ከመሬት ወረራ ወደ ማንነት ጥያቄ በዘመነ ትሕነግ፣ የኦሕዴድ ካድሬ አዲስ አበባ እና ዙርያው ላይ ያለውን መሬት በመቀራመት ፊት-አውራሪ እንደነበረ አይዘነጋም። ሁላችንም እንደምናስታወሰው፣ ድርጅቱ ላይ የተለጠፉ ካድሬዎች ከራሳቸው አልፈው ተርፈው፣ ለሌላው መሬት በማደልም ሆነ በመቸብቸቡ ረገድ የሚስተካከላቸው አልነበረም። በርግጥ፣ ይኽን የዐደባባይ እውነት እነሱም ክደውት አያውቁም። ከ8 ዐመት በፊት፣ በእነ አባዱላ ገመዳ መሬት የተሰጠው አንድ የምቀርበው ኦሮሞ ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ያጫወተኝን አስታውሰዋለሁ። መምህራን ተሰብስበው አለን የሚሉትን ጥያቄ ያቀርባሉ።
እነ አባዱላም መሬት እንደሚሰጧቸው ቃል ገብተው አፋቸውን ያስይዟቸዋል። በሌላ ጊዜ፣ የድርጅቱ ካድሬዎች እነዚያኑ መምህራን ሰብስበው፣ የተሰጣቸውን መሬት ምን እንዳደረጉት ሲጠይቋቸው፣ “ቤት እንዳንሠራበት ገንዘብ የለንም፤” የሚል አጭር ምላሽ ይሰጧቸዋል። በወቅቱ፣ ኦሕዴዶች ለዚህ ችግር መፍትሔ አድርገው ያቀረቡት ሌላ ተጨማሪ መሬት በመስጠት አንዱን ሸጠው፣ በሌላኛው ቤት እንዲሠሩ ነበር። ይህን ያደረጉት ለመምህራኑ አዝነው አይደለም። መሬቱ ከአርሶ ዐደሩ የተቀማ እንጂ፤ ከሰማይ የወረደ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በወቅቱ፣ የድርጅቱ አመራሮች ይህን እርምጃ የወሰዱበት ዋናው ምክንያት ከመምህራን የተነሳባቸውን ተቃውሞ አቀዝቅዘው፣ ለጊዜውም ቢሆን ድጋፍ ለማግኘት ነበር። የዘመኑ ተቃውሞ ማብረጃ መላ ይህ እንደነበረ በታሪክ እንዳይረሳ ሆኖ ተመዝግቧል።
እዚህ ጋ ልብ መባል ያለበት፣ ለመምህራን ሁለት ሁለት መሬት የሚያድል ካድሬ፤ ለራሱ ምን ያህል ሊቀራመት እንደሚችል መገመቱ ቀላል አለመሆኑን ነው። ሦስት? አራት? ዐሥር? ወይስ ከዚያ በላይ? ዘግይቶ የመጣው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ ደግሞ ኦሕዴድ በግለሰብ፣ በማኀበራት… እየሸነሸነ ሲያከፋፍል የነበረውን አካባቢ የሚመለከት ነበር። እነሱ ግን ጥያቄውን ጠልፈው ለፖለቲካ የበላይነት መታገያ ወደማድረግ ለወጡት እንጂ። በዚህም፣ ራሳቸው በግላጭ ዋና አሳላፊ ሆነው የአርሶ ዐደር መሬት ያስወረሩበትን አጀንዳ ወደ ማንነት ጥያቄ ለመቀየር አልከበዳቸውም።
ሙዝ እንደ መላጥ ቀሏቸው ነበር። ማስተር ፕላኑን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ቁጣ፣ ‹ኹነቱ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ እንድትስፋፋ የሚያደርግ ነው› የሚል ይዘት አለው። የኦሮሚያ ካድሬዎች የወቅቱን አጋጣሚ ከላይ ሲታይ የማንነት እና የፍትሐዊነት ጥያቄ በማስመሰል ሲያቀርቡት፤ በውስጠ-ዘ ግን፣ ሕወሓት የፌደራል መንግሥቱ ላይ የነበረውን የበላይነት፣ በኦሕዴድ ለመተካት ወደሚያስችል ግብ ቀይረው አስጮኹት። በዚህም፣ ከአርሶ ዐደር የመሬት ነጠቃ ጥያቄ አልፈው፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን የሚጠቀልሉበትን ኃይል ማሰባሰቢያ አጀንዳ አደረጉት። በዋንኛነትም፣ ዓላማቸውን ለማሳካት ኦሮ-ማራ የሚባል ጥምረት ፈጥሩ፡፡ ወይም በኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ቋንቋ ገሚሱን ኮንቪንስ፣ የተቀረውን ኮንፊውዝ አድርገው የአራት ኪሎን መንበር ተቆጣጠሩበት፡፡ ይህን ተከትሎም፣ የአርሶ ዐደር መሬት ሲሸጥ የነበረ ካድሬ በመሃል አዲስ አበባ የሚፈልገውን ለማድረግ ከልካይ አጣ። የኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ፣ የፈቀደውን ክፍት ቦታ ለራሱም ሆነ ለሌላው ቢያድል የጋራ ዓላማ እንጂ፣ ስርቆት አይመስለውም።
በርግጥ ይህ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን፤ በድርጅቱ ውስጥም አዲስ አበባን ለመንጠቅ የሚደረግ ስልታዊ ተግባር እንጂ፤ ሌብነት ተብሎ አይወሰድም። በዚህ ድርጊት፣ በመካከላቸው መወቃቀስ የለም። ኧረ ፈጽሞ አይታሰብም። “አዲስ አበባን የተቆጣጠረ፣ ኢትዮጵያን ይቆጣጠራል!” በአንድ ወቅት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ አዲስ አበባ እና ስለ ኢትዮጵያ ሲያወራ በድብቅ ተቀርፆ በወጣበት ድምፅ፣ የከተማ ፖለቲካ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲናገር መደመጡ ይጣወሳል። ይህ ንግግሩ የግለሰብ አቋም ወይም የአፍ ወለምታ አይደለም። ኦዴፓም በጅምላ የሚያምንበት ነውና። እዚህ አቋም ላይ የደረሰውም በግምት ሳይሆን፤ በደንብ አስበውበትና ተዘጋጅተውበት ነው።
በዚህ አጋጣሚ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ከሌላው በተሻለ በሰነድ እና መግለጫ የዳበረ ልምድ እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። ኦነግ እድሜውን የፈጀው ከኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ጋር ሲፋለም ሳይሆን፤ በእንዲህ ዐይነቱ ተግባር ተጠምዶ እንደነበረም የዐደባባይ እውነት ነው። አሁናዊውን የኦሮሞ ፖለቲካ በቀኝና በግራ እያጣደፈ ያለው፣ በፕሮቴስታንትም ሆነ በውሃቢዝም የታሸው የፖለቲካ ሰነድ ገና በማለዳ ድርጅቱ ያዘጋጀው ነውና። የአዲስ አበባ ጉዳይ በስሁት ትርክት ተሞልቶ እና በጥንቃቄ ተሰንዶ በቀዳሚነት የሚንቀሳቀሱበት አጀንዳ እንደሆነ በግላጭ ይታወቃል። በአጭሩ፣ አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ ኦሮሚያንም ኢትዮጵያንም መቆጣጠር እንደሚችሉ የሚያስቡበት የጂኦ-ፖለቲካ ፅንሰ-ሀሳባቸው እምብርት ነው።
እንዲህ ያጋመዱትን ጉዳይ አጣምረው ይዘውታል። ይህን ዓለም ዐቀፍ “የማዕከል እና ዳር” ጂኦ-ፖለቲካዊ ፅንሰ-ሀሳብ ወደ ኢትዮጵያ ጎትተው አዲስ አበባ ላይ ሲያመጡት የሆነውን በግልፅ እያየን ነው። ሁሉንም ነገር ወደ አዲስ አበባ አዙረው ሲሠሩ፣ በአንድ ቀን አዳር ከሻሸመኔ እስከ ሀረር፣ ከአሰላ እስከ ዝዋይ… የወደመውን የኦሮሚያ ክፍል የምናስታውሰው ነው። አዲስ አበባ ላይ ጎዳና እና ቢሮ ሲያሳምሩ “ፋይዳ የለውም” ያሉት የኦሮሚያ ክልል ክፍል ለንፁሃን ዜጎች ሲኦል ከሆነ ሰንብቷል። በርግጥ፣ በክልሉ ላይ እየደረሰ ያለው ውደመት፣ እዚያው ተወስኖ የሚቀር አልሆነም። በተለይ፣ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ፣ ከየአከባቢው ዱላ ይዞ ወደ መዲናቱ የተመመውን ወጣት እና የተፈጠረውን ሁከት፣ በቦታውና በወቅቱ የነበረ ሁሉ የሚዘነጋው አይደለም። በሌላ በኩል፣ ኦዴፓ እነ ጃዋር መሃመድን መሪው አድርጎ የተቀበለውን ቄሮ፣ ወደ አዲስ አበባ እያስመጡ በመሬት እና በቤት በመደለል ለመቀማት ቢጥሩም፤ መሬቱንም ሆነ ጥቅማ-ጥቅሙን ለሁሉም ማዳረስ የሚቻል ባለመሆኑ እንዳሰቡት የተሳካላቸው አይመስለኝም።
