>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9244

ተገልጦ ያልተነበበው መፀሐፍ ወደ ማህደሩ ገባ!!!

ኢትዮጵያዊው ሲድኒ ሪሊ አረፈ_!!!
ነጋሪት
• ተገልጦ ያልተነበበው መፀሐፍ ወደ ማህደሩ ገባ!!! 

*…. አምባሳደር ካሳ ከበደ በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል ።
የታጠቅ ጦር ሠፈርን፣ የህፃናት አምባ ፣ የጀግኖች አምባ ፣በማቋቋም ትልቅ ድርሻ አላቸው። የህዝብ ለህዝብ አደይ አበባን የባህል ቡድንን በመምራት የመጨረሻዎቹን ቤተእስራኤላዊያን በማጓጓዝ  ጉልህ ሚና ነበራቸው። ግንቦት19 1983 ዓ_ም ከሀገር የወጡ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የመጨረሻው ባለስልጣን ናቸው።  
የደጃዝማች ከበደ ተሰማና የወ/ሮ ይታጠቁ ኪዳኔ ልጅ፣ የኒታ ኢፍሮኒ ፍቅረኛ፣ የሞሳድ ቅምጥል፣ ካሳ ከበደ (ዶ/ር) አረፈ፣ የተዋጣለት ዲፕሎማት፣ ድንቅ ሰላይ (የደህንነት ባለሙያ)፣ ጉምቱ የፖለቲካ ተንታኝ!!
በሚስጥር የታጨቀው፣ እሱ ራሱ ሚስጥር የሆነ ሰው ላይመለስ ሄደ፣ እስራኤሎቹ “a fascinating, but controversial figure” ብለው የሚገልፁት ካሳ እስከወዲያኛው አሸለበ፣ እንደ መንፈስ ሲረቅብን፣ እንደ ሰው ሲገዝፍብን የኖረው ካሳ ተከተተ፣ ከእንግዲህ አድራሻውን መደበቅ አይቻለውም፣
ተገልጦ ያልተነበበው መፀሐፍ ወደ ማህደሩ ገብቷል፣
ታዋቂው የእስራኤል ጋዜጠኛ ሮነን በርግማን ያለህበት ቦታ ልምጣና ኢንተርቪው ላድርግህ ብሎ የተማፀነው ካሳ፣ ታሪኩ በገናናው “Hebrew Language Daily” ጋዜጣ ላይ በምዕራፍ የተተረከለት ካሳ፣ ለሰሚ ፊልም ወይም ልብወለድ የሚመስል ኑሮ የኖረው ካሳ በ80 ዓመቱ ከዝች አለም በሞት ተለየ፣
በወጣትነት ዘመኑ አለባበስ አሳማሪ ነበር ያባልለታል፣  በሀገረ እስራኤል ተማሪ በነበረበት ወቅት  የእየሩሳሌም ቆነጃጁቶችን ፍጅቷቸዋል ነው የሚሉት አብረው የተማሩ እስራኤላዊያን፣ ካሳ የሚያስተባብለው ክስ አይደለም፣ “እውነት ነው፣ ሴት አውል (naughty) ነበርኩ” ብሎታል ለመርማሪ ጋዜጠኛ ሮነን በርግማን፣ በ60ዋቹ የጥቁርና የነጭ የፍቅር ግንኙነት እንግዳ በነበረበት ጊዜ ሰው ጤፉ ካሳ ቆንጆዋን ኒታን ጉያው ስር ሸጉጦ ፣ ሲጋራውን በቄንጥ እያቦነነ በእየሩሳሌም ጎናዋች ላይ ሲገማሸር በአግራሞት የሚመለከተው ብዙ ነበሩ፣
የሞሳድን inner circle የካሳን ያህል ቀርቦ ያወቀ፣ ጓዳ ጎድጓዳውን እንዲበረብር የተፈቀደለት (የበረበረ) ሌላ የውጭ ዜጋ መኖሩን እጠራጠራለሁ፣
ካሳ ከእስራኤል ትልልቆች ጋር ትከሻ የተጠባጠበ ሰው ነው፣ ይዛክ ሻሚርና ኢሁድ ባረክን ጨምሮ ትልልቅ የጦር ጄነራሎችና ስመ ጥር የደህንነት ባለሙያዋችን በቅርብ ያውቃቸዋል፣ ያውቁታል፣
ዲፕሎማሲና ስለላ በአንድ ላይ ሲመጡ ካሳ ከበደን ይመስላሉ፣ ካሳ ከኢትዮጵያ ሳይወስድባት፣ ለእስራኤል ሳያጎልባት ሚዛን ጠብቆ የኖረ ሰው ነው፣ የደህንነት ሰራውን የሚገራው ዲፕሎማሲው ነው፣ እከኪልኝ-ልከክልሽ ነው መርሁ፣ ራሱን የሚያከብር ይከበራልና እስራኤሎቹም አክብረውታል፣ እንደ ሌሎች ኤጀንቶች ተጠቅመው አልወረወሩትም፣
በአስራ አንደኛው ሰዓት እንደ መሽራ አጅበው ከኢትዮጵያ አስወጥተውታል፣ እስራኤል ሲደርስ ሳምሶናይት ሙሉ ብር ሰጥተውት ሆቴል አቀማጥለውታል፣ በቃኝ ሲል ጄኔቫ ወስደው ከሚስቱ ጋር ቀላቀሉት፣ ጄኔቫ ሰለቸኝ ሲላቸው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ የእስራኤሎች “አማካሪ” ድርጅት ውስጥ ስራ ተገኝቶልሀል ብለው ወደ አሜሪካ አሻገሩት፣
በነገራችን ላይ ካሳ ሚዛን ሲጠብቅ የኖረው በዲፕሎማሲው ጭምር ነው፣ እስራኤል ወዳጅ ነች ብሎ የአረቡን አለም አላስቀየመም፣
ካሳ ከሞሳድ ጋር እያለ የተለያየ ሚስጥራዊ ስም ይጠቀም እንደነበር ቢታመንም ለጊዜው የሚታወቀው “ኬ ሬይኖልድስ” የሚለው ስም ብቻ ነው፣
ህይወቱን ሳይገልፅልን አመለጠ፣ “ንገረን” ስንለው “መፀሐፌ ላይ ታገኙታላችሁ” ነበር መልሱ፣ መፀሐፋ ሊወጣ አንድ ምዕራፍ ቀርቶታል ካለ አመታት ተቆጥረዋል፣ እንዲህ እያለ ነበር ያዘናጋን፣ ይሄኔ አንድ መስመር አልፃፈም፣ You never know!
ነብስ ይማር አምባሳደር (ዶ/ር) ካሳ ከበደ፣ you are truly a legend!!
Filed in: Amharic