>

ለሰላማዊ ዜጎች ጥያቄ ጥይት መፍትሄ አይሆንም! [ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ]

በባህርዳር ከተማ ለዘመናት የእምነት ቦታ ሆኖ ለአምልኮ አገልግሎት ሲውል የነበረ የህዝብ ይዞታ በማያውቁትና ባልመከሩበት ሁኔታ ባለሀብት እንዲያለማው በከተማው መስተዳድር ተሰጥቷል መባሉን ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች ባዶ እጃቸውን ሆነው በሰላማዊ መንገድ ባሰሙት የተቃውሞ ድምጽ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን በወሰደው ዘግናኝና አሰቃቂ በጥይት የታገዘ የኃይል እርምጃ እስካሁን የአምስት ንፁኃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ አዛውንት እማሆይንና አካል ጉዳተኛ ጨምሮ በርካቶችን በማቁሰል የአካል ማጉደል ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ የኃይል እርምጃ በምንም መለኪያና ሁኔታ፣ ባለሥልጣናት ጥያቄው ያስከትላል ብለው የቱንም ታሳቢ ቢያደርጉ የህግም ሆነ የሞራል መከራከሪያ ሊቀርብለት የማይችል ህገወጥና ኃላፊነት የጎደለው ‹‹መንግሥት ነኝ›› ከሚል አካል የማይጠበቅ ዘግናኝ የአረመኔ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የከተማ ልማትም ሆነ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ህዝብን በማሳመን በህዝብ ተቀባይነት ካላገኘና ለህዝብ ጥቅም ካልሆነ ለማን እንደሚሆን ያልገባቸው እብሪተኛ ባለሥልጣናት ፍርኃትና ሥጋት ወለድ አምባገነናዊ እርምጃ ነው፡፡ በመሆኑም የኃይል እርምጃው እስከዛሬ ‹‹ይህ መንግሥት የማን ነው፣ የቆመውስ ለማን ነው?›› ለሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄ ‹‹የሥልጣኑና ለሥልጣኑ ብ ›› መሆኑን በግልጽ ያሳየበትና በህገ አራዊት ስለመመራቱ የማያሻማ ምላሽ የሰጠበት በመሆኑ ትብብራችን እርምጃውን አበክሮ ያወግዛል፡፡ የተወሰደው እርምጃ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በሰጡ ባለሥልጣናትና እርምጃ በወሰዱት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲከፈል ይጠይቃል፣ ለተፈጻሚነቱም ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ጎን በመቆም ይታገላል፡፡

ይህ አምባገነናዊና የጭካኔ እርምጃ በቅርቡ ህዳር 27/07 ዓ.ም በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ ለሠላማዊ ሠልፍ የወጡ የትብብራችን አባላትና ደጋፊዎች ላይ የተወሰደውን ዘግናኝ የኃይል እርምጃ፣ በየጊዜውና በተለያዩ ቦታዎች በተናጠል ለተደረጉ ሠላማዊ የህዝብ ተቃውሞዎችና ጥያቄዎች (የሙስሊሙ ማኅበረሰብ፣ የኦሮሞ ተማሪዎች፣…) ላይ ገዢው ፓርቲ/መንግሥት የተጠቀመውን ተመሳሳይ የኃይል እርምጃ፣ በፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ በነጻው ፕሬስ አባላት፣… በሽብር ሥም በፈጠራ ወንጀል የፈጸመውን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዜጎች ላይ ‹‹በከፋፍለህ ግዛ›› ስልት እያሳደረ ያለውን የማስፈራሪያ ተግባራት ያስታውሰናል፡፡

በዚህ መሠረት የዚህ እርምጃ ግልጽ መልዕክት ኢትዮጵያዊያን እኔ ፖለቲከኛ ወይም የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ አባል አይደለሁም፣ እኔ ሙስሊም ወይም ክርስቲያን አይደለሁም፣ እኔ አማራ ወይም ኦሮሞ፣ የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ አባል አይደለሁም፣ እኔ ተማሪ፣ መምህር፣ የመንግስት ሠራተኛ ወይም ነጋዴ፣ … ከዚህ ከዚያ ማኅበረሰብ ክፍል አይደለሁም፣… አይደለሁምና ጥያቄውና ትግሉ አይመለከተኝም በሚል የወር ተራችንን ከመጠበቅ እንድንላቀቅና ይህን አምገነናዊ ሥርዓት ለማስወገድ በአንድነት ቆመን በጽናት ለመታገል እንድንነሳ ወቅቱ መሆኑን፤ በተናጠል በየተራ በህገ ወጥ እርምጃ የሚደርስብንን በአንድነት ቆመን እስካልመከትን በየተራ የያንዳንዳችንን በር ማንኳኳቱ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ዓይነቱ የኃይል እርምጃ እየከፋና እየተስፋፋ፣ ጭቆናው እየከፋና የህዝብ ብሶት እየጨመረ ሲሄድና ከማናችንም ቁጥጥር ውጪ ሲሆን በአገራችን የሚያስከትለውን ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ኢኮኖሚያዊ ውድመትና ማኅበራዊ ትርምስ ቀድሞ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም፡-
1ኛ/ ገዢው ፓርቲ የተያያዘው የአፈና መንገድ ለጥያቄዎች መልስ ሊሆን ወይም ትግሉን ሊያቆም እንደማይችል በቅርቡ ከታየው ያለፈው ጁምኣ የቤኒ መስጂድ የሙስሊሞች ተቃውሞ ስልትና አተገባበር ተረድቶ ቆም ብሎ እንዲያስብና ለህዝብ ጥያቄዎች ጆሮውን፣ ለህዝብ ብሶት ልቡን ፣ለመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለህግ የበላይነት በሩን እንዲከፍት፤
2ኛ/ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የእያንዳንዱ በር እስኪንኳኳ ሳንጠብቅ ይህን ዓይነቱን ኢ-ህገመንግሥታዊና አረመኔያዊ እርምጃ በአንድነት ቆመን እንድናወግዘውና እንድንታገለው፤
3ኛ/ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የአገርና ህዝብ ጉዳይ የበላይና ቀዳሚ ስለሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከትብብራችን ጋር በጋራ ለመስራት ትብብሩን እንድትቀላቀሉ፤ ጥሪያችንን እያቀረብን፤

በእኛ በኩል ትግሉ የሚጠይቀው ዋጋ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ከዓላማችን ሳናፈገፍግ ይህን አምባገነናዊ ሥርዓት በመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች እስኪመለሱ ድረስ የተያያዝነውን የጋራ ትግል አጠናክረን ለመቀጠል የገባነውን ቃል እንጠብቃለን!

በዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው ህገወጥ አረመኔያዊ እርምጃ እስከሚያበቃ የጋራ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!!

ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ

Filed in: Amharic