>

አሜሪካ አንደኛ ዓመቱን የደፈነው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳሰበች...!!!

አሜሪካ አንደኛ ዓመቱን የደፈነው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳሰበች…!!!

 አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷና በልማት ተራድኦ ድርጅቷ በኩል ነው ማሳሰቢያውን ያቀረበችው ።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ-ገፁ ላይ ባሰፈረው መግለጫ በአገር ውስጥም ሆነ ውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት መፍትሄ በመፈለግ ሕዝቡን ከስቃይ ሊገላግሉት ይገባል ብሏል።

አብረው በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት በተለይ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ከሁሉም ወገኖች በሚመጡ አላስፈላጊ ንግግሮች እየተጋጋለ ነው በማለት ጉዳዩ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ጠብ ጫሪ ንግግሮች ግጭቱን ያባብሱታል፤ መፍትሔም እንዳይመጣ ሊያደርጉ ይችላሉ ስትል አሜሪካ እንደምትሰጋ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

አክሎም አዲስ አበባ ውስጥ “ብሔርን መሠረት ያደረገ እሥር እየተካሄደ መሆኑ” ስጋት ውስጥ ጥሎናል ብሏል።

በግጭቱ ምክንያት ሚሊዮኖች ደኅንነታቸው ስጋት ላይ በወደቀበት ወቅትና እንዲሁም ከ900 ሺህ በላይ ሰዎች የረሃብ አፋፍ ላይ በሆኑበት ሁኔታ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች ትጥቃቸውን አስቀምጠው ለንግግር የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ቢሠሩ መልካም ነው ብላለች አሜሪካ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጦሩን እንዲገታ፣ በመቀለ የሚያደርገውን የአየር ጥቃትና ብሔር ተኮር ሚሊሻዎችን መመልመል እንዲያቆም እንጠይቃለን ይላል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ።

አክሎም የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ እንዲወጣ፤ ህወሓትና ኦነግ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ እንዲያቆሙ መግለጫ ይጠይቃል።

የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉም ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ በሮችን እንዲከፍቱ የጠየቀ ሲሆን ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔት እንዲደራደሩና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማስቆም እንዲሠራ ጠይቋል።

በተያያዘ ዘገባ የአሜሪካ መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት [ዩኤስኤይድ] በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት አንደኛ ዓመቱን መያዙን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ የከፋ ነው ብሏል።

ድርጅቱ፤ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የሚኖሩ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የምግብ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የድርጅቱ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል ብቻ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚሹና 900 ሺህ ያክሉ ደግሞ ረሃብ አፋፍ ላይ እንዳሉ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

በትግራይ ትልቅ ቀውስ ያስከከተለው ግጭት አሁን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛምቶ በርካቶችን ያለቤት ንብረት እንዳስቀረ የዩኤስኤይድ መግለጫ አውስቷል።

አሜሪካ፤ ህወሓት ጦርነቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋፋቱን እንደምታወግዝና ይህ ኃይል ከአፋርና ከአማራ ክልሎች እንዲወጣ ጥሪ እንደምታቀርብ የተራድዖ ድርጅቱ ኃላፊ የለቀቁት መግለጫ ያመላክታል።

ሳማንታ፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማንን ዋቢ አድርገው ህወሓት ወደ አዲስ አበባ እያደረገ ያለውን ግስጋሴ አሜሪካ እንደምታወግዝ ጠቁመዋል።

ሳማንታ ፓወር የሚመሩት ዩኤስኤይድ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለጥፋታቸው የታሰሩትን እንዲፈታና የጥላችን ንግግርንም እንዲገታ ጠይቋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ እርዳታ ከሚያደርጉ መካከል ግንባር ቀደሟ ናት የሚለው መግለጫው በሰሜን ኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው ግጭት ምላሽ ይሆን ዘንድ የ663 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ እርዳታ አሜሪካ ማድረጓን ሳምንታ አስታውሰዋል።

በትግራይ የተቀሰቀሰው ግጭት አንደኛ ዓመቱን የደፈነ ሲሆን ግጭቱ ከትግራይ አልፎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል።

መንግሥት የአማጺያኑ እንቅስቃሴ ለመግታት አቅም ያለው በሙሉ ወደ ጦርነቱ አካባቢ እንዲዘምት ጥሪ በማድረግ ሠራዊቱን እያንቀሳቀሰ ሲሆን አማጺያኑም ግፊታቸውን መቀጠላቸውን እየተናገሩ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁን አጽድቆታል።

Filed in: Amharic