>

ዓብይ አህመድ የኦህዴድ ብልጽግና ስራ አስፈፃሚዎችን ሰብስቦ አስፈራራቸው ....!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ዓብይ አህመድ የኦህዴድ ብልጽግና ስራ አስፈፃሚዎችን ሰብስቦ አስፈራራቸው ….!!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

*…. ለኦነግ ሰራዊትም ሚስጥራዊ መልዕክት ልኳል…!!!
በሌላም በኩል ኦቶ ሌንጮ ለታ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት መሰረቱ ምን እንደሆነ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለው እንደማያምኑም ገልፀዋል።
ዝርዝሩ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሰሞኑን ዓብይ አህመድ የኦህዴድ ብልጽግና ስራ አስፈፃሚዎችን ሰብስቦ ነበር። በስብሰባው ላይ እያንዳንዳቸውን የኦህዴድ ብልጽግና ባለስልጣናት በስም እየጠራ “ምን አየሰራችሁ እንደሆነ እናውቃለን፤ አሁን እያደረጋችሁት ባለው ድርጊት ከፊት ሳይሆን ከጀርባ ነው ካራው የሚያርፍባችሁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። በኦህዴድ ብልፅግና ውስጥ ያለውን እርስ በርስ መጠራጠርና መፋዘዝ በአስቸኳይ እንዲቀለብሱ ትዕዛዝ ሰጥተዋቸዋል። እያንዳንዱ አመራር ፌስቡክ እና ቲውተር ገጹን መጠቀሙን ያቋረጠበት ምክንያት በተናጠል አመራሮቹ እንዲናገሩ በማድረግ ሂሳቸውን እንዲውጡ አድርገዋል። ከዚህ በኋላም ማህበራዊ ድረገጾቻቸውን ያለማቋረጥ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። ሜይን ስትሪም ሚዲያውን ከሽመልስ አብዲሳ ጀምሮ ሁሉም ካድሬዎች እንዲቆጣጠሩት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።  ሕዝቡ ከኦህዴድ ብልጽግና ጋር መሰለፉን ሰላማዊ ሰልፍን ጨምሮ በተለያየ መንገድ እንዲያሳይ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል።
በማስከተል ዓብይ አህመድ መልዕክት የላከው ወደ ኦነግ የፓለቲካና የወታደር ክንፎች ጋር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ዓብይ በመልዕክቱ “ኦሮሞ በብዙ ትግል ቤተመንግስት ገብቷል፤ እንዴት በብዙ የኦሮሞ ልጆች መስዋዕትነት አራት ኪሎን የተቆጣጠረውን ኦሮሞ ለማስወጣት ከፀረ-ኦሮሞ ኃይሎች ጋር ትሰራላችሁ? ስልጣን የምትፈልጉ ከሆነ ባስቸኳይ መጥታችሁ በድርድር ልንከፋፈል እንችላለን” ብሏቸዋል። በአፀፉው ከትላንት ስህተታችን ተምረናል ያለው የኦነግ ሰራዊት ዓብይ አህመድን “ለእኛ የላከውን መልዕክት በአደባባይ ተናገረውና ወደ ድርድር እንገባለን” የሚል ምላሽ ሰጥተውታል። ከህውሃት ጋር ታክቲካል ጥምረት የፈጠረው የኦነግ ሰራዊት ኢትዮጵያን በማፍረስ በኮንፌዴሬሽን ለመተሳሰርና የአዲስ አበባ ባለቤት መሆን ከህውሃት የተገባለት ቃል የልብ ልብ እንደሰጠው ለማወቅ ተችሏል።
በሌላም በኩል የኦሮሞ ፓለቲካ ኃይሎችን በማነጋገር ወደ ስምምነት ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው አቶ ሌንጮ ለታ በተዘዋዋሪ መንገድ አስገራሚ መልስ መስጠታቸውም ለማወቅ ተችሏል። አቶ ሌንጮ በሚዲያ ቀርበው “አይደለም የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች ፣ ኢትዮጵያም ወዴት እየሄደች እንደሆነ ግራ ገብቶኛል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ሌንጮ ለታ አክለውም በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምን አላማ ለማሳካት እንደሆነ ግልፅ እንዳልሆነላቸውና የበፊቶቹ ጦርነት ማሳካት የሚፈልጉት ግልጽ ተልዕኮ እንደነበራቸው ተናግረዋል። ኦቦ ሌንጮ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና አገሪቷን ወዴት መውሰድ እንደሚፈልግ መገንዘብ እንዳልቻሉና በግልፅም ተናግሮ እንደማያውቅ ይፋ አድርገዋል። አቶ ሌንጮ ለታ በማስከተል እንደገለጡት በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለው እንደማያምኑ የገለጹ ሲሆን በአጠቃላይ አገሪቷ ወዴት እየተጓዘች እንደሆነ ማወቅ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
Filed in: Amharic