>
5:30 pm - Sunday November 2, 6036

ከቃላት ጮማው በስተጀርባ ያለው ደባ ! (አሥራደው - ከፈረንሳይ)

ከቃላት ጮማው በስተጀርባ ያለው ደባ !

አሥራደው ከፈረንሳይ


የህወሃት ወንጀለኞች፤ እነ ስብሃት ነጋን የፈታው ዓብይ አህመድ፤ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድና ታምራት ነገራን አስሮ በመድረክ ላይ ስለ ይቅርታ ለማውራት የሞራል ብቃት የለውም! መዓዛ መሐመድና ታምራት ነገራ የህሊና እስረኞች ስለሆኑ በአስቸኳይ ይፈቱ !!    

ማስታወሻ

እስክንድር ነጋ፤ አንዷለም አራጌ፤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ በቀለ ገርባ፤ መራራ ጉዲና……ወዘተ: በታሰሩበት ወቅት፤ አታስብ ይሉኛል !  በምትለዋ መጣጥፌ እንደዘከርኳቸው፤ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድና ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ: በዚች ጽሁፌ ይታሰቡልኝ::    

መንደርደዲያ

« La morale est étrangère à la politique qui ne vise que le pouvoir »  Nicolas Machiavel (1469- 1527) Florence (une ville d’Italie)

« ግቡን በስልጣን ላይ ለመቆየት ብቻ ያደረገ የመንግሥት ፖለቲካ፤ ለሞራል ብቃት ወይም ለስነ ልቦና ልዕልና እንግዳ ነው፤ (አይጨነቅም) » ኒኮላ ማኪያቬል  *በሰረዝ ያለው እኔ  የጨመርኩት 

በማክያቬል መሠሪ ጽንሰ ሃሳብ፤ 

የአንድ መንግሥት የሥልጣን ዕድሜ ሊቆይ የሚችለው፤ 

  1. « በጥንቃቄ  የተያዘ  የደህንነት የስለላ (ሰኩሪቲ) መረብ »
  2. « በጦር ሃይል : (በሰለጠነ የሰው ሃይልና በመሣሪያ ትጥቅ ክምችቱ ነው ይለንና፤ »

አንድ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን ማራዘም ከፈለገ በነዚህ ሁለት ዘዴዎች መጠቀም አለበት ሲል እንዲህ ያብራራል::

  1. « በጥንቃቄ » የሚለውን ሲተነትን፤ ሁሉንም ወገን፤ የራሱን ተከታዮች ሳይቀር በጥርጣሬና በዓይነ ቁራኛ የሚጠብቅበት፤ የደህንነት የስለላ (ሰኩሪቲ) መረብ በመዘርጋት፤ ሳይቀድሙት ቀድሞ መበተን፤ ተቃዋሚዎችን ሰርጎ በመግባት ቦርቡሮ ማዳከምና ማምከን ::
  2. በጦር ሃይል (በመሣሪያ ትጥቅ) የሚለውን ደግሞ፤ መንግሥት ሥልጣኑን የሚያስጠብቅበት፤ ጠንካራ የጦር ሃይል መገንባትና፤ እስከ አፍንጫው አስታጥቆ፤ ሳይቀድሙት ቀድሞ ተቀናቃኞቹን መበተን ወይም መደምሰስ አለበት ይለናል::

የአገዛዝ ዘዴዎቹን ሲያብራራ ደግሞ፤

  1. ከተቻለና ለሥልጣኑ የማያሰጋ ሆኖ ካገኘው፤ የሰው ልጆች የስልጣኔ ውጤት በሆነው በህግ የበላይነት ለመግዛት መሞከር::
  2. ካልተቻለው ደግሞ፤ የሰው ልጆች እንሰሳዊ ጠባይ በሆነው፤ ህዝብን በማስፈራራትና በማሸበር፤ በሃይልና በጭካኔ ረግጦ መግዛት ይለናል:: ይህም አምባ ገነን አገዛዝ መሆን የሚለውን ይጠቁመናል::

