>

አንድ ለመንገድ....!!!  (ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ)

አንድ ለመንገድ….!!!

 ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ


*….  እኔ በበኩሌ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ:- ከአብን ሊቀ መንበርነቴ በገንዛ ፈቃዴ እንደለቀቅሁት ሁሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቴንም በገዛ ፈቃዴ በመልቀቅ አዳዲስ መሪዎች በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ መወሰኔን እገልፃለሁ።

– ወደ ውስጥ መመልከት ወደ ውጭ አጥርቶ ለማየት ይረዳል

ወንድሜ ሆይ፦ አንተን ብቻ የአማራ ሕዝብ ሙሴ አድርጎ የፈጠረ ጌታ የለም፣ ቦታ ብንለቅላቸው ምን አልባት ከኛ በእጅጉ የተሻሉና አብንንም ሆነ የአማራን ሕዝብ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስዱ መሪዎች አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ።

እኛ እኮ ምንም፣ ትቢያ ነበርን። የአማራ ህዝብ ነው ከመሬት አንስቶ ለዚህ ታዋቂነትና የመሪነት ቦታ ያበቃን እንጂ ከ4 አመት በፊት ምንም ነበርን። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «እኔ ግን ትል ነኝ፣ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።» እንዳለው (መዝ ፳፩፡ ፮።)

አንታበይ፣ በግብዝነት ወደ ሌሎች ጣታችን ከመጠቆማችን በፊት እኔ ማን ነበርሁ? እኔ ማን ነኝ?  እንበል። ወደድንም ጠላንም አብንም ሆነ ህዝባችን አዲስ መሪ የሚፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ከቦታችን ለቀን አዲስ መሪ፣ አዲስ ፊት፣ አዲስ ተስፋ መፍጠር አለብን። በአጭር ጊዜ። እናሸንፋለን፣ እናቸንፋለን፣ ለማሸነፍ ነው የጀመርነው ድንፋታና መፈክር የትም አያደርሰንም። ካልሆነ በታሪክና በህዝባችን ፊት ቀለን እንገኛለን።

አብን የአማራ ህዝብ መከራ አምጦ የወለደው ድርጅት ነው። መሪዎቹ እናጠፋለን እናበላሻለን፣ ለሰራነው በጎም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ስራ ሀላፊነት እንወስዳለን። ብዙ ሺህ ወጣቶች ለመተካት የተዘጋጁ ደግሞ አሉ። ለነርሱ እድል ሰጠን እኛም ማገዝ ባለብን ልክ ከኋላ ሁነን እናግዛለን። ካልሆነ እንደ አንዳንድ ብአዴናዊያን ወንበር ላይ የጎልማሳ ዕድሜ ፈጅተን፣ በስልጣን ጃጅተን የታሪክ መሳቂያ መሳለቂያ እንሆናለን።

– ሌላ ስራም እኮ ሰርቶ መኖር ይቻላል!

እኔ በበኩሌ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ:-

“አብን ባለፈው የካቲት አካሂዶት በነበረው ጊዜያዊ የአስፈፃሚ ሪፎርም ላይ ንቅናቄው በቀጣይ 3 ወር ውስጥ የሚያካሂደው ሪፎርም ተከናውኖ አዳዲስ አመራሮች እስኪመረጡ ድረስ ከ2 እስከ 3 ወር ላልበለጠ ጊዜ ወደ ስራ አስፈፃሚ እንድመለስ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስኖ ነበር። ወደ አመራርነት የመመለስ ፍላጎት ባይኖረኝም የድርጅቴ ውሳኔ ስለነበር ውሳኔውን ተቀብየው ቆይቻለሁ።

ለአጭር ጊዜ ብየ የተመለስኩበት ጊዜ ስለተጠናቀቀ እንዲሁም ወደፊት ጊዜው ሲደርስ በምገልፃቸው ምክንያቶች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከአብን ስራ አስፈፃሚ አባልነቴ በፈቃዴ የለቀቅሁ ሲሆን፤ በማኮ አባልነት ግን የአብን ሪፎርም በስኬት እስኪጠናቀቅ የምቀጥል ይሆናል።

የንቅናቄው ሪፎርም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ አብን ተጠናክሮ ሲቆም ደግሞ ልክ ከአብን ሊቀ መንበርነቴ በገንዛ ፈቃዴ እንደለቀቅሁት ሁሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቴንም በገዛ ፈቃዴ በመልቀቅ አዳዲስ መሪዎች በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እድል እንዲያገኙ ለማድረግ መወሰኔን እገልፃለሁ።

አማራ በልጆቹ ትግል ሁለንተናዊ ህልውናው ይከበራል!”

Filed in: Amharic