>

አለን!... ( ዘመድኩን በቀለ)

አለን!…

ዘመድኩን በቀለ


“…ምንም የምነግራችሁ አዲስ ነገር ስለሌለ ነው ጮጋ ያልኩት። ነገር መደጋገም እንዳይሆንብኝም ነው የጠፋሁት። በሚገርም እና በሚደንቅ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የብልፅግና ስልታዊ የጦር ማፈግፈግ ምክንያት ከመቀሌ ሞላሌ ድረስ ስበው ያስገቡት የወራሪው የትግሬ ኃይል ሸዋ ደብረ ብርሃን እስኪገባ እየጠበቅን ያሁነያ እያልን በተጠንቀቅ ቆመን ነው የጠፋነው። ደግሞም ተዘረፈ፣ ተገደለ የሚል ዜና መደጋገሙም ይሰለቻል።

“…ካልተሰበሩ የዐማራ የኢኮኖሚ ከተሞች መካከል ከሰሜኑ ክፍል በምሥራቅ ዐማራ ግዛት በኩል ከወድመት ከቀሩቱ ከተሞች መካካከል ፈንጠር ብሎ ለአዲስ አበባም ቀረብ ብሎ የሚገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ ነው። ከሃገሪቱ ዋና ከተማ ከርዕሰ መዲናዋ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ለሸዋ ዐማራው ደብረ ብርሃን የማኩረፊያ ከተማውም ነው። የመለስ ዜናዊ የፈጠራ ውጤት ለሆነችው “የአዲሲቷ ኦሮሚያም” ድንበርተኛ ጎሮቤት ተደርጎ መሃል ላይ ተሰንቅሮም ኦሮሚያን እንደልቡ እንዳይላወስ ያደረገውም ደብረ ብርሃን ነው። በተለይ የእነ ጃዋር እና የእነ ሽመልስ አብዲሳ፣ የእነ ዐቢይ አሕመድና የእነ ለማ መገርሳ የነውጥ መሣሪያ የነበረው ቄሮ ኦሮሚያ ላይ እሳት ያነድ በነበረ ጊዜ የሞቱት ዐማሮች ሞተው በህይወት የተረፉቱ ጥሪታቸውን ይዘው የሸሹትም ወደ ዚህችው ጥንታዊ የዐማራ ግዛት ወደ ሆነችው ወደ ዘርዓያዕቆብ ርስት ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ነበረ።

“…ደብረ ብርሃን የኦሮሚያን ሰላም ማጣት ተከትሎ ኢንቨስተሮች አይናቸውን የጣሉባት፣ የኢንዱስትሪ ከተማም ወደመሆን ተሸጋግራ ለአላፊ አግዳሚው ሁሉ እዩኝ፣ እዩኝ፣ ግመጡኝም የምትል እና የምታጓጓ የዐማራ የኢንቨስትመንት ከተማም ወደ መሆን ሽግግር የማድረጊያ ወቅት ላይ በመገኘት ከፍ ብላ ለመታየት እየተንጠራራች የነበረች ከተማ ነበረች። ይሄ ነገሯ ግን ለቁማርተኞቹ የኦሮሞ ቦለጢቀኞቻችን እንብዛም ምቾት የሚሰጣቸው ሆኖም አልተገኘም። ደብረ ብርሃን በውስጧ አስተዳደሯን ከወለጋ የመጡ ኦሮሞዎች፣ ኢኮኖሚዋ ደግሞ በትግሬዎች የሚዘወር ቢሆንም አልጠግብ ባዮቹን ሰልቃጮች ይሄም ምቾት አልሰጣቸውም። እናም ደብረ ብርሃንም ልክ እንደ ደሴ፣ እንደ ኮምቦልቻም መድቀቅ፣ እንደሸዋሮቢት እንደወልድያ፣ እንደራያም መውደም አለባት። ለዚህ ደግሞ የእነ ሽመልስ አብዲሳውና የዐቢይ አሕመዱ ኦነግ ሸኔ በአንድ ወገን የእነደብረፂው ህወሓት ሸኔ ደግሞ በአንድ ወገን ሆነው ባለወቀ ሙድ ወደ ደብረ ብርሃን መግባት አለባቸው። DBን ልክ እንደ ሸዋ ሮቢት ማውደምም አለባቸው። ካደቀቁ፣ ካወደሙም ጥንቅቅ አድርጎ ነው ሁሉንም ማውደም እንጂ የምን ቁጥቁጥ ነው? ደግሞም ደስም አይልም።