*(በሰረዝ ያለው እኔ የጨመርኩት መሆኑ ይታወቅልኝ) ::

1469 እ.ኤ.አ በፍሎረንስ በመሃል ጣሊያን ተወልዶ በ1527 የሞተው ኒኮላ ማክያቬል፤

የሚታወቅባቸው ባህርያት: በተንኮል፤በውሸት፤ በከሃዲነቱና ነገሮችን በማሳከር፤ በማታለል ወይም በማጭበርበር፤ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚሯሯጥ ግለሰብ እንደነበር ነው:: ለዚህ ነው እስከ ዛሬ ድረስ፤ ከላይ የተጠቀሱትን ገጸ ባህርያት የተላበሱ ሰዎችን፤ ማክያቬሊክ እያልን የምንጠራቸው:: እንግዲህ አብይ አህመድ የማክያቬል አድናቂ ከሆነ፤ ከሚጠቀምባቸው ጽንሰ ሃሳቦችና ምግባሮች በመነሳት፤ ዓብይ አህመድን የምትመለከቱበት መነጥራችሁን እራሳችሁ ፈልጉ:: እግረ መንገዳችሁንም « ሥልጣንና መንበር  » የምትለዋን መጽሐፉን ፈልጋችሁ ስታነቡ፤ ማን መሆኑን በደንብ ትረዳላችሁ::

እልፍ ብላችሁ ደግሞ ( Confuise and convince ) « በማምታታትና  በማሳመን  »  እንዲሁም « የሰበሩንን  ሰብረናቸዋል » የሚሉትን የሽመልስ አብዲሳ ድንፋታዎች ስትጨምሩበት፤ ቢያንገጫግጫችሁም ጉዟችን ረጅም በመሆኑ፤ ዳግም ላለመውደቅና ላለመርሳት ሲባል፤ ለመንገድ ስንቅነት ሸከፍ አርጓቸው:: መርሳትን የመሰለ አስጠቂ ነገር ሕዝባችን በመላመዱ፤ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግዷል፤ ከንግዲህ ሊያበቃ ይገባል::

በመንደርደሪያዬ ስለ ማክያቬል ይህን ያህል ማለቴ፤ ስለ አገራችን ጉዳይ፤ በህወሃት የ27 ዓመታት የፋሽስት ዘመን አገዛዝ እንዳደረኩትና፤ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት 3 ዓመታት ወዲህ በህዝባችን ላይ የሚፈጸሙትን ኢፍትሃዊ ድርጊቶች፤ እንዲታረሙ ለማመላከት በመሆኑ አብረን እንቆይ::

መግቢያ  

አምባ ገነኖች በሚመሩት አገር ውስጥ፤ የህግ የበላይነት የለም፤ የሰውን ልጅ ጧት እንደ ጥጃ ያስሩና  የበሉት ክትፎና የጠጡት ውስኪ ባገሳቸው ወቅት፤ ወይም ሲያቃዣቸው ካደረ፤ በነጋታው ተፈተሃል ይሉታል:: ለምን ? ብሎ ሲጠይቅ፤ ከድንቁርናቸው ብዛት፤ ለማሰራቸውም ሆነ ለመፍታታቸው የሚሰጡት በቂ መልስ የላቸውም:: የእስክንድር ነጋንና የባልደረቦቹን እስርና ፍቺ  ትታችሁ፤ የነ ስብሃት ነጋን ከእስር መፈታት፤ አብይ አህመድም ጭምር ስለማያውቀው ሲሰማ በጣም መደንገጡን ነግሮናል:: ይች ናት ጫወታ! ህዝብን መናቅ ይሏችኋል ይች ናት!! እንግዲህ « አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው! » እንዲሉ መሆኑ ነው::

