>

በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ሶስት ወንድሞች ግድያ  ተጠርጣሪው ኦነግ ወይስ ኦህዴድ ....!?! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ሶስት ወንድሞች ግድያ  ተጠርጣሪው ኦነግ ወይስ ኦህዴድ ….!?!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ

*…. ሸኔ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ 3 ወንድሞችን ጨምሮ 8 ሰላማዊ ሰዎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መግደሉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ….!
 
የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አለማየሁ አቶምሳ ሲኤምሲ የመንግስት ቤት በምኖር ሰዓት ለሁለት ዓመታት ጐረቤቴ ነበር። ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ከስራ መልስ ዘለግ ያለ ጨዋታዎች ነበሩን።
እስከማውቀው ድረስ አለማየሁ ተግባቢ፣ አዳማጭ፣ ፍትሐዊ፣ ለደሃ የሚቆረቆር ሌብነትን የሚጠየፍ፣ ዘራፊዎችን እያሳደደ የሚቀጣ ምርጥ ኦሮሞ/ ኢትዮጵያዊ ነበር። አለማየሁ በተደራጁ ሙሰኞች ላይ በሚወስደው እርምጃ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ምክንያቱም ጠላቶቹ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የተቀመጡ የገዛ ጓደኞቹ ነበር። ዛሬም በስልጣን ላይ እና በአገዛዙ የጡት አባትነት ሹመት ተሰጥቷቸው ዝርፊያውን አጧጡፈውታል።
እናም አለማየሁ አቶምሳ ከተደገሰለት የሞት ድግስ ማምለጥ አልቻለም። በሀይላንድ የውሃ ላስቲክ ውስጥ መርዝ ጨምረው በመስጠት ገደሉት። የአዞ እንባ እያነቡ ቀበሩት። ሁሉም እውነቱን ስለሚያውቅ ትራጄዲው የአደባባይ ምስጢር ሆነ። ቤተሰቦቹም ከከፍተኛ ቅሬታቸው ጋር ኑሮአቸውን መግፋት ጀመሩ።
እነሆ ዛሬ ደግሞ የአለማየሁ አቶምሳ ቤተሰቦች (ሶስት ወንድሞቹን) ኦነግ ጨፈጨፋቸው የሚል የመንግስት ዜና እየተሰማ ነው። ለእኔ ኦነግ ፈፀመው የሚለውን ይሄን ዜና አምኖ ለመቀበል ይከብደኛል። የአለማየሁ አቶምሳ ቤተሰቦች ከፍተኛ ቅሬታና ቁጭት ያላቸው በኦህዴድ ብልጽግና ሰዎች ላይ ስለሆነ! ለጊዜው ዝርዝር መረጃ የለኝም።
 
ሸኔ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ 3 ወንድሞችን ጨምሮ 8 ሰላማዊ ሰዎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መግደሉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ
የሽብር ቡድኑ ይህን ግፍ የፈፀመው በጅማ ዞን ኖኖ ቤንጃ ወረዳ ኮንቺ ቀበሌ ታኅሣሥ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3:30 አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።በአሸባሪው ቡድን የተገደሉት የአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ቤተሰብ አባላት አቶ አደባ አቶምሳ፣ አቶ ቲሊንቲ አቶምሳ እና አቶ ሙላቱ አቶምሳ የተባሉ ወንድሞቻቸው መሆናቸውን የቤንጃ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በሬቻ ተኩ መናገራቸውን ኢቢሲ ኦቢኤንን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግልን ካቀጣጠሉት እና የአሸባሪው ህወሓት ውድቀት እንዲፋጠን ምክንያት ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ይገለጻል።የደረሰብን ኀዘን ከባድ ነው ያሉት አቶ በሬቻ ተኩ፣ ከአቶ ዓለማየሁ ቤተሰብ በተጨማሪ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችም በጭካኔ መገላቸውን እና ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።አሸባሪው ሸኔ የአርሶ አደሩን ሀብት ንብረት ማቃጠሉን እና የተረፈውም ጥቅም ላይ እንዳይውል መበታተኑን ተናግረዋል።
17 የአርሶ አደሮች ቤት በዚሁ ቡድን በመቃጠሉ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።ካቃጠሉት የአርሶ አደሩ ሰብል መካከል 9 ጎተራ በቆሎ እና በርካታ የጤፍ ክምር እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል አስተዳደሩ፣ በሚያሳዝን መልኩ ጥገት ላምን እና ጥጆችን ጨምሮ ወደ በረት አስገብተው አቃጥለዋል ብለዋል።የኖኖ ቤንጃ ወረዳ ነዋሪዎች የአሸባሪውሸኔን ድርጊት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸውም ተገልጿል።
ነብስ ይማር!
Filed in: Amharic