሪ በንቲ አዲሳባ ላይ ሥልጣኔን ተከልኩ ከማለቱ ነው ከቤተመንግሥቱ የተቀነደበው። ጄነራል አማን አንዶም አዲሳባ ላይ እያሉ ነበር በታንክ ተደፍጥጠው የሞቱት።
መንግሥቱ ኃይለማርያም አዲሳባ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እያለች ነው ጥሎ ወደ ዚምባብዌ የፈረጠጠው።
ወያኔ አዲሳባ ላይ ሙሉ ሠራዊቷን እያዘዘች ነው በእነ አብዮት በካልቾ የተባረረችው።
ሳስበው አዲሳባ ላለፉት 150 ዓመታት ለማንም ኢትዮጵያን ላስተዳደረ አንደኛውም አካል ስትራቴጂካዊ ወታደራዊ ጠቀሜታ ኖሯት አያውቅም። አዲሳባን ታቅፈህ የምታተርፈው ሥልጣን የለም።
አዲሳባ የሴረሞኒዎች ማካሄጃ ቦታ ነች። መናገሻ ነች። ከዚያ ያለፈ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ የላትም። በእኔ ግምት፣ ከአዲሳባ ይልቅ ደሴና ከምቦልቻ ትልቅ ወታደራዊ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አላቸው።
“እኔ ኑሮዬ አዲሳባ .. አንቺ ያለሽው ሐረር
በሕልሜ ትመጫለሽ በጣም … እስኪ እንነጋገር..
አልማዝ ላንቺ ይመስልሻል.. በእውነት ተጎዳሁ ብለሺ
ከሐረር አዲስአበባ .. በሃሳብ ትታዪኛለሽ
ተይ ፍቅር ስለ እኔ… ምን ይላል ልብሽ
እ ባ ክ …. ሽ !”
( – የመሀሙድ አህመድ ተወዳጅ ዜማ)
አዱዬ አዱገነት፣ የአራዶች ማጀት፣ ክፉ አይንካሽ!