በዘረኞች ዕሳቤ የሞራል ብቃት ባለመኖሩ፤ የሰው ልጅ ሰብዕና በዋልጌዎች ይደፈራል፤ የሚታሰበው በአይምሮ ሳይሆን በጠብ መንጃ አፈ ሙዝ በመሆኑ የመፍትሄ ሃሳብ ከአይምሯቸው አይፈልቅም:: በበታችነት ስነ ልቦና በመለከፋቸው፤  ቂም ቋጥረው: ዘወትር ብቀላን እንጂ ይቅርታን አያውቁም፤ የጋራ እሳቤን (Collective thinking) በማዳበር አብሮ ማደግን ሳይሆን፤ የዘርና የጎሣ ግንብ ገንብተው ለብቻቸው መቀጨጭን ይመርጣሉ ::

ለእኔ ብቻ የሚል ስስት ስለተጠናወታቸው፤ የተለያዩ ብሔር፤ ብሔረሰቦችን መጎናጎንና አብሮነትን አጥብቀው ይፈሩታል:: እዚህ ላይ የሁንዱማ ኬኛ ( ሁሉም ነገር የእኛ ነው) ተረኞች ነን ባዮች: የኦህዴድ/ኦነግ ጥምር (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ስብስቦችን መጥቀሱ በቂ ነው ::

አለማወቃቸውን ስለማያውቁ፤ ከመማር ይልቅ ዘወትር መኮፈስን ይመርጣሉ፤ እጅግ አስከፊው ነገር በያዙት የነጠፈ አይምሮ፤ አገር ካልመራን እያሉ፤ ጦር በመስበቅ አገር ማውደማቸው፤ ህዝብ ማስጨረሳቸውና ማፈናቀላቸው፤ የአገር ሃብት ማውደማቸው: አልበቃ ብሎ እንደነሱው አይምሮው የነጠፈ ትውልድ በማፍራት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመግደል ይሯሯጣሉ:: 

ኢትዮጵያዊነት: አባቶቻችን በረገፈው አፅማቸው ቋሚና ማገር አዋቅረው፤ በፈሰሰው ደማቸው ለውሰው፤ በጅማታቸው አንድ አድርገው አስረውና በፈረሰው ሥጋቸው ለስነው፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማችንን ከፍ አድርገው በማውለብለብ ያስረከቡን፤ ለማንም፤ በምንም፤ መቼም፤ የማንደራደርባት የቃልኪዳን አገራችን መሆኗን እኛም በተራችን ቢመራችሁም አንዴ ሳይሆን ደግማችሁ ደጋግማችሁ ዋጡት እንላችኋለን:: 

እዚህ ላይ ምንሊክንና አደዋን እንድናስታውሳችሁ ምናባችን የግድ ይለናል:: ለወገኖቼ! የአገራችን ጉዳይ ልብ እንደሚያቆስል ይገባኛል፤ እስቲ ይችን ማስፈንጠሪያ በመጫን፤ የአጅጋየሁ ሽባባውን አድዋ የሚለውን ሙዚቃ እያዳመጣችሁ ጥቂት ዘና በሉ::   https://www.youtube.com/watch?v=Yc3vsW-2jWA

የአምባ ገነን ሥርዓት ሲሰፍን፤ የአገር ሃብት ለህዝብ ደህንነት፤ ለዕድገት፤ ለትምህርት መስፋፋት፤ ለህክምና፤ ለቴክኖሎጂና ለምርምር መዋሉ ቀርቶ፤ ለአንባ ገነኖች ጥበቃና መዝናኛ፤ ዝርፊያና ንቅዘት (ሙስና) ስለሚውል፤ ህዝብ በድህነት ይማቅቃል፤ በሽታ ይስፋፋል፤ የኑሮ ውድነት ህዝቡን ይለበልባል፤ የትምህርት (የዕውቀት) ደረጃው ስለሚያቆለቁል፤ አገሪቱ የምታፈራቸውን ወጣቶች፤ የአይምሮ ሰንካላ በማድረግ፤ የማሰብ፤ የመመራመርና የመጠየቅ አድማሳቸውን በመገደብ፤ ብኩን፤ ደካማ፤ ዘወትር አጎንባሽና እሺ ባይ ብቻ አድርጎ ያስቀራል:: 

