>

ንሥር...!!! ~ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ንሥር…!!!

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
…………………………..
ንሥር እጅግ ግዙፍ ከሆኑ የአዕዋፍ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክብደቱ እስከ 6.7 ኪሎ ሲደርስ ቁመቱ ደግሞ ከአንዱ ክንፉ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ 2 ሜትር ተኩል ይደርሳል፡፡ በዓለም ላይ እስከ ስድሳ የሚደርሱ የንሥር ዝርያዎች ይገኛሉ፡
በኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ንሥር የትንሣኤ ሙታን፣ አርቆ የማሰብ፣ ወደ ላይ የመምጠቅና የመነጠቅ፣ የጥበቃና የምናኔ ተምሳሌት ሆኖ ተገልጧል፡፡ ግብጻውያን ደግሞ የተቀበሩ ሰዎችን አጋንንት እንዳይደርሱባቸው በመቃብራቸው በር በድንጋይ ላይ የንሥርን ምስል ያስቀርጹ ነበር፡፡ ይጠብቃቸዋል ብለው፡፡ በግሪክ አፈ ታሪክ የአማልክት ንጉሥ የሚባለው ዜውስ በንሥር የሚመሰል ነበር፡፡ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች እጅግ ለሚያከብሩት የሌላ ወገን ሰው የንሥርን ላባ በመስጠት ክብራቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ ሞቼ የተባሉት የፔሩ ሕዝቦችም ንሥርን ያመልኩት ነበር ይባላል፡፡
ንሥር ይህንን ያህል ቦታ በሕዝቦች ባሕል ውስጥ ሊይዝ የቻለው በተፈጥሮው በታደላቸው የተለያዩ ጸጋዎች የተነሣ ነው፡፡
ንሥር ከእንስሳት ሁሉ ወደ ሰማይ በመነጠቅ የሚተካከለው የለም፡፡ እርሱ የሚደርስበትን የሕዋ ከፍታ የትኛውም ዓይነት ወፍ አይደርስበትም፡፡ አንዳንድ አዕዋፍ እስከ ተወሰነ ድረስ ቢከተሉትም እንኳ እርሱ ግን ጥሏቸው ማንም በማይደርስበት የሰማይ ጥግ ብቻውን ይንሸራሸራል፡፡ ለዚህም ነው ጥንታውያን ሰዎች በሐሳብ የመምጠቅ፣ ማንም ከማይደርስበት የጸጥታ ሕዋ ላይ አእምሮን የማሳረግ፣ ተራ ነገር ማሰብና ተራ ነገር መሥራት ከሚችሉ ደካማ ልቦች ርቆ በሉዓላዊ ሐሳብ ላይ የመምጠቅ ምሳሌ ያደረጉት፡፡
#ታድያ_ይኼ_ንሥር_እንዲህ_ይልሃል፡- ከቁራዎችና፣ ከሌሊት ወፎች፣ ከጥንብ አናሣዎችና ከድንቢጦች፣ ከተባዮችና ከነፍሳት ጋር እዚህ ምን ታደርጋለህ? በወረደ ሐሳብ ለምን ትመስላቸዋለህ? ውጣ ወደላይ፤ ሂድ ዐርግ፣ ምጠቅ ተመሰጥ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስ ዝንብና ትንኝ፣ እስከ ተወሰነ ቦታ ድረስም ነፍሳት፣ እስከ ተወሰነም ቦታ ድንቢጦችና የሌሊት ወፎች፣ እስከ ተወሰነውም ቁራዎችና ጥንብ አንሣዎች ይከተሉህ ይሆናል፡፡ ሐሳብህን ከፍ፣ አእምሮህንም ሉዓላዊ፣ ልቡናህንም ምጡቅ፣ አመለካከትህንም ከፍ ያለ ባደረግከው ቁጥር ግን ደካቹ ከሥር እየቀሩ ከሚመስሉህ ከንሥሮች ጋር ብቻ በጸጥታው ሕዋ ላይ ትንሳፈፋለህ፡፤ ሂድ ዐርግ፡፡
