>

ጂጂ አታውቅም....!!!   (መስከረም አበራ)

ጂጂ አታውቅም….!!! 

 መስከረም አበራ

ምን ያክል እንደምንወዳት አታውቅም!
.
አንድ ቀን ልክ እንደ ሌላ ቀን እህቷ ደወለችላት። አነሳችው። “ጂጂ ሰው ባንቺ ፍቅር አብዷል” አለቻት። ጂጂ እየሳቀች መለሰች…”ለመሆኑ ግን ጂጂ የምትባል ዘፋኝ እንዳለች ያውቃሉ?” hell yeah ሁሉም ለሷ ፍቅር መስጠት የጀመረው በጣሞ ዘግይቶ ነው። ጎድተናትም ይሆናል።
:
:
ጂጂ ጀማሪ ሁና አታውቅም
.
አዲስ ድምፃዊ ሁና በሀገሪቱ ትላልቅ በሚባሉ የዜማና የግጥም ደራሲዎች በርካታ ሙዚቃዎችን እንድትሰራ ተጋብዛ ነበረ። እንደ ጀማሪ ሙዚቀኛ አልተስገበገበችም። ግራም አልተጋባችም። ያመጡትን አዳመጠችላቸው። ቆም ብላም አሰበች። እናም እንዲህ አለቻቸው “እነዚህ ዘፈኖች በጣም ሀሪፍ ዘፈኖች ናቸው። ደስ ይላሉ። ነገር ግን የኔ ቀለም አይደሉም” ..እውነት ነው ይችን ልጅ አማተር ብሎ ከመጥራት የባሰ ምንም ነውር የለም። ያደረገችው ነገር እንዲሆን ያቺ ሰው የግድ ጂጂ መሆን ነበረባት። የጀማሪዎች ችግር ቀለማቸውን አለማወቅ ነው።
:
:
ጂጂ ንቃን አታውቅም!
.
የጥበብ ሰዎች ለኛ ያላቸውን ክብር የምለካው በሚሰሩት ስራ ነው። ጂጂ በፍፁም ልቧ ታከብረናለች ለማለት ሥራዎቿን ማዬት በቂ ነው። አዎ ከአንድ ኢትዮጲያ እስከ ጉራማይሌ፤ ከአድዋ እስከ አባይ፤ ከናፈቀኝ እስከ ጉዴ ፈላ፤ ከባለዋሽንቱ እስከ ካህኔ ድረስ ንቃን አታውቅም። እሷም ስትናገር “ሙዚቃ ለህዝብ የምሰጠው ውዱ ስጦታዬ ነው። ለምትወጂው ህዝብ ደግሞ የማትወጂውን ነገር አትሰጭውም” ትላለች ጂጂ በእያንዳንዱ የሙዚቃዋ ሰከንዶች እያከበረችን ነው የሰራችው።
:
:
ጂጂ ምን ያክል ጥሩ እንደሆነች አታውቅም!
.
የሷን ድምፅ፡ ሮፍናን ሰብስቦ እንደሚሰራቸው የድምፅ ቅንብሮች እግዜር፣ አላህ፣ ጦሳ፣ ዋቃ ተሰብስበው እንደቀመሙት አታውቅም። ጭራሽ ደምህን ስታፈላው “እኔ የምሰራውን ቅላፄኮ ቀላል ነው። የትኛዋም ድምፃዊ ልትሰራው ትችላለች” ትልሀለች
:
:
ጂጂ ጥበብን በድላ አታውቅም።
.
ከልቧ ስለምትሰራ ጥበብ አኩርፋት አታውቅም። ተወነች ተሸለመች። ዘፈነች ተሸለመች። እሷን ተዋናይ “እንበልሽ ዘፋኝ?” ብለህ ስትጠይቃት ደግሞ “ሰዓሊ ነኝ” ብላ ትንግርት ትሆንብሀለች የጥበብ መንደር ውስጥ ገብተህ እሷ ያልደቀሰችበት ቦታ አታገኝም። ራሷን ለጥበብ አድምታ ነው የኖረችው። ጥበብን አቀማጠለቻት እንጂ አልሸቀለችባትም። እና እንዳልኳችሁ ነው… ምናልባት ጥበብ ጂጂን በድላ ይሆናል እንጂ ጂጂ ጥበብን በድላ አታውቅም።
:
ከሁሉም በላይ ግን..
:
:
ጂጂ መንደሬ ሁና አታውቅም
.
እሷ አድዋን ስታቀነቅነው ለምን ይመሰልሀል አጥንትህን የሚቀጠቅጥ…ቅስምህን የሚሰብር ስሜት የሚሰማህ? ምክኒያቱም ዘፈኑን የምትጀምረው “የሰው ልጅ ክቡር…ሰው መሆን ክቡር” ብላ ነው። በዚያ ስልት ስታንጎራጉረው ላንተ ሲል የረገፈው የሬሳ መዓት ከፊትህ ተከምሮ ይታይሀል። አደራ አለብኝ ትላለህ። አየህ እሷ የሰበከችህ ከኢትዮጲያዊነትም የዘለለ ነገር ነው። እሷ የነገረችህ ስለ አርበኞቻችን ብቻ ሳይሆን ሰውነት እና ነፃነት ስላላቸው ዘላለማዊ ግመዳም ጭምር ነው። yeah she was never been መንደሬ!!
:
ጂጂ ለኔ ዘፋኝ አይደለችም ዘፋኞች ናት። የሀገሬ ልጅ አይደለችም ሀገሬ ናት። እንኳንም ተወለድሽልኝ…እንኳን ደህና ሁነሽ አየንሽ!! ሁሌም እወድሻለሁ🖤
Filed in: Amharic