በህወሃትና አሁን በኦህዴድ/ኦነግ ጥምር (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ዘመናት በዩኒቨርስቲ ደረጃ ተማሪዎች ሆነው፤ ሆዳቸው ከሞላ የአገር ጉዳይ የማይቆረቁራቸው ከመሆኑም በላይ፤ በዘርና በጎሣ እየተቧደኑ የሚፋለጡትን መጥቀሱ በቂ ነው::

የአብይ አህመድ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ አገር ከማጥፋቱ በፊት፤ ለአገራችንና ለህዝባችን ዘብ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው! ይህ ሰው ስንት ጊዜ ያታለን? ስንት ጊዜ ይክዳን? ስንት ጊዜ ከአንጀቱ ሳይሆን፤ ለመደለያ ብቻ: ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያለ ይቀልድብን?! 

አብይ አህመድ: ከታጠረበት የዘርና የጎሣ ግንብ ውስት ወጥቶ፤ ህብረ ብሔራዊና አገራዊ አንድነት እስካልፈጠረ ድረስ፤ በምንም መስፈርት የምንሊክን ስም ለመጥራትና፤ የአድዋን ጦርነት ድል በምሳሌነት ለመጥቀስ፤ የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም፤ የለውምም:: 

ከአሁን በኋላ ከአፍ ጮማው በስተጀርባ ያለውን ደባ በተጨባጭ እያየን ስለሆነ፤ ለእሱ የሚታለል ሰው ካለ: በእውነት ጤንነቱን እንዲመረመር ይመከራል::  

ዋልጌና: አፈ ዘረጦ የነበረው መለስ ዜናዊ፤ ዘወትር በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ እያለ: ጣቶቹን እንደ እንትን ቀስሮ፤ ዓይኖቹን እንደ ተናካሽ ውሻ እያጉረጠረጠና፤ በመቀመጫው ላይ እንደ ነገረኛ አሮጊት እየተቁነጠነጠ፤ ስድ በሆኑ ቃላት:

« የአዲስ አበባ ቦዘኔዎች: ባንክ ሲዘርፉ ያዝናቸው፤ የአድዋ ድል ለደቡቡ ምኑ ነው፤ አማራውን ዳግም እንዳያንሰራራ ቅስሙን ሰብረናል፤ ወርቅ ከሆነው ከትግራይ ህዝብ በመወለዴ እኮራለሁ » ….ወዘተ  ብሎን እንደነበር አንዘጋም:: በመጨረሻም « በሙስና በክተናል » የምትለዋን ዕውነት ብቻ ተናግሮ፤ እመራታለሁ የሚላትን አገር በስሟ ሳይጠራት፤ በደፈናው ይች አገር! እያለ እንዳንጓጠጣት ወደ መቃብር ወርዷል::  

መለስ ዘናዊን እንደ ጣኦት እያመለከ ያደገው፤ ዓብይ አህመድ፤ ልክ እንደ አሰልጣኙ መለስ ዜናዊ፤ የቴሊቪዥን መስኮትን አዘወትሮ በመጠቀም፤« እነዚያኑ በሙስና የበከቱ፤ ዘራፊና አዘራፊዎች ጓደኞቹን ደምሮና ደማምሮ » በድግግምና አሰልቺ፤ በሆነ ንግግሩ: ሲመቸው እየተቁነጠነጠና እየደነፋ፤ ሲጨንቀው: እየተለማመጠና እየተቅለሰለሰ፤ ነገሮችን በማሳከርና በማዘናጋት፤ ብዙ ወገኖቻችንን፤ አደንዝዟል እልፍም ብሎ አጃጅሏል:: 