ንሥር እጅግ አስደናቂ የሆነ የማየት ችሎታ የተሰጠው ፍጡር ነው፡፡ እስከ አምስት ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ አንዲትን ትንሽ ጥንቸልን አንጥሮ ማየት ይችላል፡፡ የንሥር ዓይን ከጭንቅላቱ በተነጻጻሪ ሲታይ እጅግ ታላቅ ነው፡፡በንሥር ዓይን ውስጥ በአንድ ሚሊ ሜትር ስኩዌር ረቲና አንድ ሚሊዮን ለብርሃን ስሱ የሆኑ ሴሎች አሉት፡፡ ሰዎች ስንት ያለን ይመስላችኋል? ሁለት መቶ ሺ ብቻ፡፡ የንሥር አንድ አምስተኛ ማለት ነው፡፡ ሰው ሦስቱን መሠረታዊ ቀለሞች ብቻ ማየት ሲችል ንሥር ግን አምስቱን ማየት ይቻለዋል፡፡ እንዲያውም ከሩቁ አንጥሮ በማየት ንሥርን የሚተካከለው እንስሳ የለም የሚሉ ጥናቶችም አሉ፡፡
ንሥር የሚፈልገውን ለማሰስ እስከ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ ይዞራል፡፡ ሲያገኝ ግን ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ በሚያድነው ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት› የሚለውን የአማርኛ ብሂልና ‹jack of every thing master of non› የሚለውን የእንግሊዝኛ አባባል በደመ ነፍስ ዐውቆታል፡፡ ከትኩረቱ ፈጽሞ ንቅንቅ የለም፡፡ ምንም ዓይነት ግርዶሽ፣ ምንም ዓይነት መሰናክል፣ ምን ዓይነት መደለያ አያዘናጋውም፣ ተስፋም አያስቆርጠውም፡፡ የዚያን የአደኑን ነገር በንቃትና በትጋት እስከ መጨረሻ ይከታተለዋል፡፡ እንዲሁ አይወረወርም፤ ጊዜና ሁኔታ ይመርጣል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲገጥሙለት ትኩረቱን ሰብስቦ በመወርወር ታዳኙን ይሞጨልፈዋል፡፡
#ንሥር_እንዲህ_ይልሃል፡- ደጋግመህ አስብ፤ ለመወሰን ጊዜ ውሰድ፤ ዙር ተዟዟር፡፡ ልፋ ድከም፤ አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሺ ጊዜ ለካ፡፡ በመጨረሻም ዒላማህን ለይ፡፡ አስተካክል፡፡ ትኩረትህንም በዒላማህ ላይ ብቻ አድርግ፤ ምንም ዓይነት ማታለያ፣ ምንም ዓይነት መደለያ፣ ምንም ዓይነት ማሰናከያ፣ ምንም ዓይነት ፈተና፣ ምንም ዓይነት ተስፋ መቁረጥ ከዓላማህ ሊያግድህ አይገባም፡፡ ማየትና ማሰብ ያለብህ ሁሉም ሊያየውና ሊያስበው የሚችለውን ተራ ነገር አይደለም፡፡ ሊታይ የማይችለውን ለማየት፣ ሊለይ የማይችለውን ለመለየት፣ ሊተኮርበት ያልቻለውን ለማተኮር ጣር፡፡ ዒላማህን ካገኘህ አትልቀቅ፤ ጊዜና ሁኔታ አመቻችና ዒላማህ ላይ ተወርወር፡፡ ያንተ ከመሆን ማንም አያግደውም፡፡