“…ምንአልባት ከደብረ ብርሃን በኋላ አጅሪት ህወሓት ስምምነታቸውን አፍርሳ፣ አንደዜ ስንትና ስንት መቶ ሺ ልጆቼን ገብሬ እዚህ ድረስ ከመጣሁ በኋላማ አዲስ አበባ ሳልደርስ፣ ግዮን ሁቴል፣ ሂልተን እና ሸራተንማ ሻይ ሳልጠጣ፣ 22 ጎራ ብዬ ማሳጅ ሳልደረግ፣ ቦሌ ገብቼ ማኪያቶ ሳልጠጣ፣ የቺቺንያን ኮቦሌዎች ሳልጎበኝ አልመለስም ብላ ሄጵ ካላለች በቀር ሂዊ ወደ ሰሜን ወሎ ትመለሳለች። የቀረውን የደቀቀ የሸዋ ዐማራ ክፍል በተጠንቀቅ ቆሞ የሚጠብቀው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ይረከበዋል። የደቀቀው ዐማራ በበረታው የኦሮሞ አባ ገዳ አስተዳደር እና ቁጥጥር ስር ይወድቃል የሚል ግምት አለኝ።

“…እደግመዋለሁ ህወሓት መሃላና ስምምነቱን አፍርሳ… ነሸጥ አድርጓት ደብረ ብርሃንን አልፋ ከምር ወደ ሸገር ወደ አዲስ አበባ የምትገሰግስ ከሆነ አጅሬ ብልፅግና ኦነግም መሃላ ስምምነቱን አፍርሶ እርሱም በአፋር በኩል መቀሌ፣ በጎንደርም፣ በሰሜን ወሎም፣ በዋግኽምራም በኩል ወደ ትግራይ ገብቶ ሊያበሳጫት፣ ሊያደበያትም ይችላል። በኤርትራና በኦሮሚያ ሠራዊት የተዘረፈባትን ንብረት ከዐማራ እንደማካካሻ እንድትወስድ ዐቢይ የፈቀደላት ሂዊ አይበቃኝም ብላ “የታላቋን” ኦሮሚያ ሰላም ለማደፍረስ፣ ኢኮኖሚዋንም ለማደናቀፍ የምትሞክር ከሆነ ቁማርተኛው ብልፅግና አሁን የምሩን ይነሣል። እሳትም ይተፋል። ያ ለክፉ ቀን የተቀመጠውም የኦሮሞ ልዩ ኃይልም የሞት ሞቱን ይወራጫል። ዐማራን አደንነው ብለው ሥነ ልቦናውን ለመቅበር መወራጨቱን ይጀምራሉ። አካኪ ዘራፉም ይቀጥላል።

… ይህ ብቻ አይደለም እጅ እግሩን ታስሮ ጦርነትን እንደቋመጠ እያፏሸከ፣ እያዘጋ ድንበር ላይ ተከምሮ ያለውጊያ እንዲቀመጥ የተደረገው የዐማራ ፋኖና፣ የዐማራ ልዩ ኃይሉ፣ ሚኒሻውንም ጭምር የማርያም መንገድ ይሰጠዋል። ስበር፣ ቁረጥም እየተባለ እንዲሰብር ይታዘዛል። ያነክታታልም። ዐቢይ ሳያዘው አልዋጋም ብሎ የተቀመጠው ዐማራም መልሶ በሪሞት ኮንትሮሉ off እስኪያደርገው ድረስ ለጊዜው on አድርጎ ያዋጋዋል። ትንሽ ውዳሴ፣ ትንሽ ፉገራ ብቻ ለዐማራው በቂው ነው።