የሰሞኑን የዲያስፖራ ተብዬ፤ ወደ አገር ቤት ገብቶ የ 90% (ዘጠና ፐርሰንት) እረጥ እንበጥ፤ አጎንባሽነትና አጨብጫቢነት፤ ስንመለከት፤ ዲያስፖራው: ወደ ሰለጠነው ዓለም ሄዶ፤ ሆዱን ብቻ እየመገበ፤ ዓይምሮውን ግን እያስራበ፤ የሚኖር መሆኑን፤ በተግባር ባየናቸው ጉዳዮች መታዘብ ችለናል:: (ይህ ትዝብት በሃቅ የአገራቸውና የወገኖቻቸው ችግር አሳስቧቸው ያቅማቸውን ዕርዳታ ለማድረግ ወደ አገር ቤት የመጡ ዲያስፖራዎችን አይመለከትም) እነሱም ቢሆኑ አገር ቤት ባዩትና፤ በዓብይ አህመድ የፖለቲካ ሸፍጥ፤ አንጀታቸው ተልጦ እንደተመለሱ አልጠራጠርም:: *(የ % የፐርሰንቱ ቀመር በዓብይ አህመድ የተሠራ መሆኑን አንባቢ እንዲረዳልኝ እሻለሁ) :: 

አብይ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ፤ ባገኛቸው አጋጣሚዎች በሙሉ፤ ከልቡ ሳይሆን ከአንገት በላይ፤ በአፍ ብቻ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! እያለ ህዝቡን በማጃጃል፤ ከመጋረጃ በስተጀርባ፤ በዘርና በጎሣ ግንብ ተከልሎ፤ የኦህዴድ/ኦነግ (ኢህአዴግ ቁጥር 2) አጀንዳውን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም ይኸው 4ኛ ዓመቱን ይዟል:: በአንጻሩ ኢትዮጵያችን: በየዕለቱ እንደ ሳሙና እየሟሟች፤ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው መጤ እየተባሉ በመፈናቀል ስደተኞች፤ ረሃብተኞችና እርዳታ ጠባቂዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል :: 

የማኪያቬል አድናቂው አብይ፤ በማክያቬል ጽንሰ ሃሳብና ድርጊት፤ ለራሱ ሥልጣንና፤ እወግነዋለሁ ለሚለው ዘርና ጎሣ የተረኝነት አባዜ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ማኪያቬሊያዊ የሆነ ሥራውን እየከወነ፤ ከአሰልጣኙ ከመለስ ዜናዊ በወረሳት ዘዴ ደግሞ፤ በተደጋጋሚ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ እያለ፤ በኢትዮጵያውያን ፊት የአዞ ዕንባውን ያነባል::

ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ፤ አብይ አህመድ ለ27 ዓመታት የህወሃት አገልጋይ በመሆን፤ ህዝባችንን በወህኒ ቤት አብሮ ያጎረ፤ ያሰቃየ፤ እንዲሰደዱ ያደረገ፤ በዕርዳታና በብድር የተገኘን ገንዘብ፤ ከዘራፊዎች ጋር አብሮ አገራችንን በማዘረፍ፤ ገና በማህጸን ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ሦስት ትውልድ ያህል፤ ዕዳ ከፋይ ያደረገ ሰው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ትግል፤ እሱንና የህወሃት አሽከሮች የነበሩትን ኦህዴድ፤ ኦነግ፤ ብአዴንና ደህዴን….ወዘተ ጨምሮ ከወያኔ ባርነት ነፃ አውጥቶ ለዚህ ያበቃቸው፤ የህዝብ ትግል መሆኑን ዘንግተውታል::

አብይ አህመድ በጦርነት ያለቁ ወገኖቻችን ደም ሳይደርቅ፤ ስብሃት ነጋን ከእስር በመፍታት፤ የህወሃት (TPLF) ጀሌዎች ከበሮ እየደለቁ እንዲጨፍሩ የገና ስጦታውን ያበረከተላቸው ሲሆን፤ በህወሃት ጦር ልጆቻቸው በጦር ሜዳ በወደቁ ቤተሰቦች፤ አባቶቻቸውን በጦር ሜዳ በተነጠቁ ህፃናት፤ ባሎቻቸውን በጦር ሜዳ ባጡ ሴቶች፤ ንብረታቸው በወደመ ዜጎቻችን፤ ቤታቸውና ሰብላቸው በእሳት በጋየ ገበሬዎች፤ ከሚኖሩበት ተፈናቅለው ያለ መጠለያ በቀሩት ወገኖቻችን የልብ ቁስል ውስጥ እንጨት ሳይሆን የጋለ ብረት እንደ ሰደደበት ይሰማናል::

በተከፈተው ጦርነት፤ በየ ጦር ግንባሩ ያለቁ ወገኖቻችን፤ ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን፤ ወያኔ በወሎ፤ በጎንደር፤ በጎጃምና በሸዋ፤ የዘረፈውና ያወደማቸው ት/ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ የግብርና መሳሪያዎች፤ የምርት እህል….ወዘተ. ለአብይ አህመድና ለመሰሎቹ በይሁንታ የተያዙ ዕቅዶቻቸው አካል በመሆኑ ብዙም አያስጨንቃቸው::

ይህ ዓይኑን በጨው የታጠበ ሰውዬ፤ ምንም ዓይነት ሃፍረት ስላልፈጠረበት፤ ከህወሃት ጋር በድብቅ የዶለተውን የአገር ክህደት፤ ቢመራችሁም ዋጡት: እያለ ያላግጥብን ይዟል:: እሱ ማን ስለሆነ ነው ለእኛ የመረረ ኮሶ ጋች የሚሆነው?! ሕዝብ አብይን ካልፈለገው አሽቀንጥሮ ይጥለዋል እንጂ፤ እሱ ህዝብን መራራ ኮሶ የሚግትበት መብት ማን ሰጠው?!

አሱ የበጠበጠውን የመረረ የፖለቲካ ኮሶ፤ አሱ እራሱ ይጋተዋል እንጂ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጋትበት ምንም ምክንያት አይኖርም:: 

አብይ አህመድ: ውስን በሆነ የማስታወስ ችሎታው፤ ( short memory) ለዚህ ያበቃውን የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እረስቶ፤ ዛሬ ተመልሶ የህወሃት ባርያ መሆን ካማረው፤ እሱና መሰሎቹ በቀድሞ ጌቶቻቸው፤ በህወሃት እግር ስር እየተንከባለሉ ይለምኑ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም የህወሃት ባሪያ ላለመሆን፤ ከፈጣሪው ጋር ቃል ለምድርና ለሰማይ ገብቷል !! 

ማሳረጊያ

ባሳለፍናቸው የ27 ዓመታት ዝምታ፤ ለ27 ዓመታት ዝርፊያ፤ የ27 ዓመታት ፍርሃት ለ27 ዓመታት ውርደት ፤ የ27 ዓመታት እበላ ባይነት፤ ለ27 ዓመታት የብዙ ወገኖቻችን በረሃብ ማለቅ፤ የ27 ዓመታት ሆዳምነት፤ ለ27 ዓመታት ሽንፈት፤ የ27 ዓመታት መደንዘዝ  (being passive)፤ ለ27 ዓመታት አገር የለሽ መሆን፤ የ27 ዓመታት ቅጥ ያጣ ትዕግሥት፤ የ27 ዓመታት ባርነትን አጎናጽፎን አልፏል::

አሁን ደግሞ፤ በአብይ አህመድ ዘመን፤

3 ዓመታት ድለላ፤ የ 3 ዓመታት ቅጥፈትና ውሽት፤ የ 3 ዓመታት ማጭበርበር፤ የ 3 ዓመታት ሰበካ፤ የ 3 ዓመታት የጀርባ ማከክ፤ የ 3 ዓመታት የፖለቲካ ቁማር፤ ያተረፍነው ነገር ቢኖር፤

