>

የዘውድ ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል! (ግዛቸው ጥሩነህ (ዶ/ር))

የዘውድ ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል!

 

ግዛቸው ጥሩነህ (/)


ከአንድ አመት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው የእርስበርስ ጦርነት፤ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይዎታቸውን ከማጣታቸውም በላይ፤ እጅግ በጣም ከፍ ያለ የንብረት፤ የትምህርት ተቋማት፤ ሆስፒታሎች፤ ክሊኒኮች፤ ፋብሪካዎችና የመንግስት መስሪያቤቶች ውድመት ተከትሏል፡፡ በዚህም ጦርነት፤ ለህሊና የሚዘገንኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከመታየታቸውም በላይ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ህዝቦች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህንንም በማስተዋል፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገራዊ ምክክር እንደሚደረግ እቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ እኔም ለዚህ ድንቅ አላማ ይረዳል ብዬ የማስበውን ሀሳብ ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ይኧውም ስላምንና አንድነትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምጣት የሚረዳው፤ የሰለሞናዊው ንጉሣዊ ስርአት ይመለስ የሚል ነው፡፡  ከንግሥት ማክዳ ከንጉሥ ሰለሞን ግዜ እንደተጀመረ የሚነገርለት፤ ከዚያም በጥንታዊው የዳሞት (ዳማት) መንግሥት እንደቀጠለ የሚታሰበውና በኋላም በትግራይና በሸዋ ግዛቶች ውስጥ ገንኖ የነበረው የሰለሞናዊው ስርዎመንግሥት፤ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አንድ አካል ሆኖ የኖረ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊና እስከቅርብ ግዜ

ድረስ ስልጣን ላይ የነበረው የዘውድ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ ቢመለስ፤ የሀገሪቱን አንድነትና የህዝቦቿን ህብረት ማጠናከር ይችላል፡፡

የዲሞክራሲ ምሁር የሆነው ሲይመር ማርቲን ሊፕሰት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1959 . ሲጽፍ፤ በአለም ላይ በወቅቱ ከነበሩት 12 ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ፤ አስሩ በህገመንግስታዊ ዘውድ ስርአት የሚመሩ እንደነበሩና ከነዚህም ውስጥ እንደ ታላቋ ብሪታኒያ፤ ሆላንድ፤ ስዊድን፤ ኖርዌና ዴንማርክ እንደሚገኙባቸው አትቷል፡፡ በሊፕሰት አስተሳሰብ፤ እነዚህ ሀገሮች አዲስ የመሰረቱትን የዲሞክራሲ ስርአት በህዝብ እንዲደገፍና እንዲታቀፍ የረዳቸው፤ ህገመንግስታዊ የሆነ የዘውድ ስርአት እንዲኖራቸው በመወሰናቸው ነው፡፡ ህገመንግስታዊው የዘውድ ስርአት፤ በተለይም መሳፍንቱ፤ ባላባቱ፤ የቤተክህነት ሰዎችና ሌሎችም ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ቡድኖች፤ ዲሞክራሲን እንዳይፈሩና እንዲያቅፉት ገፋፍቷቸዋል፡፡ በሊፕሰት ግምት፤ የዲሞክራሲያዊው ስርአት ደግሞ፤ ወግ አጥባቂ ቡድኖችንና እንደ ሰራተኛ፤ የገንዘብ ከበርቴና ምሁራን ያሉትን ለውጥ ፈላጊ (ፕሮግሬሲቭ) አካሎች፤ በመካከላቸው ትብብርና መቻቻል እንዲኖር ረድቷቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ግን፤ የዘውዱ ስርአት 1966 . በተነሳው አብዮት ምክንያት ወድቋል፡፡ አብዮቱ ሊፈነዳ የቻለው፤ የቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ወቅታዊ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች ለማምጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ እንደ መሳፍንቱና የመሬት ከበርቴ ያሉት ወግ አጥባቂ ቡድኖችም በተለያዩ ምክንያቶች ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ጠፍተዋል ወይም ተዳክመዋል፡፡ ንብረታቸውም በደርግ መንግስት ተወርሷል፡፡ በፈረንሳይ (1789) በሩሲያ (1917) በቻይና (1911) በመሳሰሉት ሀገሮች የተካሄዱት አብዮቶችም፤ ለነበሩት የዘውድ ነገስታት መውደቅ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ወድቆ ይቀራል ለማለት ያዳግታል፡፡ አርኖልድ ቶይንቢ የተባለው ምሁር እንደጻፈው፤ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ልዩ የሚያደርጓት ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ፤ በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ያልወደቀች አፍሪካዊ ሀገር እሷ ብቻ ናት፡፡ ሁለተኛ፤ የሰሜንና የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች 7ተኛው ክፍለዘመን የእስልምና ሃይማኖት ተቀባይ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖቷን ይዛ የቀረች ሀገር ናት፡፡ ቶይንቢ ባለው ላይ ለመጨመር፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት በዛግዌ ስርዎመንግስት ተሸንፎ 11ኛው እስከ 13ተኛው ክፍለዘመን ተዳክሞ ከቆየ በኋላ፤ 1262 . ወደ ስልጣን ተመልሷል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ግዜም የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት 68 አመታት ቢቋረጥም፤ 1845 . ጀምሮ በአፄ ቴዎድሮስ፤ በአፄ ዮሃንስና በአፄ ምኒልክ ጥረት ስልጣኑን ተቀዳጅቷል፡፡ ታዲያ ታሪክ ራሱን ደጋግሞ፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት እንደገና እንዲመለስ ያደርግ ይሆን? ሺህ አመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሚዛናዊ ክብደቱ አይሎና የብዙ ኢትዮጵያውያንን ፍላጎትና ዝንባሌ አሳድጎ፤ የዘውዱን ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲመለስ ያደርገው ይሆን?

የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ከሆነ፤ የዘውዱ ስርአት ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ መቋቋም ይችላል፡፡ ህገመንግስታዊ ያልሆነ የዘውድ ስርአት ግን ግዜ ያለፈበት በመሆኑ ተመልሶ የመምጣት እድል  አይኖረውም፡፡ የህገመንግስታዊው ዘውድ ስርአት ዋናው ሃላፊነት፤ ነገስታቱ የኢትዮጵያ አንድነትና ባህል ምልክት እንዲሆኑ ነው፡፡ የዘውድ ስርአቱ፤ ዘመናዊ ከሆኑት የሰውልጅ እኩልነትና ግለሰባዊ ነጻነት (ወይም ዲሞክራሲ) ጋር መሄድ የሚችለው፤ ህገመንግስታዊ ሲሆንና ቀን በቀን ከሚካሄደው የፖለቲካ ስራ ራሱን ማግለል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ህገመንግስታዊ የዘውድ ስርአት፤ ንጉሥ እንጂ ንጉሠነገስት አያስፈልገውም፡፡ ንጉሠነገስት የሚለው ቃል የሚያመለክተው፤ በንጉሠነገስቱ ስር ያሉ ንጉሦች በሀገሪቱ ውስጥ እንዳሉ ነው፡፡

በርግጥ የዘውድ ስርአቱን መመለስ የማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ መገመት አያስቸግርም፡፡ ለምሳሌ እኒህ ግለሰቦች፤ የዘውድ ስርአቱ ግዜ ያለፈበት ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ፈንድቶ፤ 1966 እስከ 1983 . የተካሄደውን ለውጥ ሲያዩና ከአብዮቱም በኋላ የተቋቋሙትን የሪፓብሊክ መንግስታት ሲያስቡ፤ የዘውድ ስርአቱን መመለስ ላይደግፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን 1966 . ጀምሮ የተካሄደውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ታሪክ ስናይ፤ ሪፓብሊኳ ኢትዮጵያ ብዙ ችግር እንደደረሰባት፤ እንዲያውም የሚያሳዝን ስቃይ ውስጥ የወደቀች መሆኑን ማጤን እንችላለን፡፡ በደርግ ግዜ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ አልቋል፡፡ የሀገሪቱ የወደፊት ንብረትና አለኝታ ይሆናል ተብሎ የታሰበው የተማረው ህዝብ ተጨፍጭፏል፡፡ በኢህአዴግም ሆነ በአሁኑ የብልጽግና ፓርቲ ግዜ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነት አዳጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ የዘርና የክልል ፖለቲካ፤ ከኢትዮጵያዊነት በላይ እየታየ በመምጣት ላይ ነው፡፡

በተጨማሪም እንደ ኦሮሞ ካሉ ብሄረሰቦች የተወለዱ አንዳንድ ግለሰቦች፤ ሰለሞናዊው የዘውድ ስርአት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ባህል የሚወክል አይደለም ሊሉ ይችላሉ፡፡ በርግጥ ሰለሞናዊው ስርዎመንግስት፤ በመካከለኛው ሰሜንና በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙት የአምሀራና የትግሬ ብሄረሰቦች ባህል ጋር ተሳስሮ የመጣና ያደገ ነው፡፡ ይህም ሆኖ፤ ሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ከዛሬ 300 አመታት አካባቢ ከነገሱት ከአፄ እያሱ (17231747) ዘመነመንግስት ጀምሮ ከኦሮሞ ብሄረሰብ ጋር ተዋልዷል፡፡ የአፄ እያሱ ባለቤት ኦሮሞ ስለነበሩ፤ ልጃቸው አፄ እዮአስ (1747-1761) ግማሽ ኦሮሞ ነበሩ፡፡ በቅርብ ግዜ የሆነውን ብናይ፤ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእናታቸው፤ እቴጌ መነን አስፋው በእናታቸው ኦሮሞነት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልዕልት ሰብለ ደስታም፤ ኦሮሞውን ደጃዝማች ካሳ ወልደማሪያምን አግብተው ልጆች ወልደዋል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ልዑል ሳህለሥላሴም፤ ኦሮሞዋን ልዕልት ማጽንተ ሃብተማርያምን አግብተው ነበር፡፡ የአሁኑም የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት ፕሬዘዳንት፤ ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ፤ የልዕልት ማጽንተ ሃብተማርያምና የልዑል ሳህለሥላሴ ልጅ ናቸው፡፡ ባጭሩ፤ የኦሮሞ ህዝብ የሰለሞናዊውን ስርዎመንግስት የራሱ አድርጎ የመቁጠር መብት አለው ማለት ነው፡፡ ዳነልድ ለቪን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1974 . በጻፈው መጽሃፉ በትክክል እንዳስቀመጠው፤ ኢትዮጵያ በግዜ ብዛት የብዙ ብሄረሰቦች ቅልቅል እየሆነች የመጣች ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ሂደትና ባህላዊ ውህደት ትልቅ አስተዋጾ አድርጓል፡፡