“…እስከዚያው የሚሆነውን ከዳር ሆኖ ማየት ብቻ ነው። አፋርን በእሳት አጥሮ፣ ወልቃይትን ወፍ ዝር እንዳይል ያደረገው መንግሥት በወሎ በኩል የወሎዬው ዐማራ የተከፋፈለ ፖለቲካ ሰለባ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በመከላከያ ሽሽት እንደሃገር የተሸነፈውን የወሎና የሸዋ ዐማራን ቀሽም አድርጎ የመሣሉ ተግባርም በሚገርም ሁኔታ ሐዲዱን ሳይስት መስመሩን ይዞ መደስኮሩን ቀጥሏል። አፋር በመከላከያ ሙሉ ሜካናይዝድ ጦር፣ በአየርም፣ በምድርም እየተጠበቀ የሚፋለም መሆኑን የማናውቅ ይመስል የአፋር ሚኒሻ ብቻውን በክላሽ ከወያኔ ሜካናይዝድ ጦር ጋር የተዋጋ ይገኛል፣ ተካድን አይል፣ ሴራ አለ አይል፣ መከላከያ ሸሸ አይል፣ ጥይት አለቀበኝ አይል፣ ስንቅ አቀብሉኝ ደጀን ተቋረጠብኝ አይል፣ ብቻውን በጀግንነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በአላህ ችሮታ እየተዋደቀ ነው የሚለውን የብልፅግና ሰበር ዜና ሰባሪ ገሌ አክቲቪስቶቻችን ፉተታም እየሰማን ያሁነያ።

“…ሲፈጥረው አፋር ጀግና ነው። ይሄን ደግሞ ሁሉ የሚያውቀው የማይካድ ሃቅ ነው። ታዲያ አፋር የወያኔን መንጋ ወራሪ ሠራዊት ያቆመው ግን በክላሽ ብቻ ነው የሚለውን ፉገራ እኔ በበኩሌ አልቀበልም። 10 ሺ መንጋ በ10 እና 20 የአፋር ሚኒሻ ተመለሰ፣ ተደመሰሰ የሚለው ሰበካ አይሰራም። በወልቃይትና በአፋር የመከላከያ ሠራዊቱ ምራቅ የዋጠም ነው። ከዚህ ቀደም በአፋር ከወያኔ ጋር የተካሄደውን ውጊያም በቪድዮም አይተነዋል። አፋር ታንክ የለውም። አለቀ። ከአሁኑ “ዐማራ ግን ቀሽም ነው፣ የማይረባ፣ ውጊያም የማይችል አስመስሎ የማውራት የማስወራቱ የፕሮፓጋንዳ ምንጩም ከወዴት እንደሆነም የሚታወቅ ነው።

“…ዓላማው ባይገለፅልኝም የዐቢይ አሕመድን ፎቶና #NOMORE የሚል መፈክር ያነገቡ፣ ባለ ኮኮቡን የወያኔ ባለ አንባሻውን ባንዲራና የዐቢይ አሕመድ መንግሥትም የሚጸየፈውን ንፁሁን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማም የያዙ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን፣ ግልብጥ ብለው ሰልፍ ወጥተው ምዕራባውያንን ሲቃወሙ ውለዋል። ሰልፉንም አቢቹ ” የመደመር ውጤት” ብሎ በፌስቡኩ ላይ ለጥፎታል። ጠለፈው። ኢቢሲን የመሰለ ቀዳዳ ውሸታም ከቤት አስቀምጦ የውጪውን ሲኤንኤንና ቢቢሲን ሲቃወሙም ውለዋል። ሰልፈኞቹ ለአማሪካም ማስጠንቀቂያ ሁሉ ሲሰጧት ውለዋል። ስብስቡ ደስስ ይላል። ወኔውም ደስስ ይላል። በአማሪካ የተከፋውን ዓለም ጃስ ብሎ ለማነሣሣትም ይረዳል። ነገር ግን ወያኔ በሴራ ደብረ ሲና ስትደርስ ዓይቶ ደንግጦ ሰልፍ የወጣን ሰልፈኛ ሁሉ የመደመር ውጤት ተብሎ ከካድሬ እኩል ቆጥሮ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማዋሉ ግን ይደብራል። ከቤት የቀረም ያለ አይመስልም። ለምን ወጣህ ቢባል መልስ የሌለው ሰልፈኛም የትየለሌ ነው። ደግሞም የጨነቀው ሃሌሉያ ባዩም ይበዛል።