3 ዓመታት እስርና እንግልት፤ ለ 3 ዓመታት ስደት፤ ለ 3 ዓመታት ዝርፊያ፤ ለ 3 ዓመታት የወገኖቻችን ዕልቂት፤ ለ 3 ዓመታት የወገኖቻችን መፈናቀል፤ ለ 3 ዓመታት የወገኖቻችን በኑሮ ውድነት መለብለብ፤ አሁን ደሞ ይባስ ብሎ ጦርነት እንጂ ምንም የመጣ ለውጥ የለም::  

  • በዚህ የ30 ዓመታት ቆይታ፤ አምባ ገነን ገዢዎች፤ ሁለት ጊዜ ጦርነት በመክፈት የብዙ ወገኖቻችን ህይወት እንዲቀጠፍ፤ ብዙዎች የአካል ጉዳተኞች እንዲሆኑ፤ ብዙ የአገር ሃብት እንዲወድም፤ እጅግ ቁጥሩ የበዛ ህዝብ እንዲፈናቀል ምክንያት ሆነዋል::
  • ላለቁት ወገኖቻችን ተጠያቂዎቹ፤ መለስ ዜናዊና አሽከሩ አብይ አህመድ ከነ ተከታዮቻቸው ናቸው ::
  • አገራችን ባሳለፍናቸው 30 ዓመታት ለተዘረፈችው ሃብት፤ ተጠያቂዎቹ ህወሃትና የአብይ አህመድ፤ የኦህዴድ/ኦነግ/ብአዴን (ኢህአዴግ ቁጥር 2) እና ተከታዮቻቸው ናቸው ::
  • 30 ዓመታት ጥላቻን እየጋቱ ላመከኑት አንድ ትውልድ ጠያቂዎቹ ህወሃትና የአብይ አህመድ፤ የኦህዴድ/ኦነግ/ብአዴን (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ከነ ተከታዮቻቸው ናቸው ::
  • ለ30 ዓመታት ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን ተጠያቂዎቹ: ህወሃትና የአብይ አህመድ፤ የኦህዴድ/ኦነግ/ብአዴን (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ከነ ተከታዮቻቸው ናቸው ::
  • ለወደሙት፤ ትምህርት ቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ ክሊኒኮችና፤ የአገርና የወገን ሃብት፤ተጠያቂዎች ህወሃትና የአብይ አህመድ፤ የኦህዴድ/ኦነግ/ብአዴን (ኢህአዴግ ቁጥር 2) እና ተከታዮቻቸው ናቸው ::

በመጨረሻም፤

  • ፈራጁ አብይ አህመድ ብቻ ስለሆነ፤ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ባለመኖሩ፤ ፍርድ ቤቶች በሙሉ ይዘጉ !
  • በአገር ጉዳይ ሁሉንም ውሳኔዎች ወሳኙ፤ አብይ አህመድ ብቻ በመሆኑ፤ ፓርላማው ሥራ ስለሌለው ይበተን !
  • አብይ አህመድ ለደረሰበት የፖለቲካ ክስረት፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን፤ ማወናበጃ ማድረጉን በአስቸኳይ ያቁም!
  • በኦህዴድ ሙርጥ የሚኩራራው፤ ጃንደረባው ብአዴን፤ ከአማራው ህዝብ ትከሻ ላይ ይውረድ !
  • ባላለቀ ጦርነት፤ « ድህረ ጦርነት በሚል የአጭበርባሪዎች ደባ » ፋኖንና የአማራውን ሃይል ለመበተን የሚደረገውን ሸፍጥ፤ ህዝብ ሊያወግዝ፤ ብሎም በዓይነ ቁራኛ ሊጠብቅ ይገባል !! 
  • የገጠር ፖለቲከኞችንና፤ ቀበጥ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮችን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ቅብጠታቸውን ማስቆም አለበት !! 
  • የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ አስተሳሰባቸው ዳፍንታም በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ በተማሩና አርቀው በሚያስተውሉ፤ ብቃት ባላቸው፤ የሰለጠነና የሰከነ የፖለቲካ አቅጣጫ በሚቀይሱ ልጆቿ ትመራ (ትተዳደር) !!!

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!

Filed in: Amharic