ወለጋ እና ጉጂን ከአዲስ አበባ አንፃር ‹ምንም ፋይዳ የሌላቸው› ብለው ሲረሱት፤ መጀመሪያም ከኤርትራ አምጥተው ሲያባብሉት በነበረው ኦነግ ሸኔ በሚባል አረም ተውጠው አረፉት። የወለጋ እና ጉጂ ጫካዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ፊታቸውን ወደ ሸገር ሲያዞሩ የረሱት የኦሮሚያ ቢሮክራሲም፣ የኦነግ ሸኔ ተባባሪ ሆኖ አራት ኪሎ ላይ ‹ተደላድለን እንቀመጥበታለን› ያሉትን ሥልጣን ለስጋት ዳረገው። የስብስቡ ዐቅም ከኦሮሚያ ሽፋኑ እየሳሳ መጥቷል። የታጠቀው ቡድንም እንቅልፍ በሚነሳ መልኩ ሸዋ አካባቢ ደርሷል። የኦሮሞ ፖለቲከኞች በስንዴ ማሳ ሊሸፍኑት ቢሞክሩም፣ በግል አውሮፕላን እንደ ሆሊውድ አክተር በየክልሉ እየዞሩ ‹እርዳታ ያስፈልገዋል› ለሚባለው ማኀበረሰብ ዳጎስ ያለ የገንዘብ እርጥባን እንደሚሰጡ በየሚዲያው ቢያስነግሩም፤ ‹የዳር ፖለቲካ› ብለው ንቀው አዲስ አበባን ለመዋጥ ያደረጉት ጥረት፣ ለኦሮሚያም ለኢትዮጵያም ምን ያህል አውዳሚ እንደሆነ በየቀኑ ከአፈናው ሾልኮ በሚወጣው ዜና የምንሰማው ክስተት አንደኛ ደረጃ ማስረጃ በመሆን ያረጋግጥልናል። የኦሮሞ ልሂቃን ዋና አጀንዳቸው አዲስ አበባን አድርገው፤ “ሌላው እዳው ገብስ ነው!” ቢሉም፣ ለአገር ያተረፉት በቀላሉ የማይፈታ ምስቅልቅሎሽን ነው።
የመሃል ከተማውን ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው የሚገኘውን አርሶ ዐደር መሬት ለግል ሲቀራመቱ እንዳልነበረ ሁሉ፤ አሁን ኢትዮጵያውያንን በዋነኛነት የሚፈልጓቸው አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ እንደሆነ አቶ ርስቱ ይርዳው በአንድ መድረክ ተናግረውት የወጣው የድምጽ ቅጅ በቂ ማሳያ ነው። አቶ ርስቱ፣ ጉራጌ ከኦሮሞ ብልፅግና ጎን እንዲሰለፍ የተፈለገበት ገፊ-ምክንያት “አዲስ አበባ ላይ ዐማራ ያሸንፈናል” ከሚል ስጋት ስለመሆኑ በግላጭ ተናግሮበታልና። ሌላውን የኢትዮጵያም የኦሮሚያም ክፍልን ትቶ፣ አዲስ አበባ ላይ ያተኮረው የኦሮሚያ ብልፅግና፣ በከተማዋ ጉዳይ ከጎኑ ያልተሰለፉ አካላት ላይ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃም አስፈሪ ስለመሆኑ ከዚሁ ንግግር መረዳት ይቻላል።
የኦሮሞ ፖለቲከኞች ገደብ-የለሽ ፍላጎት አዲስ አበባንም ለሌላ ሽብር እየዳረጋት እንደሆነ ብዙ አመላካች ኹነቶች አሉ። ከሁለት ዐመት በፊት የአርበኞች ግንቦት-7 አመራሮች አቀባበልን ተከትሎ፣ ከቡራዩ እስከ አዲስ አበባ የተፈፀመው ሽብር፣ ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ ከየአቅጣጫው በነፃነት ገብቶ በከተማይቷ ላይ ሁከትና ሥርዐት አልበኝነት የፈጠረው ኃይል፣ ሕዝባዊ በዓላትን ተንተርሶ በንፁሃን ላይ የሚደርሰው እስር እና ማዋከብ፣ አዲስ አበባን የፈለጉበት አካሄድ አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። ከየትኛውም የኦሮሚያ ክፍል እየተላኩ መታወቂያ ታድሏቸው የከተማው ነዋሪ እንዲመስሉ የተደረጉ እንዳሉ ሁሉ፤ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በክልል ፖሊስ መንገድ ተዘግቶባቸው የሚመለሱ መኖራቸውንም ስናስተውል፣ ሸገርን ለጊዜው ይፈልጓት እንጂ፤ ከቆይታ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተፈፀሙት ወንጀሎች ሰለባ እንደማትሆን እርግጠኛ አያደርገንም።
ይህ ሁሉ ርብርብና የትኩረት ማዕከል ማድረጉም፣ የከተማዋን የስጋት ደረጃ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ እንዲሆን ገፍቶታል። አዲስ አበባ በጠራራ ፀሐይ ውንብድና የሚፈፀምባት፣ በመሃል አስፓልት ዜጎች የሚዘረፉባት፣ ታግተው የሚቀሙባት፣ ባስ ሲልም የሚገደሉባት ከሆነች ሰንብታለች። ቀደም ሲል የኪስ ሌባ የነበሩ፣ በአሁኑ ወቅት መኪና ነድተው የሚሄዱባት ከተማ ሆናለች። የኦሮሚያ ብልፅግና ሰዎች “የአባትህ ቤት ሲወረር፣ አብረህ ውረር!” መርህን ተመርኩዘው ሃብት ማግበስበስ ላይ እንጂ፤ ለከተማዋ ሰላምና ፀጥታ ግድ የሚሰጣቸው እንዳልሆኑ በስፋት ታይቷል። እነዚህ ተያያዥ ክስተቶች ወደ አንድ ድምዳሜ ይመሩናል። ለሸገር የታሰበላት ከባድ አደጋ ነገር መኖሩን። ለአዲስ አበባ ያልበቁ ተቃዋሚዎች መዲናይቱ ከኢትዮጵያም አልፋ በአፍሪካም ትልቅ ትርጉም ያላት መሆኗ የታወቀ ነው።
በከተማዋ የሚደረግ ያልተገባ ፖለቲካ በየትኛውም ኃይል መታገያ መሆን ሲኖርበት፤ አብዛኛው ተቃዋሚ ድርጅት በአርምሞ የሚመለከተው ሆኗል። ምንም እንኳ በምርጫ ጊዜ ስሙን የምንሰማው እና ከምርጫ ውጭ ለመንቀሳቀስ የማይጥረው ፓርቲ ሁሉ በአዲስ አበባ ቢሮ ቢኖረውም፤ በከተማዋ ጉዳይ የሚታዩትን ዓይን ያፈጠጡ እውነታዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ አጀንዳ ሲያደርግ ግን አይስተዋልም። ካሉት በርካታ ፓርቲዎች መካከል የአዲስ አበባን ጉዳይ አጀንዳቸው የሚያደርጉት፣ የሚፈፀመውን በደል የሚያወግዙት፣ ችግሮችን ለማጋለጥ የሚሞክሩት… ከአምስት አይበልጡም። ‹የልዩ ዞን እና ወረዳ ይሰጠኝ› ጥያቄ ያላቸው አካላት በሙሉ ፓርቲ መስርተው በሚታገሉበት አገር፤ ከበርካታ ክልሎች የሚበዛ ሕዝብ፣ እጅግ አሳሳቢ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ያላት አዲስ አበባን በቋሚነት አጀንዳ ሲያደርግ የቆየው አንድ ባልደራስ ብቻ መሆኑ አስደንጋጭ ነው።
አዲስ አበባን አናግተው መንጠቅ የፈለጉ ኃይሎች፣ አንድ ዐደባባይን እንኳ ሳይንቁ ለመውረስ ከበርካታ ኃይሎች ጋር ቅንጅት ሲፈጥሩ፣ በአካባቢው ያልነበረ የእምነት ተቋም የዐደባባይ ባለቤትነት ጥያቄን እንዲያነሳ ሲያደርጉ፣ አዲስ አበባ ላይ ቢሮ ከፍቶ ‹ካሸነፍኩ ዋና ከተማዬ አደርጋታለሁ› ከሚለው መካከል ጥቂቱ ኃይል የከተማዋን ጉዳይ አጀንዳ የሚያደርገው በገዥዎች ስህተት ወይም በአንዳንዶች ጥንካሬ ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ ከዋለ በኋላ ነው። ገዥዎቹ ፍላጎታቸውን በውስጥ፣ ማደናገሪያቸውን ደግሞ በይፋ ለማስፈጸም አዲስ አበባ ላይ ከሚተገብሩት መካከል እጅግ ጥቂቱ፣ ለትችት የሚዳርጋቸው ቢሯቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ፓርቲዎች ለዋና ከተማ አጀንዳ ያልበቁ በመሆናቸው ነው። በግንባር ቀደምነት የአዲስ አበባን ጉዳይ የያዘው ባልደራስ፣ ከሌሎቹ አንፃር በከተማዋ የሚፈፀመውን ሕገ-ወጥነት በመቃወም በጉልህ የሚታይ ቢሆንም፤ ገዥዎቹ በከተማዋ ላይ ከሚያሳርፉት በትር፣ እያሰባሰቡት ካለው ኃይል እና ከፖለቲካ አረዳዳዳቸው አንፃር፣ የከተማዋን አጀንዳ በማንሳትና ውጤት በማምጣት ረገድ ብቁነቱ አጠራጣሪ ነው። የሚደርስበት ጫና እንዳለ ሆኖ፣ ባልደራስ በሕዝብ ንቅናቄነት በነበረበት ወቅት እና የፖለቲካ ፓርቲ ከሆነ በኋላ ሕዝብን በማንቀሳቀስ፣ አደረጃጀትና ጥምረት ፈጥሮ ለአዲስ አበባ የሚመጥን ፖለቲካ በመሥራት ረገድ በርካታ ክፍተቶች ይታዩበታል።
ገዥዎቹ ‹ወለጋን፣ ጉጂን እና ሀረርጌን የገጠር ፖለቲካ ነው› ብለው ያላቸውን ዐቅም በሙሉ አዲስ አበባ ላይ ባደረጉበት ሁኔታ፤ ባልደራስ የተለመዱ አመራር እና አባላቱን ይዞ ገጠር ለገጠር መዞሩ ከተማይቷ ከተሸከመችው ጫና አኳያ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም። የኦሮሞ ብልፅግና የቻለውን አባብሎ፣ ሌላውን አስፈራርቶ በአዲስ አበባ ጉዳይ ከጎኑ እንዲቆም በሚያደርግበት ወቅት፣ ባልደራስን ጨምሮ ሌሎች ‹የሸገር ጉዳይ ያገባናል› የሚሉ ድርጅቶች በዋና ከተማዋ ጉዳይ ሁነኛ አጋር ለመፈለግ የሚደክሙ አይመስሉም።
አብዛኛው የአዲስ አበባ ጉዳይ በዝግ የሚዶለት፣ የተወሰነውን ደግሞ በዐደባባይ የምናየው አልያም ሲፈፀም የምንመለከተው ሆኗል። ይህን ርዕሰ ነገር የምር ለሚይዝ ኃይል የተቃውሞው ስብስብ ብቻ ሳይሆን፤ ቢገኝ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አጀንዳውን የሚጋራ የገዥዎቹ አካል እገዛም ያስፈልገዋል። ከተቻለም የገዥዎቹ መዋቅር ውስጥ ገብቶ ድጋፍ እስከማግኘት ድረስ መሄድ ይጠበቅበታል። ይህም ሆኖ ግን፣ እውነታቸውን ሥልጣን እና ጥቅም ባደረጉ ገዥዎች፤ እንዲሁም ፖለቲካ ውስጥ ሆነው ሴራን በሚፀየፉ ኃይሎች መካከል የሚደረገው የአዲስ አበባ ፍልሚያ የሚጠበቀውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የጊዜው ባለወንበሮች ሲፈልጉ ወጣቱን አጉርሰው፣ ሲያሻቸው በየእምነት ተቋማቱ እየተመሳሰሉ፣ አልያም የአጀንዳቸው ተካፋይ እንዲሆን የሚፈልጉትን ብሔር እሴት ተላብሰው በሚያቦኩት ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ሀቅ የያዙት እነ እስክንድር ነጋ በአቋም ከሚለዩዋቸው ኃይሎች ጋር ተወያይተው አጋር መፈለግን ምንፍቅና አድርገው መውሰዳቸው የሚገመት ነው። አዲስ አበባ ላይ ከሚሠራው በርካታ ውስብስብ ሴራ አንጻር፣ አጋር ፍለጋ የራሳቸውን ደረቅ ሀቅ ጥለው የፖለቲካ እውነት የማይይዙ አካላት፣ ከተማዋ የገጠማትን የውስልትና ፖለቲካ በመጋፈጥ ራሳቸውን እና አባላቶቻቸውን ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ፤ ብዙ ያልተነገሩ ጉዶችን የተሸከመችውን አዲስ አበባን የመታደጋቸው ነገር አጠያያቂ ነው።