“…ለመድገም ያህል ወያኔን ሰይፍ እንጂ ሰልፍ አያስቆማትም። ወያኔ በፀበልም በጩኸትም አትለቅህም። ወያኔ የምትለቀው በነፍጥ ብቻ ነው። ወያኔ አሜሪካ ረድታት ከመቀሌ ሞላሌ ድረስ አልደረሰችም። እንግሊዝ ደግፋት ሸዋሮቢት አልመጣችም። እነ ሲኤንኤንና ሮይተርስ፣ አልጀዚራና ቢቢሲም አዲስ አበባ ዙሪያ ደርሳለች ብለው ፕሮፓጋንዳ ስለሠሩላት እንደተመኙት አዲስ አበባ ዙሪያ አልደረሰችም። አዎ ወያኔ ወሎን አልፋ ሸዋ የገባችው በኦሮሞ ብልጽግና ፀረ ዐማራ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ ፈርጣጭ መከላከያ ስለመደቡ ነው። የጋዜጠኛ መሳይ መኮንን አንጀት አርስ አማላይ ጦማር አንተን ራስህን በራስህ እንድታረካ ካላደረገህ በቀር ወያኔን አያቆማትም። የዐማራ ቴሌቭዥን 5 ጊዜ ክተት ወያኔን አያስቆማትም። ለውጊያ የጠራኸውን ወታደር በቀረርቶ፣ በሽለላ፣ በፉከራ ልቡን ካጠፋኸው በኋላ እንዳይዋጋ ሽባ አድርገህ አስቀምጠህ ወያኔን አታሸንፋትም። ወያኔን እየሮጥክ እየፈረጠጥክ አታስቆማትም። በአዳነች አቤቤ ቀረርቶ፣ በዐቢይ አሕመድ የፌስቡክ ቀደዳም አትቆምም። ወያኔን የፓስተር ወንድሜነህ ዲስኩር የብሔራዊ ትያትር ተረታተረትም አያስቆማትም። ደመሰስናት፣ ረገፈች፣ አፈገፈገች ስላልካትም ወፍ የለም። ዐማራን እንዳይዋጋ ትእዛዝ ሳትሰጠው፣ ሽሽ አምልጥ እያልክ እየሸሸህም ወያኔን አታስቆማትም። በኢቲቪ ዜና፣ በሚዲያ ላይ ቀረርቶና ፉከራም አታስቆማትም። ከወያኔ ይልቅ የዐማራን ፋኖ እየፈራህ ወያኔን አታስቆማትም። እውነቱ ይሄ ነው። ወያኔን የሚያቆማት ዐማራው በራሱ ዕዝ እየተመራ ከፈርጣጩ መከላከያ ስር ወጥቶ እንደ ህዝብ ነቅሎ ወጥቶ ሲገጥማት ብቻ ነው። ከሚፈረጥጥ፣ ከሚሸሽ መከላከያ ስር ተጠግቶ፣ በብአዴን እየተመራ ዐማራ ድልን አይጠብቅ። ከመዋረድ በቀር ጠብ የሚልለትም ነገር የለም። ከመላመዱ ብዛት የተነሣ ድንበር ላይ ከወያኔ ጋር ቡና ተጠራርቶ መጠጣት ብቻ የቀረው የዐማራው ኃይል የዐብይን ትእዛዝ መጠበቁን ትቶ በራሱ ይግጠም። ይሄ አሁንም የማይለወጥ ምክሬ ነው። የዐማራ የፀጥታ እና የደህንነት ኦፕሬሽን ራሱን ችሎ ካልተንቀሳቀሰ የዐማራ ህልውና ያበቃል ብዬ ተስፋ ባልቆርጥም ዋጋ ግን ማስከፈሉ አይቀርም።

