>
5:13 pm - Thursday April 19, 4846

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ - ምን እናድርግልዎ ሳይሆን ምን እንሁንልዎ...??? (አሳዬ ደርቤ)

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ – ምን እናድርግልዎ ሳይሆን ምን እንሁንልዎ…???

አሳዬ ደርቤ

▬▬▬▬

‹‹ላም እሳት ወለደች፡፡ እንዳትጥለው ልጇ ሆነባት፣ እንዳትልሰው እሳት ሆነባት›› ሲባል ሰምተው ያውቃሉ?

ኢትዮጵያም እርስዎን ወልዳ ሾመች፡፡ እናም በቃኝ እንዳትልዎ ወንበርዎን የማያስነኩ ብርቱ መንግሥት ሆኑባት፡፡ አሜን ብላ እንዳትገዛ ደግሞ እሳት ሆነው አቃጠሏት፡፡

እጦት ሆነው አራቆቷትg፡፡

ጭንቀት ሆነው እንቅልፍና ሰላም አሳጧት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ መጻፍ ያስፈለገኝ ሕልምዎን እና ከሕዝብ የሚፈልጉትን ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ምን እናግዝዎ?›› በማለት ፈንታ ‹‹ምን እንሁንልዎ?›› ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ለባለፉት አራት ዓመታት ‹‹በፖለቲካው ዓለም ቋሚ ጠላትም ሆነ ቋሚ ወዳጅ የለም›› በሚል የክሕደት ፍልስፍና እየተመሩ ‹‹መንግሥትን በመደገፍ፣ አገር ማትረፍ›› በሚል መርሕ እገዛ ያደረገልዎትን ሁሉ አሽቀንጥረው ሲወረውሩ ስላየሁ ስለ እገዛና ድጋፍ አላወራም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-

ቤት ውስጥ ገብታ ያስቸገረችን ዐይጥ ለመያዝ የወጥመዱ ምላስ ላይ አትክልት ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የእርስዎ መንግሥትም በአትክልት ፈንታ የሰው ልጅ ሕይወትን ከወጥመድ ላይ እያስቀመጠ አስቸጋሪ መስሎ የታየውን አካል ሲያጠምድ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት እነ እንቶኔን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት የታሰበ ቀን የ86 አማራዎች ሕይወት ወጥመድ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ የሰኔ አስራ አምስቱም ሆነ የጥቅምት ሃያ አራቱ ዘመቻ ሲካሄድም የሚፈለገው አካል ይበላቸው ዘንድ ወጥመድ ላይ የተቀመጡ ነፍሶች ነበሩ፡፡ አብዲ ኢሌንም መያዝ ሲፈለግ ከተበሉ በኋላ ‹‹የተከሳሽ ጥፋት›› የሚባሉ ነፍሶች ወጥመድ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡

አሁንም ይሄው ልማድ በመጠናከሩ የተነሳ ፋኖን ለመምታት የሚያስችል ጥፋትና ምክንያት ፍለጋ በርካታ ነፍሶችና እሴቶች እንዲወድሙ እየተደረገ ነው፡፡

ሆኖም ግን አልገባኝ ያለው ነገር መንግሥትዎ በአማራ ሕዝብ ላይ ይሄን ማድረግ የፈለገበት ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ከዓመት በፊት ‹‹አገር ተደፈረች›› የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ የአማራ ሕዝብም ልክ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥሪዎን ሰምቶ ፈጥኖ በመድረስ ለአገሩም ሆነ ለወንበሩ ቀጣይትነት የሚችለውን እርዳታ አድርጎ ነበር፡፡ እርስዎ ግን  በሽልማት ፈንታ ጠላት አምጥተው ከምድሩ ላይ ከዘረገፉበት በኋላ በሬሳ መሃከል ቆሞ ‹‹የአገር ያለህ›› እያለ ሲጣራ በማሳ መሃከል እየተዟዟሩ ‹‹ፈጣሪ ይሁንህ›› የሚል መልዕክት አስተላለፉለት፡፡

ወጣት ልጆቹን በመከላከያ ሠራዊትነት ካስመዘገበ በኋላ ‹‹የአገሬ ሠራዊት የት አለ?›› ብሎ ሲጠይቅ ‹‹የመጣብህ ጠላት በመደበኛ ኃይል የሚመከት ስላልሆነ ጩኸትህን አቁመህ እንደ ሕዝብ የመጣብህን ጠላት እንደ ሕዝብ መክት›› የሚል ትዕዛዝ ሰጡት፡፡

ከዚያም የመከራ ጊዜ ትምህርት ወስዶ በፋኖነት በመደራጀት እራሱን ለመከላከል ሲሞክር ደግሞ በሃይማኖት ተከፋፍሎ የሚባላበትን እና ትጥቅ የሚፈታበትን ሤራ ወረወሩለት፡፡

እኔ እምልዎት ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፦  ፋኖ እራሱንና ክልሉን ከማስከበር ባለፈ የእርስዎን ወንበር የሚመኝ አለመሆኑ እየታወቀ፣ ትጥቁን ለማስፈታት ይሄን ያህል ርቀት መጓዝ ያስፈለገው ለአማራ ሕዝብ ምን ያህል የጅምላ መቃብር ተቆፍሮ ቢጠናቀቅ ነው?

➔በወራሪው ኃይል የተፈጸመው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትስ ከመንግሥትዎ እቅድ ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ በምን ያህል ፐርሰንት ወርዶ ቢገኝ ነው?

➔በሥልጣን ዘመንዎ ማሳካት የሚፈልጉት ሕልም እውን እንዲሆንስ ከአገሩ ሲሳደድ የከረመው የአማራ ሕዝብ ክልሉን ጥሎ ወዴ’ት ይፍለስ? የቀልብዎ እንዲደርስ በጥይትና በርሐብ ስንት ልጆቹን ቀብሮ ያልቅስ? ስንት ቤተ-እምነት እንደ ሻማ ይለኩስ?

➔ከመንግሥት የሚያገኘውን ጥቅም ቀርቶ የተነጠቀውን ሰላም ያገኝ ዘንድ ስንት ዞን ይውደምልዎት?

➔ኢትዮጵያዊነቱ፣ አማራነቱ፣ ሙሥሊምነቱ፣ ክርስቲያንነቱ ሁሉ እልቂት የሚያመጣ ጥፋት ሆኖ ከተገኘ ምን ይሁንልዎት?

ከእራሱ ርሐብ በተጨማሪ የመንግስትን ጥጋብና ጭቆና መቻሉ በቂ መስሎ ካልታየዎት የአትላስን ጫንቃ ተውሶ ምን ይሸከምልዎት?

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እያደነዘዙ በማካቬሌ አስተምህሮ አፈር ድሜ ያስበሏት አገር’ስ አንጀትዎን እንዲትበላዎት ምን ያህል ትንኮታኮትልዎት?

Filed in: Amharic