>

"የአሸናፊነት እና ተሸናፊነት፤ የበላይነት እና የበታችነት መርህ ተቀብዬ አልኖርም....!!!"  (አቶ ጸጋዬ አራጌ ትኩዬ)

“የአሸናፊነት እና ተሸናፊነት፤ የበላይነት እና የበታችነት መርህ ተቀብዬ አልኖርም….!!!”

አቶ ጸጋዬ አራጌ ትኩዬ

*… ፓርቲያችን ብልፅግና አሁንም ራሱን ቆም ብሎ ማየት አለበት…!
ስማችን በማያሻማ መንገድ ህብረ ብሄራዊ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ግብራችንና ምግባራችን ግን ከዚህ በተቃርኖ በአታካች ሁኔታ እየተጓዘ መሆኑ ለማንም ሰው ግልፅ ነው። በኢህአደግ ውስጥ ለውጡ በተቀጣጠለበት የመጨረሻው ጊዜ ህዝቡን ካስቀዬሙትና ካስከፉት ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው ፍረጃ ነው፡፡ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ‹‹ትምክህተኛ፣ ጠባብ›› እያልን የጥያቄውን ፍሬ ነገር ተረድቶ መልስ በመስጠት ፋንታ ጥግ እያስያዙ መፈረጅ ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ ከሰነድ እንድንወጣ ስምምነት ተደርሶም ነበር፡፡ ሳይውል ሳያድር የለውጥ መስመር ይዘን ተሳፍረናል ባልንበት ጊዜ ‹‹የቀኝ አክራሪ፣ የግራ አክራሪ›› እየተባለ በልምምድ የተጀመረው ፍረጃ፤ ዛሬ ወርዶ ወርዶ ‹‹የአማራ ፅንፈኛና አክራሪ›› የሚል ፍረጃን ተሻግሮ ‹‹እንደመስሰዋለን›› የሚል መግለጫ ሲሰማ ያስገርማል፡፡
በመሠረቱ አማራ ፅንፈኛ ሆኖም አያውቅም፤ መሆንም አይፈልግም፡፡ ይልቁንም ፅንፈኛ መስሎ ከታዬው እንኳን ይታገላል። አሁን በፓርቲው ውስጥ ሆነን ጥያቄ የምናነሳ ግለሰቦች እንኳን በፓርቲ ድስፕሊን ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን፣ በችግሩ ልክ ሳይሆን ካለው ችግር በጣም ርቀን፣ ለምናነሳቸው ጥያቄዎች የተሰጠን የዳቦ ስም “ፅፈኝነት” ነው። ይሄ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ መጠየቅ፣ መከራከር፣ ኢ-ፍተሃዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲን፣ አድሎን፣ አምባገነንነትንና ማን አለብኝነትን፣ የበላይነትን መታገል የመታገያ መድርክ ብለህ በፈጠርከው ፓርቲ ውስጥ ምንድን ነው ችግሩ? በአዲስ አበባ ከተማ፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች ለእውነትና ለፍትህ ስለታገሉ፣ አሠራር እየተጣሰ ነው ብለው ስለተናገሩ፣ በ2014ዓ.ም ብቻ ስንቶቹ ወጣት መሪዎች ከአመራርነት አልተባሩም? አልታሠሩም?
ወያኔም በዘመኑ በሚያስርበት ጊዜ ትምክህተኛና የግንቦት ሰባት ተላላኪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሎ ነው የሚያስረው፡፡ ተለጣፊ ኮድ ሳይሰጥና ታርጋ ሳይለጥፍ አስሮ አያውቅም። አሁንም ይመከርበት፣ ይታሰብበት፡፡
1. የህዝብ ጥያቄን በአግባቡ አዳምጠን እንመልስ።
2. ከፋኖ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች በአግባቡ ይታዩ፡፡ ፋኖ ወረራ ተፈፀሞበት ህዝቡን ከጥቃት ለመመከት ራሱን ያደራጀ ሀይል እንጅ ሌላ አላማ የለውም፡፡ ስለሆነም ትንኮሳ አያስፈልገውም።
3. በፓርቲው ውስጥ ያለው የመዋቅር ግንባታ አቅጣጫ በአሸናፊነትና ተሸናፊነት  በአስፈሪነትና ተፈሪነት፣ በአዛዥነትና በታዛዥነት ሳይሆን በተግባቦትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ የውስጠ ፓርቲ ተቋማዊ ግንባታ ይካሄድ። ፍረጃ ይቁም፣ የመብት ጥያቄ ያነሳን አመራርና አባል ፅንፈኛ ወዘተ እያሉ ማዋከብ ይብቃ፡፡ መብታችን ይከበር ብለው የሚታገሉ ወገኖችን ማሸማቀቅ ያለ ቅድመ ሁኔታ ሊቆም ይገባዋል።
4.የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በማንኛውም መንገድ መቋጫ ሊበጅለት ይገባል።
5. ብሄር ተኮር ይሁን በሌላ በማንኛውም መንገድ የሚደርግ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ሊቆም ይገባል፡፡ መንግስት ከዚህ ችግር ጋር ተለማምዶ ሊኖር አይገባም።
እኔ በግሌ ማንኛውንም ‹‹የአሸናፊነት እና ተሸናፊነት፤ የበላይነት እና የበታችነት›› መርህ ተቀብዬ አልኖርም፡፡ የሚያኖረኝ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መከባበር ብቻ ነው። ዛቻ እና ማስፈራራትን የሚያምንም፤ የሚቀበልም የሞራል ስሪት የለኝም።
Filed in: Amharic