>
5:13 pm - Friday April 18, 8104

"የአብይ ሚኒስትሮች የሃሰት ሪፖርት እና ኮፒ - ፔስት ቀጥሏል - በጣም ያሳፍራል...!!!" (ምኒልክ ሳልሳዊ)

“የአብይ ሚኒስትሮች የሃሰት ሪፖርት እና ኮፒ ፔስት ቀጥሏል – በጣም ያሳፍራል…!!!”

ምኒልክ ሳልሳዊ

አሳፋሪው ሚኒስትር ምስሉ ከታች የሚታየው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከሁለት አመት በፊት በተዘጋጀ የዶክተር ስለሺ በቀለ ሪፖርት ፓርላማውን ለማጭበርበር ሲሞክር ተደርሶበት በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ተወግዟል። ይህ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት በተደጋጋሚ በሚኒስትሮች እየታየ ሲሆን የአብይ አሕመድ ካቢኔ የሃሰት ሪፖርት በሚያቀርቡ ሚኒስትሮች የተሞላ መሆኑ ሲታወቅ ከዛ በባሰ መልኩ የድሮ ሪፖርቶችን ደግሞ በማቅረብ ፓርላማውን እያታለሉ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የቀረበን ሪፖርት በቀጥታ ገልብጦ ያቀረበው የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር” እጅግ ነውር ተግባር” ፈጽሟል ሲል ቋሚ ኮሚቴውን ገለጸ
የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርብ በተገኘበት መድረክ ምንም ዓይነት የሪፖርት ማሻሻያ ሳያደርግ በቀጥታ እየገለበጠ እንደሚያስተላልፍ ደርሼበታለዉ ሲል የዉሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አከባቢ እና አከባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ቋሚ ኮሚቴ የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ባደመጠበት ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርቶችን በቀጥታ ገልብጦ ከማምጣቱም ባሻገር የተቋሙ የበላይ ሃላፊዎች የማያዉቁት እና ያልተገመገመ ሪፖርት ለ ምክርቤት መላኩ እጅግ ነዉር ነዉ ሲል ቋሚ ኮሚቴዉ ወቅሷል፡፡
ሪፖርቱ በ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካለንበት 2014 የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርቶች በቀጥታ ተገልብጠዉ የተላለፉ ናቸዉ ብሏል ቋሚ ኮሚቴዉ፡፡
ለማሳያነትም በስነምግባር እና ጸረ ሙስና ብልሹ አሰራሮች ናቸዉ ተብለዉ ከቀረቡት 16 ጥቆማዎች መሀል 13ቱ ተጣርተዉ መልስ የተሰጣቸዉ ሲሆኑ 3 ጥቆማዎች በሂደት ላይ የሚገኙ ናቸዉ የሚለዉ አፈጻጸም ከ 2012 የዘጠኝ ወር ሪፖርት ቃል በቃል ምንም ለዉጥ ሳይደረግበት ተገልብጦ የመጣ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፣ ይህንንም ሀሰት ነዉ የሚል አካል ካለ በርካታ ተጨባጭ የሰነድ ማሳያዎች ማቅረብ እንችላለን ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፈትያ አህመድ ተናግዋል፡፡
በሚኒስቴር ዲዔታ ማዕረግ የሚኒስቴሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በሪፖርቱ ላይ የቀረበዉ ትችት ትክክል እንደሆነ አምነዉ የሪፖርት ጥራትና ወቅታዊነት ጉዳይ በፍጹም ለጥያቄም ቢሆን የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ አንስተዉ መስተካከል እንዳለበት እንደሚያምኑ እና የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አንድ ላይ መዋሃድ ይህንን ክፍተት መፍጠሩን እንደምክንያት ያነሱ ሲሆን በቀጣይ ይህንን አስተካክለዉ እንደሚቀርቡ ገልጸዉ ፣ ቋሚ ኮሚቴዉን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ያሳፍራል ።
Filed in: Amharic