ሌላው ደግሞ፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ነገሥታት ሃይማኖት ክርስትና መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የእስልምና ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን፤ የዘውድ ስርአቱን መመለስ ሊደግፉ ይችላሉ ዎይ? በርግጥ የሰለሞናዊው ነገስታትና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የእስልምና ተከታይ ብሄረሰቦች፤ 13ተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ፤ ግጭትም ሰላማዊ ግንኙነትም እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ በአፄ አምደጽዮን (1297-1327) ዘመነመንግስት፤ የአዳል ህዝብ መብቱን ለማስከበር ወደኋላ እንደማይል ንጉሠነገስቱ ሲረዱ፤ ለዚህ ኩሩ ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር መብቱን እንደጠበቁለት ይነገራል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከአለቅሳንደሪያ ጳጳስ እንዲመጣላት በጠየቀች ቁጥር፤ የግብጽ ሱልጣኖች የኢትዮጵያን ነገስታት በሀገራቸው ውስጥ ያለውን የእስልምና ተከታይ የሃይማኖት መብት እንዲጠብቁ ይጠይቋቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ነገስታትም ቃላቸውን ይጠብቁ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከሁሉም በላይ፤ በኢትዮጵያ ክርስትያኖችና እስላሞች መካከል በተለይም 20ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ይህ ነው ለማለት በቀላሉ የማይቻል፤ የመቻቻልና የመከባበር ባህል በመካከላቸው ለመኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ግን የዘውድ ስርአቱን መመለስ፤ የእስልምና ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሚደግፉት በወቅቱ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ አንድ ነገር ግን ይታወቅ፡፡ የዘውድ ስርአቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሶ ሊቋቋም የሚችለው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሙሉ የሃይማኖት ነጻነት መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡

እንግዲህ / ጌታቸው መካሻ 1983 . በኢትዮጵያን ሪቪው መጽሄት ውስጥ በእንግሊዝኛ ያሳተሙትን ጽሁፍ ልጥቀስ፡፡ በዚህ አርቆ አስተዋይነት ላይ በተመረኮዘ የጽሁፋቸው ርእስ (እውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ መምጣቱን በቅርብ እንረዳለን) ከደርግ ውድቀት በኋላ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ ከተፈለገ፤ የዘውድ ስርአቱ መመለስ አለበት ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን የዶ/ ጌታቸውን ምክር በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ሰዎች አልተቀበሉትም፡፡ አሁንም ቢሆን የኒህን ምሁር ምክር ለመቀበል ግዜ አለ፡፡

ሰለሞናዊው የዘውድ ስርአት ቢመለስ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ንብረት እንጂ ጉዳት አምጪ ተቋም አይሆንም፡፡ ነገስታቱ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት አጠናካሪ አካልና አባታዊ ምስል ሆነው ሁሉንም የሀገሪቱ ብሄረሰቦች ማገልገል ይችላሉ፡፡ የባህልና የታሪክ ምልክቶችና አካሎች በመሆን፤ ነገስታቱ በሀገሪቱ ውስጥ በመዳከም ላይ ያለውን የመተማመን፤ የመከባበርና የመቻቻል ባህሪዎች እንደገና እንዲዳብሩ ይረዳሉ፡፡ ነገስታቱ፤ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ስርአት ህዝቡ ድጋፍ እንዲሰጥ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ህገመንግስታዊ የዘውድ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋቋመ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የጠነከረ ዲሞክራሲ ይሰፍናል፡፡

 

 ይህ ጽሁፍ 20082011 2014. በእንግሊዝኛ ቋናቋ በኢትዮጵያ ማህበራዊ መጽሄቶች ካሳተምኩት የተተረጎመና የተሻሻለ እንደዚሁም የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ የዳሰሰ ነው፡፡ የእንግሊዝኛውን ጽሁፌን ለማንበብ ወይም የተጠቀምኩባቸውን የዋቢ ጽሁፎች ለማየት ከፈለጉ በሚከተለው ርእስ ያገኙታል [An Institution That Can Unite All Ethiopians].

Filed in: Amharic