• ፋኖ በራሱ አደረጃጀት ብቻ ይመራ።

• የዐማራ ሚሊሻም በራሱ አደረጃጀት ብቻ ይመራ።

• የዐማራ ልዩ ኃይልም በራሱ አደረጃጀት ብቻ ይመራ።   ሦስቱም እየተናበቡ ይደጋገፉ። ጮማ፣ ሰንጋ እያረድ ከኮቾሮ አውጥተህ ማኛ እንጀራ፣ ቁርጥና ቢራ እያበላኸው ደጀን የሆንከው መከላከያ ካልጠበቀህ ያራስህን ዐማራ የሆኑ አደረጃጀቶች ደግፍ። የእስከአሁኑ የዐማራ ኃይልና የመከላከያው በአንድ ዕዝ ሰንሰለት ውስጥ የሥራ ውጤት ካላመጣ ከዚያ ውጣ። ከአላማጣ እስከ ሸዋ ሮቢት ሲሮጥ ተከተለኝ ከሚልህ መከላከያ ተለይተህ በራስህ ሞክር። መከላከያ መሣሪያውን ያስረክብህ። በድሮን መልሶ እንዳይመታህ አስደርገህ በራስህ መክት፣ አንክት።

“…ይኸውልህ አባው የትግራይ መንግሥት ህዝቡን ያምነዋል። በዚህም በዚያም ብሎ ያገኘውን፣ የማረከውን መሣሪያ ሁሉ ለህዝቡ ያድለዋል። ይሄ  ትግሬ መተማመን ነው። ይናበባሉ። የተማመናሉ። ሲጨፈጭፍህ ከርሞ ሲማረክ ሲማረክ እያለቀሰ ተገድጄ ነው። ወደ ውጊያ ከገባሁ ገና ሁለት ቀኔ ነው ነው የሚልህ።

… እዚህ ደግሞ ተመልከት። የፌደራሉን ተወውና፣ በድኑን ብአዴንን ተመልከተው። ቅንጭሩ ብአዴን ህዝቡን አያምነውም። “ከታጠቀ ከድል በኋላ ወደኛ ይዞራል” በሚል ስጋት ፈፅሞ አያምነውም። ከተማው ተከቦ “ኧረ አስታጥቁኝ” እያለ ሲጮህ እያየው፣ በሚዲያ “ገጀራና ዱላ ይዞ ቁርጠኝነቱን አሳየ!” እያለ ያሾፍበታል። ከህዝቡ ማለቅ ይልቅ፣ የነገ ስልጣናቸው ያለመረጋገጡ ዕድል ያሳስባቸዋል። ብአዴን በድን ነው። ህወሓት በለስ ቀንቷት ሥልጣን ብትይዝ እንኳ ምንአልባትም ደመቀ መኮንን ምክትልነቱን፣ አገኘሁ ተሻገር፣ ገዱ አንዳርጋቸውና ላቀ አያሌውም የተላላኪነት ሥፍራ እንደማያጡ ስለሚያስቡ ደንታቸው አይደለም። ዐማራ ከምድ ረ ገጽ ከምን አይጠፋም። ለእነሱ ኬሬዳሽ ነው።

“…በዐማራ ኪሳራ ዐቢይ አሕመድ አዲስ ታሪክ ለማጻፍ ይወራጫል። ዐማራ ግን በድጋሚ ተዘጋጅ። ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ደብረታቦርና ደብረ ማርቆስም በተጠንቀቅ ቁሙ። አማሪካንም አውሮጳንም አትፍሩ፣ አትሸበሩም። ለዐረቡም ልባችሁ አይሸበር። ለኦነግም ለህወሓትም አትሩጡ። ሴራውን ብቻ ተጋፈጡ። እንደህዝብ ውጡ፣ ተፋለሙ ውቀጡ፣ ክተቱ፣ መክቱ፣ አንክቱ። ከማሸነፍ በቀር ሁለተኛም፣ ሦስተኛም ምርጫ እንደሌላችሁ እወቁ። የዳያስጶራን እርጥባን አትጠብቁ። ለራሱ በብዙ እስራት ውስጥ ከሚዳክረው ስደተኛ ብዙም አትጠብቁ። መፍትሄው ነፍጥ ነው። ለመሰደብ፣ ለመዋረድ ዝግጁ አትሁን። ጀምረው። አከተመ።

• ወያኔ ይሸነፋል !!

• ኢትዮጵያም ዐማራም ያሸንፋሉ !!

• ዐቢይ አህመድ አያማልድም !! አያድንህምም !!

• አዚሙ ያልተፋታህ ዐማራ የራስህ ጉዳይ !! … ኬሬዳሽ ‼

… ለነጋላችሁ መልካም ውሎ!  ለመሸባችሁ ደግሞ ደህና እደሩልኝ !!

Filed in: Amharic