ንሥር በምንም ዓይነት የሞቱ እንስሳትን አይበላም፡፡ እርሱ እቴ፡፡ በሕይወት ያለውን እንስሳ የገባበት አሳድዶ፣ ከተደበቀበት ጠብቆ አድኖ ይበላዋል እንጂ እርሱ እንደ ቁራና ጥንብ አንሣ የሞተ ላይ አያንዣብብም፡፡ እንደ አራዳ ልጆች ከተበላ ዕቁብ ጋር አይጨቃጨቅም፡፡ ቀላል ነገር ቢያጣ በግና ፍየልም ቢሆን ተወርውሮ አድኖ፣ ከዐለት ላይ ፈጥፍጦ እንደ አጥንት ወዳጅ አበሻ ቅልጥም ሰብሮ ይበላል እንጂ የሞተ ጥንብ ሲያልፍም አይነካው፡፡ ያቺን ከባዷንና በድንጋይ የተሸፈነችውን ዔሊ እንኳን ከዐለት ስባሪ ላይ ከስክሶ ድንጋይዋን አራግፎ ይበላታል እንጂ ያላወቀውን ነገር አይበላም፡፡
#ንሥር_እንዲህ_ይልሃል፡- ልቡናህንና ኅሊናህን፣ አእምሮህንና መንፈስህን ምን እንደምትመግባቸው አስብ፡፡ የሞተ፣ የማይሠራ፣ የተበላሸ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ ቁራና ጥንብ አንሣ የሚጫወቱበትን አትመግበው፡፡ ፊልምና ፕሮፓጋንዳ፣ ዋዛና ፈዛዛ፣ የወረዱና የበከቱ አስተሳሰቦችን አትመግበው፡፡ ከተፋና ለብለብ ሐሳቦችን አትጋተው፡፡ ይልቅ አድን፣ ድከም፣ ልፋ፣ ተሟገት፣ ተመራመር፣ እንደ ዔሊ ድንጋይ የከበደውን አስተሳሰብ ገልብጠህ፣ ፈንክተህ ተመገብ፤ ድካምና፣ ጽሞና፤ ማሰብና መመርመር የሚሻውን ንባብ ውደድ፤ ሳይለፉና ሳይደክሙ እንደ ሞተ እንስሳ ሥጋ የትም የሚገኘውን ነገር ሳይሆን ጥረትና ግረት የሚሻውን፤ ላብ ጠብ የሚያደርገውን ሞያና እንጀራ ፈልግ፡፡
ንሥር ዐውሎ ይወዳል፡፡ ሰማዩ ሲጠቁርና ደመናው ሲሰበሰብ ወጀቡም ሲያይል ሌሎች አዕዋፍ በዐለት ንቃቃትና በጫካው ችፍርግ ውስጥ ይደበቃሉ፤ በቤት ታዛ ሥርም ይሠወራሉ፡፡ ንሥር ግን ደስ ይለዋል፡፡ ወጀቡና ዐውሎው ሲጀምር ንሥር የንፋሱን ኃይል በመሞገት የራሱን ጥንካሬ ይለካበታል፡፡ የነፋሱን አቅጣጫ በመከተልም ይበራል፡፡ ራሱን ወደ ላይ ለማምጠቅና የከፍታውን ጫፍ ለመጨበጥ ይጠቀምበታል፡፡ በዚያ ጠንካራ ነፋስ ትከሻ ላይ ሲጫን ነው ንሥር ዕረፍት የሚወስደው፡፡ ክንፉን ብቻ ዘርግቶ በዕረፍት ስሜት ከደመና በላይ የኃያሉን ዐውሎ ዐቅም ተጠቅሞ ይንሸራሸራል፡፡
#አንተንም_ንሥር_እንዲህ_ይልሃል፡- መከራንና ፈተናን አትፍራ፤ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥም ቢሆን መንገድ አለና፡፡ መከራውንና ችግሩን፤ ፈተናውንና ግብግቡን የአዳዲስ ሐሳቦች መነሻ፤ የጥንካሬህ መለኪያ፤ ዐቅምህን የምትሰበስብበት አጋጣሚ፣ ወደላይ የምትመጥቅበትና ከችግር ደመናዎች በላይ የምትንሳፈፍበት ዕድል አድርገው፡፡ እንደ ሌሎች ወፎች ከመከራው አትሽሽ፤ ከችግሩም አትደበቅ፤ መከራን ለበረከት ተጠቀምበት፡፡
Filed in: Amharic