>

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ቀሪ ምስክሮችን  ከኅዳር  6 እስክ 10 /2014 ዓ.ም እንዲያሰማ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጠ...!!! ባልደራስ

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ቀሪ ምስክሮችን  ከኅዳር  6 እስክ 10 /2014 ዓ.ም እንዲያሰማ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጠ…!!!
ባልደራስ

       በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ. ም ዐቃቤ ሕግ አስቀድሞ ከስመዘገባቸው ዘጠኝ ምስክሮች ውስጥ ቀሪ ሦስቱን በተመለከተ ካቀረበው አቤቱታ በተጨማሪ ማንነታቸው ስላልታወቁት ሌሎች 12 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ መቅጠሩ ይታወቃል። ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን አቤቱታ እና በተከሳሽ ጠበቆች በኩል የተሰጠውን ምላሽ አድምጦ በመመርመር  በዛሬው ዕለት ብይን ሰጥቷል።
     በዚህ መሰረት ለ 8ኛ እና 9ኛ  ቀሪ የፌደራል አቃቤ ሕግ ምስክሮች ፍ/ቤቱ መጥሪያ እንዲልክ እና ታመመ የተባለው 4ኛ ምስክር ሳይንሳዊ የህክምና ማስረጃ በማቀረብ መመስከር ይችላል ብሏል።
  የፌደራል አቃቤ ሕግ ከህዳር 6/2014 ዓ.ም እስከ ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ማንነታቸው ያልታወቁትን 12  ምስክሮች እና ቀሪ ሦስት ምስክሮችን ስም ዝርዝር እና ማንነታቸው አስቀድሞ በግልጽ  እንዲቀርብ እና እንዲያስመሰክር ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
     4ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት አስካለ ደምሌ  ከቤተሰብ ጋር የስልክ ግንኙነትን እንዲፈቀድላቸው በትናንትነው ዕለት ያቀረብትን አቤቱታ አስመልክቶ  ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ  ለህዳር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጧዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
     የፌደራል ቀሪ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመሰማት ከ9 ቀናት በኋላ መቀጠሩ የተከሳሾችን በአካል ነፅ የመሆን መብት ስለሚያዘገየው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቀጥል የተከሳሽ ጠበቆች አቤቱታ ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ በቀጣይ ሌላ መዝገብ አለኝ በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል።
      ከዚሁ መዝገብ ጋር በተያያዘ ፤  በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጽ ከችሎት ዘገባ ጋር በተያያዘ በሚለጠፉ ጽሁፋች የሚሰጡ  አስተያየቶች ( Comment )  ላይ በምስክሮች ላይ ዛቻ እና ስድብ እየደረሰ ነው፤በመሆኑም በቀጣይ የሚቀርቡ ምስክሮች ማንነት በሚዲያ እንዳይገለፅ በማለት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን አቤቱታ አስመልክቶ ፍ/ቤቱ ተከታዩን ብይን ሰጥቷል።
    አስተያየት ሰጪዎች በአግባቡ ባልተለዩበት እና የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች መሆናቸውን በግልጽ ስለመታወቁ በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረበ አስረጂ ነገር ባለመኖሩ እና ከዚህ በፊት በተሰጠው ብይን መሰረት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ መሆኑ ፍርድ ቤቱ ገልጿል ።
Filed in: Amharic