ገዥዎቹን በማጋለጥ እንቅልፍ የሚነሱባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ፤ አንዳንዴ በዐደባባዩ የሚደረጉ ተገማች ፖለቲካን በየዕለቱ በመደጋገም ከፊት ለፊት የሚያሰልፉበት አካሄድ ለገዥዎቹ ቀጣይ እቅድ ምቹ ሆኗል። የአዲስ አበባ ወጣት የ1997ቱን ቁስል እያስታወሰ፣ በኑሮ ውድነት፣ በሥራ እጦት፣ በገዥዎቹ ማባበያና ማደናገሪያ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እየባከነ በዋና ከተማው ጉዳይ ዋና ተሳታፊ መሆን አልቻልም። በገዛ መኖሪያው ባይተዋር እንዲሆን ተገድዷል። አልፎ አልፎ በሚታዩት የጎዳና ላይ ተቃውሞዎች፣ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ተጠንቶ ፖለቲካው የሚሠራ ባለመሆኑ፣ ይህ ዐቅም ያለው ትኩስ ኃይል እየታፈነ ለቀጣይ ትግል እርሾ ሳይሆን ያልፋል።
ገዥዎቹ ወቅታዊ ተቃውሞን ለማፈን፣ በአዲስ አበባ ወጣት ላይ የሚያደርጓቸው እስር እና ወከባዎች፤ እንዲሁም በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወስዷቸው አቋሞች በዓለም ፊት የሚያጋልጧቸው ቢሆንም፤ ከአንድ ሰሞን የፌስቡክ አጀንዳ እንዲያልፉ አድርጎ የሚሠራባቸው ስለሌለ፣ ውጤታቸው የገዥዎቹን ስህተት የሚመጥን ሳይሆን ባክኖ እየቀረ ነው። ለአብነትም፣ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ እየሠሩ ያለውን ማየት ብቻ በቂ ነው። ለአዲስ አበባ የቆሙ ድርጅቶች ከሚያሰልፏቸው ግለሰቦች መካከል ሀቀኛና የከተማዋ ጉዳይ ያንገበገባቸው የመኖራቸውን ያህል፣ አካሄዳቸው ገዥዎቹ የራሳቸውን ሰዎች አስርገው ለማስገባት የተመቸ እንዲሆን ያደረጉ መኖራቸውንም መገመት ይቻላል። ተቆርቋሪ አስመስለው አብረው ዐደባባይ ማስወጣት፣ የተቃዋሚውን አጀንዳ አስጠንተው፣ ድርጅቱን እና መሪዎቹን የሚወዱ አስመስለው አስረው የሚፈቷቸው አባላቶች እንደነበሯቸው መኢአድ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ውስጥ የነበሩ አባላት ምስክር ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ፓርቲዎች በድንገት የሚይዟቸው፣ በገዥዎች ግን ሆን ተብለው የታቀዱ አጀንዳዎች መኖራቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በጥቅሉ፣ አዲስ አበባ እንደ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ አንደ አፍሪካ መዲና፣ እንዳላት የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ዐቅም እየተሠራበት አይደለም። ገዥዎቹ “ሁሉም ነገር ወደ አዲስ አበባ” ብለው ግዙፍ አደጋ ደቅነውባታል። ይኽን የሚመጥን የተናበበ፣ በሰነድ የተደገፈ እና አስፈላጊ ሲሆን የጊዜው ፖለቲካ የሚጠይቀውን አካሄድ ሊያደርግ የተዘጋጀ ኃይል የግድ ያስፈልጋታል። ያን መፍጠር የማይቻል ከሆነ፣ ወለጋን እና ጉጂን ለአሸባሪ የሰጡት ኃይሎች አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያንም አደጋ ላይ መጣላቸው የማይቀር ነው።