>

" 'ጌታቸው ረዳ ሒሳብ እናወራርዳለን' ብሏል... ደረሰኙ ያለው ፋኖ ጋ ነው....!!!"  (ፋኒት ሮማን ገዛኸኝ )

” ‘ጌታቸው ረዳ ሒሳብ እናወራርዳለን’ ብሏል… ደረሰኙ ያለው ፋኖ ጋ ነው….!!!” 
ፋኒት ሮማን ገዛኸኝ 

*….  “ፋኖ ፖለቲከኛ አይደለም። ሥልጣን አይፈልግም። አንድ ነገር ግን ይፈልጋል። የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ሰላም መጠበቅ….!!!
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ልዑክ ቡድን ዛሬ ሰኞ ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ሸዋ ሮቢት ከተማ ገብቷል። የአማራ ፋኖ በይፋት ወታደራዊ አቀባበል ያደረገለት ሲሆን የሸዋ ሮቢት ከተማ ኗሪዎችም በስታዲየም ተገኝተው የፋኖ መሪዎች፣ የባልደራስ ልዑክ አባላትና የአቀባበል ዝግጅቱ አስተባባሪዎች ያደረጉትን ሕዝባዊ ንግግር ታድመዋል። ንግግሮቹ በአመዛኙ ወታደራዊ ማነቃቂያዎች፣ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች እና የታሪክ ትንተናዎች ናቸው። መርሃ ግብሩ የተጀመረው የአማራ ብሔርተኝነት አባት፣ የቀድሞው የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) መስራችና መሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መስራች፣ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐኪም . . .  ለነበሩት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና ባለፉት 30 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሲታገሉ ለተሰው አማሮች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎት በማድረግ ነው።
“ጌታቸው ረዳ ‘ከአማራ ጋር ሒሳብ አወራርዳለሁ’ ብሏል። ደረሰኙ ያለው ፋኖ ጋ ነው። ደረሰኙን እስከምንሰጠው የአማራ ‘ክልላዊ’ መንግሥት እንዳይልፈሰፈስ። የሚልፈሰፈስ ከሆነ ግን ወንበሩን ይልቀቅ” ብለዋል የአቀባበል ዝግጅቱ አስተባባሪ ፋኒት ሮማን ገዛኸኝ።
የአማራ ፋኖ-በይፋት ለልዑክ ቡድኑ መሪ አቶ እስክንድር ነጋ የፊታውራሪ አስማረ ዳኘን ምስል በክብር አዘጋጅቶ ሸልሟቸዋል። ፊትከውራሪ አስማረ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በተለይም ሰው በላውን የትግራይ ወራሪዎች ስርዓት በነፍጣቸው ሲታገሉ የኖሩ የአማራ አርበኛ ናቸው።
ፋኖ እስክንድርን ጨምሮ ለባልደራስ ልዑክ አባላት ማለትም ለአቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ለወ/ሮ አስቴር ስዩም (ቀለብ)፣ ለወ/ሪት አስካለ ደምሌ፣ ለወ/ሪት ዘባባ ኢብራሒም ነጭ የሸማ ጋቢ ሸልሟቸዋል። በተጨማሪም የአቀባበል ዝግጅቱን ለአስተባበሩት  ደራሲ አሰግድ መኮንን ይኸውን ጋቢ ሸልሟቸዋል።
አቶ እስክንድር ነጋ “ትክክለኛ አላማ ያልያዘውን ጎበዝ ተዋጊ ጀብደኛ ነው የምንለው። ጀግና አንለውም። አንድ ጀግና ጀግና ለመባል ለትክክለኛ ዓላማ መቆም አለበት። በዚህ አግባብ ፋኖ ጀግና ነው” ብለዋል። 11 ዓመት ከመንፈቅ በግፍ መታሰራቸውን ያስታወሱት አቶ እስክንድር ከእሳቸው ይልቅ ፋኖ በአንድ አመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ያበረከተው አስተዋፅዖ እንደሚበልጥ ገልፀዋል።
“ሀገራችን ውስጥ ብዙ ችግር አለ። በጥቅሉ ግን በሁለት ይከፈላል። የፖለቲካ ችግርና የሀገር ህልውና ችግር። ወደ እዚህ የመጣነው የኢትዮጵያን የሕልውና ችግር አስቀድመን ነው። አሁን ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ የሆነው ሕወሓት ነው። ሌሎች ፍላጎት አላቸው፤ ነገር ግን ለጊዜው ስጋት አይደሉም” በማለትም አብራርተዋል።
ሕወሓት የአንድ መንደር ስብስብ መሆኑን የገለፁት አቶ እስክንድር
” ‘አደዋ ላይ ኢንዱስትሪ፤ ማይጨው ላይ እስር ቤት ተገንብቷል’ የሚል ተቃውሞ አሁንም አለ። የእንደርታውን፣ የአጋሜውን ጥያቄም ካየን በርካታ ነው። ሕወሓት እንኳን ለኢትዮጵያ ለራሱ ለትግራይም አይጠቅምም” ብለዋል።
በትግል ላይ በነበረበት ወቅት ‘የአንድ ቤተሰብ ስብስብ ነው’ በሚል ተቃውሞ ተነስቶበት የነበረው ወያኔ ለመፍረስም ጫፍ ደርሶ ነበር። ህልውናውን ያስቀጠለው ጥያቄ አቅራቢዎችን በመረሸን እና ከፊሉንም ከድርጅቱ በማባረር ሲሆን ዋነኛው ደግሞ ‘አማራ ጠላትህ ነው’ የሚለው ፕሮፖጋንዳው መሆኑን አቶ እስክንድር ተንትነዋል።
