>

የባልደራሶቹ ሰናይት ታደገና ሱራፌል አንዳርጌ  የድል በዓሉን እንዳያከብሩ ተከልክለው ታሰሩ!

የባልደራሶቹ ሰናይት ታደገና ሱራፌል አንዳርጌ  የድል በዓሉን እንዳያከብሩ ተከልክለው ታሰሩ!
 
ባልደራስ

 

 ሰናይት ታደገና ሱራፌል አንዳርጌ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን(3ኛ) ገብተዋል!
 
# የእስሩ ዘመቻ ቀጥሏል፣ በእስሩ ዘመቻ ዙሪያ ከቀኑ 10:30 ሰዓት በዋሽንግተን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል!
 
የጣሊያን ወራሪ ኃይል በአምስት አመቱ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ትግል ድል የሆነበትን ዕለት ለመዘከርና አዲስ አበባ፤ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልቱ ስር የክብር የአበባ ጉንጉን ለማኖር የባልደራስ ለእውነተኛ ድሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮችና አባላት ዛሬ ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ከደቂቃዎች በፊት ወደ ሥፍራው አቅንተዋል።
 የባልደራስ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ አምሀ ዳኛው፣ የፓርቲው አባል የሆኑት ወ/ሮ ሰናይት ታደገ እና የካሜራ ባለሙያው ሱራፌል አንዳርጌ ወደ ሐውልቱ ሲያቀኑ የድል በዓሉን እንዳያከብሩ በፖሊስ ተከልክለዋል።
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የጣሊያን ወራሪ ኃይልን ድል የአደረጉበትን 81ኛ ዓመት የድል መታሰቢያ ቀን ለማክበር እንቅስቃሴ ያደረጉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አባሏ ወ/ሮ ሰናይት ታደገ እና የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የካሜራ ባለሙያው አቶ ሱራፌል አንዳርጌ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል። የወሰዱትን የአበባ ጉንጉን በድል ሐውልቱ ስር እንዳያስቀምጡ ተከልክለው ነበር ለእስር የተዳረጉት።
ለቀረፃ ይዘውት የወጡትን የቪዲዮ ካሜራ ጨምሮ ንብረቶቻቸውም በፖሊስ ተይዘዋል።
ከሁለቱ በተጨማሪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለእስር ከተዳረጉት መካከል የባልደራሱ ቢኒያም ታደሰ፣ ታዋቂው ጋዜጠኛ ጎበዜና ሌሎች በርካታ የዐማራ ክልል ወጣቶች ይገኙበታል።
ይህን የእስር ዘመቻ አስመልክቶ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጰያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል። በዚህ ባልደራስ የፌስቡክ ገፅ እና በሌሎች ሚዲያዎች ከቀኑ 10:30 ጀምሮ በቀጥታ (live facebook) ይተላለፋል። ይከታተሉት።
Filed in: Amharic