>

ጋሼ እና ባለ ወደቧ ጎንደር...!!! ፡ አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ

ጋሼ እና ባለ ወደቧ ጎንደር…!!!

አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ

ከጥቂት አመታት በፊት እኔ እና የተወሰኑ ሀገር ወዳድ ወዳጆቼ ሆነን ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን ፓርቲ ለማቋቋም ተነሳን፡፡
በኛ ብርታት ሳይሆን “ኢትዮጵያ” ብለን ስለተነሳን ብቻ ብዙ ድጋፍ አገኘን፡፡ ከሰሜን እስከደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ ተዘዋውረን ደጋፊ አሰባሰብን፡፡ ኋላ ላይ ትንሽ የተደራጀን ሲመስለን አዲአበባ ካሉ “ኢትዮጵያ” ከሚሉ ፓርቲዎች ጋር ህብረት እንፍጠር አልንና በኔ ግምት አንድ ቀን የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ  ወ/ት ብርቱካንን በነገር ሲሸነቁጡ አይቼ  “ቆፍጣና” ብዬ ካሰብኳቸው አንድ የፓርቲ አመራር ጋር ከአብሮ መስራት አስከ ውህደት ድረስ ለመነጋገር ቀጠሮ ያዝን፡፡
ለመጀመሪያ ቀን የአንድ ለአንድ ግኑኝነት እኔ ኢብንን እንድወክል ተመረጥኩና ወደ እሳቸው ፓርቲ ቢሮ አመራሁ፡፡
ስማቸውን መጥቀስ ስለማልፈለግ ከዚህ በኋላ “ጋሼ” ብለን እንጥራቸው፡፡
ጋሼ እንደነገሩኝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ80ዎቹ ጀምረው ጥርሳቸውን ነቅለዋል፡፡(በርግጥ በስኳር ይመስለኛል የታችኛው ጥርሳቸውም ሁለቱ ተነቅሏል)
ገና እንደደረስኩ ጋሼ ስሜንና ፓርቲዬን እንኳን በደንብ ሳይጠይቁኝ  ያለ ምንም መንደርደርያ  የፖለቲካ ገድላቸውን መተረክ ጀመሩ፡፡
በወያኔ ግዜ ከሚጠቅስላቸው ትላልቅ ገድሎች መካከል ዋናው በአንድ የግል ጋዜጣ የፊት ፔጅ ላይ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ፎቶዋቸው መውጣቱ ብቻ ነበር፡፡(ጋዜጣውንም አጋጣሚ በሚመስል ሁኔታ ጠረጴዛቸው ላይ ጣል አድርገውታል)፡፡
ስለ አይዶሎጂ እና መሰል ነገሮች ያወራነውን ምናልባት” ህይወቴና ፋታ ያልሰጠኝ የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚለው መጽሃፌ  ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ ሎል
ከንግግራችን እንደገባኝ  ጋሼ “ፌዴራሊዝም” የሚል ቃል መስማት እንኳን ያማቸዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ራሱ “የእግር ኳስ አሃዳዊ ጽ/ቤት” ቢባል ደስ ሳይላቸው ይቀራል!?)፡፡
ግን ደግሞ ጋሼ እንደነገሩኝ አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ ስለሆኑ ምናልባት ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ግዴታ ከሆነ በሚል አማራጭ የራሳቸውን መጠባበቂያ መፍትሄ አዘጋጅተዋል፡፡
 “ጂኦግራፊያዊ ፌዴራሊዝም  ስራ ላይ የሚውል  ከሆነ በታሪክና በፖለቲካ ሊቃውንት ተጠንቶ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ካርታ” የሚል አንድ በላስቲክ የተጠቀለለ ዶክመንት ከመሳቢያቸው አወጡና ጠረጴዛው ላይ ዘረጉት፡፡
በእውነቱ አስቀድመው ” የኢትዮጵያ” ባይሉኝ ኖሮ ካርታው የሀገሬ ይሁን የሩስያ  ማወቅ አልችልም ነበር፡፡
በካርታው ሰሜናዊ ክፍል ጋሼ “ጎንደር” ብለው የሰየሙት በሰሜን  ቀይ ባህር የሚያዋስነው ታላቅ ክፍለሀገር አለ፡፡በታች በኩል መጀመሪያ ጅቡቲ የመሰለችኝ ትንሽ ክ/ሀገር ኋላ ላይ በደንብ ጠጋ ብዬ ሳያት “ኤርትራ” የተሰኘች ነቁጥ ክልል ትታያለች፡፡
አሁን ላይ ሳቄ በጣም እያፈነኝ ነው፡፡
..”ጋሼ …ግን ይህ ካርታ ትንሽ ከጎረቤትም ከተቀረው አለምስ  አያጣላንም?!” አልኳቸው…ፈራ ተባ እያልኩ፡፡
“አይ የዛሬ ልጆች ምንም የምታውቁት ነገር ሳይኖር እኮ ነው ዘላችሁ ፖለቲካ ውስጥ የምትገቡት” አሉና …ተቆጡ፡፡
ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ለምን ይህን አይነት አካሄድ መከተል እንዳለብን የኢትዮጵያን ታሪክ ከስሩ ጀምረው እያጣቀሱ አስረዱኝ፡፡ብቻ አሁን ትዝ እንደሚለኝ የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪ የጠቀሱት አጼ ካሌብን ነው መሰለኝ፡፡
…ጋሼ ሲያወሩ  እየሰማሁ እያስመሰልኩ ካርታው ላይ ያደኩባትን አርሲ ለማግኘት በአይኔ ሳማትር ቆየሁ፡፡አርሲ ድሮም ትንሽ ናት በሳቸው ካርታ ያለ አጉሊ መነጽር እርዳታ አትታሰብም፡፡
ኋላ ላይ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡
“….ለምን የፓርቲያችንን የሥራ አስፈጻሚ አባላት አላዝናናቸውም” የሚል …
ሀሳባቸውን ገታ ሲያደርጉ ጠበኩና “ጋሼ ጥሩ ነገር ያነሱት! በቀጣይ ታዲያ ለምን በስራ አስፈጻሚ ደረጃ ሰብሰብ ብለን አንወያይም? ..ሰባት ሰባት ሰው እንምረጥና ሁለተኛውን ስብሰባ እናድርግ ..በዛውም እርስዎም በእኛ ቢሮ ያሁኑን ግሩም ሃሳብ ፕረዘንት አያደርጉልንም?!” አልኳቸው.፡፡
ደነገጡ!
ለመጀመሪያ ጊዜ ኮንፊደንሳቸው ከፊታቸው ላይ ብን ብሎ ሲጠፋ አየሁ፡፡
ከዛ ጋሼ የሞት ሞታቸውን ምን ቢሉ ጥሩ ነው..
“ወንድሜ በዛሬ ጊዜ የሚታመን ሰባት ሰው ከየት ይመጣል ብለህ ነው?!”
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች
Filed in: Amharic