 “ሥልጣን ሲይዝም ያን መንደርተኝነቱን ይዞ ነው የቀጠለው። ሕወሓት ከተደመሰሰ በኋላ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሌላው ተገንጣንይ ሁሉ ተስፋ ይቆርጣል” ሲሉ ጨምረዋል።
የባልደራስ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊና የልዑኩ አባል አቶ ስንታየሁ ቸኮል ‘አለን’ የሚለው የፋኖ መፈክር ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ‘አለን! አለን!’ እያልን በተግባር ማሳየት እንደሚገባም አሳስበዋል።
 “ከአማራ ሕዝብ በመፈጠራችን ልንኮራ ይገባናል” ያሉት አቶ ስንታየሁ
“ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሕይዎት ሰጥተው ሀገር አስረክበውናል። አሳምነው ፅጌ ሕይዎት ሰጥተው ኢትዮጵያን አስረክበውናል።
ዘጠኙን ጥያቸው ከልጄ ከይታገሱ ጎን እቆማለሁ ብለው የተሰውት የእሸቴ ሞገስ የመንፈስ አስቀጣዮች ነን። የተሰውበት ቦታ ላይ ሄደን አፈሩን ጨብጠን በማምጣት አደራውን እንቀበላለን” ብለዋል። በዚሁ መሰረትም ልዑኩ ነገ ማለዳ ጀግናው አርበኛ እሸቴ ሞገስ እና ልጃቸው ይታገሱ ሞገስ ወደ ተሰውበት ስፍራ ሳላይሽ ያቀናል።
የአማራ ፋኖ-በይፋት ዋና መሪ ጀግናው አርበኛ መከታው ማሞ
የይፋት ፋኖ ብዙ ውጣ ውረዶችን አማለፉን ገልፀዋል። “የትግራይ ወራሪ ሲጨንቀው እንጂ ይፋት ገብቶ እንደማይወጣ ያውቀዋል። በደጃዝማች ከበደ ርገጤ በሚመራ የአርበኞች ጦር ጣሊያንም የተደመሰሰበት ቦታ ነው። በምንም ተዓምር በወያኔ ተሸንፈን ታሪካችንን ልናበላሽ አንችልም” ብለዋል አርበኛው።
በተጨማሪም የአቀባበል ስነ ስርዓቱ አስተባባሪ አንጋፋው ደራሲ አሰግድ መኮንን “ፋኖ ፖለቲከኛ አይደለም። ሥልጣን አይፈልግም። አንድ ነገር ግን ይፈልጋል። የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ሰላም መጠበቅ፤” ብለዋል።
ሌላኛው የፋኖ መሪ ሻለቃ እንዳላማው ወርቅነህ ከሸዋ ሮቢት እስከ ራያ ቆቦ ዘምተው መዋጋታየውን ተናግረዋል። እስከ መጨረሻው ተከትለው ጠላትን ለማጥፋት ቢሞክሩም መንግሥት መከልከሉን እና መመለሳቸውን ገልፀዋል። የባልደራስ ልዑክ ሰራዊቱን በመጎብኘቱም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ምስጋናውን የተጋሩት ደራሲ አሰግድ በበኩላቸው “እስክንድርን የማውቀው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ነው። የመጀመሪያውን ጋዜጣውን ሲያሳትም የሚያከፋፍለውም ራሱ ነበርና ሲያከፋፍል ወያኔዎች እጁን ሰብረውታል። ከዚያ በኋላም የግድያ ሙከራዎች ተደርገውበታል። ‘እንግደልህ’ እያሉት ያልሞተ ሰው ነው። በእርሱ ፊት ዛሬ እንዲህ በመገኘቴ ደስ ብሎኛል” ብለዋል።
በተጨማሪም
“እስክንድር በሳምንት ውስጥ ሦስት ጋዜጦች ያዘጋጅ ነበር። ሳተናው፣ ምኒልክና አስኳል። ፅሁፉን ሌሎች ፅፈውታል እንኳን ቢባል አርትኦት መሥራት አለበት። እዚህ ውስጥ ስንቶቻችሁ ናችሁ በሳምንት 10 ገፅ መፅሐፍ የምታነቡት?
እስክንድር ፖለቲከኛ ብቻ አይደለም። ምሁርም ነው።
ይሄን ጭንቅላት ነው ወያኔ ስታስረው የኖረችው። የሚገርመው ግን ይሄ ጭንቅላት ዛሬም ይሠራል” ብለዋል።
ፋኖ ከወያኔ ጋር ሲፋለም ብዙ ምሽጎችን መስበሩን ያስታፈሱት የባልደራስ ልዑክ አባሏ ወ/ሮ አስቴር ስዩም (ቀለብ) ፋኖ በጀግንነቱ ሊኮራ እንደሚገባ ገልፀዋል።
“ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣች ጊዜ አርበኞች እንደየ እምነታቸው ፈጣሪን ነዝንዘውታል። በነፍጣቸውም ጠላትን ጠዝጥዘውታል።
ፋኖን ለመከፋፈል የምትነሱ የውስጥ ባንዳዎችም ሆናችሁ ሌሎች እጃችሁን ከፋኖ አንሱልን” ሲሉም ጨምረዋል።
ሌላኛዋ የልዑኩ አባል ወ/ሪት አስካለ ደምሌ አማራ ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ አለመሆኑን ገልፀዋል። “እናንተ የእምየ ምኒልክ ልጆች ፈርጦች ናችሁ። የእምየ ምኒልክን እና የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ታሪክ እንደምታድሱ አልጠራጠርም” በማለትም ተስፋቸውን ገልፀዋል።
ወ/ሪት ዘቢባ ኢብራሒም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ለሚፋለሙ ፋኖዎች ያላቸውን ክብር ገልፀዋል።
ጌጥዬ ያለው (ከሸዋ ሮቢት)
Filed in: Amharic